News

የኦዲት ግኝት ባለድርሻ አካላት ትብብር ፎረም አፈጻጸሙን ገመገመ

የኦዲት ግኝት ባለድርሻ አካላት ትብብር ፎረም የ2011 በጀት ዓመት አፈፃፀሙን ሰኔ 26 ቀን 2011 ዓ.ም ገመገመ፡፡ ፎረሙ የ2012 በጀት ዓመት እቅድ የትኩረት አቅጣጫዎችንም አስቀምጧል፡፡

የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል የተከበሩ አቶ ጀምበሩ ሞላ የ2011 በጀት ዓመት የፎረሙን እንቅስቃሴ የግምገማ ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት የቋሚ ኮሚቴውና የፎረሙ አባል መ/ቤቶች ባዘጋጁት የጋራ እቅድ መሠረት የተለያዩ ተግባራቶች ሲከናወኑ መቆየታቸውን ገልፀዋል፡፡

የተከበሩ አቶ ጀምበሩ በበጀት ዓመቱ በተደረገው እንቅስቃሴ የታዩ ጥንካሬዎችና ድክመቶችን በዝርዝር አቅርበዋል፡፡

ሁሉም የፎረሙ አባላት በተናጠልና በቅንጅት የሚፈፅሟቸውን ተግባራት አቅደው በወቅቱ ማቅረባቸውና የአፈጻጸም ሪፖርት መላካቸው፣ 7 የሂሳብና 11 የክዋኔ በድምሩ 18 የኦዲት ሪፖርቶች ላይ ህዝባዊ ይፋዊ የውይይት መድረኮች መካሄዳቸው፣ አብዛኞቹ ባለድርሻ አካላት በመድረኮቹ ላይ ተገኝተው መረጃና ሌሎች ለእርምት እርምጃ የሚጠቅሙ ግብዓቶችን መስጠታቸው፣ የፎረሙ ባለድርሻ አካላት ለኦዲት ግኝቶች መታረም ተገቢውን ሚና መጫወታቸው እንዲሁም አንድ የከተማና ሶስት የገጠር የመስክ የክትትል ስራዎች መሰራታቸው የተከበሩ አቶ ጀምበሩ በጥንካሬ ከጠቀሷቸው ጉዳዮች መካከል ይገኛሉ፡፡

በተጨማሪም በዋና ኦዲተር መ/ቤት ግኝቶች ላይ በመመስረት ኦዲት ተደራጊ መ/ቤቶች ስላደረጉት ማስተካከያ በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል የክትትል ኦዲት ተደርጎ የተላከው ሪፖርት ለክትትልና ለቁጥጥር ማገዙ፣ ምክር ቤቱ ልዩ ኮሚቴ በማቋቋም ተደጋጋሚ የኦዲት ግኝት ችግር ያለባቸው መ/ቤቶችን በመለየት በጊዜ ገደብ መፍትሄ እንዲያበጁ አቅጣጫ መሰጠቱና ሌሎች ቋሚ  ኮሚቴዎች በተጠሪ ተቋማት ላይ ኦዲትን መሰረት ያደረገ ክትትልና ቁጥጥር እያደረጉ መሆኑ በጥንካሬ ተጠቅሰዋል፡፡

ከዚህ ሌላም በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመን ያልወጣላቸው ክፍያዎች የክፍያ መመሪያ እንዲወጣላቸው መደረጉ፣ ህጋዊ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግና የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት መረጃዎችን በመለዋወጥ በህግ የሚያስጠይቁ ጉዳዮች ተለይተው ወደ ሥራ መግባቱ እንዲሁም ምክር ቤቱ የኦዲት ማሻሻያ እርምት እንዲደረግ የውሳኔ ሀሳብ ማፅደቁ በጥንካሬ ተነስተዋል፡፡

በአንጸሩ አንዳንድ ባለድርሻ አካላት በህዝባዊ ይፋዊ መድረኮች ላይ የተሟላ መረጃ ሳይዙና በአግባቡ ሳይዘጋጁ መምጣታቸው፣ የአንዳንድ የፎረሙ ባለድርሻ ተቋማት ዓመታዊ ሪፖርት በሚፈለገው መልኩ አዘጋጅተው አለመላካቸው፣ ሚዲያዎች በይፋዊ ህዝባዊ ስብሰባዎችና ሌሎች ኦዲት ነክ መድረኮች ላይ የቋሚ ኮሚቴው፣ የተገምገሚውን መ/ቤትና የዋና ኦዲተርን ማጠቃለያና የሚቀመጡ አቅጣጫዎችን ያላካተተ ያልተሟላ ዘገባ መዘገባቸውና የሽፋንና የጥራት ችግር አልፎ አልፎ መታየቱ በድክመት ተነስተዋል፡፡

እንደዚሁም አንዳንድ መ/ቤቶች በህዝባዊ ይፋዊ ውይይት ወቅት የሚሰጣቸውን አስተያየት በአዎንታ ያለመቀበልና ወደ ሥራ ያለመግባት ሁኔታ በመኖሩ በዚህ ረገድ በፎረሙ አባላት በኩል አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ለማድረግና ተጠያቂነትን ለማምጣት የተደረገው ጥረት በቂ አለመሆኑ በተለይም የተቆጣጣሪነትና ህግ የማስከበር ስልጣን ያላቸው ምክር ቤቱ፣ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ እና ገንዘብ ሚኒስቴር ካለፈው ዓመት የተሻለ እንቅስቃሴ እያደረጉ ቢሆንም ተጠያቂነትን ከማረጋገጥ አንፃር ውስንነት የታየባቸው መሆኑ በድክመት ተጠቅሷል፡፡

የባለድርሻ አካላት የጋራ እቅድና የቅንጅት ስራ እየተጠናከረ መምጣቱ፣ ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ መረጃ የማሰባሰብ ስራ መሰራቱና በተወሰኑ ተቋማት ላይም የተጠያቂነት ስራ መጀመሩ እንዲሁም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ የሚታይ ተደጋጋሚ የኦዲት ግንቶችን በዘላቂነት ለመፍታት የህግ ማሻሻያን ጨምሮ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑ በተደረጉ ጥረቶች የተገኙ ውጤቶች እንደሆኑ ተገልጿል፡፡

በኦዲት ተደራጊ መ/ቤቶች ረገድም አንዳንድ መ/ቤቶች በኦዲት ግኝት ላይ የማስተካከያ እርምት እርምጃ መወሰዳቸው፣ በመንግሥት ግዥ እና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት በኩል ንብረት ማስወገዳቸውና ማሻሻያ በሚፈልጉ ጉዳዮች ላይ የህግ ማሻሻያ ያደረጉ አንዳንድ ተቋማት መኖራቸው በአዎንታ ታይቷል፡፡

በአንጻሩ አብዛኞቹ ኦዲት ተደራጊ መ/ቤቶች የማስተካከያ የድርጊት መርሃ ግብር ቢያዘጋጁም እርምጃ የማይወስዱ መሆኑ፣ እርምጃ የወሰዱትም ስለወሰዱት እርምጃ ለሚመለከታቸው አካላት የማያሳውቁ መሆናቸው፣ ሁሉም ችግር ያለባቸው መ/ቤቶች የሂሳብ ኦዲት ግኝቶችን በኦዲት አስተያየት መሠረት በተሟላ መልኩ ለመፈፀም የሚያሳዩት ቁርጠኝነት አናሳ መሆኑ፣ ተቋማት የኦዲት ክፍላቸውን በሰው ሀይልም ሆነ በአደረጃጀት በአግባቡ አለመደገፋቸው ብሎም በህዝባዊ ይፋዊ መድረኮች ላይ የውስጥ ኦዲት የሥራ ሀላፊዎች እንዲገኙ አለማድረጋቸው እንዲሁም የክዋኔ ኦዲት ግኝቶችን ለማረም ያለው ዝግጁነት አናሳ መሆኑ የተልዕኮ አፈጻጸምና የፕሮጀክቶች አመራር የክትትል፣ የቁጥጥርና የቅንጅት ስራ ደካማ መሆኑ ተገልጻóል፡፡

የ2012 በጀት አመት የባለድርሻ አካላት ዋና ትኩረት የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ያቀረበው የ2010/2011 የኦዲት ግኝትን መሠረት በማድረግ ሂሳባቸው የጎላ ችግር ያለባቸውን 49 ተቋማትና አስተያየት መስጠት ያልተቻለባቸውን 11 ተቋማት ካሉበት ችግር እንዲወጡ ማድረግ መሆኑ ተገልጿል፡፡ በተለይም የተጠራቀሙ ተሰብሳቢ ሂሳቦች መፍትሄ እንዲያገኙ ማድረግና ተደጋጋሚ ችግር እንዳይፈጠር አስፈላጊው የህግና የአሰራር ማሻሻያ እንዲደረግ ማድረግ ትኩረት እንደሚሰጠው ተጠቅሷል፡፡

በበጀት አመቱ በባለድርሻ አካላት ፎረሙ በኦዲት ዙርያ የሚሠሩ አስተዳደራዊና ሀጋዊ ተግባራት እንዲሁም የክትትል፣ የቁጥጥርና የድጋፍ ስራዎች በዝርዝር ቀርበዋል፡፡ በአጠቃላይ የ2011 በጀት አመት ፎረሙ በነበረው አፈፃፀምና በቀጣይ መከናወን ባለባቸው ተግባራት እንዲሁም ትኩረት በሚሹ ሌሎች ጉዳዮች ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡

በመጨረሻም የፎረሙ አባላት እስከ ሐምሌ 20 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ የቀጣዩን በጀት አመት እቅዳቸውን አዘጋጅተው ለማቅረብ ስምምነት ላይ በመድረስ መድረኩ ተጠናቋል፡፡

የፎረሙ አባላት የመንግሰት ወጪ አስተዳደር ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የፌዴራል ዋና ኦዲተር፣ የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የመንግስት ግዢና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ፣ የመንግስት ግዢና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት፣ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ፣ የፌዴራል ፀረ ሙስና እና ስነምግባር ኮሚሽን፣ የፌዴራል ገቢዎች ሚኒስቴር፣ ጉምሩክ ኮሚሽን፣ ብሔራዊ ፕላን ኮሚሽንና የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ናቸው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *