የፌዴራል ዋና ኦዲተር /ፌዋኦ/ መ/ቤት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር መ/ቤት ለመጡ ኦዲተሮች ስልጠና ሰጠ፡፡
በስልጠናው መዝጊያ ስነ-ስርዓት ላይ የተገኙት የፌዋኦ መ/ቤት ም/ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ አበራ ታደሠ የክልል እና ከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በሚተገብረው ዓለም አቀፍ የኦዲት ስታንዳርድ መሠረት እንዲሠሩ ለማስቻል ታስቦ የተዘጋጀ ሥልጠና መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ሰልጣኞች በቆይታቸው እውቀት አግኝተዋል፣ የአመለካከት ለውጥ አምጥተዋል ወይም ግንዛቤ ጨብጠዋል ብለው እንደሚያምኑ የጠቆሙት ምክትል ዋና ኦዲተሩ ነገር ግን ይበልጥ ኦዲተሮቹ ሥልጠናውን መነሻ በማድረግ በግላቸው ክፍተቶቻቸውን ለመሙላት እና አቅማቸውን ለማሳደግ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡
በቀጣይም የአቅም ግንባታ ሥራዎች ለክልልና ለከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች ኦዲተሮች ብቻ ሳይሆን ለኦዲት ተደራጊ መ/ቤቶች የውስጥ ኦዲተሮችም ጭምር በተለያዩ አግባቦች የመስጠት እና የኦዲት አሠራር ሥርዓቶችን የማጋራት ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ክቡር አቶ አበራ ገልጸዋል፡፡
ሥልጠናው በኢዲሱ የፋይናሽያል ኦዲት ማኑዋልና በክዋኔ ኦዲት የስልጠና ርዕሶች ላይ ያተኮረ ሲሆን በፋይናንሽያል ኦዲት ረገድ የቅድመ ኦዲት ተግባራት፣ የመግቢያ ስብሰባ ምንነት፣ የስጋት ግምገማ እና ምላሾች ዙሪያ ይዘቶችን የያዘ እንደነበር የመ/ቤቱ የትምህርትና ስልጠና ዳይሬክቶሬት ተወካይ አቶ ቴዎድሮስ ሽመልስ ገልጸዋል፡፡
የክዋኔ ኦዲትን በተመለከተም የክዋኔ ኦዲት ምንነት፣ የኦዲት ዕቅድና ዲዛይን፣ ዝርዝር ኦዲት፣ የኦዲት ሪፖርትና የክትትል ሂደት በስልጠናው የተካተቱ ይዘቶች መሆናቸውን አቶ ቴዎድሮስ አብራርተዋል፡፡
ስልጠናው በገለጻና በቡድን ውይይት የተካሄደ መሆኑን ጨምረው የገለጹት አቶ ቴዎድሮስ ስልጠናው አዲሱን የፋይናንሽያል ኦዲት ማኑዋል በማስተዋወቅና በአግባቡ በስራ ላይ እንዲውል በማድረግ ረገድ እንዲሁም በክዋኔ ኦዲት አተገባበር ላይ ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በስልጠናው የተሳተፉ ሰልጣኞች በሰጡት አስተያየት ከስልጠናው የፋይናንሽያል እና የክዋኔ ኦዲት አተገባበርን በተመለከተ በርካታ ጠቀሜታ ያለው ዕውቀት የቀሰሙ መሆኑን ጠቅሰው በተለይም በአዲስ ተሻሽሎ በተዘጋጀው የፋይናሽያል ኦዲት ማኑዋል እንዲሁም በክዋኔ ኦዲት አተገባበር ላይ የወሰዱት ስልጠና ወቅቱ ከሚጠይቀው ዓለም አቀፍ የኦዲት አሠራር ጋር የበለጠ ያስተዋወቃቸውና በስራቸው ላይ ያሉባቸውን ክፍተቶች የሚሞላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ስልጠናው ከሐምሌ 18-22 /2014 ዓ.ም በመ/ቤቱ የስልጠና ማዕከል የተሰጠ ሲሆን 40 የሚሆኑ ሰልጣኝ ኦዲተሮች ተሳትፈዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ቀደም ባሉት ጊዜያት በተለያዩ ክልሎች ለሚገኙ የዋና ኦዲተር መ/ቤቶች ኦዲተሮች ተመሳሳይ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና መስጠቱ ይታወቃል፡፡