የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ለክዋኔ ኦዲተሮች በአከባቢ ኦዲት አሠራር ዙሪያ ሥልጠና እየሠጠ ይገኛል፡፡
በፌዴራል ዋና ኦዲተር /ፌዋኦ/ መ/ቤት የአከባቢ ኦዲት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሻሾ መኮንን ለአከባቢ ኦዲት በተሰጠው ትኩረት ከዚህ ቀደም በክዋኔ ኦዲት ሲሰራ የነበረውን ሰራ ይበልጥ ለማጠናከር በዳይሬክቶሬት ደረጃ በተቋሙ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋቀረ መሆኑን አውስተው የሥልጠናው ዓለማም በኦዲቱ ዓይነት ላይ የክዋኔ ኦዲተሮችን ግንዛቤና ክህሎት ለማሳደግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በፌዋኦ የትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አበራ ታደሰ በበኩላቸው ሥልጠናው አጠቃላይ የአከባቢ ኦዲት ምንነት ጽንሰ-ሀሳብ ጀምሮ በዕቅድ ዝግጅት፣ በኦዲት ክንውን፣ በሪፖርት ዝግጅትና ክትትል ስለሚሠሩ ሥራዎች ድረስ ያሉ ተግባራትን የሚዳስስ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ሥልጠናው ከአፍሪካ የእንግሊዘኛ ተናጋሪ የዋና ኦዲተሮች ማህበር /AFROSAI-E/ በመጡ ሁለት አሠልጣኞች እየተሠጠ የሚገኝ ሲሆን ለተከታታይ 5 ቀናት የሚሰጥ እና ከ70 በላይ የክዋኔ ኦዲተሮች የሚሳተፉበት መሆኑ ተገልጿል፡፡
የአካባቢ ኦዲት ራሱን የቻለ የመንግስት ድርጅቶችን፣ ፕሮግራሞችን፣ እንቅስቃሴዎችን ወይም ተግባራትን ከአካባቢ ጋር በተገናኘ የመፈተሽ እና የመገምገም ሂደት ነው።
ይህም የመንግስት መርሃ ግብሮች እና ተግባራት በአካባቢ ላይ ስለሚያስከትሏቸው ውጤቶች ለፓርላማው ገለልተኛ መረጃ ለመስጠት፣ የአካባቢ ጥበቃ ሂደትን ለማሻሻል እና ወደ ዘላቂ ልማት የሚያመሩ ምርጥ ተሞክሮዎችን ለማበረታታት የሚያስችል ነው።
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤትም ከዚህ ቀደም ሲያካሂዳቸው በቆያቸው የክዋኔ ኦዲቶች የአከባቢ ጥበቃ ሥራን የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ተገቢውን ትኩረት ሰጥተው ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ለማስቻል በርካታ የአከባቢ ኦዲቶችን ሠርቷል፡፡