በውጤት ተኮር ስርአት እቅድ ዝግጅት፣ ትግበራና የአፈጻጸም ስርአት ላይ ለፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የድጋፍ ዘርፍ ሰራተኞች ከሚያዝያ ከ24-25/2010 ዓ.ም ስልጠና ተሰጠ፡፡
በስልጠናው ላይ በመ/ቤቱ የለውጥ ስራ አመራር ዳይሬክቶሬት የለውጥ ስራ አመራር ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አቶ ሀይሉ ፈረደ እስካሁን ድረስ የውጤት ተኮር እቅድ ስርዐት በአለም አቀፍና ሀገሪቱ የነበረውን አፈጻጸምና ያጋጠሙትን ችግሮች እንደመነሻ አቅርበው የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤትም ከነዚህ ችግሮች አስቀድሞ ትምህርት በመውሰድ የተሻለ የውጤት ተኮር እቅድ ዝግጅት፣ ትግበራና ምዘና እንዲኖረው ማድረግ እንደሚኖርበት ገልጸዋል፡፡
አቶ ሀይሉ ስለ ውጤት ተኮር ስርአት ጠቀሜታ፣ ስለስርአቱ ግንባታና ትግበራ ደረጃዎች ንድፈ ሀሳባዊ ማብራሪያ በመስጠት፣ ከመ/ቤቱ ተልእኮ ጋር በማያያዝና ስርአቱ በተጨባጭ እንዲተገበሩ ከሚጠይቃቸው አሰራሮች ጋር በማዛመድ በዝርዝር አስረድተዋል፡፡
በዳይሬክቶሬቱ የለውጥ ስራ አመራር ባለሙያ የሆኑት አቶ አክሊለ ለማ በበኩላቸው በ2010 ዓ.ም. በፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስቴር ተሻሽሎ በወጣው የውጤት ተኮር እቅድ ዝግጅት፣ ትግበራና የአፈጻጸም መመሪያ ላይ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን በዝርዝር አተገባበሩ ላይ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ አቶ አክሊሉ የ2010 በጀት አመት ሁለተኛ አጋማሽ የሰራተኞች የስራ አፈጻጸም ምዘናና የ2011 በጀት አመት የዳሬክቶሬቶች እቅድ በተሻሻለው የውጤት ተኮር አሰራር መሰረት እንደሚተገበር ገልጸዋል፡፡ አክለውም ከሀምሌ 01/2010 ዓ.ም ጀምሮ በመ/ቤቱ የውጤት ተኮር ስርአት አውቶሜሽን ስራን ለማስጀመር ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ከመድረኩ ተሳታፊ በነበሩ ሰራተኞች በተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ላይ ባለሙያዎቹና የለውጥ ስራ አመራር ዳይሬክተሩ አቶ አበራ ተፈራ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ዳይሬክተሩ አቶ አበራ በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ በሰጡት አቅጣጫ ሰራተኛው ለውጤት ተኮር ስርአቱ ተገቢውን ትኩረት መስጠት እንዳለበትና አሰራሩን በተግባር እየተለማመደ በውጤታማነት ሊያስተገብረው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የውጤት ተኮር ስርአቱ ስልጠና ከሚያዝያ 9-10/2010 ዓ.ም ለኦዲት ዘርፍ ባለሙዎች ተሰጥቷል፡፡