News

ቋሚ ኮሚቴው የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የአገሪቱን የወጪ ንግድ በአግባቡ እንዲመራ አሳሰበ

በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የአገሪቱን የወጪ ንግድ በአግባቡ እንዲመራ አሳሰበ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ታህሳስ 01፣2012 ዓ.ም ባካሄደው የሕዝብ ይፋዊ ውይይት የፌደራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በንግድና አንዱስትሪ ሚኒስቴር ከ2008-2010 በጀት ዓመት የወጪ ንግድ አፈጻጸም ላይ አከናውኖ ባቀረበው የክዋኔ አዲት ሪፖርት መሰረት ሚኒስቴሩ በወሰዳቸው እርምጃዎች ላይ ውይይት አድርጓል፡፡

በፋይዊ ሕዝባዊ ስብሰባው ላይ በርካታ ቁጥር ያላቸው ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ሪፖርት ያሳያቸው ዋና ዋና ግኝቶች ለውይይት መነሻ ቀርበዋል፡፡

በዚህም የወጪ ንግድ እቅድ ሲዘጋጅ ባለድርሻ አካላት መሳተፍ ቢኖርባቸውም አዳዲስ ላኪዎች፣ ቢዝነስ ፕላን የሚያሟሉ እና በማህበር ያልታቀፉ ላኪናዎች በእቅድ ላይ እንደማይሳተፉ እንዲሁም ሚኒስቴር መ/ቤቱ ወደ ውጪ የሚላኩ ምርቶች በዓይነት፣ በመጠንና በጥራት የሚያድጉበትን ስርዓት መዘርጋት ቢኖርበትም የዘረጋው ስርዓት አለመኖሩን ኦዲቱ አረጋግጧል፡፡ ከዚህም ሌላ ኦዲቱ በላኪ እና ገዥ ድርጅቶች መካከል የሚፈጸሙ ውሎች ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል ግልጽ የሆነ መመሪያ አለመኖሩን፣ ውል የሚያፈርሱ ገዥ ሀገራትን መረጃ ለይቶ  እንዲጠነቀቁ ለላኪዎች የማይላክላቸው መሆኑን እንዲሁም በላኪ እና በገዢዎች የሚፈጸሙ ውሎች  ወጥ አለመሆናቸውን ኦዲቱ አረጋግጧል፡፡

ኦዲቱ በተጨማሪም በወጪ ንግድ ላይ ለሚሣተፉ አካላት የሚያደርገው ድጋፍ፣ ክትትል እና የጥራት ቁጥጥር በቂ አለመሆኑና ላኪዎች ባዘጋጁት የወጭ ንግድ እቅድ መሠረት ውል እንዲገቡና እንዲልኩ ክትትልና ድጋፍ እንደማያደርግ አሳይቷል፡፡

ሚኒስቴር መ/ቤቱ ለላኪዎች የሚሰጠውን የወጪ ንግድ ፈቃድ ላኪዎቹ ለዚሁ ዓላማ ብቻ ማዋላቸውን ስለመቆጣጠሩ ኦዲት ሲደረግ የድርጅቶቹ አድራሻ ተደራጅቶ ያልተያዘ መሆኑ እና ለኤክስፖርት ተብሎ በማበረታቻ መልክ የሚሰው ብድር ለታለመለት ዓላማ ማዋሉን ለማረጋገጥ ክትትል የማያደርግ መሆኑ በኦዲቱ ተገኝቷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ሚኒስቴር መ/ቤቱ ክትትል ባለማድረጉ ላኪዎች በአነስተኛ ዋጋ ኤክስፖርት በማድረግ የኤክስፖርቱን ኪራሣ በኢምፖርት በማካካስ የአገር ውስጥ የገበያ ዋጋ እንዳይረጋጋ ተፅዕኖ ከመፍጠራቸውም በላይ ከዘርፉ ሊገኝ የሚገባው የውጭ ምንዛሬ ገቢ እንዳይገኝ ምከንያት እንደሆነ ኦዲቱ አሳይቷል፡፡

ሚኒስቴር መ/ቤቱ የላኪዎችን የመደራደር እና የመወሰን አቅም ለማጎልበት ወቅታዊ አና ታማኝ የሀገር ውስጥ እና የዓለም ገበያ ዋጋ ትንበያንና  የተፎካካሪ አምራች ሀገራት የምርት ሁኔታ መረጃዎችንም በመሰብሰብ ለላኪዎች እንደማይሰጥም ኦዲቱ አመልክቷል፡፡ እንዲሁም ለወጪ ንግድ ማነቆ የሆኑ ችግሮች በጥናት ባለመለየታቸውና ለችግሮች የመፍቻ ስርዓት ባለመኖሩ እንዳይፈቱ እንዳደረጋቸው በኦዲቱ ተመልክቷል፡፡

የቋሚ በኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ መሐመድ ዩሱፍ እነዚህንና ኦዲቱ ያሳያቸውን ሌሎች የወጪ ንግድ አፈጻጸም ችግሮች ከመሠረቱ በመፍታት የወጪ ንግድ ከዓመት ዓመት መቀነስን ለማስቀረት ሚኒስቴር መ/ቤቱ የወሰዳቸውን ተጨባጭ የማስተካከያ እርምጃዎች የመ/ቤቱ ኃላፊዎች እንዲያብራሩ ጠይቀዋል፡፡

በሚኒስቴር መ/ቤቱ የወጪ ንግድ ዳይሬክተር አቶ አሰፋ ሙሉጌታ በሰጡት መልስ የኦዲቱ ግኝቶች  የዘርፉን ተጨባጭ ችግሮች የሚያሳዩ እንደሆነ  አረጋግጠው የአገሪቱ የወጪ ንግድ በርካታ ጉድለቶች ያሉበት ቢሆንም ሚኒስቴር መ/ቤቱ የሚጠበቅበትን ሀላፊነት በሚፈለገው ደረጃ አለመወጣቱን ገልጸዋል፡፡

በግኝቶች ላይ ዝርዝር ሲያብራሩም ባለድርሻ አካላትን በእቅድ ማሳተፉን በተመለከተ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ከባለድርሻ አካላት ጋር የጋራ መድረኮች እንደሚደረጉ ገልጸዋል፡፡ አንዳንድ ላኪዎች ደግሞ የግል እቅዳቸውን ወደ ሚኒስቴር መ/ቤቱ የሚልኩበት ሁኔታ መኖሩንና ይህም በእቅድ ውስጥ የሚካተትበት ሁኔታ እንዳለ ኃላፊው አብራርተዋል፡፡ ሁሉንም የወጪ ንግድ ምርቶች ሚኒስቴር መ/ቤቱ እንደማይከታተልና ሪፖርት ብቻ እንደሚደርሰው ያነሱት ዳይሬክተሩ ለአብነትም የቡና፣ የማዕድንና የአበባ ምርቶች የወጪ ንግድ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ክትትል እንደማያደርግባቸው ጠቅሰዋል፡፡

የወጪ ምርቶች በዓይነት፣ በመጠንና በጥራት የሚያድጉበትን ስርዓት መዘርጋትን በተመለከተ በአገራችን በአብዛኛው ወደ ውጭ የሚላኩ የግብርና ምርቶች በመሆናቸው ከአመራረት ጀምሮ እስከመጨረሻው ድረስ ያለውን ጉዳይ የግብርና ሚኒስቴር የሚከታተለው መሆኑን ገልፀው ችግሩን ለመፍታት በጋራ መድረካችን እየገመገምን ነው ብለዋል፡፡ በቀጣይ ችግሩን ለመፍታት ትኩረት ሰጥተን እንሰራለን ብለዋል፡፡

የውል አፈፃጸምን በተመለከተ ዋናው ችግር የሀገራችን ላኪዎች የገቡትን ውል አለማክበራቸውና  ወይም ማፍረሳቸው መሆኑን አብራርተው ይህንን ችግር ለመፍታት የሚያስችል መመሪያ በማዘጋጀት ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡ የውል ግዴታቸውን ባልተወጡ ላኪዎች ላይም ፍቃዳቸውን እስከመሰረዝ የሚያደርስ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በሌላ በኩል ምርቶች በጊዜ  በጥራት እና አስፈላጊ ሰነዶች ተሟልተው  ባለመላካቸው ምክንያት የሚፈርሱ ውሎች በመኖራቸው እነዚህንና ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ቁጥጥር ውጭ የሆኑ ምርቶችን በሚቀበሉ አካላት በኩል ያሉ ችግሮች ደግሞ በኢትዮጵያ ኢምባሲዎች በኩል እንዲፈቱ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

የጥራት ቁጥጥር ስራን በተመለከተም በኦዲቱ ወቅት የጥራት መቆጣጠሪያ ላቦራቶሪ ባለመኖሩ የተፈጠረ ችግር እንደነበረ የገለጹት ኃላፊው በአሁኑ ጊዜ በአገር ውስጥ የላቦራቶሪዎች የመፈተሽ አቅም እየጨመረ በመሆኑ ችግሩ በአሁኑ ጊዜ እየተሻሻለ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የውጭ ንግድ ፈቃድ ለታለመለት አላማ መዋሉን በተመለከተ የወጪ ንግድ ዕውቀትና ችሎታ የሚጠይቅ በመሆኑ ፍቃዱን ካወጡ በኋላ ወደ ስራ የማይገቡ በመኖራቸው ችግሩ መፈጠሩን ገልጸው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ችግሩን ለማሻሻል መ/ቤቱ መረጃዎችን የማጥራት ስራ እያከናወነ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ የማበረታቻ ስርአቱ ከፍተኛ ክፍተት ያለበት መሆኑን የገለጹት ኃላፈው መ/ቤቱ የጥናት ቡድን በማደራጀት ችግሩን የሚፈታ ጥናት በመደረግ ላይ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ላኪዎች በአነስተኛ ዋጋ ኤክስፖርት በማድረግ የኤክስፖርቱን ኪሳራ በኢምፖርት በማካካስ የአገር ውስጥ ገበያ ዋጋ እንዳይረጋጋ እያደረጉ መሆኑን በተመለከተ የቀረበው ጉዳይ ትክክል መሆኑን ገልፀው ችግሩን ለመፍታት መመሪያ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ እርምጃ ለመውሰድ ከጥቅምት 17/2012 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ስራ ተገብቷል ብለዋል፡፡

የወጪ ንግድ አፈፃፀምን የሚያሳይ የተደራጀ መረጃ አለመኖሩን በተመለከተ ለተነሳው ጥያቄ ማብራሪያ የሰጡት አቶ አሰፋ ችግሩ ትክክል መሆኑን በመገንዘብ መ/ቤታቸው የንግድ መረጃ ለማደራጀት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የወጪ ንግድ ማነቆዎች ብዙ መሆናቸውን የገለጹት ኃላፊው ከአቅርቦት፣ ከሎጅስቲክስ፣ ከግብይት ስርዓት፣ ከኮንትሮባንድ እና ከፕሮሞሽን ጋር የተያያዙ ችግሮችን መ/ቤቱ መለየቱን ጠቅሰው ዋናው ክፍተት ችግሮቹ በተለዩበት ፍጥነት ወደስራ በመግባት ተጨባጭ ለውጥ አለማምጣት መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የዘርፋ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ በተነሱት ጥያቄዎች ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ሚንስትር ዴኤታው የታዩት የኦዲት ግኝቶች በትክክል የዘርፉን ችግሮች የሚያሳዩ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ በማያያዝም የአገራችን የወጪ ንግድ አፈፃፀም እየቀነሰ እንጂ እየጨመረ ሲሄድ አይታይም ያሉ ሲሆን ለዚህም ዋናው ማነቆ የአቅርቦት አለመጨመር መሆኑንና በተጨማሪም የግብይት ስርዓቱ በህገወጥ አካላት የሚረበሽበት ሁኔታ መኖሩ እንደሆነ ጠቅሰው ከዚህም ውስጥ ኮንትሮባንድ አንዱ ችግር በመሆኑ ገበያው የተረጋጋ የወጪ ንግድ አፈፃፀም እንዳይኖር አድርጎታል ብለዋል፡፡

የወጪ ንግድን ውጤታማ ለማድረግ የምርት ጥራት መጠንና አይነትን መጨመርና ተወዳደሪነትን ማሳደግ ያስፈልጋል ያሉት ሚኒስቴር ዴኤታው መ/ቤታቸው ይህንን ለማሻሻል ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልፀው በተለይም የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰቶ ይሰራል ብለዋል፡፡

የፌደራል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ በሰጡት አስተያየት ሚኒስቴር መ/ቤቱ ለኦዲቱ ትኩረት ሰጥቶ ግኝቶችን ለማስተካከል እየሰራ ነው ብዬ ለማመን እቸገራለሁ፤ ለዚህም ማሳያ  ኦዲቱ ያመላከታቸውን ግኝቶች መቼ እና በምን መንገድ ማስተካከል አንዳለባቸው የሚያሳይ የድርጊት መርሀ ግብር አዘጋጅቶ አለማቅረቡ ነው ብለዋል፡፡

ክቡር አቶ ገመቹ በመቀጠልም የአገራችን የወጪ ንግድ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ዋና ጉዳይ መሆኑን ገልጸው ችግሩ የሚፈታው በመዋቀራዊ ለውጥ ነው ብለው እንደሚያምኑ አስረድተዋል፡፡ የወጪ ንግድ አፈፃጸም ችግርን ለመፍታት ሚኒስቴር መ/ቤቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት መስራት አለበት ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል የወጪ ንግድ መረጃ አያያዝ ጋር የለውን ችግር በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ፈጥኖ ማስተካከል እንደሚገባ የገለጹት ዋና ኦዲተሩ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ለዘርፋ እድገት በቂ ድጋፍ እያደረገ ባለመሆኑ የድጋፍ ስራ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡ የወጪ ንግዱን ለመደገፍ የሚሰጠው ብድር ለታለመለት አላማ መዋሉን በቂ ክትትል ማድረግ እንደሚገባ የገለጹት ክቡር አቶ ገመቹ ውል በማፍረስ በውጭ ንግድ አፈፃጸም ላይ ችግር የሚፈጥሩ ላኪዎች ላይ የተጀመረው እርምጃ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴዉ ሰብሳቢ የተከተሩ አቶ መሀመድ የሱፍ በሰጡት የማጠቃለያ ሀሳብ የኦዲት ግኝቶችን ለማስተካከል እንዲያግዝ ሚኒስቴር መ/ቤቱ የውስጥ ኦዲቱን በማጠናከር ወደ ስራ ማስገባት እንደሚያስፈልግ ገልጸው በወጪ ንግድ ላይ በኦዲቱ የተነሱ ችግሮችን መ/ቤቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር እንዲያስተካክልና የተወሰዱትንም ማስተካከያዎች እንዲያሳውቅ አሳስበዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *