የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሰራተኞችን መብት በማስከበርና ለአካል ጉዳተኞች አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል በማድረግ ረገድ የተሰጠውን ስልጣን በአግባቡ መወጣት እንዳለበት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡
ቋሚ ኮሚቴው የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የሰራተኛ ማህበራት አደረጃጀትና መብት አጠባበቅን በተመለከተ በ2009 ባደረገው የክዋኔ ኦዲት እንዲሁም ለአካል ጉዳተኞች የሚደረገውን ድጋፍና ክትትል በተመለከተ በ2009 በጀት አመት ባደረገው የክዋኔ ኦዲት ላይ ይፋዊ ህዝባዊ ስብሰባ አድርጓል፡፡
በመድረኩ ላይ በሁለቱም የክዋኔ ኦዲቶች በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ላይ የተገኙ የኦዲት ግኝቶች ቀርበዋል፡፡
በዚህም የሰራተኛ ማህበራት አደረጃጀትና መብት አጠባበቅን በተመለከተ በሀገሪቱ ከሚገኙ የተለያዩ አሰሪ ድርጅቶች ውስጥ የሰራተኞች ማህበር የተደራጀባቸው ቁጥራቸው በጣም አነስተኛ መሆናቸው፣ ከሰራተኛ ማህበራት አደረጃጀት ጋር የተያያዙ ህጎችና መመሪያዎችም አለመውጣታቸውና ሊሻሻል የሚገባው ህግም አለመሻሻሉ እንዲሁም የሰራተኞች የመደራጀት መብት እንዳይከበር በሚከለክሉ አሰሪዎች ላይ እርምጃ አለመወሰዱ በኦዲቱ ተመልክቷል፡፡
በተጨማሪም ከአመት እረፍትና ከወሊድ ፈቃድ አሰጣጥ፣ ለሴቶችና ለወንዶች እኩል ክፍያ ከመክፈል፣ ከትርፍ ሰአት ክፍያ እና ከስራ አካባቢ ደህንነት ጋር በተያያዘ የሰራተኞች መብት በአሰሪዎች እንዲከበር የሚያስችል አሰራር አለመዘርጋቱ እንዲሁም የሴቶችን እኩል ተሳትፎና ተጠቃሚነትን የሚያረጋጥ አሰራር አለመኖሩ ብሎም ለሰራተኞች የሚከፈል ዝቅተኛ የደመወዝ መጠን እንዲወሰን አለመደረጉና በአሰሪና ሰራተኛ ዘርፍ ብሄራዊ ዘመናዊ የመረጃ ስርአት አለመዘጋጀቱ በኦዲቱ ተገኝቷል፡፡
ለአካል ጉዳተኞች መደረግ የሚገባውን ድጋፍ በተመለከተም ሀገሪቱ የፈረመችውን የአካል ጉዳተኞች መብቶች ስምምነትን ለማስፈጸም በሚኒስቴሩ ሰብሳቢነት የተቋቋመው ብሄራዊ የአተገባበርና የክትትል አስተባባሪ ኮሚቴ ሀላፊነቱን መወጣቱን እንዲሁም ስምምነቱን የማይተገብሩ አስፈጻሚ አካላት እንዲጠየቁ የሚያደርግ የሚከታተልበት ስርአት አለመዘርጋቱን፣ በክልል ደረጃም ኮሚቴው ተመስርቶ ሀላፊነቱን እንዲወጣ ድጋፍና ክተትል አለማድረጉንና ስለስምምነቱ አፈጻጸም ሪፖርት የማይቀርብና ግብረመልስም የማይሰጥ መሆኑን ኦዲቱ አሳይቷል፡፡
ከዚህም ሌላ አካል ጉዳኞችን ከጥቃት የሚከላከልና ጥቃቱ ሲደርስባቸውም ፈጻሚው አካል ላይ እርምጃ እንዲወሰድ የሚያደርግ ስርአት አለመዘርጋቱን፣ አካል ጉዳኞች ስራ ሲቀጠሩና ስራቸውን ሲፈጽሙም መብታቸው መከበሩና አስፈላጊውን ድጋፍ ማግኘታቸው አለማረጋገጡን፣ ከክልሎችና ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር የአካል ጉዳተኞች ጉዳይን አካቶ በመስራት ረገድ የተቀናጀ አሰራር አለመኖሩን፣ ለአካል ጉዳተኞች ሰው ሰራሽ አካልና የአካል ድጋፍ የሚያመርቱ ማእከላት እንዲሁም ለአካል ጉዳተኞች የሚሰጣቸው የአካላዊ ተሀድሶ አገልግሎት በከተማም ሆነ በገጠር ላሉ አካል ጉዳተኞች ውጤታማ በሆነ አግባብ የሚመረቱበትና ተደራሽ የሚሆኑበት ስትራቴጂ አለመቀረጹን ኦዲቱ አመልክቷል፡፡
በተጨማሪም ሚኒስቴር መ/ቤቱ ከአካል ጉዳተኞች የእንቅስቃሴና የትምህርት ፍላጎት ጋር ግንኙነት ባላቸው ጉዳዮች ላይ ከሚሰሩ እንደኮንስትራክሽን ሚኒስቴር፣ ትምህርት ሚኒስቴርና ትራንስፖርት ሚኒስቴር ካሉ አካላት ጋር ተቀናጅቶና ተናቦ የማይሰራ መሆኑን እንዲሁም ለአካል ጉዳተኞች የሚሰጡ የድጋፍ አይነቶችን የተመለከተና አካል ጉዳተኞችን በጾታና በእድሜ ለይቶ የሚያሳይ መረጃ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ አደራጅቶ አለመያዙ በኦዲቱ ተጠቅሰዋል፡፡
ሚኒስቴር መ/ቤቱ በህግ የተሰጠው ሀላፊነት በአግባቡ ለመወጣት ያልቻለበትን ምክንያትና በሁለቱ የክዋኔ ኦዲቶች የተመለከቱትን ግኝቶች ለማረም የወሰዳቸውን እርምጃዎች እንዲያብራራ ቋሚ ኮቴው በጠየቀው መሰረት የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ጌታሁን አብዲሳ እና የመ/ቤቱ የስራ ሀላፊዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ኃላፊዎቹ በሰጡት ምላሽም ሰራተኞች በማህበር እንዲደራጁ አሰራር ለመዘርጋት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተሰሩ ስራዎች እንዳሉ ገልጸዋል፡፡ ከተሰሩ ስራዎች ውስጥ በኢንደስትሪ ማእከላት ውስጥ ሰራተኞች በማህበር እንዲደራጁና የማህበራቱም ተወካዮች በአሰሪ ድርጅቱ የስራ አመራር ውስጥ እንዲካተቱ የሚያደርግ አሰራር የመዘርጋት፣ በዚህ አግባብ ያላደራጁ ኢንደስትሪ ባለቤቶች ላይ እርምጃ አንዲወሰድ የማድረግ፣ በየኢንደስትሪ ማእከላቱ በተለይም አዳዲስ ኢንደስትሪዎች ውስጥ ይህንን የሚከታተል ፎካል ፐርሰን የመመደብ እንዲሁም ክትትልና ድጋፍ የማድረግ ስራዎች እንደተሰሩ ገልጸው ባጠቃላይ ግን ሰራተኞች በማህበር እንዲደራጁ የማድረግ ስራው ገና በጅምር ያለ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የሰራተኞች መብቶች እንዲከበሩ ከማድረግ አኳያም ከኦዲቱ በኋላ አሰራር መቀረጹንና አሰራሩ ላይ ግልጽነት የመፍጠር፣ ክትትል የማድረግ እንዲሁም ለኢንደስትሪ ባለቤቶች ስልጠና የመስጠት ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡ ሰራተኞች እንዳይደራጁ የሚከለክሉ አሰሪዎችን በተመለከተም በክልሎች ባሉ የስራ ደህንነትና ቁጥጥር በሚያደርጉ ባለሙያዎች በኩል እየተሰራበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የሰራተኞች መብት ሲጣስም ከሚመለከታቸው የህግ አካላት ጋር እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
ዝቅተኛ የሰራተኛ ደመወዝን ለመወሰን በመካከለኛው ምስራቅ እስያ ከሚገኙ ሀገራት መንግስታት ጋር ድርድር መደረጉንና እስካሁን ከሳውዲ አረቢያ፣ ከጆርዳንና ከኦማን ጋር ስምምነት ላይ መደረሱን፣ ስምምነት ላይ ካልተደረሰባቸው ሀገራት ጋርም ድርድሩ መቀጠሉን አስረድተዋል፡፡
የሰራተኛና አሰሪ መረጃ አያያዝ ጋር በተገናኘም መ/ቤቱ እስካሁን መረጃን በማንዋል ስርአት ሲይዝ እንደቆየና በቀጣይ ወደ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለመግባት ጥረት መጀመሩን አስረድተዋል፡፡
ለአካል ጉዳተኞች ተገቢውን ድጋፍና ክትትል በማድረግ በኩል ስለተሰሩ ስራዎች ሲገልጹም ሀገሪቱ የፈረመችውን የአካል ጉዳተኞች ስምምነት አስፈጻሚና ፈጻሚ ተቋማትን በኮሚቴ ከማደራጀት ጎን ለጎን የድርጊት መርሀ ግብር በማውጣት በ2011 በጀት አመት በተሰጣቸው ስልጣን መሰረት አቅደው ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጉን፣ ተቋማቱ በእቅዳቸው መሰረት ስለመተግበራቸውና ወቅታዊ ሪፖርት ስለማቅረባቸውን ክትትል መደረጉን፣ የአፈጻጸም ግብረ መልስ የመስጠትና ይህንንም ለማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የማሳወቅ ስራ መሰራቱንና የተጠያቂነት አሰራርን ለማስፈን እንዲረዳም ለቋሚ ኮሚቴው አባላት ስልጠና መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡
አካል ጉዳተኞችን ከስራ ስምሪት መብት ተጠቃሚ ከማድረግ አኳያም በመንግስትም ሆነ በግል ዘርፉ የአካል ጉዳተኞችን መብት በመተግበር በኩል ችግር እንዳለ መገምገሙን ገልጸው ለሁሉም ክልሎች የሰው ሀብት ሰራተኞች ስልጠና መሰጠቱንና ክትትል መደረጉን ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ሌላም የግል ድርጅቶች አካል ጉዳተኞችን በሚያስተናግዱበት ሁኔታ ላይ እንዴት ክትትል መደረግ እንዳለበት በሁሉም ክልል ላሉ የስራ ሁኔታ ክትትል ባለሙያዎች ስልጠና እንደተሰጠ አስረድተዋል፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ ዘርፉ በአደረጃጀትና በአፈጻጸም ወጥ አለመሆኑን ገልጸው መ/ቤቱ ከክልሎች ጋር ያለው የቅንጅት ስራ ያልተሟላ መሆኑንና በተለይም ወደታች ላሉ አካላት የሚሰጠው ድጋፍ ጉድለት እንዳለበት መገምገሙን ተናግረዋል፡፡ ከአደረጃጀት አኳያም በሚ/ር መ/ቤቱ ውስጥ የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ራሱን ችሎ እንዲቋቋም መደረገጉና በቀጣይም አካል ጉዳተኞችን አስመልክቶ ከክልሎች ጋር በቅንጅት ለመስራት መታቀዱን ተናግረዋል፡፡
የሰው ሰራሽ አካልና የአካል ድጋፍ ማምረቻ ማእከላትን አስመልክቶም በውጤታማነት አገልግሎቱን ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ ከማድረግ አኳያ ችግር እንዳለ ገልጸዋል፡፡ በማእከላቱ ለአካል ጉዳተኞች የሚሰጠው አብዛኛው አገልግሎት ከጤና ተቋማት ጋር የተያያዘና የሚሰጠውም በሆስፒታሎች ሆኖ ሳለ ማእከላቱ በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ስር እንዲተዳደሩ መደረጉ ውጤታማ አገልግሎት ለመስጠት እንዳላስቻለ በመገንዘብ አለም አቀፍ ተሞክሮው እንዲጠና መደረጉን አስረድተዋል፡፡ በጥናቱም አለም አቀፍ ተሞክሮው ተቋማቱ በጤና ጥበቃ ሚስቴር ስር እንደሚተዳደሩና የሶሻል ሰርቪስ ስራው ደግሞ በማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል የሚፈጸም መሆኑን በማሳየቱ ማእከላቱ ወደ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንዲተላለፉ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ከሚመለከታቸው አስፈጸሚ አካላት ማለትም ከኮንስትራክሽን ሚስቴር፣ ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ከጤና ጥበቃና ከሌሎች ሚኒስቴር መ/ቤቶች ጋር በመሆን ከኦዲቱ በኋላ የተሰሩ ስራዎች እንዳሉ ኃላፊዎቹ ገልጸዋል፡፡ በዚህም ህንጻዎችና መሰረተልማቶች ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ እንዲሆኑ ከኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ጋር እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡ የመንቀሳቀስ ችግር ላለባቸው እንዲሁም መስማትና ማየት ለተሳናቸው ዜጎችም ትምህርት ቤቶችን ምቹ ለማድረግ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር እየተሰራ እንደሆነና ሁሉንም የጉዳት አይነቶች አካቶ በመስራት ላይ ግን ጉድለት እንዳለ አስረድተዋል፡፡ ከትራንስፖርት ሚኒስቴርም ጋር በመሆን ተሽከርካሪዎችና የቀላል ባቡር አገልግሎቶች ለአካል ጉዳተኞች ምቹ እንዳልሆኑ መገምገሙን ገልጸዋል፡፡ ከሌሎች አካላትም ጋር የተጀመሩ ስራዎች እንዳሉና በአካል ጉዳተኞች ዙርያ ግንዛቤ ለመፍጠር ስልጠናዎች እየተሰጡ እንደሚገኙኝ አክለው ገልጸዋል፡፡
አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ ያለውን መረጃም በተመለከተ ተቀባይነት ያለው መረጃ ለማግኘት በቀጣዩ የቤቶችና የህዝብ ቆጠራ አካል ጉዳተኞችን የተመለከተ የተሟላ መረጃ እንዲሰበሰብ ለማድረግ ከማእከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ጋር እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው አባላት፣ የማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላትና በመድረኩ የተካፈሉ ባለድርሻ አካላት ተጨማሪ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን አቅርበዋል፡፡
በሰጡት አስተያየትም የሰራተኞች የመደራጀት መብት ህገ መንግስታዊ በመሆኑ መብታቸው በሚጠበቅበት ሁኔታ ላይ መስራት እንደሚገባ፣ የስራ አካባቢ ደህንነት አጠባበቅ ሁኔታ ደካማ በመሆኑ ሰራተኞች ደህንታቸው ተጠብቆ ስለመስራታቸው የሚደረገው ቁጥጥር ትኩረት ሊሰጠው እንደሚያስፈልግ እንዲሁም ከሀገር ውጭ ለሚሰሩ ሰራተኞችች ዝቅተኛ የደመወዝ መጠንን ለመወሰን እንደተሰራው ስራ ሁሉ በሀገር ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች ዝቅተኛ ደመወዝ መጠን አንዲወሰን ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በተጨማሪም ሚኒስቴሩ የአካል ጉዳተኞችን መብትና ጥቅም የማያስጠብቁ ተቋማትን ተጠያቂ የማድረግ ሀላፊነት በዋናነት የራሱ መሆኑን በመገንዘብ መስራት እንደሚጠበቅበት፣ የአካል ጉዳተኞችን መብት ሆን ብለው በሚጥሱ ላይ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት፣ የአካል ጉዳተኞችን በተመለከተ ኃላፊነታውን ያልተወጡ አካላትን ለምክር ቤቱ ማሳወቅ እንደሚገባ፣ መ/ቤቱ በህዝብና ቤት ቆጠራውን መረጃ ከመሰብሰብ ባለፈ እስክ ክልል ያለውን የራሱን አደረጃጀት ጭምር በመጠቀም አካል ጉዳተኞችን የተመለከተ መረጃ መሰብሰብ እንደሚኖርበት ገልጸዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የኦዲት ዘርፍ ምክትል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ በሰጡት አስተያየት በአዲስ አበባ በማህበር መደራጀት ካለባቸው ሰራተኞች አንጸር የተደራጁት በጣም ጥቂት መሆናቸውን ለአብነት ጠቅሰው በበክልል ደረጃ ያሉትንም ጭምር ለይቶ ሰራተኞች በማህበር እንዲደራጁ ማድረግ እንደሚገባ እንዲሁም በሀገር አቀፍ ደረጃ የተደራጁና ያልተደራጁትን ለይቶ መረጃ ማደራጀት እንደሚያሻ ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም በውጭ ሀገር ለሚሰሩ ሰራተኞች ዝቅተኛ የደመወዝ መጠን ለማስወሰን በሚኒስቴሩ እየተሰራ ያለውን ስራ በበጎ ጎኑ ጠቅሰው በተመሳሳይም በሀገር ውስጥ ለሚሰሩ ሰራተኞችም ዝቅተኛ የደመወዝ መጠን እንዲወሰን ጥረት ማድረግ አንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡
ክብርት ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ በአካል ጉዳተኞች ረገድ የወጡ ህጎችን ያልፈጸሙ አካላትን ለማገዝና እርምጃ ለመውሰድ በሚያስችል መልኩ የሰሩትንና ያልሰሩትን ስራ መለየትና ለሚመለከተው አካል ማቅረብ ይገባል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም የሰው ሰራሽ አካልና የአካል ድጋፍን በተመለከተ ከሜቴክ ጋር የተደረገ ስምምነት እንደነበረ አስታውሰው በዚህ ረገድ ሌሎች አማራጮችን ማየት እንደሚገባ እንዲሁም ከህንጻ ግንባታ ጋር በተያያዘ የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡ መስማት ከተሳናቸው ዜጎች የመረጃ ፍላጎት ጋር አያይዘውም እንደመንግስት ሚድያዎች ሁሉ በግል ሚድያዎች በኩልም አካል ጉዳተኞች መረጃ የሚያገኙበት ሁኔታ እንዲፈጠር ከብሮድካስት ባለስልጣን ጋር መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
በመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የክዋኔ ኦዲት ንኡስ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ት ወይንሸት ገለሶ የመ/ቤቱ አመራር ችግሮቹን ለመረዳትና ለመፍታት ያለውን ዝግጁነት በመልካም ጎኑ ጠቅሰዋል፡፡
ሆኖም ግን መ/ቤቱ እያከናወናቸው ያላቸው ተግባራት ከሂደት አልፈው በውጤት ደረጃ እንዲለኩ ማድረግ ላይ ትኩረት መስጠት አለበት በማለት የተከበሩ ወ/ት ወይንሸት አስገንዝበዋል፡፡ የሰራተኞች በማህበር መደራጀት አሰሪዎች የሰራተኛውን መብት እንዲያከብሩ ብቻ ሳይሆን ሰራተኛውም ግዴታውን እንዲወጣ የሚያደርግ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ያሉት የተከበሩ ወ/ት ወይንሸት ተደራጅተው ያሉ ሰራተኞች መብትም በአግባቡ እየተጠበቀ መሆኑን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም ከሰራተኛ አደረጃጀት ጋር ተያይዘው ባሉ ችግሮች ላይ ጥናት በማድረግ መፍታት እንደሚያስፈልግ፣ መ/ቤቱ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባል በመሆኑ በዘርፉ ያሉ ችግሮች እንዲፈቱ ጥረት ማድረግ እንዳለበትና ይህም በዋናነት የራሱ ሀላፊነት መሆኑን መገንዘብ እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡ አያይዘውም አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ ከክልሎች ጋር ዘላቂ የቅንጅት ስራና የተጠያቂነት አሰራር የሚኖርበትን አግባብ የማጥናት፣ ግንዛቤ የመፍጠርና የመገምገም ስራ መስራት እንደሚኖርበት በመረጃ አደረጃጀት በኩልም በተቋም ደረጃ የራሱን መረጃ ማደራጀት እንደሚኖርበትና ከዚህ በተጨማሪም ከማእከላዊ ስታትስቲክስ ጋር በሚሰራ ስራ መረጃ ማሰባሰብ እንደሚገባው የተከበሩ ወ/ት ወይንሸት አስገንዝበዋል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ መሀመድ ዩሱፍ በሰጡት ማጠቃለያ ሚ/ር መ/ቤቱ በተሰጠው ስልጣንና ኃላፊነት መሰረት የሰራተኞችን የመደራጀት መብት፣ የሴቶችን በእኩል የመሳተፍና የመጠቀም መብት እንዲሁም የአካል ጉዳተኞችን ችግሮች አስመልክቶ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ቅንጅት በመፍጠር ፈጣን ምላሽ መስጠት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ጥብቅ የሆነ የክትትልና የቁጥጥር ስርአት በማዘጋጀትና የውስጥ አዲት አቅምን በማጠናከር በተለይም በዋና ኦዲተር መ/ቤትና በመድረኩ የተሰጡ ግብአቶችን በመቀበል በአስቸኳይ ስክተቶችንና ክፍተቶቹን በማረም ሀላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡