News

ሚኒስቴሩ የገቢ አሰባሰብና የጉምሩክ አሰራሩን ማዘመን እንዳለበት ቋሚ ኮሚቴው አሳሰበ

የገቢዎች ሚኒስቴር ወደ ዘመናዊ አሰራር በመግባት በገቢ አሰባሰብና በጉምሩክ አሰራር ላይ አፈጻጸሙን ማሻሻል እንዳለበት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡ ቋሚ ኮሚቴው በገቢዎች ሚኒስቴር የ2009 በጀት አመት የሂሳብ ኦዲት ላይ ሚያዝያ 02፣ 2011 ዓ.ም ይፋዊ ህዝባዊ ስብሰባ አድርጓል፡፡

የኦዲት ሪፖርቱ  በገቢዎችና ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች በቀረጥና በታክስ አሰባሰብ፣ በበጀት አጠቃቀም እንዲሁም በጉምሩክ መጋዘኖች ያሉ ንብረቶችን በማስተዳደር በኩል በርካታ ድክመቶች እንዳሉ አሳይቷል፡፡

ኦዲቱ በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች የጉምሩክ እና የሀገር ውስጥ ገቢ አሰባሰብ ህጎችና አሰራሮችን በአግባቡ ባለመከተል ምክንያት በግብርና በቀረጥ መልክ ሊሰበሰብ ይገባ የነበረ በብዙ ሚልዮኖች የሚቆጠር ብር በበጀት አመቱ ሳይሰበሰብ እንደቀረ በዝርዝር አሳይቷል፡፡ መ/ቤቱ በበጀት አመቱ ለመሰብሰብ ካቀደው 185.49 ቢልየን ብር ውስጥ 25.87 ቢልየን ብር ሳይሰበስብ መቅረቱንም አመልክቷል፡፡

በበጀት አጠቃቀም ረገድም መ/ቤቱ ለካፒታል በጀት ከተመደበለት ውስጥ በሶስት የሂሳብ መደቦች 80.2 ሚልየን ብር ሳይጠቀም መቅረቱ በኦዲቱ ታይቷል፡፡ ተሰብሳቢ ሂሳቦችን ተከታሎ እንዲሰበሰቡ ባለማድረጉም ከ1999-2009 ዓ.ም ድረስ 52.04 ሚልየን ብር እንዲሁም ከማን እንደሚሰበሰብ ያልታወቀ 48.44 ሚልየን ብር እንዳለም ተጠቅሷል፡፡ በአንጻሩም በዚሁ ጊዜ ውስጥ መከፈል ሲገባው ተከፍሎ ሳይወራረድ የቆየ 33.7 ሚልየን ብር እንዲሁምና በቂ ማስረጃ የሌላቸው በድምሩ 79.47 ሚልየን ብር መኖሩ ተመልክቷል፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ከመመሪያ ውጪ አላግባብ የተከፈሉ ክፍያዎች እንዳሉም ኦዲቱ አሳይቷል፡፡

በተጨማሪም መ/ቤቱ በጉምሩክ በቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ያሉ ንብረቶችን በአግባቡ እያስተዳደረ አለመሆኑንና መወገድ ሲገባቸው ባለመወገዳቸው ለብልሽትና ለጥፋት የተዳረጉ ንብረቶች እንዳሉ በኦዲቱ ተገኝቷል፡፡

በነዚህ ጉዳዮች ላይ የገቢዎች ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እና ከሚኒስትሩ እና ከጉምሩከ ኮሚሽን የተገኙ ሌሎች የስራ ሀላፊዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ክብርት ሚኒስትሯ የኦዲት ግኝቱ በመ/ቤቱ ያሉ በርካታ ድክመቶችን አውጥቶ ያሳየ መሆኑና ግኝቶቹን ለማረም ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይህንንም ለማድረግ የራሱ አደረጃጀትና ሰራተኛ ያለው አካል በተቋሙ መቋቋሙን፤ እንዲሁም በየጊዜው ከቅርንጫፍ መ/ቤቶች ጋር በመገናኘት የመገምገምና ተስተካከሉ የተባሉትን ጉዳዮች ጭምር የማረጋገጥ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በትኩረት ማጣት፣ በአሰራርና በሌሎች ክፍተቶች ምክንያት በታክስና በቀረጥ መልክ ሊሰበሰብ እየቻለ ያልተሰበሰበው ገንዘብ ተለይቶ ከ2.2 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን ክብርት ወ/ሮ አዳነች ገልጸው ቀሪውንም በቀጣይ ለመሰብሰብ እየተሰራ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በበጀት አጠቃቀም ረገድም የአቅም ክፍተት እንደነበረ ተገምግሞ በቀጣይ  ለማስተካከል እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ከጉምሩክ እቃዎች አያያዝና አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ችግሩን መሠረት በማድረግ መጋዘኖችን የማስተካከል ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝና በዚህም የተበላሹ፣ የሚበላሹ፣ መቆየት የሚችሉ፣ በስጦታና በሌላ አግባብ  መወገድ የሚገባቸውን ዕቃዎች በመለየት ሁኔታውን ለማስተካከል እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በደረቅ ወደብ ለረጅም ጊዜ የተከማቹ ንብረቶችን በመለየትም እርምጃ ተወስዶ በአሁኑ ወቅት የደረቅ ወደብ ቆይታን ወደ 20 ቀናት መቀነስ እንደተቻለና በተቋማት ተገዝተው በወደቦቹ የተከማቹ ንብረቶችን በማስወገድ ሂደት ላይ ችግር በመኖሩ ከመንግሥት ጋር በመሆን ለማስተካከል ጥረት እየተደረገ እንዳለ አስረድተዋል፡፡ ከዚህም አኳያ የተሰሩ የህግ ማሻሻያ ሥራዎች እንዳሉም ጠቅሰዋል፡፡፡

በገቢ አሰባሰብ ረገድ ሊሰበሰብ የሚችለውን ገቢ በትክክል ለማቀድ አቅጣጫ ተቀምጦ የፕሮጀክት ጽ/ቤት ተከፍቶ ሥራው መጀመሩን አስረድተዋል፡፡ እንደዚሁም የቆዩና በአሁኑ ወቅት ያሉ ተሰብሳቢ እዳዎችን በመለየት በዳይሬክተር ደረጃ ክትትል በማድረግ ባለፈው አንድ አመት ብቻ ከ14 ሚሊዮን ያላነሰ ብር  ተሰብስቧል ብለዋል፡፡

ክብርት ወ/ሮ አዳነች ከኦዲት ግኝት ከማረም ባለፈ የገቢና የጉምሩክ ሥርዓቱን ለማሻሻል እንዲቻል ሥርዓትን መዘርጋት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንና በዚህም በቴክኖሎጂ ለመታገዝ፣ ክፍተቶችን በአሰራር ለማሻሻል፣ እስከ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ድረስ የውስጥ ኦዲት ክፍልን ለማጠናከርና የተቋሙን የሰው ሀይል ላይም የማስተካከያ ስራ ለመስራት የተከናወኑ ተግባራት እንዳሉ አስረድተዋል፡፡ በተለይም በሰው ሀይልና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት ታቅዶ እየተሰራ ነው ያሉት ሚኒስትሯ   በቴክኖሎጂ ማሻሻያ ረገድ የፍተሻ ማሽኖችን በመቀየር በተሻለ ሁኔታ ከሰው ንክኪ የፀዱ እንዲሆኑ የማድረግ ስራ መጀመሩን እንዲሁም ከጉምሩክ መረጃ አያያዝና አወሳሰን ጋር በተያያዘ አሲኩዳን በሙከራ ደረጃ መጠቀም መጀመሩን ገልጸዋል፡፡ እንደዚሁም የአንድ መስኮት አሰራርን ለመዘርጋትና መረጃዎችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት የመለዋወጥ ስራ በሙከራ ደረጃ ተጀምሯል ብለዋል፡፡ የካሽ ሬጅስተር ማሽንን አሰራርንም ለማስተካከል መታቀዱን ክብርት ወ/ሮ አዳነች ተናግረዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ ለ2009 በጀት አመት የኦዲት ግኝት ትኩረት ተሰጥቶ በሚኒስቴር መ/ቤቱ በኩል ለማስተካከል እየተደረገ ያለው ጥረት ጥሩና እውቅና ሊሰጠው የሚገባ ነው ብለዋል፡፡ የተሟላ ባይሆንም በተጠቃለለው የ2010 ኦዲት በተደረገው ክትትል የፌዴራል ዋና ኦዲተር ይሰብሰቡ ካላቸው ሂሳቦች ውስጥ ሚኒስቴሩ እስከ ታህሳስ 2010 ዓ.ም. ድረስ 1.1 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡ መረጋገጡን ተናግረዋል፡፡

በአንጻሩ ግን የበጀት አጠቃቀም ድክመት፣ ከቤትና ሙያ አበል ጋር ተያይዞ ያልተቀነሰ የስራ ግብር፣ ያለአግባብ የተከፈለ መዘዋወሪያ አበልና የትርፍ ሰዓት ክፍያ፣ ለሠራተኞች ተከፍሎ ያልተወራረደ የቅድሚያ ክፍያ፣ በብልጫ የተከፈለ የውሎ አበል፣ በሰነድ መወራረዱ ያልተረጋገጠ ገንዘብ፣ ለምን እንደተከፈለ ያልታወቀ ማስረጃ የሌለው ሌተር ኦፍ ክሬዲት፣ ከተሰብሳቢ ጋር ተያይዞም በጊዜ መወራረድ ሲገባው ያልተወራረደ ሂሳብ፣ ከማን እንደሚሰበሰብ የማይታወቅ ሂሳብ፣ መከፈልና መወራረድ ያለበት ያልተወራረደ ሂሳብ ወዘተ. እንዳለ ገልጸው ለነዚህ የኦዲት ግኝቶች ትኩረት መስጠት ይገባል ብለዋል፡፡

ጥሬ እቃ በቀረጥ ነፃ መብት ተጠቅመው ወደ ሀገር አስገብተው ያመረቱትን ምርት ከሀገር ውጭ በመሸጥ የውጭ ምንዛሬ ማስገኘት ሲገባቸው ምርታቸውን በሀገር ውስጥ በሚሸጡ ኢንደስትሪዎች ላይ መንግስት ጥብቅ እርምጃ ሊወስሰድ እንደሚገባም ክቡር ዋና ኦዲተሩ አስገንዝበዋል፡፡

በጉምሩክ ህግ ከተፈቀደው ጊዜ በላይ ተከማችተው የተቀመጡና መወረስ ያለባቸው ንብረቶችን በተመለከተም ይህንን የሚያከማቹ አካላት እንዲጠየቁ ማድረግና የተከማቸው ንብረትም ዋጋውን ሳያጣ ወይም ሳይበላሽ ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡

የገቢዎች ሚኒስቴር የማስተካከያ እርምጃ ለመውሰድ ጥረት እያደረገ ቢሆንም የጊዜ ሰሌዳ ተቀምጦ ሀብት ተመድቦለት ወደ ቴክኖሎጂ የሚደረገው ሽግግር የሚፋጠንበት ሁኔታ ላይ መስራት ይገባል ያሉት ክቡር አቶ ገመቹ ለዚህም መንግሥት በቂ ሀብት መመደብ እንዳለበትና ምክር ቤቱም ይህን መደገፍ እንደሚገባው አስገንዝበዋል፡፡ አክለውም ኢኮኖሚው የሚያመነጨውንና ሀገሪቱ ማግኘት የሚገባትን ገቢ ለማግኘት ዘርፉ ቅድሚያ  ተሰጥቶ በቴክኖሎጂና በስርአት ግንባታ ላይ ትኩረት  ማድረግ ያሻል፣ ከዚህ ጎን ለጎንም የክትትልና ቁጥጥር ሥርዓቱን ማጠናከር ይገባል ብለዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ መሀመድ ዩሱፍ መ/ቤቱ በአዋጅ ከተሰጠው ስልጣንና ተግባር አንጻር ለኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ ተቋም ቢሆንም በገቢ አሰባሰብና በጉምሩክ አሰራር በርካታ የኦዲት ግኝቶች እንደተገኙበት አስታውሰዋል፡፡ ከዚህ አኳያ የሂሳብ ኦዲት ግኝቱን በማረም ቀልጣፋና ውጤታማ አሰራር ካልተዘረጋ ከፍተኛ የኦኮኖሚ አውታር የሆነው ይህ ዘርፍ ግቡን እንደማይመታ ገልጸው ይህም ከፍተኛ ተጠያቂነት የሚያስከትል ነው ብለዋል፡፡ ይህንን በመረዳትም ሚኒስቴር መ/ቤቱ ዘመናዊ አሰራርን መከተል፣ ጥብቅ የክትትልና የቁጥጥር ስርዐት ማዘጋጀትና የውስጥ ኦዲት አቅምን ማጠናከር አለበት ሲሉ አሳስበዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *