የገንዘብ ሚኒስቴር በመንግሥት ፕሮጀክቶች አመራርና አስተዳደር ዙርያ ያሉ ችግሮችን መፍታት እንዲሁም ፐሮጀክቶች በተመደበላቸው በጀትና ጊዜ እንዲጠናቀቁ ክትትል ማድረግ እንዳለበት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ከ2008-2010 በጀት አመታት እንዲሁም በ2011 ዓ.ም እስከ መጀመሪያው ሩብ ዓመት ድረስ ሲካሄዱ በነበሩ የመንግሥት ፕሮጀክቶች አፈፃፀም ላይ ያደረገውን የክዋኔ ኦዲት መነሻ በማድረግ ቋሚ ኮሚቴው ጥር 6 ቀን 2012 ዓ.ም ይፋዊ ህዝባዊ ስብሰባ አካሂዷል፡፡
በስብሰባው ወቅት በፕሮጀክቶች አፈፃፀም ላይ በክዋኔ ኦዲቱ ከተገኙ በርካታ የኦዲት ግኝቶች መካከል የተመረጡ ዋና ዋና ግኝቶች ቀርበዋል፡፡
በወቅቱ ከተነሱት ግኝቶች ውስጥ 16 የመንግሥት ፕሮጀክቶች የአዋጭነት ጥናት ሳደረግባቸው ከተጀመሩና ከብር 246.5 ሚሊዮን በላይ ከወጣባቸው በኋላ መቋረጣቸው ይገኝበታል፡፡
ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ ካለመጠናቀቃቸው ጋር በተያያዘም ከታቀደላቸው ጊዜ ከስድስት ወር እስከ አንድ ዓመት የዘገዩ 75 ፕሮጀክቶች፣ ከአንድ ዓመት እስከ ሦስት ዓመት የዘገዩ 208 ፕሮጀክቶች፣ ከሶስት እስከ እስከ አምስት ዓመት የዘገዩ 54 ፕሮጀክቶች እንዲሁም ከአምስት ዓመት በላይ የዘገዩ 32 ፕሮጀክቶች በድምሩ በወቅቱ ያልተጠናቀቁ 369 ፕሮጀክቶች እንዳሉ ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም የበጀት ጭማሪ ሳይፈቀድላቸው (የበጀት ክለሳ ሳይደረግ) 26 ፕሮጀክቶች በህግ ከተፈቀደው የገንዘብ መጠን በላይ ከብር 1.54 ቢሊዮን በላይ ክፍያ ተፈፅሞባቸው መጠናቀቃቸውንና 28 ፕሮጀክቶች ደግሞ ከብር 1.59 በላይ ክፍያ ተፈጽሞባቸው ያልተጠናቀቁ መሆኑን በድምሩም ፕሮጀክቶቹ ከብር 3.1 ቢልየን በላይ ተጨማሪ ወጪ ያስከተሉ መሆኑን ኦዲቱ አሳይቷል፡፡
ከዚህ ሌላም በፕሮጀክቶቹ አፈጻጸም ዙርያ ፕሮጀክቶቹን በሚያከናውኑ አስፈጻሚ መ/ቤቶች ለገንዘብ ሚኒስቴር የቀረቡ የፕሮጀክቶችን ወቅታዊ የሂሳብንና የፊዚካል ክንውንን የተመለከቱ ሪፖርቶች ህግና ስርዓትን ያልተከተሉ፣ በወቅታዊ መረጃ ያልተደገፉና ሊሳኩ የማይችሉ እንደሆኑ ኦዲቱ አሳይቷል፡፡ በዚህ ረገድ የ57 ፕሮጀክቶች መረጃ እስከ 2010 በጀት አመት መጨረሻ ድረስ ጥቅም ላይ ያዋሉትን በጀት ቢያሳይም የፊዚካል ስራዎችን አፈፃፀም እንደማያሳዩ፤ የ13 ፕሮጀክቶች ሪፖርት መቼ ተጀምረው መቼ እንደሚጠናቀቁና አፈፃፀማቸው ምን ያህል እንደሆነ እንደማያመለክት፤ የ75 ፕሮጀክቶች ሪፖርት እስከ 2010 በጀት አመት መጨረሻ የፊዚካል አፈፃፀም ክንውን ቢያሳይም የተጠናቀቁበትን በጀት መጠን አንደማያሳይ ፤ የ81 ፕሮጀክቶች ሪፖርት እስከ 2010 በጀት አመት መጨረሻ ያለውን የተጠቀሙበትን በጀትና የፊዚካል ሥራዎች አፈጻፀም እንደማያሳይ ፤ እንደዚሁም 64 ፕሮጀክቶች ደግሞ የተሟላ መረጃ የሌላቸው በመሆኑ የተመደበላቸውን በጀትም ሆነ ያሉበትን ደረጃ ለመረዳት እንዳላስቻለ አሳይቷል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ሚኒስቴር መ/ቤቱ የፊዚካል አፈፃፀምና የፋይናንስ ክፍያዎችን በማነፃፀር መክፈል ሲገባው የፊዚካል አፈፃፀሙ ዝቅተኛ ሆኖ እያለ የ109 ፐሮጀክቶች የፋይናንስ ክፍያን በአብላጫ እንደከፈለ ኦዲቱ አሳይቷል፡፡ እንዲሁም በአስፈፃሚ መ/ቤቶች የሚቀርቡ የመንግሥት ፕሮጀክቶች ግንባታም ሆነ የትግበራ ስራ ከመፈቀዱ በፊት የፕሮጀክቶች አዋጭነት ጥናት እና የቅደመ ግምገማ ሪፖርት በመከታተል በጀት መመደብ ሲገባው 209 ፕሮጀክቶች ላይ ተደጋጋሚ የጊዜና የገንዘብ መጠን ክለሳ በመደረጉ ምክንያት ከ10% እና ከዚያ በላይ ክለሳ ለተደረገባቸው ፕሮጀክቶች የ44.2 ቢሊዮን ተጨማሪ በጀት እንዲመደብ ተደርጓል፡፡
ሚኒስቴሩ በተቋሙ የተዘጋጁ የፕሮጀክት ማስፈፀሚያ መመሪያዎችን ለአስፈፃሚ መ/ቤቶች በማሰራጨት ተግባራዊ አለማድረጉንና በፕላንና ልማት ኮሚሽን እና በአስፈፃሚ መ/ቤቶች መካከል የፕሮጀክቶችን አተገባበር በተመለከተ ቅንጅታዊ አሠራር ዘርግቶ ተግባራዊ አለማድረጉን፣ በፕሮጀክቶች አፈፃፀም ላይም ከባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ በማዘጋጀት ግምገማና ክትትል እያደረገ አለመሆኑን ኦዲቱ አሳይቷል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ መሀመድ ዩሱፍ በኦዲት ግኝቶቹ ላይ የሚኒስቴሩ የስራ ኃላፊዎች ማብራሪያ እንዲሰጡ በጠየቁት መሠረት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ክቡር አቶ ኢብራሂም ዑስማንና ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
የስራ ኃላፊዎቹ በሰጡት ምላሽም የመንግሥት ፕሮጀክቶች አመራር፣ አስተዳደርና ክትትል ላይ ኦዲቱ ባሳየው መልኩ መጠነ ሰፊ ችግሮች እንዳሉ በመቀበል ችግሮቹ በሚኒስቴሩ ብቻ የሚፈቱ ሳይሆን የሌሎች ባለድርሻ አካላትን ትብብርና ቅንጅታዊ ስራ የሚጠይቁ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል የራሱን ሚና በመለየት በመንግሥት ፕሮጀክቶች አፈፃፀምና አስተዳደር እንዲሁም በበጀት አፈቃቀድ ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት የተለያዩ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በዚህም የመንግስት በጀት በአግባቡ ስራ ላይ መዋሉን ለማረጋገጥ በተለይም ትኩረት የሚሰጣቸውንና ከፍተኛ በጀት የተያዘላቸውን ድህነት ተኮር የሆኑ ፕሮጀክቶችን በመስክ ጭምር በመገኘት ሚኒስቴር መ/ቤቱ ለመከታተልና ግብረመልስ በመስጠት ለማስተካከል ጥረት እያደረገ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በ2011 እና የ2012 በጀት አመታት በጀት ዝግጅት ወቅትም አዳዲስ ፕሮጀክቶች የተጠኑ፣ የተገመገሙና አዋጭነታቸውና ዲዛይናቸው በኮንስትራክሽን ስራዎች ተቆጣጣሪ ባለስልጣን ወይም እንደ ፕሮጀክቱ አይነት በፕላንና ልማት ኮሚሽን በኩል የተረጋገጠ መሆኑን፣ የአዋጭነት ጥናት በማያስፈልጋቸው ፕሮጀክቶችም መነሻ ጥናት ቀርቦላቸው የተገመገመ መሆኑን በማጣራት ለበጀት እንዲቀርቡ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ስርዓት ዝርጋታ በኩል የሚቀርቡ ፕሮጀክቶችም በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስቴር በኩል ታምኖባቸው ማረጋገጫ ሲሰጣቸው ብቻ በጀት የሚያዝበት አሰራር መጀመሩን አስረድተዋል፡፡ በዚሁ አሰራርም አስፈላጊው ጥናት ያልተደረገባቸው አንዳንድ ፕሮጀክቶች እንዲመለሱ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
ከበጀት ዝግጅት አኳያም ፕሮጀክቶች ከመነሻቸው እስከ መጨረሻቸው ያሉበትን ሂደት (የህይወት ታሪክ) ሊያሳይ የሚችል የፕሮጀክት ፕሮፋይል በማዘጋጀት በዚሁ መሠረት የዘገዩና ችግር ያጋጠማቸው ፕሮጀክቶችን በተመለከተ ከሚያስፈጽሟቸው መ/ቤቶች የበላይ ሃላፊዎች ጋር ውይይት በማድረግ ችግሩን ለመፍታት ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በቀጣይ የፕሮጀክቶቹን አፈፃፀም ችግር በተመለከተ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር መድረክ በማዘጋጀት ውይይት እንደሚደረግ የስራ ኃፊዎቹ ገልጸዋል፡፡ በፕላንና ልማት ኮሚሽን ተዘጋጅቶ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የመንግስት ፕሮጀክቶች አስተዳደር አዋጅ ሲጸድቅም ተግባራዊ እንደሚደረግና የፕሮጀክቶች ክትትልና ግምገማ ስራንም ለማጠናከር እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡
በቋሚ ኮሚቴው አባላትና ከበጀትና ፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ አባል በተሰጠው አስተያየት መንግስት በብድር በሚያመጣውና ከህዝቡ በግብር መልክ በሚሰበስበው ገንዘብ ሀገሪቱን ወዳለመችው የልማት የእድገት ራዕይ ያደርሷታል ተብለው በመላ ሀገሪቱ የተጀመሩ በርካታ ፕሮጀክቶች በአግባቡ በማይመሩበትና በማይተዳደሩበት እንዲሁም የሚመደብላቸው በጀት ክትትል በማይደረግበት ብሎም ተጀምረው ዳር በማይደርሱበትና በሚጓተቱበት ሁኔታ የተቀመጡት ሀገራዊ ግቦች መሳካታቸው፤ ሀገሪቱና ህዝቧም የሚፈለገውን ጥቅም ማግኘታቸው አጠያያቂ ነው ብለዋል፡፡ በዚህ ረገድም በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል በጉዳዩ አስፈላጊነት ልክ በአግባቡ እየተሰራ አይደለም ብለዋል፡፡
ፕሮጀክቶችን በአግባቡ ባለመምራት የደረሰውን የሀብት ብክነት በተለይም ካለጥናት ተጀምረው የተቋረጡትን ፕሮጀክቶች በማንሳት የፈሰሰባቸው ሀብት ለመሰረታዊ የህዝብ አገልግሎቶች ውሎ ቢሆን ኖሮ የተሻለ ጥቅም ይገኝ ነበር በማለት በቁጭት ገልጸዋል፡፡ የሚታየው የፕሮጀክቶች አመራር ድክመት ሀገሪቱን ብድር ውስጥ በመክተትና ህዝቡም ተጠቃሚ ባለማድረግ ድርብ ጉዳት አስከትሏል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴዎቹ አባላት ከኃላፊዎቹ ምላሽ በመነሳት ሚኒስቴሩ ለፕሮጀክቶች ገንዘብ የመክፈል እንጂ የመከታተልና የመገምገም ሚና ያለው አይመስልም ብለዋል፡፡ እንደዚሁም በኦዲቱ የቀረቡት ግኝቶች እንዳይከሰቱ ማድረግ ስላልቻለበትና ከህግና ከአሰራር ውጪ በቢልዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ክፍያ ስለፈጸመበት ምክንያት በቂ ምላሽ ማቅረብ አልቻለም ብለዋል፡፡ ለኦዲት ግኝቱም በሚኒስቴሩ በኩል በቂ ትኩረት የተሰጠው አይመስልም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በመድረኩ ከተካፈሉ ባለድርሻ አካላት ውስጥም በፕላንና ልማት ኮሚሽን በኩል አስተያየት የሰጡት የስራ ኃላፊ ኮሚሽኑ በመንግስት ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ችግሮች ላይ ጥናት ማካሄዱንና በመንግስት ፕሮጀክት አስተዳደርና አመራር ዙርያም ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅቶ ለምክር ቤት ማቅረቡን ገልጸዋል፡፡
ኮሚሽኑ ባደረገው ጥናት የፕሮጀክት አመራሩ በዋናነት ተገቢውን የፕሮጀክት አመራር ስርዐት ካለመዘርጋት ጋር የተያያዘ ችግር እንዳለበት መታወቁን የስራ ኃላፊው ጠቅሰዋል፡፡ ለአብነትም የፕሮጀክት ጥናቶች በበቂ ሁኔታ የማይካሄዱ መሆኑን፣ ፕሮጀክቶች ሳይጠኑ በፖለቲካ ውሳኔ ብቻ የሚወሰኑበት ሁኔታ መኖሩን፣ የወሰን ማስከበርና የካሳ ክፍያዎች ሳይፈጸሙ ፕሮጀክቶች እየተጀመሩ የሚዘገዩ መሆኑን፣ የክትትልና ግምገማ ስርአቱም ደካማ መሆኑን እንዲሁም የፕሮጀክቶች ዑደት የማይጠበቅ መሆኑን ይህንንም የሚመራ ባለቤት የሆነ አካል አለመኖሩን ጠቅሰዋል፡፡ በቀጣይ በመንግስት ፕሮጀክት አስተዳደር ረገድ ሊወሰዱ የታቀዱ ተግባራትንና ሊወሰዱ ይገባሉ ያሏቸውን እርምጃዎችም ገልጸዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ በበኩላችው በመስሪያ ቤታቸው የተከናወነው ይህ የክዋኔ ኦዲት የመንግስት ባለበጀት መ/ቤቶች የሚያካሂዷው ፕሮጀክቶችን ብቻ የተመለከቱ በመሆኑ የፕሮጀክቶች አመራርና አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የገንዘብ ሚኒስቴር በሚያከናውነው ስራ ውስጥ ከነዚህ ፕሮጀክቶች በተጨማሪ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ፕሮጀክቶች ጭምር ማካተት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡
ክቡር ዋና ኦዲተሩ በፕሮጀክቱ አፈፃፀም ውስጥ ዋና ዋና ችግሮች እንደሚስተዋሉ ገልጸው ከነዚህም ውስጥ የፕሮጀክቶች አዋጭነትና ሌሎች ጥናቶች ተሟልተው አለመካሄድና በገለልተኛ አካል አለመገምገም፣ የግንባታ ፕሮጀክቶች ዲዛይን በተሟላ ሁኔታ በጥናትና ነባራዊ ሁኔታ ላይ ተመስርቶ አለመሠራትና በገለልተኛ አካል አለመገምገም እንዲሁም በአስፈፃሚው አካል ተገቢው ክትትል አለመደረግ እንደሚገኙበት ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም ከፕሮጀክት ጥናት እስከ ክትትል ድረስ በሚመለከታቸው አካላትና በገለልተኛ አካላት ጭምር ግምገማ መደረግ አለበት ብለዋል፡፡ መካከለኛና ከፍተኛ ፕሮጀክቶችን በፕላንና ልማት ኮሚሽን ለማስገምገም የተያዘው እቅድም በቶሎ መተግበር እንዳለበት ገልጸው አነስተኛ ፕሮጀክቶችን ደግሞ ገንዘብ ሚኒስቴር በመገምገም መከታተል አለበት ብለዋል፡፡ የኢንጂነሪንግ ግምታዊ በጀት ጥናትም በአግባቡ ታይቶ በጀት የሚፈቀድበት አሰራር ሊኖር እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ከመንግስትና ከከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር ያላቅማቸው የፕሮጀክት ኮንትራት የሚወስዱትን ተቋራጮችና ይህንንም ሳይቆጣጠሩ የሚቀሩ አማካሪ ድርጅቶች የሚቀጡበትና በሌሎች ፕሮጀክቶች ውስጥ እንዳይሳተፉ የሚከለክል ስርዓት እና የሚቀጣ ህግ ሊኖር ይገባልም ብለዋል፡፡
ክቡር አቶ ገመቹ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ከሁሉም ባለበጀት መ/ቤቶችና የልማት ድርጅቶች ጋር መድረክ አዘጋጅቶ ከፕሮጀክት አመራርና አስተዳደር ጋር ተያይዞ ባሉ ችግሮች ላይ መወያየትና ግንዛቤ መፍጠር አለበት ብለዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ተከበሩ አቶ መሀመድ የገንዘብ ሚኒስቴር በፕሮጀክት አመራርና አስተዳደር በኩል የታዩ ችግሮችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ቀልጣፋና ውጤታማ ስራዎችን በመስራት በአጭር ጊዜ በመፍታት ለፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤትና ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሪፖርት ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡