News

የኦዲት ስራ ውጤታማ እንዲሆንና የህዝብ ሀብት እንዳይባክን ባለድርሻ አካላት በባለቤትነት መንፈስ ሊሰሩ አንደሚገባ ተገለጸ

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት፣ የገንዘብ ሚኒስቴር እና በ2013 በጀት አመት የኦዲት ሪፖርት ተቀባይነት የሚያሳጣ አስተያየት ያገኙ የመንግስት ባለበጀት መ/ቤቶች በጋራ ከኦዲት ግኝት ጋር በተያያዘ የምክክር መድረክ አካሂደዋል።

መድረኩ የገንዘብ ሚኒስቴር ከዚህ ቀደም በነበሩ የኦዲት ግኝቶች ተቀባይነት የሚያሳጣ አስተያየት ባገኙ ተቋማት ላይ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያና የገንዘብ ቅጣት መውሰዱን ተከትሎ በአንዳንድ ተቋማት ቅሬታዎች በመነሳታቸው እና በቀጣይ በጋራ የመፍትሔ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑ ተጠቁሟል።

በ2013 በጀት ዓመት ተቀባይነት የሚያሳጣ አስተያየት ያገኙ የመንግስት ባለበጀት መ/ቤቶች የሥራ ኃላፊዎችም ለጎላ የኦዲት ግኝት የሚጋለጡባቸውን ምክንያቶች አና ያሉባቸውን ችግሮች አብራርተዋል።

በተለይም የኦዲተሮች አቅም ማነስ፣ የስነ-ምግባር ችግር፣ ከኦዲት ተደራጊ ተቋማት የሚፈለገውን ግዴታ በግልጽ ያለማሳወቅና ሌሎች ጉዳዮችን  አንስተው መፍትሄ እንዲፈለግላቸው ጠይቀዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው ኦዲቱ የሚከናወንበትን አግባብና በኦዲት ተደራጊ ተቋማትና ባለድርሻ አካላት ሊወሰዱ በሚገቡ የመፍትሔ እርምጃዎች ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ዋና ኦዲተሯ በማብራሪያቸው የኦዲት ስራ ዋነኛ ዓላማ የኦዲት ግኝት ተስተካክሎ ለስራ የተመደበው በጀት በአግበቡ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ማስቻል መሆኑን አመልክተው ኦዲተሮችና ኦዲት ተደራጊ መስሪያ ቤቶች ለጋራ ዓላማ ተባብረው መሥራት እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በኦዲተሮች የአቅም ማነስ እና የስነ-ምግባር ችግሮች ዙሪያም መ/ቤታቸው ልዩ ትኩረት ሰጥቶ የሚሠራበት መሆኑን ክብርት ወ/ሮ መሠረት ተናግረዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር እዮብ ተካለኝ በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት የኦዲት ስራ በየመ/ቤቱ የተዘረጋውን የቁጥጥር ስርዓት ውጤታማ አንዲሆን፣ በጥብቅ ስልትና ስርዓት ተመርቶ የህዝብ ሃብት እንዳይባክን ለማድረግ እንዲሁም ተቋማት የተመሰረቱበት ዓላማ ግቡን እንዲመታ በመሆኑ ሁሉም በባለቤትነት መንፈስ ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ብልሹ አሰራርን በማስተካከል የህዝብ ሀብት እንዳይባክን ኦዲተሮች በሚያደርጉት ጥረት ሁሉም ባለድረሻ አካለት ለኦዲት አፈጻጸም ውጤታማነት በትጋት መስራት እንዳለባቸውም ዶ/ር እዮብ ተካልኝ ገልጸዋል፡፡

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *