በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ የ2012 በጀት ዓመት በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በተዘጋጀ የሂሳብ ኦዲት ሪፖርት ላይ ይፋዊ ስብሰባ አካሂዷል፡፡
በይፋዊ ስብሰባው የሂሳብ ኦዲት ሪፖርቱን መሠረት በማድረግ ቋሚ ኮሚቴው ከህግና ከመመሪያ ውጪ ለተፈጸሙ ግኝቶች የስፖርት አካዳሚውን ማብራሪያ እንዲሰጥ ጠይቋል፡፡
ከግኝቶቹ መካከልም ለ19 ሠራተኞች ከዕቅድ ከተያዘው በላይ በጠቅላላ ድምር ብር 39,128.00 በብልጫ የውሎ አበል ክፍያ ተፈጽሞ መገኘቱን እና አንድ ሠራተኛም ስብሰባው ላይ ተገኝተው አቴንዳንስ ላይ ሳይፈርሙ ብር 1,930.00 ተከፍሏቸው መገኘቱ ተገልጿል፡፡
የወጪ ሂሳብ አያያዝን በተመለከተም በበጀት ዓመቱ በጠቅላላ ድምር ብር 1,001,269.84 የበጀት አርዕስታቸውን ያልጠበቁ የወጪ ምዝገባዎች ተከናውነው መገኘታቸውን፤ 2,207,833.55 (23.71%) ሥራ ላይ ያልዋለ በጀት መገኘቱን እንዲሁም የስልክ አጠቃቀም ተመን ሳይወጣ በድምሩ ብር 271,567.21 ተከፍሎ መገኘቱ ተጠቁሟል፡፡
ከንብረት አስተዳደር ጋር በተያያዘም በተለይም አዳዲስ ተሸከርካሪ ወንበሮች ያለአገልግሎት ለ9 ዓመታት ተቀምጠው መገኘታቸውን ቋሚ ኮሚቴው አንስቶ የሚኒስቴር መ/ቤቱ እንዲሁም የስፖርት አካዳሚው ከፍተኛ አመራሮችና የሥራ ኃላፊዎች ምላሽና መብራሪያ እንዲሰጡ ጠይቋል፡፡
የስፖርት አካዳሚው ዋና ዳይሬክተር አቶ አምበሳው እንየው እና ሌሎች የተቋሙ የሥራ ኃላፊዎች በሰጡት ምላሽ ተቋማቸው የኦዲት ግኝቱን መሠረት በማድረግ የተለያዩ የዕርምት እርምጃዎችን መውሰዱን አብራርተዋል፡፡
ከወጪ ሂሳብ አያያዝ ጋር በተያያዘ በኦዲት ግኝቱ የበጀት አርዕስቱን ያልጠበቀ የወጪ ምዝገባ ተብሎ መያዙን ተገቢነቱን ለመቀበል እንደሚቸገሩ እና መ/ቤታቸው የሥልጠና ተቋም እንደመሆኑ በተፈቀደ በጀት እየተጠቀሙ ነው ብለው እንደማያምኑ አቶ አምበሳው አስረድተዋል፡፡
ከንብረት አያያዝ ጋር በተያያዘም ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ብቃት ያለው የሰው ሃይል አለመሟላት ጋር ተያይዞ መሆኑን ገልጸው ጊዜያቸው ያለፈባቸውን መድሃኒቶች ለማስወገድ የሄዱበት ርቀት ውጤታማ አለመሆኑንም ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡
የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር አቶ ቀጀላ መርዳሳ በበኩላቸው በስፖርት አካዳሚው በታዩ በተለይም ከሂሳብ መደብ ውጪ መጠቀም፣ ከበጀት አጠቃቀም፣ ከመደበኛ የስልክ አጠቃቀም እና ከንብረት አስተዳደር ጋር በተያያዘ ለተነሱ ጉዳዮች ሚኒስቴር መ/ቤታቸው በራሱ በኩል ተቋሙን እንደሚፈትሽ እና በአሠራሮቻቸው ላይ ተቋማዊ ለውጥ በማድረግ የተሻለ ለመስራት ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ም/ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው ተቋሙ የሂሳብ መደቡን ያልጠበቀ ወጪ ሂሳብ ጋር በተያያዘ የቀረበው ምላሽ አሁንም እንደ ፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ተቀባይነት የሌለው መሆኑን እና የማዕከሉ የበጀት አጠቃቀምም መታረምና መስተካከል እንደሚገባው ገልጸዋል፡፡
በንብረት አያያዝ በኩል በአካዳሚው ብዙ መሻሻሎች ቢኖሩም ለ9 ዓመታት እልባት ያላገኙ አዳዲስ አገልግሎት ላይ ያልዋሉ የእንግዳ ወንበሮች መፍትሔ ሊፈለግላቸው እንደሚገባ ገልጸው የባህልና ስፖርት ሚኒስቴርም የስፖርት አካዳሚውን የ2012 እና 2013 በጀት ዓመት የሂሳብ ኦዲት ሪፖርት በመመልከት የተጠናከረ ቁጥጥርና ክትትል ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ስብሳቢ የተከበሩ አቶ ክርስቲያን ታደለ በበኩላቸው የስፖርት አካዳሚው በቀጣይ የሉበትን ችግሮች በመቅረፍ ምሳሌ የሚሆን ሥራ መሥራት እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል አላግባብ ክፍያ በመፈጸም ስህተት በፈጠሩ ሠራተኞች ላይ ተገቢው አስተዳደራዊ እርምጃ ተወስዶ ሪፖርት ለቋሚ ኮሚቴው እንዲደረግ እና ከንብረት አስተዳደር ጋር በተያያዘም ያሉ ችግሮችን ከግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ጋር በጋራ መሥራት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡
አያይዘውም የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የአካዳሚውን መሠረታዊ ችግሮች በመመርመር ዘላቂ መፍትሔ ሊያበጅ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡