News

ለፋይናሺያል ኦዲተሮች ሲሰጥ የነበረው ሥልጠና ተጠናቀቀ

በፌዴራል ዋና ኦዲተር  መ/ቤት በሦስት ዙር ለሦስት ሳምንታት ለፋይናሺያል ኦዲተሮች ሲሰጥ የነበረው ሥልጠና ተጠናቀቀ፡፡

ሥልጠናው በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት አዘጋጅነት በተቋሙ አሰልጣኝ ባለሙያዎች እና ከኦዲት ስርቪስ ኮርፖሬሽን በመጡ ሙያተኞች ቅንጅት የተሰጠ ነው፡፡

በሥልጠናው ማጠናቀቂያ መርሃግብር በመገኘት መልዕክት ያስተላለፉት የፌዋኦ መ/ቤት ም/ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ ሥልጠናው የኦዲተሮችን አቅም ከማሳደግ ባለፈ በኦዲት ጥራት መሻሻል ላይ ጉልህ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል፡፡

ኦዲት ተጠያቂነትን በየደረጃው ለማረጋገጥ የተቋማትን አፈጻጸም፣ የአገልግሎት አሰጣጥ፣ የሀብትና ንብረት አጠቃቀም እንዲሁም ዜጎች በመንግስትና በተቋማት ላይ ያላቸውን እምነት የሚያጠናክር በመሆኑ ሁሉም ኦዲተር ይህን ኃላፊነት ለመወጣት ተግቶ ሊሠራ እንደሚገባ ክብርት ወ/ሮ መሠረት ገልጸዋል፡፡

ክብርት ዋና ኦዲተሯ አክለውም የፌዋኦ መ/ቤት በመንግስት የተጣለበት ኃላፊነት ከፍተኛ መሆኑን አስታውሰው እያንዳንዱ ኦዲተርም በስልጠና ቆይታው ያገኘውን እውቀት በሥራው ተፈጻሚ ማድረግ እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል፡፡

የመ/ቤቱ የትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አበራ ታደሰ በበኩላቸው ለሦስት ሳምንታት ሲሰጥ የቆየው ሥልጠና ለኦዲት ሥራው መሻሻል ጠቃሚ ግብዓቶች የተገኙበት እንደሆነ ገልጸው በቀጣይም የሥልጠና ክፍሉ አቅሙን በማጠናከር የኦዲተሩን ክፍተት ታሳቢ ያደረጉ ሥልጠናዎችን ያዘጋጃል ብለዋል፡፡

ከኦዲት ሰርቪስ ኮርፖሬሽን ሥልጠና በመስጠት የተሳተፉት የተቋሙ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ጋሼ የማነህ እንደገለጹት ሥልጠናው በአፍሪካ የእንግሊዘኛ ተናጋሪ ዋና ኦዲተሮች ማህበር እንዲሁም በፌዋኦ መ/ቤት የኦዲት ጥራት ማረጋገጥ ክፍል በተለዩ ክፍተቶች ላይ መሠረት አድርጎ የተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሥልጠናው ኦዲተሮች ምን እንደሚጠበቅባቸው ከማሳየት ባለፈ አቅማቸውን እንዲፈትሹ እና ከቅርብ ኃላፊዎቻቸው ጋር ተመሳሳይ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ያስቻለ መሆኑን ም/ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመው በተለይም በአዳዲስ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አሰራሮች ላይ ያላቸውን ግንዛቤ ለማሳደግ እድል የፈጠረ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

ከኦዲት ሙያ ውጪ ያለው ዘርፍ በብዙ መልኩ እየተቀየረ መምጣቱንም በመገንዘብ እንዲሁም የኦዲት ግኝት በመንግስትም ሆነ በሌሎች አካላት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራበት ያለበት ጊዜ በመሆኑ ተቋሙ በአቅም ግንባታ ላይ የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አቶ ጋሼ አሳስበዋል፡፡

ሥልጠናው በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ለሚሠሩ ከዳይሬክተር እስከ ጀማሪ ኦዲተሮች ድረስ የተሠጠ ሲሆን ከ350 በላይ ኦዲተሮች ተሳትፈውበታል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *