የመንግስት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን በፌዴራል ዋና ኦዲተር /ፌዋኦ/ መ/ቤት የመንግስት ግዥ አፈፃፀም ዙሪያ የጋራ የምክክር መድረክ አካሄደ።
በመድረኩ የተገኙትና የውይይት መድረኩን ያስጀመሩት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በምክር ቤቱ ከሚጸድቀው በጀት 70 በመቶ ለግዥ የሚውል እንደመሆኑ ይህንን ሥርዓት በተቀመጠው ህግና ሥርዓት እንዲፈጸም ግንዛቤ መፍጠሩ አስፈላጊነቱ የጎላ ነው ብለዋል።
የፌዋኦ መ/ቤት ከመንግስት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን ጋር በቅንጅት መስራታቸውም በወጡ አዋጆችና መመሪያዎች መሰረት ተናቦ ለመስራት የሚያግዝና በዘርፉ ያሉትን በርካታ ችግሮች በጋራ ለመፍታት የሚያስችል እንደሆነም ዋና ኦዲተሯ ጠቁመዋል።
የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀጂ ኢብሳ በበኩላቸው የመንግስት ተቋማት ግዥዎቻቸውን በእቅድና በተቀመጡ የአሰራር ሥርዓቶች መሠረት እንዲሆን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
ለዚህም የፌዋኦ መ/ቤት ጨምሮ ለትምህርት ተቋማት፣ ለዳኞች እና ለፌዴራል መንግስት ተቋማት የውይይት መድረኮች መዘጋጀታቸውን አቶ ሀጂ ጠቁመዋል።
በቀጣይም የተቋማት የግዥ አፈጻጸም በኦዲት ነቀፌታ የሌለበት አስተያየት እንዲያገኝ የተጠናከረ ሥራ እንደሚሰራም ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
የውይይት መድረኩ ለ2 ቀናት የተካደ ሲሆን በባለስልጣን መ/ቤቱ ረቂቅ የመቋቋሚያ ማሻሻያ አዋጅ፣ በኤሌክትሮኒክስ የግዥ ስርዓት እና በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት አሰራር ዙሪያ ገለጻና ውይይት ተደርጓል።
በመድረኩም በአጠቃላይ 39 የፌዋኦ ዳይሬክተሮች፣ ማናጀሮች እና ከፍተኛ ኦዲተሮች ተሳትፈዋል።










