የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኢትዮጵያ ኢነርጂ ባለሥልጣን የ2006-2008 በጀት ዓመት የክዋኔ ኦዲት ግኝት ላይ ይፋዊ ስብሰባ ሚያዚያ 10፣ 2010 ዓ.ም አካሄደ፡፡ ተቋሙ በኦዲት በተሰጡ አስተያቶች መሰረት መሠረታዊ የሚባል የማሻሻያ እርምጃ እንዳልወሰደ ተገለጿል፡፡
በኦዲት ግኝቱ እንደተመለከተው ባለሥልጣን መ/ቤቱ በአዋጅ በተሠጠው ሥልጣን መሠረት የኢነርጂ ብቃትና ቁጠባ የሚመለከቱ ድንጋጌዎችን ለማስፈፀም ደንብና መመሪያውን አዘጋጅቶ ተግባራዊ ማድረግ ሲገባው ደንብና መመሪያው በረቂቅ ደረጃ ከማዘጋጀት ያለፈ አፀድቆ ተግባራዊ አለመደረጉ፤ የኢነርጂ ብቃት መፈተሻ ሥርዓት እንዳልተዘረጋ፤ የኢነርጂ ብቃት መፈተሻ ላብራቶሪዎችም እንዳልተቋቋሙ መረጋገጡንና በዚህም ምክንያት ብቃት ያላቸውና የሌላቸውን የኢነርጂ መጠቀሚያ መሣሪያዎች እና የቴክኖሎጂ ዕቃዎች ተለይተው እንዳይታወቁ ከማድረጉም በላይ ወጭ ቆጣቢና ኃይል ቆጣቢ የሆኑትን ለይቶ ሥራ ላይ እንዳላዋለ ተገልጿል፡፡
ባለሥልጣን መ/ቤቱ ለኢነርጂ መጠቀሚያና ለኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚውሉ ቴክኖሎጂዎች ያጠቃቀም ደረጃ አዘጋጅቶ ተግባራዊ ማድረግ ሲገባው በጅምር ደረጃ እንጂ በተጨባጭ አስገዳጅ የአጠቃቀም ደረጃ ባለመውጣቱ በገበያ ላይ ያለው የኤሌክትሪክ ዕቃዎች ምርትና የቴክኖሎጂዎች የአጠቃቀም ደረጃቸው እንዳይታወቅ ማድረጉን፣ ከፍተኛ ብቃት ያላቸውና የሌላቸውን ለይቶ ለማወቅ እና ኢነርጂ ቆጣቢ የሆኑ መሣሪያዎችን ለማበረታታትና ድጋፍ ለማደረግ እንዳልተቻለ ተመልክቷል፡፡
በአገሪቱ ውስጥ ኤሌክትሪክ በማመንጨት፣ በማስተላለፍ በማከፋፈል እና በመሸጥ ሥራ ላይ ለተሰማሩ የፈቃድ አሰጣጥ የአሠራር ሥርዓት በሚገባው ደረጃ አለመሠራቱ በዘርፉ ለመሠማራት ለሚፈልጉ ባለሃብቶችና ባለሙያዎች ችግር የሚፈጥርና የኢነርጂ ዘርፍ እንዳያድግ የራሱን አሉታዊ ተጽዕኖ ማድረጉ፤ ባለሥልጣን መ/ቤቱ ከፍተኛ የኢነርጂ ተጠቃሚዎች የቁጥጥርና ክትትል ሥራ በመሥራት የኢነርጂ አጠቃቀማቸው የተሻለ እንዲሆንና ብቃት ያላቸውን የኢነርጂ ቴክኖሎጂዎች እንዲጠቀሙ ያለመሠራቱ እንዲሁም የኢነርጂ ተጠቃሚዎች ኃይል ቆጣቢ ያልሆኑና ብቃት የሌላቸው ማሽነሪዎች፣ መሣሪያዎች፣ ጀነሬተሮች እንዲሁም አምፑሎች እንዲጠቀሙ እና ኢነርጂው እንዲባክን መደረጉ በኦዲት ግኝቱ ተገልጿል፡፡
ባለሥልጣን መ/ቤቱ የሀገሪቱ የኢነርጂ ፍላጎት፣ የተመረተ፣ ጥቅም ላይ የዋለ፣ እና ያልዋለ የኢነርጂ መጠን ለይቶ ማወቁን ለማረጋገጥ ኦዲት ሲደረግ ተግባራዊ አለመሆኑንና በዚህም ምክንያት መቆጠብ የሚገባን የኢነርጂ መጠን እንዳይቆጥብ እንቅፋት መሆኑ እና ጥቅም ላይ የዋለና ያልዋለ የኢነርጂ መጠን መረጃዎችንም በመተንተን ውጤቱን ለስትራቴጂክ እና ፖሊሲ ውሳኔ ግብዓት እንዲሆን አለመደረጉ እና ከፍተኛ የኢነርጂ ተጠቃሚ አካላት የኢነርጂ አጠቃቀም ዕቅድና መርሀ-ግብር እንዲያወጡና አፈፃፀማቸውንም ሪፖርት እንዲያደርጉለት ሥርዓት ዘርግቶ ተግባራዊ አለማድረጉ፤ የሚቀርብለትን የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ከመርሃ-ግብር አንፃር ገምግሞ ውጤቱን ለሚመለከታቸው ተቆጣጣሪ አካላት ማሳወቅ ቢገባውም ከፍተኛ የኢነርጂ ተጠቃሚዎች የፈቃደኝነት ስምምነቱን ያልፈረሙ በመሆኑ የኢነርጂ አጠቃቀም ዕቅድና መርሃ ግብር እንደማያዘጋጅና በዕቅዱ መሠረት ግምገማ ውጤታቸውንም ለሚመለከተው አካል እንደማያሳውቅ ተገልጿል፡፡
በናሙና ተመርጠው ከታዩ ከፍተኛ የኢነርጂ ተጠቃሚ ፋብሪካዎች፣ ድርጅቶች፣ ሆቴሎች እና ሆስፒታሎች የተደረገላቸው የቴክኒክና ፋይናንስ ድጋፍ እንደሌለ እንዲሁም ኃይል አባካኝ የሆኑ የኢነርጂ መጠቀሚያ ቴክኖሎጂዎች በኃይል ቆጣቢ ለመተካት የመግዛት አቅም የሌላቸው ተቋማት የፋይናንስ ድጋፍ እንዳይኖራቸው ክፍተት ከመፈጠሩም በላይ ላላስፈላጊ ወጪ እንዲዳረጉና ተቋሞቹ መቆጠብ የሚገባቸውን የኢነርጂ መጠን እንዳይቆጥቡ እንዳደረጋቸው እንዲሁም የኢነርጂ ብቃትና ቁጠባን በሚመለከትም የሚነሱ ቅሬታዎች አፈታት ሥርዓት ያልዘረጋ መሆኑ በኦዲት ግኝቱ ተገልፆ ባለሥልጣን መ/ቤቱ በአዋጅ የተሠጠውን ተግባርና ኃላፊነት እንዳይወጣ ያደረገውን ምክንያት እንዲያስረዳ ቋሚ ኮሚቴው ጥያቄውን አቅርቧል፡፡
አቶ ጌታሁን ሞገስ የኢትዮጵያ ኢነርጂ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ለተነሱት ጥያቄዎች ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ደንብና መመሪያ ያልወጣው ከፍተኛ የኤሌክትሪክ የማመንጨት ፍላጎት በግል ባለሃብቱ በመነሳቱና ተያይዞም የፈቃድ አሠጣጥ ጥያቄዎች በመምጣቸው የአዋጅ ማሻሻያ ጥያቄ ቀርቦ ለምክርቤቱ መላኩንና አወጁ ሲፀድቅ ደንቡም ተያይዞ ይፀድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ፤ ደንቡ በሚፈለገው ጊዜ አለመፅደቅ በርካታ ጉዳዮችን በወቅቱ ተግባራዊ ለማድረግ እንዳላስቻላቸው፤ ላብራቶሪዎችን በተመለከተ የ2006 አዋጅን ተከትሎ ተፈፃሚ ለማድረግ መዋቅራዊ ማስተካከያ የሚፈልጉ በመሆኑ ለመተግበር መቸገራቸውን ነገር ግን የተለያዩ የላብራቶሪ እቃዎች ግዥዎችን የመፈፀም ሂደት ላይ እንደሚገኙ፤ አስገዳጅ የአጠቃቀም ደረጃን በተመለከተም በኢነርጂ ብቃትና ቁጠባ ፕሮግራም ውስጥ ሁሉንም እቃ ማስገባት እንደማይችሉ ገልፀው በዋናነት የእንጀራ ምጣድ፣ ምድጃ እና ኢንዱስቲሪያል ሞተሮች ላይ አስገዳጅ ደረጃ ለማውጣት የምርት ማኑዋል ከማዘጋጀት ጀምሮ የተለያዩ ተግባራት እየተሰሩ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡
የፈቃድ አሠጣጥ በተመለከተም በአዲሱ አዋጅ ውስጥ ያለና ደንቡ ያልፀደቀ በመሆኑ ተግባራዊ አለመደረጉን፤ ከፍተኛ የኢነርጂ ተጠቃሚዎች ብቃት ያለቸውን ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀሙ ከማድረግ አኳያ የ2006 አዋጅ ቅጣትንም የሚደነግግ ቢሆንም በቀጥታ ተግባራዊ ለማደረግ ደንቡ ባለመፅደቁ ተፈፃሚ ለማድረግ እንደተቸገሩና በዋናነትም ከቅጣት ይልቅ በማግባባትና በስምምነት ሊሠሩ የሚችሉ እንደዝርዝር እና ዎክሥሩ /walkthrough/ ኦዲት ያሉ መንገዶችን በመጠቀም የክትትልና የቁጥጥር ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኝ፤ በቁጠባ በኩልም ኃይል ቆጣቢ ቴክኖሎጂዎችን ቢጠቀሙ ኢንዱስትሪው አዋጭ መሆኑን የማስተማር ሥራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ፤ የኢነርጂ አጠቃቀም የፈቃደኝነት ስምምነትን በተመለከተም ሥልጠና መሰጠቱን፣ ረቂቅ ሰነድ መዘጋጀቱንና በሰነዱ ላይ አንድ ዙር ምክክር ካደረጉ በኋላ ወደመፈራረም ሥርዓት እንደሚገቡ፤ በኢነርጂ ፈንድ በኢነርጂ ብቃትና ቁጠባ ለሚሣተፉ የኢነርጂ ተጠቃሚ ተቋማት የቴክኒክና የፋይናንስ ድጋፍ ከማድረግ አንፃር አሠራር ለመዘርጋት መመሪያና ሌሎች ስታንዳርዶች መጽደቅ ጋር ምላሽ የሚያገኙ መሆናቸውን እና የቅሬታ አፈታት ሥርዓትም ደንብና መመሪያን ተከትሎ ተግባራዊ የሚሆን መሆኑን አቶ ጌታሁን አስረድተዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴ አባላት በተሰጡት ምላሾች ላይ የተለያዩ አስተያየቶችንና ተጨማሪ ጥያቄዎችን የሰጡ ሲሆን በዋናነት በተቋሙ ላይ ኦዲቱ የተደረገው ከረጅም ጊዜ በፊት ቢሆንም ተቋሙ አስካሁም ምንም እርምጃ አለመውሰዱ ለኦዲት ግኝቱ ትኩረት አለመስጠቱን እንደሚያሳይ፤ ደንብና መመሪያ የማያስፈልጋቸው ሥራዎችም ደንብ አልወጣም በሚል ምክንያት አለመሰራታቸውን፤ ከፍተሻ ላብራቶሪ ጋር በተያያዘም ተቋሙ አጥጋቢ ምላሽ አለመሠጠቱን ገልፀው ደንብና መመሪያ ለማፀደቅ ረጅም ጊዜ ተቋሙ የወሰደበትን ምክንያት ለተከበረው ምክር ቤት ማብራሪያ እንዲሠጡ ተጠይቀዋል፡፡
በውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ፍሬህይወት ወልደሃና (ዶ/ር) በሰጡት ምላሽ በተቋሙ የአቅም ውስንነት መኖሩን እና ያለውን የአቅም ውስንነት ለመቅረፍ አቅም የማጎልበት ከፍተኛ ሥራ ሚኒስቴር መ/ቤቱ በቀጣይ እንደሚሠራ ገልፀዋል፡፡
ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ የፌዴራል ዋና ኦዲተር ምክትል ዋና ኦዲተር ተቋሙ የኢነርጂ ብቃት መፈተሸ ሥርዓት ሊዘረጋ እንደሚገባ፤ የኢነርጂ ብቃት ማረጋገጫ ኮዶች ተግባረዊ ማድረግ እንዳለበት፤ ከፍተኛ ኢነርጂ በሚጠቀሙ ተቋማት ላይ ኢነርጂ ቆጣቢ ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀሙ የቁጥጥርና የክትትል ሥርዓት ሊዘረጋ እንደሚገባ፤ የኢነርጂ ውጤታማነት ጋር በተያያዘ የቁጥጥርና የክትትል ሥራውን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ፤ መ/ቤቱ በአገሪቱ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለውንና የሌለውን ኢነርጂ ሊያውቅ እንደሚገባ እና የኢነርጂ መጠቀሚያ ቴክኖሎጂዎች ገበያ ላይ ከመዋላቸው በፊት ፍተሻ ሊደረግልቸው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ የፌዴራል ዋና ኦዲተር በሰጡት አስተያየት ደንቡን መ/ቤቱ በወቅቱ አለማዘጋጀቱንና የውሃ፣ መስኖና ኤሊክትሪክ ሚኒስቴርም ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ፤ 2006 ዓ.ም የወጣው አዋጅ እንደገና የሚሻሻል ከሆነ ደንቡም ጎን ለጎን ተሸሽሎ የማቅረቡ ሥራ ሊጠናቀቅ እንደሚገባ፤ የመፈተሻ ለብራቶሪ ግንባታ ደንቡ ባይወጣም ተግባራዊ ማድረግ የሚቻል በመሆኑ ትኩረት ተሰጥቶት ተግባረዊ ሊደረግ እንደሚገባ፤ የአስገዳጅ ደረጃን ተፈፃሚ ማድረግ የሚያስችለውን መመሪያም ደንቡ ፀድቆ እንደወጣ በቶሎ ወደተግባር መግባት በሚያስችል ደረጃ ተዘጋጅቶ ሊቀመጥ እንደሚያስፈልግ እና የኢነርጂ ፈቃድ ቁጠባ የሚነሱ ቅሬታዎች መቅረፍ የሚያስችል የቅሬታ አፈታት ሥርዓትም ሊዘረጋ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የተከበሩ ወ/ት ወይንሸት ገለሶ በመጨረሻ በሰጡት አስተያየት በኦዲት አስተያየት ላይ መሠረታዊ የሚባል የማሻሻያ እርምጃ አለመውሰዱን፤ ደንብ የማያስፈልጋቸውና ደንብ ባይወጣም ሊሠሩ የሚችሉ ሥራዎች በአግባቡ ተለይተው አገልግሎት ሊሰጥና የኢነርጂ ብቃት ማሻሻያ ቴክኖሎጂዎች ትኩረት ተሰጥቶባቸው ሊሠሩ እንደሚገባ፤ ቅንጅታዊ አሠራር ከምርምርና ቴክኖሎጂ ተቋማት ጋር ማድረግ እንደሚያስፈልግ እና የቅሬታ አፈታት ሥርዓት በሚፈለገው ደረጃ ባለሥልጣን መ/ቤቱ ሊዘረጋ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ባለሥልጣን መ/ቤቱ በኦዲት አስተያየት ትኩረት እንዳልሰጠ ተገለፀ
