የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በቀድሞው የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ በአሁኑ የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፈቃድ አሰጣጥ እና ጥራት ቁጥጥር የ2012/2013 በጀት ዓመት የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት መነሻ በማድረግ የመንግስት ወጪ እስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ይፋዊ ስብሰባ አካሂዷል፡፡
በይፋዊ ስብሰባው ባለሥልጣን መ/ቤቱ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ 17 የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ በተወሰደ ናሙና ለበርካታ የትምህርት ዘርፎች የእውቅና ስታንዳርድና የብቃት ማዕቀፍ መመሪያ አለማዘጋጀቱን እና በነዚህ በናሙና በታዩ ተቋማት ከአዋጅና መመሪያ ውጪ በመጀመሪያ እና በሁለተኛ ዲግሪ ከተፈቀደላቸው የተማሪዎች መጠን ከ180 እስከ 2000 ፐርሰንት በብልጫ መዝግበው እያስተማሩ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በሌላ በኩልም ባልስልጣን መ/ቤቱ ከጤና እና ከሕግ ተማሪዎች በስተቀር በሌሎች የትምህርት መስኮች የሙያ ብቃት ምዘና የሚካሄድበት ሥርዓት አለመዘርጋቱን፣ የግል ትምህርት ተቋማት ለተመረቁ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና የማይሰጡ መሆኑን እና ባለስልጣኑም ምዘናውን ተግባራዊ በማያደርጉ ተቋማት ላይ እርምጃ ያልወሰደ መሆኑ በመድረኩ ላይ ተጠቁሟል፡፡
ድንገተኛ የአካዳሚክ ኦዲት ከማድረግ ጋር በተያያዘም የብቃት ማረጋገጫ ሲኦሲ /COC/ መፈተናቸው ሳይረጋገጥ የዲግሪ ፕሮግራም የሚማሩ እንዳሉ፣የመማሪያ ክፍሎች ደረጃቸውን በጠበቁ ቁሳቁሶች ያልተደራጁ መሆኑና እና ለመማር ማስተማር ሂደቱ ምቹ ያልሆኑ ሆነው መገኘታቸው እና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚያስተምሩ መምህራን የፔዳጎጂ ሥልጠና ያልወሰዱ መሆናቸው ተመላክቷል፡፡
በባለሥልጣኑ የእውቅና እድሳት ፈቃድ አሰጣጥ ግምገማ ለሚያደርጉ ኮሚቴዎች የስነ-ምግባር መመሪያ ማውጣት ሲገባው መመሪያ ያላዘጋጀ መሆኑ እና የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እኩል በሆኑ ሴሚስተሮች ማስተማራቸውን በተመለከተ በ17ቱም በናሙና በታዩ የትምህርት ተቋማት ከ300 ቀናት በላይ የማያስተምሩ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የተቋማቱ የማስተማሪያ ህንጻዎችን በተመለከተም ለአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ምቹ ያልሆኑ፣ አሳንሰር/ሊፍት/ የሌላቸው፣ ወለላቸው የሚያንሸራትቱ እና ለአካል ጉዳተኞች የማይመቹ የመጸዳጃ ቤቶች ያላቸው መሆኑም በኦዲት ግኝቱ ተመላክቷል፡፡
የመንግስት ወጪ እስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴም ተቋሙ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ለምን ኃላፊነቱን እንዳልተወጣ እና ባለስልጣን መ/ቤቱ ከኦዲት ግኝቱ በኋላ በወሰዳቸው የማስተካከያ እርምጃዎች ዙሪያ ማብራሪያ እንዲሰጥ ጠይቋል፡፡
የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን ከፍተኛ አመራሮችና የሥራ ኃላፊዎች ቋሚ ኮሚቴው ባቀረባቸው ጥያቄዎች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
የባለሥልጣን መ/ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አንዱዓለም አድማሴ በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በኦዲት ሪፖርት የቀረቡ ግኝቶች ትክክለኛ መሆናቸውን እና በውይይቱ የተነሱ ሃሳቦችና አስተያየቶች በግብዓትነት የሚወሰዱ መሆኑን ገልጸው ለችግሮቹ መብዛት ተቋሙ ተልዕኮውን የሚመጥን የሰው ኃይልና አደረጃጀት የሌለው፣ ተጠሪነቱም ለአስፈጻሚ ተቋማት መሆኑ ሥራውን በነጻነት እንዳይሠራ እንዳደረገው አስረድተዋል፡፡
የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በሰጡት አስተያየት ባለሥልጣን መ/ቤቱ በርካታ ውስብስብ ችግሮች ያሉበት መሆኑን ጠቅሰው የራሱን ጉድለት በራሱ ከመፍታት ይልቅ ችግሮቹን ወደሌሎች ተቋማት ማስተላለፉ ተቀባይነት የሌለው እና በቀጣይም በናሙና ኦዲቱ የታዩ ችግሮችንም ሆኑ ሌሎች በተቋሙ ያሉ ብልሹ አሠራሮችን መ/ቤቱ በጥልቀት ተመልክቶ መሠረታዊ የማስተካከያ እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የፌዴራል የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር ሳሙኤል ኦርቃቶ በበኩላቸው ተቋሙ ካለበት ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመውጣት ውስጣዊ ችግሮቹን ማጥራት፣ የአደረጃጀት ችግሩን መፍታት፣ ለአሠራር ሥርዓቶች ትኩረት ሰጥቶ መስራት እና የከፍተኛ ትምህርት መቆጣጠሪያ ሥርዓት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ተቋሙን ወደ ተሻለ ደረጃ ለመውሰድ እና እንደሀገር በዘርፉ ያለውን ውስብስብ ችግር መቅረፍ እንዲቻል ቋሚ ኮሚቴው የምክር ቤቱ አፈጉባኤ፣ የትምህርት ሚኒስቴርና ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የሚገኙበት የውይይት መድረክ አዘጋጅቶ የመፍትሔ አቅጣጫ ማስቀመጥ እንደሚገባም ዶ/ር ሳሙኤል ጠቁመዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ም/ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው መ/ቤታቸው በባለሥልጣን መ/ቤቱ ላይ በ2001 ዓ.ም ተመሳሳይ ኦዲት አደርጎ እንደነበረ አስታውሰው እነዚህ ችግሮች ከ11 ዓመታት በኋላም ሳይፈቱ መገኘታቸውን ገልጸዋል፡፡
ባለሥልጣን መ/ቤቱ አቅም ኖሮት ለሀገር የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ነጻና ገለልተኛ ሆኖ ሊቋቋም እና ብቃት ባላቸው ሙያተኞች ሊደራጅ እንደሚገባም ም/ዋና ኦዲተሯ ገልጸዋል፡፡
ከሙያ ምዘና ማረጋገጫ /COC/ እና የእውቅና ፈቃድ አሰጣጥ ጋር በተያያዘም በርካታ ብልሹ አሠራሮች በተቋሙ መኖራቸውን ገልጸው የመልካም አስተዳደር ችግር እየፈጠሩ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
ም/ዋና ኦዲተሯ አክለውም ተቋሙ በተለያዩ ጊዜያት በአዋጅ ሲደራጅ የስነ-ምግባር መመሪያ አለማዘጋጀቱ ተቋሙ ህገወጥ አሠራርን የሚያበረታታ መሆኑን የሚያሳይ መሆኑን ጠቅሰው ለማስተማሪያ ህንጻዎች ፈቃድ ሲሰጥም አስቀድሞ አስገዳጅ የሆነ መመሪያ ሊያስቀምጥ ይገባ እንደነበረ አንስተዋል፡፡
በመሆኑም የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴም ሆነ የሰው ሃብት ልማት ሥራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በተቋሙ ላይ ያሉ ችግሮች ላይ አቅጣጫ ሊሰጡበት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ክርስቲያን ታደለ በበኩላቸው ባለሥልጣን መ/ቤቱ የኢትዮጵያን ነገ የተሸከመ ተቋም ቢሆንም በተሰጠው ኃላፊነት እና ተልዕኮ ልክ አለመገኘቱን ገልጸዋል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው በኦዲት ግኝቶቹና በተቋሙ አመራሮች በተሰጡ ምላሾች መሠረት ባለሥልጣን መ/ቤቱ በተሰጠው ሥልጣን ልክ ሥራውን እየሠራ አለመሆኑን ሰብሳቢው ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም ባለሥልጣን መ/ቤቱ አስከ ሚያዚያ 8 ቀን 2014 ዓ.ም የድርጊት መርሃ ግብር አዘጋጅቶ ለቋሚ ኮሚቴው እንዲልክ፣ የትምህርት ሚኒስቴር በባለሥልጣን መ/ቤቱ ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ፣ የፌዴራል የስነ-ምግባር እና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን በባለሥልጣን መ/ቤቱ አሠራሮች ዙሪያ ብልሹ የስነ-ምግባር አሠራሮችን በማጥናት በ2 ወር ጊዜ ውስጥ አጣርቶ ውጤቱን እንዲያቀርብ ሰብሳቢው አሳስበዋል።
በተጨማሪም የፍትሕ ሚኒስቴር በባለሥልጣን መ/ቤቱ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች እንዲሁም ከባለሥልጣን መ/ቤቱ የአሠራር አቅጣጫ ውጪ በሚንቀሳቀሱ የትምህርት ተቋማት አመራርና ባለንብረቶች ላይ ከኦዲት ግኝቱ አንጻር በወንጀል የሚያስጠይቁ ጉዳዮችን መርምሮ ክስ እንዲመሰርት እና ሁሉንም አፈፃፀም በ2 ወር ጊዜ ውስጥ ለቋሚ ኮሚቴው እንዲያሳውቅ አቅጣጫ ሰጥተዋል።