የአፍሪካ እንግሊዝኛ ተናጋሪ ሀገሮች ዋና ኦዲተር ተቋማትን (AFROSAI-E) ጨምሮ ከሌሎች የተለያዩ የዓለም ክፍሎች የመጡ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት 17ኛው የአፍሪካ እንግሊዝኛ ተናጋሪ ሀገሮች ዋና ኦዲተር ተቋማት ማህበር (AFROSAI-E) ዓመታዊ ጉባኤ በደቡብ አፍሪካ ተካሄዷል፡፡
ጉባኤው በዋናነት የቴክኒክ ኮንፍረንስ ሲሆን ማህበሩ በቅርብ ጊዜ አዘጋጅቶ በ2022 ለማህበሩ አባል ሀገራት እያሰራጫቸው ያሉ ማንዋሎችን የማሻሻልና ለዋና ኦዲተር ተቋማት (SAIs) የማስተዋወቅ ሥራ ተከናውኗል፡፡
በግንዛቤ ማስጨበጫ የቴክኒክ ኮንፍረንሱ ላይ አሳታፊ የሆኑ ውይይቶችና ወርክሾፖች የተካሄዱ ሲሆን ስለ ፀረ ገንዘብ ማጭበርበር (Anti-Money Laundering) እና የፋይናንስ ሽብርተኝነትን ስለ መከላከል (Counter-Financing of Terrorism) ጨምሮ ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይቶች ተደርገዋል፡፡
በተጨማሪም የዘላቂ ልማት ግቦች ኦዲት ላይ ውይይት የተደረገ ሲሆን በሁለት ለኦዲት ሥራ የሚውሉ የበለጸጉ ሶፍትዌሮችንም የማስተዋወቅ ስራ ተሠርቷል፡፡
ጉባኤውም ከጥቅምት 8-10 ቀን 2015 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ -ፕሪቶሪያ የተካሄደ ሲሆን የፌዴራል ም/ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ አበራ ታደሰን ጨምሮ ከፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት 2 ኦዲተሮች እና 11 የክልልና የከተማ አሰተዳደር ዋና ኦዲተሮች በድምሩ 14 አባላት በጉባኤው ላይ ተሳተፈዋል።

