የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት አዲስ ለተቀጠሩ የፋይናሽያል ጀማሪ ኦዲተሮች የትውውቅ /Induction /ስልጠና ሰጠ፡፡
ስልጠናው ከሰኔ 13-17/2014 ዓ.ም ድረስ በመ/ቤቱ የስልጠና ክፍሎች የተካሄደ ሲሆን የተለያዩ የስራ ኃላፊዎችና ከፍተኛ የኦዲት ባለሙያዎች በአሰልጣኝነት እንዲሁም በጥቅሉ 36 የሚሆኑ አዲስ የተቀጠሩ ጀማሪ ኦዲተሮች በሰልጣኝነት በስልጠናው ተሳትፈዋል፡፡
የስልጠናው ዓላማ ሰልጣኝ ኦዲተሮቹ ለመ/ቤቱ የአሠራር ስርዓት አዲስ እንደመሆናቸው የተቋሙን አሰራር በማሳወቅ የኦዲት ማንዋሉን አውቀውና ተገንዝበው ሥራቸውን በአግባቡና በተቀመጠው ስታንዳርድ መሰረት እንዲሰሩ ማስቻል እና ሥራቸውን ሲያከናውኑም ሁለንተናዊ የኦዲተር ሥነ-ምግባርን የተላበሱ እንዲሆኑ እና ሙስናን እና ብልሹ አሰራሮችን እንዲጸየፉ ግንዛቤ ለማስጨበጥ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናው የመ/ቤቱን ደንብና መመሪያ፣ በመቤቱ ውስጥ ተግባራዊ እየተደረጉ ስለሚገኙ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሥርዓቶች፣ አጠቃላይ የኦዲት አሰራር እንዲሁም የሥነ-ምግባርና ፀረ- ሙስናን የተመለከቱ ይዘቶችን ያካተተ መሆኑ ታውቋል፡፡
ሰልጣኞች በስልጠናው ማጠቃለያ በሰጡት አስተያየት በርካታ የኦዲት አሠራር ዕውቀቶችንና ክህሎቶችን ከስልጠናው ያገኙ መሆኑን ጠቅሰው ስልጠናው ቀደም ሲል በንድፈ ሀሳብ የነበራቸውን ውስን ዕውቀት ማሳደግ የቻሉበትና ዕውቀታቸውን እንዴት በተግባር ማዋል እንደሚገባቸው መሰረታዊ ግንዛቤ ያገኙበት እንደነበር አመላክተዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት መ/ቤቱን ለሚቀላቀሉ አዲስ ኦዲተሮች የትውውቅ፣ እንዲሁም ለነባር ኦዲተሮች የሙያ ማሻሻያ ተከታታይ ስልጠናዎችን ከፍተኛ ልምድ ባላቸው የውስጥና የውጭ አሰልጣኞች በማካሄድ የሠራተኞቹን አቅም በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡