News

ከኦዲት ግኝቶች በኋላ ያለውን የተጠያቂነት ሥርዓት የሚያጠናክር የሁለትዮሽ ስምምነት ተደረገ

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በሚያከናውናቸው የኦዲት ተግባራት የሚወጡ የኦዲት ግኝቶችን ተከትሎ በሚመለከታቸው ህጋዊ አካላት መተግበር የሚገባውን የተጠያቂነት ሥርዓት ሊያጠናክር የሚችል የሁለትዮሽ የጋራ ስምምነት ከፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ጋር አደረገ፡፡

የሁለቱ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች እና ሌሎች የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት የካቲት 10 ቀን 2014 ዓ.ም የተካሄደው የሁለትዮሽ የጋራ ስምምነት በኦዲት ግኝቶች መሰረት ተጠያቂነትን ለመተግበር የሚያስችለውን ህጋዊ ሂደት የበለጠ የሚያጠናክር መሆኑ በስምምነት ስነ ስርዓቱ  ላይ ተገልጿል፡፡

የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ክቡር አቶ ቴዎድሮስ በቀለ  ከፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ጋር የተደረገው  የጋራ አሠራር ስምምነት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ጤናማ ከማድረግ አንጻር  ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ጠቅሰው በተለይ ትላልቅ ግዥዎችን የሚመለከቱ የኦዲት ግኝቶችን መርምሮ ጥፋተኛ አካላትን ለህግ ለማቅረብ የሚያስችል የመረጃ ልውውጥ ሥርዓትን የሚያጠናክር ነው ብለዋል፡፡ አክለውም ስምምነቱ በጥናትና ምርምር ረገድም አብሮ ለመስራት የሚስያችል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የኦዲት ዘርፍ ም/ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው ከአገልግሎቱ ጋር የተደረገው ስምምነት ከኦዲት ግኝቶች በኋላ ሊኖሩ በሚገባቸው የተጠያቂነት ሂደቶች ላይ ከተለያዩ አካላት የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመቅረፍ የሚያግዝ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በስምምነቱ መሰረት የሚተገበሩ የሁለቱም ተቋማት ስራዎችም መንግስት በህዝብ ዘንድ ያለውን አመኔታ የሚያሳድጉ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት በፋይናንስ ላይ የሚፈጸሙ ዓለም አቀፍ ወንጀሎችን ለመከላከል ከበርካታ ተቋማትና ሀገራት ጋር በትብብር የሚሰራ መሆኑ በስምምነቱ ወቅት ተጠቁሟል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *