News

የውጪ ኦዲት ድግግሞሽን ለማስቀረት የወጣ የነጠላ ኦዲት አዋጅ አፈፃፀም መመሪያ ጸደቀ

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት እንዲሁም የክልልና የከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች  የነጠላ ኦዲት አዋጅ ቁጥር 1251/2013 ለማስፈጸም በተዘጋጀው ረቂቅ መመሪያ ላይ ተወያይተው መመሪያውን አጽድቀዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ከፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት እንዲሁም ከክልልና ከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች የመጡ ዋና ኦዲተሮችና ምክትል ዋና ኦዲተሮች ተሳትፈዋል፡፡

በውይይት መድረኩ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የኦዲት ዘርፍ ም/ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ ስለ አፈጻጸም መመሪያው አዘገጃጀት ሂደት መነሻ ሀሳብ አቅርበው የመመሪያው መዘጋጀት ዓላማ  በነጠላ ኦዲት አፈጻጸም ላይ ግልጽ የሆነ የአሰራር ሥርዓት በማስቀመጥ የአዋጁን አተገባበር ቀልጣፋና ውጤታማ ለማድረግ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በክልል ደረጃ ያሉ ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች በየክልላቸው የታወጀውን የበጀት አዋጅ መሰረት በማድረግ የሂሳብ ኦዲት እንዲያደርጉ በመቋቋሚያ አዋጆቻቸው  ሥልጣንና ኃላፊነት የተሰጣቸው በመሆኑና ይህም አንድ ሂሳብ በፌዴራል እና በክልል ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች ደረጃ ተመሳሳይ ኦዲት የሚደረግበትን የኦዲት ድግግሞሽ የሚፈጥር ሆኖ መገኘቱ ለነጠላ ኦዲት አዋጁና  ለአፈጻጸም  መመሪያው መውጣት ምክንያት መሆኑ በመድረኩ ላይ ተገልጿል፡፡  የኦዲት ድግግሞሽ  በኦዲት ተደራጊ መ/ቤቶች ላይ ከፍተኛ የሥራ ጫና እና ለተመሣሣይ ሥራ የጊዜ፣ የሰው ሃይል እና አላስፈላጊ ወጪ የሚያስከትል በመሆኑ እና  ይህንን ችግር ለመቅረፍ በሀገር አቀፍ ደረጃ የኦዲት አሠራሩና ሥርዓቱን ወጥ እና ደረጃውን የጠበቀ ለማድረግ በማስፈለጉ የውጭ ኦዲት ድግግሞሽን ለማስቀረት የነጠላ ኦዲት አዋጅ መደንገጉና የአዋጁን አፈጻጸምም ቀልጣፋ፣ ውጤታማና ግልጽ ማድረግ በማስፈለጉም መመሪያው ከክልል ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች ጋር በመካከር በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት መዘጋጀቱ ተጠቅሷል፡፡

በመጨረሻም ከፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት እንዲሁም  ከክልል እና ከከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች የስራ ኃላፊዎች ግልጽነት በሚፈልጉ ጉዳዮች ላይ ውይይቶችና ተጨማሪ ማብራሪያዎች  ቀርበው የነጠላ ኦዲት አዋጅ ቁጥር 1251/2013  ማስፈጸሚያ መመሪያ ጸድቋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *