ትምህርት ሚኒስቴር ከኦዲት ግኝት ለመውጣት ጥረት ቢያደርግም አሁንም በርካታ ያልተፈቱ ችግሮች በመኖራቸው ከበፊት የኦዲት ግኝቶች ተምሮ በቀጣይ እንዳይደገሙ መሥራት እንዳለበት ተገለፀ፡፡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በትምህርት ሚኒስቴር የ2009 በጀት አመት ሒሳብ ላይ ያደረገውን ኦዲት መሰረት በማድረግ ግንቦት 26፣ 2011 ዓ.ም ህዝባዊ ይፋዊ ስብሰባ አድርጓል፡፡
ሚኒስቴር መ/ቤቱ ወደ ብሪቲሽ ካውንስል ከሚገኘው ድጋፍ የሚተካና በተሰብሳቢ መያዝ የሚገባውን ለውሎ አበልና ለሙያ አበል የተከፈለ ብር 478,200.00 አለአግባብ በቀጥታ ወጪ መዝግቦ መገኘቱን ኦዲቱ አሳይቷል፡፡ የተለያዩ የትምህርት መሣሪያዎች ለመግዛት ከተዋዋለው ድርጅት ጋር በገባው ውል መሠረት ባለመፈፀሙ በጠቅላላው 5 ዓመት ከ7 ወር ያልተከፈለውን ብር 963,577.48 እና 9% ህጋዊ ወለድ ብር 484,197.68 በድምሩ ብር 1,447,775.15 ለድርጅቱ እንዲከፍል በፍርድ ቤት እንደተወሰነበትና በዚህም አላግባብ የክትትል እና የአሠራር ችግር ምክንያት መ/ቤቱ ለብር 484,197.68 ተጨማሪ ወጪ እንዲከፍል መደረጉን የኦዲት ግኝቱ አሳይቷል፡፡
በሌላ በኩል ሚኒስቴር መ/ቤቱ በድምሩ የብር 1,778,791.68 ግዥ ያለምንም ውድድር በቀጥታ መፈፀሙ እንዲሁም የተለያዩ እቃዎች እና የአገልግሎት ግዥዎች በዋጋ ማቅረቢያና በቀጥታ የግዥ ዘዴ ከመ/ቤቱ እቅድና መመሪያ ወጪ በድምሩ ብር 24,387,606.79 ግዥ መፈፀሙ በኦዲቱ ተረጋግጧል፡፡
በውጭ አገር በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ለሚማሩ ተማሪዎች የሚያስፈልጋቸው የገንዘብ ድጋፍ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዲፕሎማቲክ ሚሲዮኖች እና በዩኒቨርስቲዎቹ የባንክ ሒሳብ ገቢ ስለመደረጉ የባንክ ማስረጃ ቢኖርም ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው ላይ ስለመሆናቸውና የተላከው የኪስ ገንዘብ በትክክል ለተማሪዎች ስለመድረሱ የሚያረጋገጥ ማስረጃ ሳይቀርብ በድምሩ ብር 157,383,533.13 ክፍያ ተፈፅሞ በወጪ ተመዝግቦ መገኘቱ ተገልጿል፡፡
ከ11 ዩኒቨርስቲዎች የግንባታ ፕሮጀክት ጋር በተያያዘ የኦዳ ቡልቱም ዩኒቨርስቲ ግንባታ ለማከናወን ከ11 የህንፃና የግንባታ ሥራ ተቋራጮች እንዲሁም ከአንድ የመሠረተ ልማት ተቋራጭ ጋር ውል ቢያዝም አስቀድሞ ለዩኒቨርስቲው ግንባታ የሚውል የቦታ ርክክብ ያልተደረገ፣ ዩኒቨርስቲው ለሚገነባበት አካባቢ ላሉ ተነሺዎች የካሳ ግምት ያልቀረበና ካሣ ያልተከፈለ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ከዚህም ባለፈም የህንፃ ሥራ ተቋራጮች የቦታ ርክክብ ሳያደርጉና ወደሥራ ሳይገቡ ቅድሚያ ክፍያ ለ9 ኮንትራክተሮች ምንም ዓይነት ሥራ ሳይሰራ እስከ ሰኔ 30/2009 በድምሩ ብር 72,037,164.75 ቅድመ ክፍያ ሚኒስቴር መ/ቤቱ መፈፀሙ በኦዲት ተረጋግጧል፡፡
የተሰብሳቢ ሒሳብ አያያዝን በተመለከተ በተደረገው ኦዲት በበጀት ዓመቱ መጨረሻ በተለያዩ የሒሳብ መደቦች ላይ በሚኒስቴር መ/ቤቱ ብር 67,156,467.64 ከአንድ ዓመት እስከ 15 ዓመት ድረስ የቆየ ተሰብሳቢ ሒሳብ መኖሩንና በተሰብሳቢነት ከሚታየው ሒሳብ ውስጥ ብር 41,479,809.89 ከ1995 በጀት ዓመት ጀምሮ የሚታይና ከማን እንደሚሰበሰብ እና በትክክል የመ/ቤቱ ተሰብሳቢ ለመሆኑ ማረጋገጥ የሚያስችል ማስረጃ የሌለው መሆኑ ተገልጿል፡፡
በተከፋይ ሒሳብም በሚኒስቴር መ/ቤቱ ከ2001 እስከ 2009 በጀት ዓመት የቆየ በድምሩ 4,724,478.22 እንዲሁም በአስራ አንዱ ዩኒቨርስቲዎች ብር 4,433,587.47 በጠቅላላው ብር 9,158,065.69 ውዝፍ ተከፋይ ሒሳብ መገኘቱ በኦዲት ተረጋግጧል፡፡
በበጀት አጠቃቀም ረገድም ለሚኒስቴር መ/ቤቱ ከተፈቀደ የመደበኛ እና ካፒታል በጀት፣ ከመደበኛ ብር 20,272,459.61 እና ከካፒታል ብር 254,268,290.98 በድምሩ ብር 274,540,750.59 ሥራ ላይ ያልዋለ እንዲሁም ና በሚኒስቴር መ/ቤቱ ለ11 ዩኒቨርስቲዎች ግንባታ ከተመደበው የካፒታል በጀት ብር 278,210,628.39 ሥራ ላይ ያልዋለ ሲሆን ብር 349,561,836.61 ደግሞ ከበጀት በላይ ጥቅም ላይ ውሎ ተገኝቷል፡፡
ከንብረት አያያዝ፣ አጠቃቀምና አስተዳደር ጋር በተገናኘ ብዛት ያላቸው ኮምፒዩተሮች፣ ፕሪንተሮች፣ ፎቶኮፒ ማሽኖች፣ ፋይል ካቢኔቶች፣ ጠረጴዛዎች፣ ወንበሮች፣ የተሸከርካሪ ጎማዎችና ሌሎች እቃዎች በተለያዩ ክፍል ታሽገው የተቀመጡ በመሆኑ ለብልሽት እየተዳረጉ እንደሚገኙ፤ አንድ ሞተር ሳይክል ያለሥራ ቆሞ እንደሚገኝ፤ 3 ተሸከርካሪዎችአገልግሎት ሳይሰጡ መቆማቸው በኦዲቱ ተገልፆ ሚኒስቴር መ/ቤቱ በኦዲት ሪፖርቱ ለተመለከቱ ግኝቶች ማብራሪያ እንዲሰጥና ከኦዲቱ በኋላ የወሰዳቸውን የማስተካከያ እርምጃዎች እንዲገልጽ ቋሚ ኮሚቴው ጠይቋል፡፡
በምክር ቤቱ የተገኙት የትምህርት ሚኒስቴር እና የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ኃላፊዎች የኦዲት ግኝቱን መሠረት አድርገው ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በትምህርት ሚኒስቴር የፋይናንስ አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ አለማየሁ ወያሞ በሰጡት ምላሽ በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የተገኙት የኦዲት ግኝቶች ትክክለኛ መሆናቸው ገልፀዋል፡፡ አቶ አለማየሁ በተሰብሳቢ መያዝ የነበረበት ሒሳብ አላግባብ በወጪ የተመዘገበው በስህተት እንደሆነና ስህተቱ በኦዲት ግኝት ከተገለፀበት 2010 ዓ.ም ጀምሮ መስተካከሉን ገልፀዋል፡፡ አላግባብ የተከፈለ የወለድ ክፍያን በተመለከተም ተቋማቸው የትምህርት አገልግሎት መሣሪያዎችን ለመግዛት ውል ለገቡት ድርጅት በውሉ መሠረት በወቅቱ ባለመክፈሉ የተነሳ ድርጅቱ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት እንደወሰደውና በፍርድ ቤት ከመወሰኑ በፊት ውል ከገቡት ድርጅት ጋር ችግሩን ለመፍታት የተደረገው ጥረት ባለመሳካቱ የተፈጠረ እንደሆነና በቀጣይ ችግሩ እንዳይፈጠር ትምህርት እንደተወሰደበት አስረድተዋል፡፡
አላግባብ የተከፈለ የግዥ አገልግሎት ክፍያን በተመለከተም አቶ አለማየሁ ሲገልፁ ብር 1.7 ሚሊዮን ወጪ የተደረገው በወቅቱ አስቸኳይ ከወረዳ እስከ ፌዴራል ያሉ 2000 የሚሆኑ የትምህርት አመራሮች ያሳተፈ የንቅናቄ መድረክ ማዘጋጀት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የአባ ገዳ አዳራሽ የመንግስት ነው በሚል በአዳማ ከተማ ግዥው መፈፀሙንና የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲን አለማስፈቀዱ ስህተት እንደነበረ ተናግረዋል፡፡
በውጭ አገር ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው ላይ መሆናቸውንና የተላከው የኪስ ገንዘብም በትክክል ለተማሪዎች በትክክል መድረሱን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች አለመቅረባቸው በኦዲት ግኝቱ በተገለፀው መሠረት ሰነዶቹን የሚያመጣ ቡድን ተማሪዎቹ ወዳሉበት አገራት በመላክ ወደ 151 ሚሊዮን ለሚሆነው ክፍያ መፈፀሙን የሚገልፅ ማስረጃ እንዲመጣ ማድረግ መቻሉንና በአንዳንድ ሀገራት ግን ቀሪ ሂሳቦች እንዳሉ አቶ አለማየሁ ገልፀዋል፡፡ ለተማሪዎች የተላከው ገንዘብ በትክክል ተማሪዎቹ ስለመድረሱ ማስረጃ ሳይደርሰው ሚኒስቴሩ በወጪ መመዝገቡን ማቆሙንና በተሰብሳቢ እየመዘገበ እንደሚገኝ አክለው ገልጸዋል፡፡
የውዝፍና ተሰብሳቢ ሒሳብን በተመለከተ የፋይናንስ ዳይሬክተሩ ሲገልፁ ችግሩን ለመቅረፍ በበላይ አመራሩ በልዩ ሁኔታ እየተመራና ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር ወደ ብር 41 ሚሊዮን የሚሆነውን ተሰብሳቢ ማሰረዝ መቻሉንና ቀሪ 25 ብር ሚሊዮን ላይ በእቅድ ምላሽ ለመስጠጥ እየተሰራ እንደሆነ ገልጸው በተከፋይ ሒሳብ የተፈጠረውን ግኝት ለማስተካከል በሚኒስቴር መ/ቤቱ እና በ11 ዩኒቨርስቲዎች በሚገኙ ተከፋይ ሒሳቦች ላይ ማስተካከያ እርምጃ መወሰዱን አስረድተዋል፡፡
በንብረት አያያዝና አስተዳደር ለተነሱ ጥያቄዎች የንብረትና አስተዳደር አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ደቢል ከድር ምላሽ የሰጡ ሲሆን በንብረት አወጋገድ በርካታ ሥራዎች መሰራታቸውን ተናግረው ሊወገዱ የሚገቡ ንብረቶች በመለየት ንብረቶቹን ሊጠቀሙባቸው ለሚችሉ 39 ት/ቤቶች ማስተላለፋቸውን፤ ቆሞ የነበረ አንድ ሞተር ሳይክል የተበላሸው የኪሎሜትር መለኪያ ጌጅ እንዲጠገን ተደርጎ ወደ ሥራ መግባቱን፤ የባለቤትነት ሰነድ ያልነበረው አንድ ተሸከርካሪ ሰነዱ ተገኝቶ ወደሥራ እንዲገባ ሲደረግ ሁለቱ ተሸከርካሪዎች የጥገና ወጪያቸው ከፍተኛ በመሆኑ በስጦታ ለቴክኒክና ሙያ ትምህርት ተቋማት መተላለፋቸውን፤ ሌሎች ሦስት ያለሥራ ለረዥም ጊዜ ቆመው የነበሩ ሞተር ሳይክሎችንም ሰነድ ዓልባ መሆናቸው እንዲረጋገጥ ተደረጎ ለፖሊ ቴክኒክ ት/ቤቶች በስጦታ ለማስተላለፍ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ የኦዳ ቡልቱም ዩኒቨርስቲ ግንባታን በተመለከተ ከ11 ዩኒቨርስቲዎች ግንባታ ፕሮጀክት ከፍተኛ የሆነ ተግዳሮት ያጋጠመበት ፕሮጀክት እንደነበረ ገልፀው ከሌሎች ዩኒቨርስቲ ግንባታዎች በተለየ ሁኔታ ከፍተኛ መጠን ያለው የመሬት ካሣ ክፍያ ተፈፅሞ ወደ ግንባታ ቢገባም ከአካባቢው ነዋሪ በተለያየ ጊዜ የሚነሱ የካሣ ያንሰናል ጥያቄዎች ግንባታው ሊስተጓጎል እንደቻለ አስረድተዋል፡፡
የትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ጥላዬ ጌቴ በሰጡት ምላሽ የኦዲት ግኝቶችን ለመፍታት ትኩረት በመስጠት እየተሰራ እንደሚገኙና በኦዲት ግኝቱ መሠረት መርሃ ግብር ተዘጋጅቶ የማስተካከያ እርምጃዎች እየተወሰዱ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡ አክለውም ድጋሚ የኦዲት ግኝቶች በዚህ ደረጃ እንዳይፈጠሩ የሚል አቋም በመያዝ የተለያዩ የማስተካከያ እርምጃዎችና የውስጥ ቁጥጥር ሥርዓታቸውን የማጠናከር ሥራዎች እንደተሰሩ ተናግረዋል፡፡
የተለያዩ እቃዎች እና አገልግሎቶች ግዥን በተመለከተም ግዥው በተፈፀመበት ወቅት የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና ተሰርቆ የነበረበት ጊዜ እንደነበረና ጥንቃቄ ለማድረግ በማሰብ በፈተና ህትመት ክፍል ለሚሰሩ ሠራተኞች የሚቀርብ ምግብ በአቅራቢያ ከሚገኝ አንድ ሆቴል ብቻ በቀጥታ ግዥ እንዲፈፀም በማድረግ ሥራው እንዲሠራ መደረጉን አስረድተው ይህ ትክክለኛ አለመሆኑ በኦዲት ከተገለፀ በኋላ በህጉ መሠረት በውድድር እንዲፈጸም ማድረጋቸውን ዶ/ር ጥላዬ ገልፀዋል፡፡ አያይዘውም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን የትምህርት ባለሙያዎች በአንድ ላይ ለመሰብሰብና የቡድን ስራዎችን ለሚሰሩ የትምህርት ሴክተሮች ቦታ ለማግኘት በሚል የአባ ገዳ አዳራሽ ክራይ በቀጥታ ግዥ መፈጸሙንና ይህም ትክክል እንዳልነበረ ገልጸዋል፡፡ የቋሚ ኮሚቴ አባላት በሰጡት አስተያየት ሚኒስቴር መ/ቤቱ አመራር ለኦዲት ግኝት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ያለውን ስራ ጥሩ እንደሆነና ይበልጥ ሊጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ተቋሙ ከኦዲት ግኝቱ በኋላ በአሠራር ላይ ማሻሻያዎችን እንዳደረገ ቢገለፅም ከፌዴራል ዋና ኦዲተር የ2010 ዓመታዊ የኦዲት ርፖርት ለመረዳት እንደሚቻለው አሁንም የኦዲት ግኝቶቹ እንደቀጠሉ በመሆኑ ሚኒስቴር መ/ቤቱ አሁንም ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራ ይገባል ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ትምህርት ሚኒስቴር በየእውቀት ዘርፉ የባለሙያዎች መፍለቂያ እንደመሆኑ በአሠራር ያሉ የአቅምና የክህሎት ውስንነቶችን በመቅረፍ ለሌሎች ተቋማት አርዓያ ሊሆን በሚገባ ሁኔታ ሊሰራ እንደሚገባውና የአሠራር ጥሰት በፈፀሙ ሠራተኞች ላይም አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃዎችን በመውሰድ ተጠያቂነትን ሊያረጋግጥ እንደሚያሻ የቋሚ ኮሚቴው አባላት ተናግረዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ በሰጡት አስተያየት የትምህርት ሚኒስቴር የኦዲት ግኝቶችን ለማሻሻል እያደረገ ያለው ጥረት ጥሩ መሆኑን ተናግረው ይበልጥ አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል፡፡
ክቡር ዋና ኦዲተሩ በተቋሙ ኃላፊዎች በተሰጡ ምላሾች ላይ አስተያየታቸውን ሲሰጡም ያላግባብ በወጪ የተመዘገበ ሒሳብን በተመለከተ ብር 478 ሺህ በወጪ መመዝገቡ ብቻ ሳይሆን ካልተፈቀደ በጀት የወጣ መሆኑና በጊዜያዊነት ከብሪቲሽ ካውንስል ተበድረው የወሰዱት ቢሆን እንኳ ሥራው ሲጠናቀቅ በጀቱን ተመላሽ ማድረግ እንደነበረባቸው አስረድተዋል፡፡
መንግስት አላግባብ የወለድ ብር 484 ሺህ ክፍያ እንዲፈፀም የተደረገውም በወቅቱ ለድርጅቱ ክፍያ ባለመፈፀሙ እንደሆነና ጥፋቱም በይቅርታ ሊታለፍ የማይገባው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ዋና ኦዲተሩ አያይዘውም ተቋሙ በ2010 በጀት ዓመትም ብር 10 ሚሊዮን የቅጣት ክፍያ መክፈሉንና ከዚህ ውስጥም ለገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በወቅቱ የተጨማሪ እሴት ታክስና ቅድመ ክፍያ ግብር ባለመክፈሉ ብር 8.2 ሚሊዮን ቅጣት የተከፈለ እንደሆነና 1.8 ሚሊዮን ብር ደግሞ ዩናይትድ ኢንጅነርስ ለተባለ የግል ድርጅት በጊዜ ክፍያ መፈፀም ባለመቻሉ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ በቅጣት የተከፈለ መሆኑን ተናገረው ካለፈው የኦዲት ግኝት ትምህርት እንዳልተወሰደ የሚያሳይ በመሆኑ ተገቢው እርምጃ ተወስዶ ለፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት እና ለምክር ቤቱ ሊገለፅ ይገባል ብለዋል፡፡
የብር 1.7 ሚሊዮን የአገልግሎት ግዢ ወጪ ጋር በተያያዘ ተቋሙ ድንገተኛ ወጪዎች ሊያጋጥሙት እንደሚችሉ ገልፀው ነገር ግን የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲን ማስፈቀድ እንደነበረበትና በወቅቱ ለአዳራሽ ኪራይ ወጪ የተደረገውም ብር 1.7 ሚሊዮን ሳይሆን 600 ሺህ ብር ብቻ መሆኑንና ብር 1.1 ሚሊዮን የሚሆነው የተከፈለው ከሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ በመሆኑ የተሰጠው ምላሽ ምንም ዓይነት ተቀባይነት እንደማይኖረው ተናግረዋል፡፡
በውጭ አገር ለሚማሩ ተማሪዎች የሚከፈል የኪስ ገንዘብ በተመለከተ ችግሩ አሁንም መቀጠሉን አቶ ገመቹ ገልፀው ተቋሙ በአሠራር ሥርዓት አላሰራ ያለው ነገር ካለ መመሪያ እንዲወጣለት ቢያደርግ የተሻለ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የ11 ዩኒቨርሰቲዎች ግንባታ በተመለከተም ስለ ኦዳ ቡልቱም አስቀድሞ ቦታው ለግንባታ ዝግጁ መሆኑ ሳይታወቅ ውል ውስጥ መገባቱ ተገቢ እንዳልነበረ ተናግረዋል፡፡
ተሰብሳቢ ሒሳብን በተመለከተም ብር 41.5 ሚሊዮን እንዲሰረዝ ተደርጓል የተባለው ከማን እንደሚሰበሰብ ታውቆ ሊሆን እንደሚገባና ይህ ሳይሆን ሒሳቡ ከተሰረዘ አግባብ እንዳልሆነ አቶ ገመቹ ተናግረዋል፡፡
ከበጀት አጠቃቀም ጋር በተያያዘ አላግባብ ሥራ ላይ ካልዋለው በጀት በተጨማሪ በጀት ዝውውር ሳይደረግ ከበጀት በላይ ብር 349.5 ሚሊዮን መጠቀማቸውንና ይህም የበጀት አዋጅን መጣስ እንደሆነ ገልፀው ሚኒስቴር መ/ቤቱ በዚህ ሳይታረም በ2010 በጀት ዓመትም ተመሳሳይ ስህተቶችን የፈፀመ በመሆኑ በተቀመጠው አሠራር ሥርዓት መሠረት ሊሰራ እንደሚገባ ክቡር ዋና ኦዲተሩ አሳስበዋል፡፡
በቋሚ ኮሚቴው የፋይናንስ ዘርፍ ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ ሶፊያ አልማሙን በሰጡት አስተያየት ሚኒስቴር መ/ቤቱ ከዚህ ቀደም ከነበረበት ግዙፍ የኦዲት ግኝት ለመውጣት ያደረገውን ጥረት በመልካም ጎኑ አንስተው በተለይም አመራሩ የኦዲት ግኝትን መፍታትን የራሱ ሥራ አድረጎ መሥራቱ ሊቀጥል የሚገባው ነው ብለዋል፡፡
የተከበሩ ወ/ሮ ሶፊያ ከኦዳ ቡልቱ ዩኒቨርስቲ ጋር በተያያዘ የቦታ ርክክብ ሳይደረግ፣ የካሣ ግምት ሳይቀርብ፣ ለተነሺዎች ካሣ ሳይከፈልና ለህንጻ ተቋራጩ የቦታ ርክክብ ሳይደረግ ቅድሚያ ክፍያ መፈጸሙ ስህተት እንደነበረ ገልጸዋል፡፡ 11 የኒቨርስቲዎች ግንባታ ላይ የሚታዩ አጠቃላይ ችግሮችን ለመፍታት በልዩ ትኩረት ሊመራ ይገባልም ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ሚኒስቴሩ የውስጥ ኦዲተር አቅም ሊገነባና የውጭ ኦዲተርን ሊያግዝ በሚችል ሁኔታ ሊጠናከር እንደሚገባ ወ/ሮ ሶፊያ አሳስበዋል፡፡ ሚኒስቴር መ/ቤቱ በየሦስት ወሩ በኦዲት ግኝቶች ላይ እርምጃ እየወሰደ ለፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤትና ለምክር ቤቱ ሊያሳውቅ ይገባል ብለዋል፡፡