የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ በኦዲት የታዩበትን ግኝቶች ለማስተካከል እየሰራቸው ያሉ ስራዎችን በበለጠ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በዩኒቨርስቲው የ2010 በጀት አመት ሂሳብ ላይ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ያካሄደውን ኦዲት መሰረት በማድረግ ጥር 22/2012 ዓ.ም ባካሄደው ይፋዊ ህዝባዊ ስብሰባ ላይ አሳሰበ፡፡
በስብሰባው ላይ በዩኒቨርስቲው ላይ የተገኙ የኦዲት ግኝቶች በዝርዝር ቀርበዋል፡፡
ከግኝቶቹ መካከል የክፍያ ተመን ሳይኖር ዩኒቨርስቲው የተማሪዎችን ጥናታዊ ጽሁፎች ለገመገሙ መምህራንና ከዩኒቨርስቲው ውጪ ለሚመጡ ፈታኞች በድምሩ 812 ሺህ ብር መክፈሉ እና በዩኒቨርስቲው ከሚያስተምሩ ህንዳውያን መምህራን መሰብሰብ የነበረበትን የገቢ ግብር ብር 1.14 ሚልየን ሳይሰበስብ መቅረቱ ይገኙበታል፡፡
ከዚህም ሌላ የሀገሪቱ ህገመንግስት ትርፍ በማያስገኙ ተግባራት በተሰማሩ የፌዴራልና የክልል መንግስታት አካላት ንብረት ላይ አንዳቸው በሌላኛቸው ላይ ግብር ወይም ቀረጥ እንደማያስከፍሉ የተደነገገውን በመጣስ ዩኒቨርስቲው ለባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ብር 2.83 ሚልየን ለመሬት ግብርና ለሌሎች ጉዳዮች አላግባብ ከፍሎ ተገኝቷል፡፡
ከግዥ ጋር በተገናኘም በግዥ አዋጁ የተደነገገውን የግልጽ ጨረታ ስርአትን ተከትሎ መግዛት ሲገባው የብር 11 ሚልየን የቀጥታ ግዢ መፈጸሙ በኦዲቱ ተመልክቷል፡፡
ዩኒቨርስቲው ለህንጻ ግንባታ ተቋጮች በውል ሰጥቶ ከሚያሰራቸው ስራዎች ጋር በተያያዘም አለማየሁ ከተማ የተባለ ህንጻ ተቋራጭ ውሉን ሲያቋርጥ ዩኒቨርስቲው ለተቋራጩ በቅድሚያ ክፍያ መልክ የሰጠውን 760 ሺህ ብር አለመሰብሰቡና ዩኒቨርስቲው በተቋራጩ ላይ ክስ መስርቻለሁ ቢልም ክስ ስለመመስረቱ ማስረጃ ማቅረብ አለመቻሉ ተገልጿል፡፡ በተመሳሳይ ኤ.ቢ.ኤም የተባለ ሌላ የግንባታ ተቋራጭ ስራውን ሲያቋርጥ የተሰጠው የቅድሚያ ክፍያ ብር 10.2 ሚልየን ሳይሰበሰብ ቀርቷል፡፡ እንደዚሁም ዩኒቨርስቲው ዮሴፍ ተከተል ከተባለ የህንጻ ስራ ተቋራጭ ያልሰበሰበው 1.1 ሚልየን ብር እንዳለና ብር 1.09 ቢልየን ወጪ የተደረገባቸው ህንጻዎች ደግሞ አገልግሎት እየሰጡ አለመሆኑን ኦዲቱ አሳይቷል፡፡
በሌላ በኩል ከመደኛ በጀት ወጪ የተደረገና ሳይሰበሰብ የቀረ ብር 3.1 ሚልየን እንዳለና ለሚመለከተው አካል መከፈል ሲገባው ካልተከፈለ ብር 111.4 ሚልየን ውስጥ በጊዜው ያልተወራደ 2.9 ሚልየን ብር እንዳለ በኦዲቴ ታይቷል፡፡
ከንብረት አያያዝ ጋር ተያያዘም በዩኒቨርስቲው የተለያዩ ኮሌጆች ያለስራ የተቀመጡ ልዩ ልዩ ንብረቶች መኖራቸውን፣ ያልተወገዱ ጊዜ ያለፈባቸው መድሀኒቶችና ኬሚካሎች መገኘታቸውን እንዲሁም የንብረት ቆጠራ መረጃው በስቶክ ካለው ጋር የሚለያይ መሆኑ ታውቋል፡፡
በዩኒቨርስቲው ውስጥ በንግድ ስራ የተሰማሩና የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚሰጡ 27 ጅርጅቶች/ግለሰቦች እንዳሉና ከአንድ አመት በላይ ሲሰሩ ለዩኒቨርስቲው ምንም አይነት ገቢ እንዳላደረጉም ኦዲቱ አሳይቷል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው በአዲት ግኝቶቹና ግኝቶቹን ለማረም በተወሰዱ እርምጃዎች እንዲሁም የውስጥ ቁጥጥርን በማጠናከር ዙርያ ስለተሰሩ ስራዎች ዩኒቨርስቲው ማብራሪያ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡
የዩኒቨርስቲው የአስተዳደር ጉዳዮች ምክትል ፕሬዘዳንት ረዳት ፕሮፌሰር ብርሀኑ ገድፍ እና ሌሎች የስራ ኃላፊዎች በግኝቶቹ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
የስራ ሀላፊዎቹ በ2010 እና አስቀድሞ በነበሩ በጀት አመቶች በዩኒቨርስቲው ውስጥ ከፍተኛ ግጭት ተፈጥሮ እንደነበረና የአመራሩም ትኩረት ችግሩን በመፍታት ላይ እንደነበረ አስታውሰዋል፡፡
በመቀጠልም ስለግኝቶቹ ሲያብራሩ ያለተመን ለመምህራንና ለፈታኞች ሲከፈል የነበረው በወቅቱ የወጣ ተመን ባለመኖሩ ምክንያት እንደሆነና ነገር ግን ሌሎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚከፍሉትን መጠን በማጥናት ዝቅተኛ ክፍያ በስራ አመራሩ እያጸደቀ ሲከፍል እንደነበረ ገልጸዋል፡፡ በመንግስት የክፍያ ተመን ከተዘጋጀ ወዲህ ግን በተመኑ መሰረት እየተከፈለ ነው ብለዋል፡፡
የህንዳውያን መምህራንን የስራ ግብር በተመለከተም ከኦዲት ግኝቱ በኋላ በዩኒቨርሲቲው ካሉ መምህራን የገቢ ግብር እየቆረጠ እንዳለ እና እስካሁን ድረስ በዩኒቨርስቲው ካሉት መምህራን 436 ሺህ ብር ለማስመለስ እንደተቻለ ገልጸዋል፡፡ ሆኖም የተወሰኑ መምህራን ተመልሰው ወደ ሀገራቸው በመሄዳቸው ምክንያት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር ግንኙነት በማድረግ ቀሪውን ማስመለስ እንዳለበት ዩኒቨርሲቲው እንደተቀበለ አስረድተዋል፡፡
ለባህር ዳር ከተማ ከከፈለው ግብር ጋር በተያያዘም የከተማ አስተዳደሩ ዩኒቨርስቲው የተጠየቀው ግብር እንዲከፍል ሳይሆን የከተማ መሬት መጠቀሚያ ክፍያ እንደሆነና ይህም ህጋዊ መሰረት አለው በሚል የከተማ አስተዳደሩ እንደገለጸ አስረድተዋል፡፡ ይህንን ሲያስረዱም በከተማ ቤትን በሊዝ ስለመያዝ በወጣው በተሻሻለው የክልል ከተሞች እንደገና ማቋቋሚያ፣ ማደራጃና ስልጣንና ተግባር መወሰኛ አዋጅ ቁጥር 245/2009 አንቀጽ 11 መሰረት በከተማ ክልል ውስጥ የሚገኘውን መሬትና የተፈጥሮ ሀብት በህግ መሠረት የማስተዳደርና የማልማት ስልጣን ለከተሞች የተሰጠ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ከከተማ መሬት ኪራይ ክፍያ ነፃ ያልተደረገ መሆኑን እንዲሁም በ2008 ዓ.ም በወጣው በከተሞችና ማዘጋጃ ቤቶች የገቢ አርዕስቶች መወሰኛ ደንብ መሠረት ከተሞች ለሚሰጡት የተለያዩ አይነት አገልግሎቶች ከተጠቃሚዎች ላይ የአገልግሎት ክፍያዎችን የመሰብሰብ ስልጣን የተሰጣቸው በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ከህግ ውጪ የተጠየቀ አለመሆኑን የከተማ አስተዳደሩ መግለጹን አስረድተዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ወቅት አጣብቂኝ ውስጥ እንዳለና ችግሮች እንዳይፈጠሩበት በሚል ክፍያውን ማቆም እንዳልቻለ ገልጸዋል፡፡ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ለጉዳዩ መፍትሄ መስጠት እንዳለባቸው ገልጸው ምክር ቤቱም ጉዳዩን እንዲስተካከል አቅጣጫ እንዲሰጥበት ጠይቀዋል፡፡
ከቀጥታ ግዢው ጋር በተገናኘም ከ11 ሚልየን በር ውስጥ የብር 6.1 ሚልየን የቀጥታ ግዥ የተፈፀመው ዩኒቨርሲቲው ካቋቋመው የህትመት፣ የእንጨትና የብረታ ብረት ኢንተርፕራይዝ እንደሆነና የተገዙትም ለዩኒቨርሲቲው አገልግሎቶች በፍጥነት መድረስ ያለባቸው የህትመትና የእንጨት ሥራዎች እንደሆኑ ገልፀዋል፡፡ ከዚሁ ጋር አይያዘውም ዩኒቨርሲቲው 8 ኮሌጆች ያሉት ከመሆኑና ከሚከተለው ያልተማከለ አስተዳደር ሥርዓት በተነሳ እንዲህ ዓይነት ግዥዎች በየቦታው እንዳይፈፀሙ በማሰብ እንዲሁም በግዥ አዋጁ አስቸኳይ የሆኑ ግዥዎችን የተቋሙ ሀላፊ ካመነበት መፈጸም እንደሚቻል መፈቀዱን መሰረት በማድረግ ለተማሪዎች አገልግሎትና ለመማር ማስተማር ስራ ለሚውሉ አንገብጋቢ የህትመት፣ የጥገናና ሌሎች ጉዳዮች ለዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ቀርበው ግዢዎች መፈጸማቸውን አስረድተዋል፡፡ የህትመቶችን ጥራትና ሚስጥራዊነትን ለማስጠበቅ በቀጥታ ግዥ ከኢንተርፕራይዝ እንዲገዛ ማድረጉንም አክለዋል፡፡ ለነዚህ አጣዳፊ ተግባራት ከዋለው ገንዘብ ውጪ ቀሪው የ5.5 ብር ግዥ አስቀድሞ መታቀድ ይችል እንደነበረ ዩኒቨርሲቲው እንደሚያምንና ዩኒቨርስቲውም በርካታ ግዥዎችን በግልጽ ጨረታ እንደሚፈጽም ተናግረዋል፡፡
የተቋረጡ ግንባታዎችን አስመልክተው ሲገልጹም የአለማየሁ ከተማ ህንጻ ተቋራጭ የውል ማቋረጥ ሂደቱ 2 ዓመት መውሰዱን ገልጸዋል፡፡ ይህን የማጠናቀቅ ስልጣን የፕሮጀክቱ አማካሪ እንደሆነና ውሉ ሲቋረጥ የነበሩ ሥራዎችን፣ በግንባታ ስፍራው ላይ የነበሩ የግንባታ ግብዓቶችንና በወቅቱ ባለው የገበያ ዋጋ ለፕሮጀክቱ ባለቤት ሊመለስ የሚገባውን ገንዘብ አጥንቶ ማቅረቡንና በቅድሚያ ክፍያ መልክ ለተቋራጩ ተከፍሎ የነበረውን ገንዘብ ለተቋራጩ ሊከፈሉ ይገቡ ከነበሩት የተለያዩ ሂሳቦች ውስጥ ተቀናሽ ማድረግ እንደሚቻል መግለጹን አስረድዋል፡፡ በዚህ መሰረትም ዩኒቨርስቲው ስራውን ለተቋራጩ ሲሰጥ ተቋራጩ አስይዞት የነበረው የኢንሹራንስ ማስተማመኛ እንዲሰጠው ዩኒቨርስቲው የኢንሹራንስ ካምፓኒውን መጠየቁንና ባለመፍቀዱ ተቋራጩ ላይ ክስ መመስረቱን ገልፀዋል፡፡ ክስ ለመመስረቱ በኦዲቱ ወቅት ሳያቀርቡት የቀሩትን ማስረጃ ማምጣታቸውንም ገልጸዋል፡፡
ኤ.ኤም.ቢ የህንፃ ተቋራጭ ድርጅትን በተመለከተ ጉዳዩን ለረጅም ጊዜ ሲንከባለል የቆየ እንደሆነና አማካሪ ድርጅቱ ወደ ዩኒቨርሲቲው ሊመለስ የሚገባ 10.2 ሚሊዮን እንዳለ መግለጹን ጠቅሰው ስራው ለሌላ ተቋራጭ መሰጠቱንና ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ ጉዳዩን ወደ ህግ ለመውሰድ በእንግሊዝኛ የተዘጋጁትን የውል ሠነዶች ወደ አማርኛ የማስተርጎሙ ሂደት ጊዜ መውሰዱንና አሁን ግን ዩኒቨርስቲው የደረሰበት ጉዳት በወቅታዊው ዋጋ ተሰልቶ የ57 ሚልየን ብር ክስ መመስረቱን ተናግረዋል፡፡
የዮሴፍ ተከተል የህንፃ ተቋራጭ ጉዳይም በወቅቱ በነበረው የሲሚንቶ ዋጋ መናር ምክንያት ተቋራጩ የገንዘብ እጥረት እንዳጋጠመውና በአማካሪው ድርጅት በኩል ቁጥጥር የሚደረግበት ለሲሚንቶ ግዥ የሚውል ገንዘብ እንዲሰጠው በጠየው መሰረት በዩኒቨርስቲው ተፈቅዶ ገንዘቡ እንደተሰጠው ገልጸው ሆኖም ግን በሂሳብ መዝገብና አከፋፈል ላይ የነበሩ ከፍተቶች እንደነበሩ አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም ግንባታው ሲጠናቀቅ ለተቋራጩ የሚሰጡ የመጨረሻ ክፍያዎች እንዲሁም በግንባታው ላይ እስከአንድ አመት ድረስ ለሚደርስ ጉዳት በመጠባበቂያነት ዩኒቨርስቲው ቀንሶ የሚያስቀረው ገንዘብ (retention) እንዲያዝና ወደ ዩኒቨርሲቲው እንዲገባ በዝግጅት ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በብር 1,09 ቢልየን የተገነቡ የሆስፒታልና የተማሪዎች ማደሪያ ህንጻዎችም ተጠናቀው ወደስራ እንዲገቡ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
በተከፋይ ካለው 2.9 ሚልየን ብር ውስጥ አንዳንዶቹ በፍርድ ቤት ይከፈል የሚል ትዕዛዝ እስኪሰጥባቸው የሚጠብቁ እንደሆኑ፣ 134 ሺ ብር ከአንድ ስራ ተቋራጭ የተያዘ የretention ገንዘብ እንደሆነና ተቋራጩ ይህንን ገንዘብ ባለመጠየቁና ከገበያ በመውጣቱ ለዩኒቨርስቲው ገቢ እንደተደረገ እንዲሁም ከሌላ ተቋራጭ የተያዘ 35 ሺህ ብር እንዳለ ገልጸዋል፡፡
ከተሰብሳቢ ሂሳቦች ጋር ተያይዞ አብዛኛው ተሰብሳቢ ሂሳብ ከፍተኛ የኮንስትራክሽን ሥራዎች ገና በሂደት ላይ ያሉ በመሆናቸው የተፈጠሩ እንደሆኑ ገልጸው በየጊዜው እየቀነሱ እንደሚሄዱና እስከ 2010 ከነበረው ተሰብሳቢ ሂሳብ ውስጥ በ2011 በጀት ዓመት በድምሩ ወደ ብር134,961,742.23 መሰብሰቡን፤ ከውስጥ ገቢ ደግሞ ከተሰብሳቢው ብር 3.1 ሚሊዮን ውስጥ ብር 1,6 ሚልየን ተወራርዶ ብር 1.48 ሚሊዮን በቀጣይ ለማስመለስ ወደ ሌላ አካባቢ ሄደው በዛው የለቀቁ ዬኒቨርስቲ መምህራንን ጨምሮ የቅድሚያ ሂሳብ የተከፈላቸውን አካላት እያፈላለገ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
ከንብረት ጋር በተያያዘ እንደ ምግብ ማብሰያ ያሉ አንዳንድ ንበረቶች በጣም የቆዩ በመሆኑ መለዋወጫ የማይገኝላቸው መሆናቸውንና ለተማሪዎች ልምምድ በማዋል ለማስወገድ መታቀዱን፣ በየጊዜው ተገዝተው የሚተራርፉ በሂደትም በአዲስ አይነት የሚተኩ ንብረቶች መኖራቸውን እነዚህንም ለታለመላቸው ተጠቃሚ ሰራተኛች ለማስተላለፍ ወይም በእርዳታ መልክ ለማስወገድ መታቀዱን ገልጸዋል፡፡ ካለስራ የተቀመጡ የህክምና መሳሪያዎችም ወደ አዲሱ የዩኒቨርስቲው ሆስፒታል እንዲገቡ መደረጉን ገልፀዋል፡፡ አብዛኞቹ የማይሰሩ UPS እንዲወገዱ መደረጉን ተጠግነው መስራት የቻሉትም ጥቅም ላይ መዋላቸውን ገልጸዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የተጠራቀሙ እንዲሁም ዋጋቸው የማይታወቅ በርካታ ንብረቶች ተከማችተው እንደነበሩ ገልፀው በካይዘን አሰራር የማጥራት ስራ መሠራቱን፤ የሚወገዱ መድኃኒቶችን ከክልል ጤና ቢሮ ጋር በመሆን ለማስወገድ ኮሚቴ መቋቋሙን፣ ሌሎች ኬሚካሎችን ከዩኒቨርሲቲ መምህራን ጋር በመነጋገር በተወሰነ ደረጃ የማስወገድ ስራ መሰራቱንና ቀሪ ስራዎች እንዳሉ አስረድተዋል፡፡
በዩኒቨርስቲው ውስጥ እየሰሩ ስላሉ አገልግሎት ሰጪዎች ሲገልጹም በአነስተኛና ጥቃቅን ማህበራት የተደራጁና ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በዝቅተኛ ዋጋ የተለያዩ አገልግሎቶች የሚሰጡ ወጣቶች እንዳሉና በዩኒቨርስቲው ስልጠና ተሰጥቷቸው ወደስራ የገቡ በመሆኑ የስራ እድል መፍጠሪያና የማህበረሰብ አገልግሎት አካል ተደርጎ በዩኒቨርሲቲው እንደሚወሰድ ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ዩኒቨርሲቲው ከነርሱ ገቢ የመሰብሰብ እቅድ እንደሌለው፣ ወጣቶቹ ለዩኒቨርሲቲው ፀጥታና ደህንነትም ድጋፍ እንደሚሰጡ፣ ኪራይ እንዲከፍሉ ቢደረጉም በዩኒቨርስቲው ካፍቴሪያ የማይጠቀሙ ተማሪዎች ላይ የዋጋ ጭማሪ እንደሚያስከትል ተናግረዋል፡፡ ሆኖም ከነዚህ በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው ከሚሰሩ ወጣቶች ውጪ ያሉ ሌሎች ከፍ ያለ አገልግሎት በዩኒቨርስቲው ውስጥ እየሰጡ ያሉ አካላትን ኪራይ ለማስከፈል እንዲለዩ ተደርጎ፣ ኮሚቴ ተዋቅሮና መመሪያ ተዘጋጅቶ የውል ጊዜያቸው እስከሚያልቅ ድረስ እየተጠበቀ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የውስጥ ቁጥጥርን በተመለከተም በዩኒቨርስቲው የውስጥ ኦዲተር እንዲሁም የፀረ ሙስና ዳይሬክቶሬት እንዳለ አሁን ደግሞ የግልፅነትና ተጠያቂነት መመሪያ በማዘጋጀትና ኮሚቴ በማቋቋም የበጀት አጠቃቀምን የሚያሳይ መረጃ የማውጣት ስራ መጀመሩን የኦዲት ግኝቶችንም ለሠራተኛውና ለሚመለከታቸው አንዲደርስ ኮሚቴ ተደራጅቶ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው አባላት በተሰጠው ማብራሪያ ላይ እንደገና የተለያዩ ጥያቄዎችን አቅርበዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የለቀቁ የህንድ መምህራን አሁን አፈላልጎ ለማስከፈል ከመሞከር ይልቅ ቀድሞውኑ ሳይሄዱ በፊት የገቢ ግብር ለምን ማስከፈል አልተቻለም፣ ዩኒቨርሲቲው ለክልሉ የሚሰጠው በርካታ ጥቅም እንዳለ በመግለጽ ከክልሉ መንግሥትና ከከተማ አስተዳደሩ ጋር ለምን ለመደራደር ጥረት አልተደረገም፣ በተሰብሳቢ ሂሳብ ረገድ ያልተሰበሰበው ቀሪ ሂሳብ ያልተሰበሰበበት ምክንያት ምንድነው፣ እንደተከፈለ ከተገለፀው ተከፋይ ሂሳብ ወጪ ቀሪው ከ2.8 ሚሊዮን ብር በላይ ያለው ሂሳብ ለምን አልተከፈለም፤ ዩኒቨርሲቲው እንደ ምርምር ተቋምነቱ የራሱንም ሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለውን የኬሚካል አወጋገድ ችግር ለመፍታት ምን ሰራ፣ አስቸኳይ ግዥ ከተባለው ውስጥ የህትመት ስራ ዋነኛው የዩኒቨርስቲው ስራ ሆኖ ሳለ ለምን አስቀድሞ አልታቀደም ወዘተ. የሚሉ ይገኙበታል፡፡
ከባለድርሻ አባላት በኩልም እንደ ጥገና ያሉ አስፈላጊ ተግባራት ቀድሞ ጨረታ በማውጣት አገልግሎቱ ሲፈለግ በአሸናፊው ድርጅት እንዲጠገን ማድረግ ይቻል እንደነበረ፣ በቅድሚያ ክፍያ ለህንጻ ለተቋራጭ የሚሰጥ ገንዘብ ከፍተኛ በመሆኑ በሪቴንሽን መልክ በሚያዝ ዝቅተኛ ገንዘብ ለማወራረድ የታሰበው አሰራር ትክክል እንዳልሆነ እንዲሁም የክልል ከተሞች አስተዳደርና ዩኒቨርሲቲዎች በመሬት አጠቃቀም ክፍያ ዙርያ ያሉበትን ሁኔታ ምክር ቤቱ ለመፍታት ጥረት ማድረግ እንዳለበት አስተያየት ተሰጥቷል፡፡
በነዚህ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ላይ የዩኒቨርስቲው የስራ ኃላፊዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ በሰጡት አስተያየት ከህንድ መምህራን ጋር በተያያዘ ችግሩ በዩኒቨርስቲው ምክንያት ብቻ የተፈጠረ ሳይሆን ገንዘብ ሚኒስቴር ተደራራቢ ታክስ ስምምነት ከተለያዩ ሀገራት ጋር ሲፈራረም ወድያውኑ ለሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ባለማሳወቁ የመጣ ጭምር እንደሆነ ገልጸው በዩኒቨርስቲው ካሉት ህንዳውያን መምህራን ተቀንሶ የተሰበሰበው የገቢ ግብር ለገቢዎች ሚኒስቴር ፈሰስ መደረግ አለበት ብለዋል፡፡
ከመሬት አጠቃቀም ግብር ጋር በተገናኘም ችግሩ በአማራ ክልል ብቻ እንዳለ ገልጸው ህገ መንግሥቱ በአንቀጽ 100 ላይ ለትርፍ የተቋቋመ ካልሆነ በስተቀር ክልሎች በፌዴራል መንግሥት ንብረት ላይ እንዲሁም የፌዴራል መንግስት በክልሎች ንብረት ላይ ግብርና ቀረጥ መጣል እንደሌለባቸው በግልጽ የሚያስቀምጥ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ለባህር ዳር ከተማ አስተዳደር እየፈፀመው ያለው ክፍያ አግባብ አይደለም ብለዋል፡፡ አያይዘውም የህገ መንግሥት ትርጉም የሚሻ ከሆነ በሚል የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ጉዳዩን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በደብዳቤ ማሳወቁንና ለህገ መንግሥት አጣሪ ጉባኤ መመራቱን ገልፀዋል፡፡
ዩኒቨርስቲው የፈጸመውን የቀጥታ ግዥ በተመለከተ ከአንዳንድ አጣዳፊ ጉዳዮች ውጪ ሌሎቹ ግዢዎች ቀድሞውኑ በእቅድ ተይዘው ሊፈጸሙ ይችሉ ነበር፣ የተሰሩት የህትመት ስራዎችም ሚስጢራዊ አልነበሩም ብለዋል፡፡ ለአብነትም የኪችን ፈርኒቸር ግዥ አጣዳፊ እንዳልሆነና የርቀት ትምህርት ሞጁል ህትመትም ሚስጢራዊ እንደማይባል ጠቅሰዋል፡፡ የአጣዳፊ የጥገና ስራ ግዢ እንደተፈጸመ ከተገለጸውም ውስጥ ሁሉም አስቸኳይ እንዳልሆኑና አስቀድሞ ጨረታ በማውጣት አገልግሎት ሰጪውን ማዘጋጀት ይቻል እንደነበረ ጠቅሰዋል፡፡ ከዚህ ሌላም መንግስት ላወጣው ገንዘብ በአነስተኛ ዋጋ ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኝ ለማድረግ የዩኒቨርሲቲው ኢንተርፕራይዝ እንደማንኛውም ነጋዴ ተወዳድሮ ስራው ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡ ቀጥታ ግዥውም ከዩኒቨርሲቲው ኢንተርፕራይዝ ብቻ ሳይሆን ከሌሎችም አካለት ጭምር የተፈፀመ ነው ብለዋል፡፡ በመሆኑም ከግዥ አሰራሩ ጋር ያሉ ጉዳዮች መስተካከል አለባቸው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ውል ካቋረጡ ተቋራጮች ጋር ስላለው ጉዳይ ክቡር ዋና ኦዲተሩ ሲገልጹም የግንባታ ስራ 80% ሲደርስ በቅድሚያ ክፍያ ተሰጥቶ ከነበረው ገንዘብ ውስጥ ተመላሽ ሳይደረግ የሚቀር ገንዘብ ሊኖር እንደማይችል ገልጸው ሁኔታው የተፈጠረበትን ምክንያት ዩኒቨርሲቲው ሊያጣራ ይገባል ብለዋል፡፡ በቅድሚያ ክፍያ መልክ የተሰጠው ገንዘብ ከፍተኛ ስለሆነ ተቋራጮች ዝቅተኛ መጠን ያለው የረቴንሽን ገንዘብ እንዲመለስላቸው እንደማይጠይቁ በማስረዳት በሪቴንሽን መልክ የተያዘን ገንዘብ ላልተመለሰ ቅድሚያ ክፍያ ማካካሻ ለማዋል መሞከሩ ትክክል እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡
ክቡር አቶ ገመቹ ተሰብሳቢና ተከፋይ ሂሳብ ላይ ክትትል መደረግ እንዳለበትና ለንብረት አያያዝና አወጋገድ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ በዩኒቨርስቲው ውስጥ ለመንግስት ምንም ገቢ ሳያስገቡ የሚሰሩ አገልግሎት ሰጪዎችን በተመለከተም የግብር ከፋይ ገንዘብ ወጥቶበት የተሰራ በመሆኑ የተወሰኑ ግለሰቦች መጠቀሚያ ሊሆን አይገባም፣ በነፃ እንዲገለገሉበት መደረጉም ትክክል አይደለም ብለዋል፡፡
በመጨረሻም ዩኒቨርስቲው ሁለንተናዊ ለውጥ ለማምጣት ከ2010 በጀት አመት ኦዲት በፊት ያሉ የኦዲት ግኝቶችን ጭምር በመቃኘት የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
በቋሚ ኮሚቴው የክዋኔ ኦዲት ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ ወይንሸት ገለሶ በሰጡት ማጠቃለያ ዩኒቨርስቲው ትኩረት ሰጥቶ የኦዲት ግኝቶችን ለማስተካከል የሞከረበት አግባብ በጥሩ ጎኑ እንደሚታይና ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቅሰው የተወሰዱ እርምጃዎች ለዋና ኦዲተር መ/ቤት አለመላካቸው ግን መሰረታዊ ጉድለት ነው ብለዋል፡፡
የተከበሩ ወ/ሮ ወይንሸት ከግዥ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ትኩረት ሊሰጥባቸው እንደሚገባና ግዥ በተቀመጡ ህጎች መሠረት ብቻ መፈጸም እንደሚገባው አስገንዝበዋል፡፡ ያላለቁ ተሰብሳቢና ተከፋይ ሂሳቦችን በተጀመረው አግባብ በትኩረት ማጠናቀቅ ይገባልም ብለዋል፡፡
የክልልና የፌዴራል ተቋማት ግንኙነትን በተመለከተ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ሲናገሩም ጉዳዩን ምክር ቤቱም እንደሚያጤነው ገልጸው ነገር ግን ዩኒቨርሲቲው መታገል እንዳለበትና ለክልሉ እየፈጸመ ያለውን ክፍያም ማቆም እንደሚገባው አስገንዝበዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የውስጥ ቁጥጥር ስራውን ማጠናከር እንደሚገባና በውስጥ ኦዲት የተገኘውን ግኝትም በቶሎ ማረም እንደሚያሻ ገልጸዋል፡፡
ከንብረት አስተዳደር ጋር በተያያዘም ዩኒቨርስቲው ከፍተኛ መጠን ያለው ንብረት የሚያንቀሳቅስ በመሆኑ የንብረት አስተዳደሩ ስርዓት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ መደገፍ አለበት ብለዋል፡፡
በመጨረሻም በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የአመራሩን ትኩረት የሚሹ አለመረጋጋቶችና ግጭቶች ቢኖሩም ተቋማዊ ስራዎች እንዳይዘነጉ ትኩረት ማድረግ ይገባል በማለት ወ/ሮ ወይንሸት አስገንዝበዋል፡፡