የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጥር 30 ቀን 2014 ዓ.ም ባካሄደው ይፋዊ ህዝባዊ ስብሰባ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በኦዲት ግኝቶች ላይ እየወሰዳቸው ያሉ አበረታች የማስተካከያ እርምጃዎችን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገለጸ፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በሚኒስቴሩ ላይ ያካሄደው የ2012 በጀት ዓመት የሂሳብና የህጋዊነት ኦዲት ግኝቶች በመድረኩ ላይ ቀርበዋል፡፡
በገቢ ሂሳብ ረገድ ድምጽን፣ ምስልንና መረጃን ለማስተላፍ በሚኒስቴሩ ከሚሰጥ ፈቃድ ክፍያ ጋር ተያይዞ የገቢው ምክንያት ያልታወቀና የተመን መጠንን የሚገልጽ መመሪያ የሌለው ብር 4,181,965.29 ገቢ ተሰብስቦ መገኘቱ እና ዕለታዊ የውጭ ምንዛሬ ማስረጃ ያልቀረበበት በድምሩ ብር 3,621,318.73 የግል ቪሳት ፈቃድ እድሳት ገቢ የተሰበሰበ መሆኑ በኦዲቱ ተመልክቷል፡፡
በወጪ ሂሳብ በኩል በኮምፒዩተር ማደሻና ማሰልጠኛ ማዕከል የሚሰሩ ኮንትራት ሠራተኞች የትምህርትና የቅጥር ፎርማሊቲ ማስረጃ ያልቀረበለት በመሆኑ ለሰራተኞቹ የተከፈለውን ብር 433,068.70 ህጋዊነት ማረጋገጥ ያልተቻለ ሂሳብ እንዲሁም ተያያዥ የወጪ ማስረጃዎች ሳይቀርቡ የተመዘገበና የተወራረደ በድምሩ ብር 71,003,321.88 ወጪ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
በግዥ ረገድ የግዥ አዋጅና ደንብን ሳይከተል በጨረታ ግዥ ሊፈጸም ይገባ የነበረ የብር 9.3 ሚሊዮን በተመሳሳይ መልኩ በጨረታ ግዥ ሊገዛ ይገባው የነበረ የብር 1.8 ሚሊዮን ግዥ በዋጋ ማወዳደሪያ እንዲገዛ ተደርጓል፡፡ በሂሳብ አመዘጋገብ በኩልም ያለሂሳብ መደቡ የተመዘገበ ብር 13,095,333.78 ተገኝቷል፡፡
ከዚህም ሌላ መንግስት ለመንግስት ሰራተኞች የፐብሊክ ሰርቪስ ተሸከርካሪ አመቻችቶ እያለ ለሠራተኞች ሰርቪስ ተሽከርካሪዎች ኪራይ ብር 461,279.62 አላግባብ መፈጸሙን ኦዲቱ አሳይቷል፡፡
የወጪ ደረሰኞችና የውል ሰነዶች እንዲሁም የክፍያ የአገልግሎት ቁጥሮች ዝርዝር በኦዲቱ ወቅት ያልቀረበበት የብር 155,910,956.38 የአገልግሎት ክፍያ ለኢትዮ ቴሌኮም መፈጸሙ የተጠቀሰ ሲሆን ለኢንተርኔት አገልግሎትና የመስመር ስልኮች ክፍያ መፈጸሙ ቢገለጽም በኦዲቱ ወቅት የተፈጸመውን ክፍያ ትክክለኛነት ማረጋገጥ አልተቻለም፡፡ እንደዚሁም መ/ቤቱ ለኢንተርኔትና ለመስመር ስልክ የከፈለ ቢሆንም የክፍያ አሠራር ያልተዘረጋ በመሆኑ አገልግሎቱ ለመ/ቤቱ የዋለ መሆኑን ማረጋገጥ አልተቻለም፡፡
ከተክለብርሀን አምባዬ ህንጻ ተቋራጭ ጋር የብር 708,693,908.02 ውል የተፈጸመበት የቡራዩ ከተማ የልዩ ተሰጥኦና ተውህቦ ትምህርት ቤት ግንባታ በውሉ መሰረት ጊዜውን ጠብቆ ያልተጠናቀቀ ሲሆን ሚኒስቴር መ/ቤቱ በውሉ ላይ በተቀመጠው ጊዜ መሰረት ለኮንትራክተሩ በየደረጃው ያሰወቀበት ዝቅተኛ የስራ አፈጻጸም እና ውሉ ያልተቋረጠበት ምክንያት እንዲሁም የውል ጊዜው እንዲራዘም የተደረገበት ማስረጃና ሙሉ የጨረታ ሰነድ ሊቀርብ ባለመቻሉ በግዥ መመሪያ መሰረት የተፈጸመ መሆኑን ማረጋገጥ አልተቻለም፡፡ በተመሳሳይ መልኩ IE Network solutions Plc የሚሰራን ስራ የተመለከተ የብር 33,641,960.54 ሙሉ የጨረታ ሰነድ በኦዲቱ ወቅት ማቅረብ አልቻለም፡፡
በገቢ ሂሳብ ረገድ በፋይናንስ ደንብና መመሪያ መሰረት በወቅቱ ተሰብስቦ ያልተወራረደ ብር 614,701,418.01 መገኘቱና ከዚህ ውስጥ የብር 595,257,114.65 ተሰብሳቢ ሂሳብ በጊዜ ተለይቶ ከማን እንደሚሰበሰብ ትንተና ያልተደረገበት በመሆኑ ሂሳቡ ሳይወራረድ ለምን ያህል ጊዜ እንደቆየ ማወቅ አለመቻሉ እና በወቅቱ ለተከፋይ ባለመብት ተከፍሎ መወራረድ የነበረበት ብር 151,662,818.89 ተከፋይ ሂሳብ ሳይወራረድ መገኘቱና ሂሳቡ በተከፋይ የተያዘበትንና የሚከፈልበትን ጊዜ እንዲሁም ተከፋዩን ባለመብት የሚገልጽ ዝርዝር መረጃ ባለመቅረቡ ሂሳቡ ሳይከፈል ለምን ያህል ጊዜ እንደቆየ ለማወቅ አለመቻሉ በኦዲቱ ተገኝቷል፡፡
የንብረት አያያዝና አጠቃቀም በተመለከተም በተለያዩ ቦታዎች በሚገኙ የሚኒስቴር መ/ቤቱ መጋዘኖች ለጉዳትና ለብልሽት ተጋልጠውና የሚያገለግሉና የማያገለግሉ በአንድ ላይ ተቀላቅለው ጭምር የተቀመጡ የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ፣ የተሸከርካሪ፣ የቢሮና ለሌሎች አገልግሎቶች የሚውሉ በርካታ ንብረቶች ተገኝተዋል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው በቀረቡት የኦዲት ግኝቶች ላይ የተቋሙ ኃላፊዎች ማብራሪያ እንዲሰጡ ጠይቋል፡፡የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩን ክቡር ዶ.ር በለጠ ሞላን ጨምሮ በውይይቱ ላይ የተገኙ የሚኒስቴር መ/ቤቱ የስራ ኃላፊዎች ከኦዲቱ በኋላ በርካታ የማሻሻያ እርምጃዎች መወሰዳቸውን በማመላከት በቀረቡ ጥያቄዎች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
የግል ቪሳት የስርጭትና እድሳት ፈቃድ አገልግሎት ገቢ አሰባሰብ ጋር በተያያዘ የገቢ አሰባሰብ ስራው ቀድሞ በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በኩል የተመን መመሪያን መሰረት አድርጎ ይሰበሰብ እንደነበረና ሚኒስቴሩ ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር ከተዋሀደ ቧኋላ በተመኑ መሰረት ሳይሰበሰብ በመቆየቱ የተፈጠረ ችግር መሆኑን የስራ ኃላፊዎቹ ጠቅሰዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ለአገልግሎቱ ገቢ የመሰብሰቡ ስልጣን ለኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለስልጣን መሰጠቱን ገልጸው በማነስ ወይም በመብለጥ የተሰበሰበውን ሂሳብ በባለስልጣኑ በኩል እንዲታይ ስምምነት ላይ መደረሱን ገልጸዋል፡፡
ለኮምፒዩተር ማደሻና ማሰልጠኛ ማዕከል ኮንትራት ሠራተኞች የተከፈለውን ክፍያ በተመለከተ በቀድሞው የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከ15 ዓመታት በፊት በፕሮጀክት መልክ የተጀመረ ማዕከል መሆኑን ጠቅሰው የማዕከሉ ተግባር በግል ዘርፍ መከናወን እንዳለበት በመታመኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር የአብዛኞቹ ሰራተኞች ቅጥር ተቋርጦ ንበረቶችን የማስወገድ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
ለምርምርና ለሌሎች አገልግሎቶች የተከፈለውን 20.7 ሚሊዮን ብር አስመልክቶም በፊት በነበረው አሠራር ሂሳቡ የሚወራረደው በሪፖርት ብቻ መሆኑንና በአሁን ሰዓት ግን ይህን አሠራር በመቀየር እያንዳንዱ ተመራማሪ ለሰራው የምርምር ስራ ያወጣውን ወጪ በማስረጃ በማረጋገጥ እንዲወራረድ የሚያስችል ስርዓት መዘርጋቱን ጠቅሰው እስካሁንም የብር 3,681,526.48 መወራረዱንና ለዚህም ማስረጃ ማቅረባቸውን አመላክተዋል፡፡ ቀሪ ሂሳቦችን ለማወራረድ እንዲቻልም ኮሚቴ ተዋቅሮ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል የብር 9.3 ሚሊዮን የቀጥታ ግዥ መፈጸሙን የጠቀሱት የሚኒስቴር መ/ቤቱ ኃላፊዎች ከዚህ ውስጥ ብር 6.9 ሚሊዮን ለተለያዩ የቀጥታ ግዥዎች እንደዋለና ይህም ትክክል ባለመሆኑ በቀጣይ እንደሚታረም እንዲሁም ብር 1.7 ሚሊዮን በዳታ ማዕከል ያሉ ማቀዝቀዣዎች በመበላሸታቸው ምክንያት በተፈጠረው ከፍተኛ ሙቀት ሳቢያ መሳሪያዎች እንዳይበላሹና ሁኔታው አፋጣኝ መፍትሔ የሚፈልግ መሆኑ በመታመኑ በማኔጅመንት የቃለ ጉባኤ ውሳኔ የማቀዝቀዣ መሳሪያ በቀጥታ ግዥ መገዛቱን ጠቅሰው ብር 677 ሺህ ለጥበቃና ለጽዳት አገልግሎት በውስን ጨረታ ግዥ መፈጸሙን የተቀሱት ኃላፊዎቹ አሁን ግዥዎች በግልጽ ጨረታ እንዲፈተሙ እየተደረገ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
በሌላ በኩል ያለሂሳብ መደብ የተመዘገበውን ሂሳብ በተመለከተም ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር ወደፊት ሂሳቦችን በትክክለኛ መደባቸው እንዲመዘገቡ ለማድረግ እየሰሩ መሆኑንና የገንዘብ ሚኒስቴር ለኮምፒዩተርና ኤሌክትሮኒክስ እቃዎች አዲስ የሂሳብ መደብ ቢያዘጋጅም የኮምፒዩተርና ኤሌክትሮኒክ ቁሳቁሶችን አሁንም ድረስ በቀድሞው የሂሳብ መደብ እየመዘገቡ እንደሆነ አንስተዋል፡፡
መንግስት ያቀረበው የፐብሊክ ሰርቪስ ተሸከርካሪ እያለ ለሠራተኞች ሰርቪስ መጠቀሚያ ለሚሆኑ ተሸከርካሪዎች ኪራይ ያለአግባብ ተከፈለ የተባለው ክፍያ በውል ላይ ባለ ክፍተት የተፈጠረ መሆኑንና ተሽከርካሪዎቹ ለሰርቪስ የሚያገለግሉ ሳይሆኑ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ካለበት የተሽከርካሪ እጥረት አንጻር ሠራተኞች ለስራ ወደተለያዩ ቦታዎች ሲዘዋወሩ እንዲጠቀሙባቸው የተከራያቸው መሆናቸውንና ክፍያውም ለዚሁ ዓላማ የዋለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ለኢትዮ ቴሌኮም የተከፈለው ክፍያ የፌዴራል መ/ቤቶችን ጨምሮ ሌሎች በየደረጃው እስከታች ያሉ ተቋማትን በወረዳ ኔት ለማስተሳሰር ለተዘረጋ አገልግሎት ይከፈል የነበረ መሆኑንና ክፍያው ለሶስት ዓመታት ያህል ሳይከፈል ቆይቶ በአሁን ሰዓት 155 ሚሊዮን ብር በመክፈል ደረሰኝ ማቅረብ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡ ለኢንተርኔትና ለስልክ መስመር ዝርጋታ የወጣው ወጪም በሀገሪቱ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሲከሰት በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት አብዛኞቹ የሚኒስቴር መ/ቤቱ ሠራተኞች ቤታቸው ሆነው ስራ እንዲሰሩ ለማስቻል በቢሮ አካባቢ ሆነው የሠራተኞቹን ስራ በስልክና በኢንተርኔት ለሚከታተሉና የሰራተኞችን ደህንነት ለሚከታተሉ የኮሚቴ አባላት እንዲሁም ቤት ሆነው ለሚሰሩ ሰራተኞች የተፈጸመ የኢንተርኔት አገልግሎትና የስልክ ቀፎ ግዥ መሆኑን አንስተው በአሁን ሰዓት አገልግሎቱ ተቋርጧል ስልኮቹም በመመለስ ላይ ናቸው ብለዋል፡፡
የቡራዩ የልዩ ተሰጥኦና ተውህቦ ትምህርት ቤት ግንባታ በአከባቢው ተፈጥሮ በነበረው የጸጥታ አለመረጋጋትና በተቋራጩ የፋይናንስ አቅም ማነስ ምክንያት የግንባታ ማጠናቀቂያ ጊዜው መራዘሙን የጠቆሙት ኃላፊዎቹ ግንባታውን በፍጥነት ማጠናቀቅ እንዲቻል ዋናው ውል ሳይቋረጥ ከዋናው ኮንትራክተር ጋር የተፈጸመውን ውል እንደ ድልድይ በመጠቀም አሁን በዋናው ተቋራጭ ስር ከነበሩ ተቋራጮች ጋር ስምምነት ተፈጥሮ ግንባታው በጥሩ ደረጃ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በኦዲቱ ወቅት ሳይቀርቡ የቀሩት ሰነዶች በጨረታው ላይ የቀረበውን ቅሬታ ተከትሎ ሰነዶቹ ለግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ለማጣራት ተልከው ባቀማመጥ ችግር ምክንያት ባለመገኘታቸው በወቅቱ ማቅረብ አለመቻሉንና በአሁን ሰዓት የጨረታ ሰነዶቹን ቅጂዎችና ለኤጀንሲው ተልከው የነበሩትን ጭምር ማግኘት በመቻሉ የጨረታ ሰነዶቹ እንዲቀርቡ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡ ከIE Network solutions Plc ጋር የተያያዙት ሰነዶችም ተገኝተው መቅረባቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በተሰብሳቢና ተከፋይ ሂሳቦች አሠራር ላይ የተፈጠረው ችግር የቀድሞዎቹ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሲዋሀዱ የየራሳቸውን ሂሳቦች ለየብቻ በውስጥ ኦዲተሮቻቸው ሳያረጋግጡና ሳይመዘግቡ የሁለቱም ተቋማት ሂሳቦች እንዲቀላቀሉ በመደረጉ የተፈጠረ መሆኑን የጠቀሱት የስራ ኃላፊዎቹ ያልተሰበሰቡትን ሂሳቦች ለመሰብሰብ ጥረት መደረጉንና በዚህም 321 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡንና ቀሪውን ለማሰባሰብ ጥረትና ክትትል እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል፡፡ አክለውም ተከፋይ ሂሳብን በተመለከተ 19 ሚሊዮን ብር ለሚመለከተው አካል መከፈሉን ገልጸው የ131 ሚሊዮን ብር ከቀደሞው የኢንፎርሜሽን ኮሙኔኬሽም ሚኒስቴር የመጣና ሰነድ ያልተገኘለት በመሆኑ እንዲሁም ይከፈለኝ የሚል አካል ባለመቅረቡ ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር ሂሳቡ ከሂሳብ መዝገብ እንዲነሳ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በንብረት አያያዝና አጠቃቀም ዙሪያ የታዩትን የኦዲት ግኝቶች ለማስተካከልም ጥረት እየተደረገ መሆኑን ኃላፊዎቹ አንስተዋል፡፡ ዋናው መ/ቤትን ጨምሮ በተለያዩ ስፍራዎች በሚገኙ መጋዘኖች የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችን ጨምሮ ሌሎች ንብረቶች መቀመጣቸውን ገልጸው አገልግሎት የሚሰጡትን ጎማዎች፣ ላፕቶፕ ኮምፒውተሮች እና ወንበሮች በስራ ላይ እንዲውሉ ማድረጋቸውንና የሚወገዱትን፣ በስጦታ የሚተላለፉትን እና ተስተካክከለው ለመ/ቤቱ አገልግሎት መዋል የሚችሉትን በመለየት ንብረቶቹን አቅጣጫ ለማስያዝ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ አያይዘውም የሞዴል 19 እና 22 እንዲሁም የቢን ካርድ አሠራር መስተካከሉንና በመ/ቤቱ አዲስ ዲጂታል ስርዓት በመፍጠር የግዥ፣ የጨረታ፣ የንብረት እና ሌሎች አሠራሮችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለማከናወን ጥረት እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በሚኒስቴር መ/ቤቱ የስራ ኃላፊዎች ምላሾችና በኦዲት ግኝቶቹ ላይ በመመሰርት አስተያየቶቻቸውን የሰጡት የቋሚ ኮሚቴ አባላትና ባለድርሻ አካላት ተቋሙ የኦዲት ግኝቶቹን ለመቅረፍ እየወሰዳቸው ያሉ እርምጃዎች የሚበረታቱ መሆኑን ጠቁመው ቀሪዎቹን ችግሮች ለመቅረፍና ክፍተቶች እንዳይደገሙ ለማድረግ ቀጣይ ጠንካራ ጥረት መደረግ ይገባዋል ብለዋል፡፡ ግኝቶቹንና የማሻሻያ አስተያየቶቹን መሰረት ያደረገ የድርጊት መርሀ ግብር በማዘጋጀትና በዕቅድ ውስጥ በማካተት የተሻለ አሠራር መፍጠር እንደሚያስፈልግ ያነሱት የቋሚ ኮሚቴ አባላትና ባለድርሻ አካላቱ በአግባቡ በስራ ላይ መዋል ያለበት የመንግስት ሀብት እንዳይባክንና በደንብና በሥርዓት በመመራት ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ሚኒስቴር መ/ቤቱ ኃላፊነት ያለበት መሆኑን ጠቅሰው ከዚህ በፊት ለተፈጠሩ ጥፋቶች ምክንያት የሆኑ አካላት ተለይተው ተጠያቂ መሆን ይገባቸዋል ብለዋል፡፡ አክለውም ግኝቶቹ በከፍተኛ ደረጃ የሚታዩ በመሆናቸው በተለይ በተሰብሳቢና በተከፋይ ሂሳብ አሰራሮች፣ በግዥ ስርዓት፣ በሂሳብ አመዘጋገብና ሌሎች አሠራሮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባና ተቋሙ አበረታች ጅምሩን የበለጠ በማጠናከር ካለበት ተቀባይነትን ከሚያሳጣ የኦዲት ግኝት ደረጃ መውጣት እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የኦዲት ዘርፍ ምክትል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ በበኩላቸው በኦዲት ግኝቶቹ ላይ እርምጃ በመውሰድ ረገድ አበረታች ጅምሮች መኖራቸውን ጠቅሰው የቀሩ ክፍተቶችና አስካሁን ድረስ የቀጠሉ ችግሮች በመኖራቸው ቀጣይ የማሻሻያ እርምጃዎች ከሚኒስቴር መ/ቤቱ ይጠበቃል ብለዋል፡፡ ላለፉት ስህተቶች ምክንያት የሆኑ አካላት ተጠያቂነት መረጋገጥ ያለበት መሆኑን ያነሱት ምክትል ዋና ኦዲተሯ ህግን ያልተከተለ ከአንድ አቅራቢና አልፎም ፈቃድ ከሌላቸው አካላት የሚፈጸም የቀጥታ ግዥ አሠራር ለግብር ስወራ መንስኤ ስለሚሆን ትኩረት ሊደረግበት እንደሚገባ አሳስበው የቀጥታ ግዥ የመጨረሻ የግዥ ሥርዓት አማራጭ በመሆኑ አስገዳጅ ምክንያት ካለም የግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲን በማስፈቀድ መፈጸም እንደሚኖርበት አሳስበዋል፡፡ አክለውም ግዥዎች በዕቅድ መመራት ያለባቸው መሆኑን ጠቅሰው በተሰብሳቢና ተከፋይ ሂሳቦች፣ በግዥ አፈጻጸም፣ በንብረት አያያዝና አጠቃቀም እና በሌሎቹም ረገድ የታዩና ያልተስተካከሉ ግኝቶችን ማስተካከል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ አራሬ ሞሲሳ በሰጡት አስተያየት ሚኒስቴር መ/ቤቱ የኦዲት ግኝቶቹን ለማስተካከል እያደረገ ያለው ጥረት ለሌሎች ተቋማት በምሳሌነት የሚጠቀስ መሆኑን አንስተው ቀሪ ክፍተቶችን ለመቅረፍ ከፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤትና ከመድረኩ የተሰጡ አስተያየቶችን በመውሰድና በጥፋተኞች ላይ ተጠያቂነትን በማረጋገጥ የማሻሻያ እርምጃዎችን የበለጠ ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ክርስቲያን ታደለ በሰጡት የማጠቃለያ ሀሳብ ተቋሙ የሀገሪቱን የአሥር ዓመት መሪ ዕቅድ በማሳካት ረገድ ትልቅ ድርሻ ያለው እንደመሆኑ ብዙ የሚጠበቅበት መሆኑን ጠቅሰው ለሌሎች ተቋማት አዳዲስና ዘመናዊ አሠራሮች መጎልበትም ሚናው ከፍተኛ በመሆኑ በተሻለ ተነሳሽነትና የአሠራር ቅልጥፍና ላይ መገኘት ይገባዋል ብለዋል፡፡
ሚኒስቴር መ/ቤቱ በኦዲት ግኝቶቹ ላይ እየወሰዳቸው ያሉ የማሻሻያ እርምጃዎች አበረታች መሆናቸውን የጠቀሱት ሰብሳቢው እርምጃ ያልተወሰደባቸው ግኝቶችን በቀጣይ ማስተካከል የሚያስፈልግ መሆኑን አመላክተው የተሰጡ አስተያየቶችን መሰረት ያደረገ የድርጊት መርሀ ግብር በአጭር ጊዜ ውስጥ ተዘጋጅቶ እንዲቀርብና የእቅድ አካል በማድረግ ሪፖርት እንዲደረግ ለሚኒስቴር መ/ቤቱ አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡ በተጨማሪም የቋሚ ኮሚቴ አባላት የሚኒስቴር መ/ቤቱን የማሻሻያ እርምጃ አፈጻጸም እንዲከታተሉና ባለድርሻ አካላትም ተጠያቂነትን የማስፈን እርምጃዎችን ጨምሮ በሚመለከታቸው ጉዳዮች ዙሪያ ድጋፍና ክትትል እንዲያደርጉ በአጽንኦት አሳስበዋል፡፡