News

አገልግሎቱ የማዕቀፍ ግዥ ስርአቱን ችግሮች በመፍታት ከተጠቃሚዎች የሚቀርቡበትን ቅሬታዎች ማስቀረት እንዳለበት ቋሚ ኮሚቴው አሳሰበ

የመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት በሚያካሂደው የማዕቀፍ ግዢ ተጠቃሚ የሆኑ ተቋማት የሚያቀርቡበትን መጠነ ሰፊ ቅሬታ በሚያስቀርና የተቋቋመበትን አላማ በሚያሳካ አግባብ ያሉበትን የአሰራር ችግሮች መፍታትና በእቅድ መንቀሳቀስ እንዳለበት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ከ2006-2008 ዓ.ም እና የ2009 የመጀመሪያ ሩብ አመት የነበሩ የአገልግሎቱ የስራ ክንውኖችን በማካተት ባደረገው የማእቀፍ ግዥ የኮንትራት ውል አፈጻጸም የክዋኔ ኦዲት እንዲሁም በ2008 በጀት አመት በአገልግሎቱ ሂሳብ ላይ ባደረገው የሂሳብ ኦዲት ላይ ቋሚ ኮሚቴው መጋቢት 26/2010 ዓ.ም ይፋዊ ስብሰባ አካሂዷል፡፡

በስብሰባው ወቅት በክዋኔና በሂሳብ ኦዲቶቹ የተገኙ ግኝቶች በዝርዝር ቀርበዋል፡፡

በክዋኔ ኦዲት በኩል አገልግሎቱ በማዕቀፍ ግዥ እቃ ለማቅረብ ጨረታ ያሸነፉ አቅራቢዎችን ከመወሰኑና ከነርሱ ጋርም ውል ከመፈራረሙ በፊት የቀድሞ የመልካም ስራ አፈፃፀማቸውን የሚገመግምበት አሰራር ቢዘረጋም ቅሬታ በቀረበባቸው አቅራቢዎች ላይ እርምጃ እንዳልወሰደና ከአቅራቢዎቹ ጋር ለ3 ዓመታት (2008-2010) የማዕቀፍ ውል ስምምነት ፈጽሞ እንደተገኘ ኦዲቱ አሳይቷል፡፡

ተጨማሪም የማዕቀፍ ግዥ ከመከናወኑ በፊት ከሁሉም የመንግስት መ/ቤቶች የግዥ ፍላጎት ተሰብስቦ የሚፈለገው እቃ መጠን በቅድሚያ ታውቆ ጨረታ በማውጣት አቅራቢዎች ውሉን ከመፈፀማቸው በፊት የሚያቀርቡትን ዕቃ በተፈለገው ጊዜና መጠን ለማቅረብ ብቃታቸው እና አቅማቸው በበቂ ሁኔታ ሳይረጋገጥ ውል እንደሚዋዋልና በማዕቀፍ ውል በተጠቀሰው መሠረት የግዥ ትዕዛዝ በደረሳቸው በ7 ቀናት ውስጥ እቃዎችን አጠናቀው በማያስረክቡ አቅራቢዎች ላዘገዩበት ጊዜ በቀረበው የውል መጠን በየቀኑ 0.1% የጉዳት ካሳ እንዳላስከፈለ ተገልጿል፡፡

የእቃዎችን ጥራት ከማረጋገጥ ጋር ተያይዞም አገልግሎቱ የማዕቀፍ ግዢ ውል ለተዋዋለላቸው የመንግስት መ/ቤቶችና ዩኒቨርስቲዎች የቴክኒክ መግለጫ (specification) በሲዲ የሚልክ ቢሆንም ናሙና ግን እየላከ አለመሆኑንና ለተጠቃሚ መ/ቤቶች ከቴክኒክ መግለጫው እና ከቀረበው ናሙና ጋር በተጣጣመ መልኩ እቃው ገቢ እየተደረገ መሆኑን የሚያረጋግጥበት ሥርዓት አለመኖሩን የኦዲት ሪፖርቱ ያሳያል፡፡ ለአብነትም የ2007 እና የ2008 በጀት አመታት ዕቅድ አፈፃፀም ላይ እቃዎቹ በአግባቡ ለተጠቃሚ መ/ቤቶች በወቅቱ መድረሳቸውን አለመከታተሉ፣ ተጠቃሚ መ/ቤቶች ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እቃዎች በስተቀር በማዕቀፍ ግዥ የተገዙ እቃዎችን ሲረከቡ በውሉ ላይ በተቀመጠው ስፔስፊኬሽንና ናሙና መሰረት ስለመሆኑ በአገልግሎቱ የማይረጋገጥ መሆኑ እንዲሁም አገልግሎቱ በማዕቀፍ ግዥ ውል የተገዙ እቃዎች በውሉ ላይ በተቀመጠው ስፔስፊኬሽን እና ናሙና መሰረት በባለሙያ ተረጋግጠው ርክክብ የተፈጸመባቸው መሆኑን የማረጋገጥ ሥራ በዓመታዊ እቅድ አካቶ አለመስራቱ ተገልጸዋል፡፡

የመንግሥት መ/ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች እቃ አቅራቢ ድርጅቶች እቃዎቹን ሙሉ በሙሉ ሲያስረክቡ በአምስት ቀናት ውስጥ ክፍያ ሊፈጽሙና አገልግሎቱም በገባው ውል መሠረት አቅራቢዎች ላቀረቡት እቃ ክፍያ ስለመከፈሉ አፈፃፀሙን መከታተል ቢገባውም የማዕቀፍ ግዥ ተጠቃሚ የመንግሥት መ/ቤቶች እና ዩኒቨርሲቲዎች እቃዎቹን ሙሉ በሙሉ ሲረከቡ ላቅራቢ ድርጅቶቹ በአምስት ቀናት ውስጥ ክፍያ የማይፈፅሙ መሆኑንና አገልግሎቱም አቅራቢዎች ክፍያ እንዲፈፀምላቸው ሲያሳውቁ ብቻ ተጠቃሚ መ/ቤቶችን እንዲከፍሉ በደብዳቤ ከማሳወቅ በስተቀር ክፍያው መፈጸሙን የሚያረጋግጥበት አሰራር ስርዓት የሌለ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ከመንግስት መ/ቤቶች እና ከአቅራቢዎች ጋር የመረጃ ልውውጥ ስርዓት በመዘርጋት በዘመናዊ መልኩ የተደራጀና ቀልጣፋ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑ ኦዲት ሲደረግም አገልግሎቱ በማዕቀፍ ግዥ ዙሪያ ከሚመለከታቸው የመንግስት መ/ቤቶች እና ከአቅራቢዎች ጋር በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ የመረጃ ልውውጥ እንደማያደርግና  የተደራጀ የመረጃ ቋት (data base) ስርዓት ዘርግቶ ተግባራዊ እንዳላደረገ ታውቋል፡፡

በሂሳብ ኦዲት በተገኙ ግኝቶች ረገድ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች መግዣ በብሔራዊ ባንክ ወደ አገልግሎቱ የባንክ ሂሳብ ቁጥር ገቢ የተደረገው ብር 6,000,000.00 ለተሽከርካሪዎች ግዥ ማስፈፀሚያ ተለይቶ የተላከ የአደራ ወይም የመያዣ ሂሳብ በመሆኑ በተከፋይ ሂሳብ መያዝ ሲገባው የገቢ ደረሰኝ ተቆርጦለት አገልግሎቱ ከተሽከርካሪዎች ሽያጭ ከሚያገኘው ገቢ ጋር ተካቶ በገቢ ተመዝግቦ ሪፖርት የተደረገ መሆኑን የኦዲት ሪፖርቱ ያሳያል፡፡

በተሰብሳቢና ተከፋይ ሂሳብ ረገድም በተለያዩ የሂሳብ መደቦች በድምሩ ብር 352,267,320.48 በተወሰነው የጊዜ ገደብ ውስጥ ያልተወራረደ ውዝፍ ተሰብሳቢ ሂሳብና በወቅቱ ክፍያው ያልተፈጸመ ብር 342,950,209.55 ተከፋይ ሂሳብ መኖሩ ታውቋል፡፡

ከዚህም ሌላ በ2008 በጀት ዓመት ለአገልግሎቱ ከተፈቀደው በጀት ውስጥ በዋና ዋና የበጀት አርዕስቶች ከ10% በላይ ያልተሰራበት በጀት መኖሩን ለማረጋገጥ ኦዲት ሲደረግ በድምሩ ብር 72,440,818.60 ያልተሰራበት በጀት መኖሩ ታውቋል፡፡

እንደዚሁም ከ2007 በጀት ዓመት የተላለፈ የ2008 በጀት የመነሻና የመክፈቻ ሂሳብ በትክክል መተላለፉን ለማረጋገጥ ኦዲት ሲደረግ በ2008 በጀት ዓመት የመነሻ ሂሳብ ላይ የጥሬ ገንዘብና የባንክ ሂሳብ በመብለጥ ብር 134,101,590.58፣ የተከፋይ ሂሳብ ደግሞ በማነስ ብር 4,740,402.45 የተላለፈ መሆኑ ታውቋል፡፡

በንብረት ማስወገድ በኩል በአገልግሎቱ የንብረት መጋዘን ውስጥ አገልግሎት የማይሰጡ ብዛት ያላቸው የተለያዩ ንብረቶች (ጠረጴዛዎች፣ ወንበሮች፣ የፋክስ ማሽን፣ ፎቶ ኮፒ ማሽን፣ ካዝና) እንዲሁም ብዛት ያላቸው ንብረትነታቸው የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን እንደሆነ የተገለጹ ልዩ ልዩ መፃህፍቶች ተከማችተው ተገኝተዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በክዋኔና በሂሳብ ኦዲቶቹ ላይ የተገኙት ግኝቶች በምን ምክንያት እንደተፈጠሩና ከኦዲቱ በኋላ ለማሻሻል የተወሰዱ እርምጃዎች ምን እንደሆኑ እንዲገለጽለት የጠየቀ ሲሆን የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ይገዙ ዳባና ሌሎች የስራ ኃላፊዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በዚህም የማእቀፍ ግዢ ለአገልግሎቱ አዲስ አሰራር የነበረ በመሆኑ በሂደቱ የተለያዩ ጉድለቶች እንዳጋጠሙ፣ የኦዲት ግኝቱ በ2010 የሚደረገውን የማእቀፍ ግዢ የተሻለ ለማድረግ እንደግብአት እንደተወሰደና ከግኝቱ በኋላም በበርካታ ጉዳዮች ላይ የማሻሻያ ስራ እንደተሰራ ጠቅሰዋል፡፡

ወደ ዝርዝር የኦዲት ግኝቶቹ ሲገቡም ከመልካም ስራ አፈጻጸም ጋር በተያያዘ አገልግሎቱ የማዕቀፍ ግዥ አቅራቢዎችን አፈጻጸም እንደሚገመግም ገልጸው ነገር ግን አፈጻጸማቸው ደካማ የሆኑት አቅራቢዎች በቀጣይ የመንግስት ግዢ እዳይሳተፉ ሊያግድ የሚችለው የመንግስት የግዥና ንብረት አስተዳደርና ኤጀንሲ እንደሆነና የጥፋተኝነት ሪፖርት የማቅረቡ ኃላፊነት የተጠቃሚ መ/ቤቶች እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ አገልግሎቱ የማእቀፍ ግዢ ሲፈጽም ካሉት ተጠቃሚ የመንግስት መ/ቤቶች ውስጥ ግማሾቹ ብቻ የግዥ ፍላጎታቸውን እንደሚያሳውቁና በዚህ ምክንያት ከቀረበው ፍላጎት ሌላ ግምታዊ ጭማሪ በማከል አቅራቢዎቹ እስከ 300% ድረስ ተጨማሪ እቃ እንዲያቀርቡ በማድረግ የግዢ ፍላጎታቸውን ያላቀረቡ መ/ቤቶችም ጭምር ከአቅርቦቱ እንዲጠቀሙ እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸው በዚህ መሀል ከአቅርቦት እጥረት ጋር ተያይዞ በሚፈጠር ቅሬታ መነሻነት ውል ከገባው በላይ እቃ ያቀረበውን አቅራቢ ማስቀጣት እንደሚያስቸግር ተናግረዋል፡፡ በሌላ በኩል ግን በገቡት ውል መሰረት እቃ የማያቀርቡትን አቅራቢዎች የመቅጣት፣ ብላክ ሊስት ውስጥ የማስገባትና ያስያዙትን የውል ማስከበሪያ የመውረስ ስራ መሰራቱን ገልጸዋል፡፡

የግዥ ውል ከመፈጸሙ አስቀድሞ የአቅራቢዎችን ብቃትና አቅም ማረጋገጥን በተመለከተም አቅራቢዎች ሊያሟሏቸው የሚገቡ መስፈርቶችን በጨረታ ሰነድ ውስጥ በማካተት መሟላታቸው እደሚገመገም በአካል በመሄድም አቅማቸው እንደሚረጋገጥ ገልጸው ችግሩ የሚመጣው ቀደም ብሎ እንደተገለጸው የመንግስት መ/ቤቶች የግዢ ፍላጎታቸውን ባለማቅረባቸው በሚፈጠረው ሁኔታ እንደሆነ አስረድተው አቅም የሌላቸው አቅራቢዎች ግን ወደ ጨረታ እንዲገቡ እንደማይደረግ ተናግረዋል፡፡

እቃን በወቅቱ በማያቀርቡ አቅራቢዎች ረገድ መ/ቤቶች እቃን በወቅቱ ያላቀረበላቸውን አቅራቢ በውሉ መሰረት አስልተው የጉዳት ካሳ እንዲቀጡ መመሪያ እንደተላከላቸው አስረድተዋል፡፡ እንዲሁም አገልግሎቱ በወቅቱ እቃ የማያቀርቡ አቅራቢዎችን የጉዳት ካሳ እያስከፈለ እንደሚገኝ ገልጸው በአቅራቢዎች በኩል ግን እነርሱ ብቻ እንደሚቀጡና ላቅራቢዎች መክፈል የሚገባቸውን ክፍያ የሚያዘገዩ የመንግስት ተቋማት እንደማይቀጡ በመግለጽ ህጉ በእኩል ደረጃ አላየንም፣ ለመንግስት አዳልቷል የሚል ከፍተኛ ቅሬታ እንዳለ ተናግረዋል፡፡

እቃዎችን ተረክበው ለአቅራቢዎች ክፍያ የማይፈጽሙ መ/ቤቶችን በተመለከተም ክፍያ በማይፈጽሙም ሆነ የግዥ ፍላጎታቸውን በማያቀርቡት መ/ቤቶች ላይ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ እንደሌለ በመግለጽ በነዚህና በስፔሲፊኬሽን መሰረት እቃ መቅረቡን ሳያረጋግጡ በሚቀበሉ ተቋማት ኃላፊዎች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ መመሪያ እንዲዘጋጅ ለገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር መጠየቁን ተናግረዋል፡፡ መመሪያው መዘጋጀት ያለበት ከመንግስት ግዥ አዋጅ ጋር ተያይዞ እንደሆነና የግዥ አዋጁ ለምክር ቤቱ ቀርቦ እስኪጸድቅ ላለፉት ሁለት አመታት እየተጠበቀ እንደሆነ በመግለጽ አሁን ባለው ሁኔታ ያልከፈሉት ተቋማት ክፍያውን እንዲፈጽሙ አገልግሎቱ በደብዳቤ እየጠየቀ እንደሚገኝ ተናግረው ቋሚ ኮሚቴው አዋጁ በቶሎ እንዲጸድቅ ድጋፉን እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡ ላቅራቢዎች ክፍያ አለመፈጸም በመልካም አስተዳደር ችግርነት በአጭር ጊዜ ይፈታሉ ተብለው ከተለዩት ችግሮች አንዱ እንደሆነ የገለጹ ሲሆን ክፍያ ላቅራቢዎች በማይከፍሉ ተቋማት ውስጥ ክፍያውን ለማስለቀቅ መማለጃ የሚጠየቅበት ሁኔታ እንዳለ ገልጸዋል፡፡

ናሙና ማቅረብንና የእቃዎችን የጥራት ደረጃን በሚመለከት የሚገዙ እቃዎች የተዘጋጀላቸውን ዝርዝር የፍላጎት መግለጫ ማሟላታቸውን በመገምገም እንዲሁም ናሙናቸው ቀርቦ በኢትዮጵያ የተስማሚነትና ምዘና ድርጅት አማካኝነት የኢትዮጵያ የጥራት ደረጃዎችን የሚሟሉ መሆናቸው በማረጋገጥ የሚገዙ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ የእቃዎች ስፔሲፊኬሽን ለመ/ቤቶቹ በሲዲ ቢላክም የቀረቡ ጥቂት ናሙናዎችን ከ200 በላይ ለሁኑ ተጠቃሚ  ተቋማት መላክ እንደሚያስቸግር ገልጸው ተቋማት ናሙናውን ከአገልግሎቱ ዘንድ ማየት እንደሚችሉና በቀረበላቸው እቃ ጥራት ላይ ጥርጣሬ ካላቸውም ናሙና በመላክ አገልግሎቱ በኢትዮጵያ የተስማሚነትና ምዘና ድርጅት በኩል እንደሚያረጋግጥ በደብዳቤ መገለጹን፤ እቃው ችግር ካለበትም እንደሚስተካከል አስረድተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የግዥ መመሪያው ምን ያህል ናሙና መቅረብ እንዳለበት እንደማይገልጽና የግዥ አዋጁ ሲጸደቅ ይህ ጉዳይ እንደሚስተካከል ገልጸዋል፡፡

ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ኦዲቱ በተካሄደበት ወቅት አገልግሎቱ የራሱ የመረጃ ማዕከል እንዳልነበረው፣ ከኦዲቱ በኋላ ግን ማዕከሉን እንዳቋቋመና መረጃዎች በሙሉ ወደ ማዕከሉ እንዲገቡ እንደተደረገ አስረድተዋል፡፡ ከዚህ ውጪ ግን በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚዘረጋ ስርአት የበለጠ ጠቃሚ ነው የሚለውን ሀሳብ ለገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር በማቅረብና ከመንግስት ግዢና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ጋር በመነጋገር በሀገር አቀፍ ደረጃ ኢ-ፕሮኪዩርመንት የሚባል ስርአት ለመዘርጋት ዝግጅት እየተደረገ እንዳለና በሚቀጥለው በጀት አመት ወደዚህ ስርዓት ይገባል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስረድተዋል፡፡ ስርዓቱ ተግባራዊ ሲደረግ ግብይቱ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተደግፎ ስለሚከናወንና ባብዛኛው ከሰው ንክኪ ነጻ ስለሚሆን ከግዥ ጋር የተገናኙ ሙስናን ጨምሮ በግዥ ስርዓቱ ውስጥ ያሉ በርካታ ችግሮችን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚቀርፍ አስረድተዋል፡፡

የሂሳብ ኦዲት ግኝቶችን ሲያስረዱም በውስጥ ገቢ የተመዘገው 6 ሚሊዮን ብር በአደራ አለመመዝገቡ ስህተት እንደነበረና እንደተስተካከለ ገልጸዋል፡፡ በተሰብሳቢና በተከፋይ ሂሳብ በያንዳንዳቸው ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ የተከማቸውም በአገልግሎቱ በኩል ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ትራንስፎርመር ግዢ ከተፈጸመ በኋላ አቅራቢው በዝርዝር የፍላጎት መግለጫው መሰረት እቃውን ባለማቅረቡ ግዥው ተቋርጦ ጉዳዩ ወደ ህግ በመሄዱ እልባት እስኪያገኝ ጌዜ በመውሰዱ የተፈጠረ መሆኑንና ጉዳዩ በድርድር መፈታቱን አስረድተው ተሰብሳቢና ተከፋይ ሂሳብ በከፍተኛ መጠን እየቀነሰ እንዳለና ከዚህ ውስጥ 270 ሚሊዮን ብር የሚሆነው የኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር የተያያዘው ገንዘብ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ከተከፋይና ከተሰብሳቢ ሂሳብ ጋር ያለው ሌላው ችግር ከውጭ የሚገዙ እቃዎች ጋር በተገናኘ የሌተር ኦፍ ክሬዲት በተለያዩ ችግሮች ሳቢያ በውሉ ባለው ጊዜ ባለመጠናቀቁ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ወደፊት በአገልግሎቱ ላይ የሚታየው ተሰብሳቢና ተከፋይ ሂሳብ ግዢ በሚፈጸምላቸው መስሪያ ቤቶቹ ሂሳብ ላይ እንዲታይ ለማድረግ በባንክ ሌተር ኦፍ ክሬዲት የመክፈቱን ስራ ወደ የመ/ቤቶቹ ለመመለስ መታቀዱን ገልጸዋል፡፡

ከበጀት አጠቃቀም ጋር ተያይዞም አገልግሎቱ መዋቅሩ ልክ በሰው ሀይል ተሟልቶ እየሰራ ባለመሆኑ ሰራተኞች ለመቅጠር እንዲቻል ተጨማሪ ቢሮዎችን ለመገንባት የታቀደው እቅድ ሳይሳካ በመቅረቱ አስፈላጊው የሰው ሀይል ባለመቀጠሩ ምክንያት ሁኔታው እንደተከሰተና በቀጣይ እቅድንና የበጀት አጠቃቀምን አጣጥሞ ለመስራት ጥረት እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡

የጥሬ ገንዘብ ጉድለትና ብልጫን በሚመለከት መ/ቤቱ ኢፍሚስ የተባለውን አዲሱን የፋይናንስ ስርዓት በሚተገብርበት ወቅት በባለሙያዎች ክህሎት ማነስ ምክንያት በተፈጠረ የምዝገባ ስህተት እንጂ 134 ሚሊዮን ብሩ በመደብ እንዳልተመዘገበና የዚህ አይነት ስህተቶች ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር እየተፈቱ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ከንብረት ማስወገድ ጋር በተያያዘ በርካታ የተከማቹ ንብረቶች በአገልግሎቱ እንደነበሩና በአሁኑ ወቅት አብዛኞቹ በሽያጭ እንደተወገዱ፤ ያልተወገዱት ንብረትነታቸው የቀድሞው ፕላን ኮሚሽን የነበሩ በርካታ መጽሀፍት እንደሆኑና ፕላን ኮሚሽን እንዲወስዳቸው በተደጋጋሚ ቢጠየቅም ኮሚሽኑ ሰነዶቹን ለምርምርና ጥናት ስራ እንደሚፈልጋቸው አሳውቆ ነገር ግን የማስቀመጫ ስፍራ ስለሌለው ሲፈለግ ከአገልግሎቱ ሄዶ እንዲጠቀም በመባሉ ማስወገድ እንዳልተቻለ አስረድተዋል፡፡ ከዚህ ውጪ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እነዚህን መጽህፍት እንዲወስድ ሀሳብ መቅረቡንና በቀጣይም የኦዲት ግኝት እንዳይሆን የሚመለከታቸው አካላት ጋር ተነጋግሮ እልባት መስጠት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

በአገልግሎቱ የስራ ኃላፊዎች በተሰጠው ምላሽ ላይ በቋሚ ኮሚቴው አባላት፣ በባለድርሻ አካላትና ከአገልግሎቱ የማእቀፍ ግዢ ዋነኛ ተጠቃሚ በሆኑ ተቋማት በኩል ተጨማሪ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ቀርበዋል፡፡

በቋሚ ኮሚቴው አባላት በኩል ከመልካም ስራ አፈጻጸምና የአቅራቢዎች ብቃት ጋር ኦዲቱ ያነሳውን ጉድለት የግዥ እቅድ በማያቀርቡ ተቋማት ምክንያት እንደተፈጠረ አድርጎ ማቅረቡ አገልግሎቱ ድክመቱን ከመቀበል ይልቅ ሌሎችን ተጠያቂ ለማድረግ እየሞከረ መሆኑን እንደሚያሳይ ገልጸዋል፡፡ እንደዚሁም ቋሚ ኮሚቴው የኦዲት ግኝትን መሰረት በማድረግ ከተቋማት ጋር በሚያደርገው ይፋዊ ስብሰባም ሆነ ከዩኒቨርስቲዎች ጋር ባለው የድጋፍና የክትትል ስራ እቃዎችን ገዝቶ በወቅቱና በሚፈለገው ጥራት ያለማቅረብ ሰፊ ድክመት በአገልግሎቱ በኩል እንዳለ በሚገለጽበት ሁኔታ ውስጥ አገልግሎቱ ተቋማት በወቅቱ የግዥ እቅድ አያቀርቡም በሚል ጉዳዩን ወደ ሌሎች አካላት መግፋቱ እንዲሁም ከሞላ ጎደል ለሁሉም የኦዲት ግኝቶች ሌሎች አካላትን ተጠያቂ ማድረጉ ተገቢ እንዳልሆነና ራሱን ከግኝቶቹ አኳያ በደንብ ማየት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

በንብረት ማስወገድ በኩልም ኦዲቱ የሚያሳየው ስላልተወገዱ መጽሀፍት ብቻ ሳይሆን ስለተከማቹ ጠረጴዛዎች፣ ወንበሮች፣ የፋክስ ማሽንና ሌሎች ንብረቶች ጭምር በመሆኑ ጉዳዩን ወደ መጽሀፍት ብቻ መውሰዱ ትክክል አለመሆኑንና ሌሎቹ ንብረቶች ላይ ስለተወሰደው እርምጃ መገለጽ አለበት ብለዋል፡፡

ከዚህም ሌላ አገልግሎቱ ለመንግስት የሚያስፈልጉ እቃዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ፣ በጊዜና በጥራት እንዲያቀርብ የተቋቋመ ሆኖ ሳለ በተጨባጭ ሲታይ እቃዎችን በጊዜ በማያቀርብበት፣ ለጥራት ማመሳከሪያነትም ናሙናዎችን ለተጠቃሚ ተቋማት በማያቀርብበት ሁኔታ ውስጥ ተቋሙ ራሱን እንዴት እንደሚገመግም እንዲገለጽ ጠይቀዋል፡፡ እንደዚሁም አነስተኛ ግድፈት ያሳዩ አቅራቢዎችን እንቀበላለን በሚል በኦዲቱ ላይ አገልግሎቱ የሰጠውን ምላሽ መሰረት በማድረግ በምን ምክንያት አገልግሎቱ ይህን እንደሚፈጽም እንዲብራራ፣ የተገዙ ንብረቶች ይግቡ ወይም አይግቡ አገልግሎቱ ክትትል አያደርግም በሚል ኦዲቱ ላይ ከተገለጸው አኳያም ይህን ካላደረገ የአገልግሎቱ ስራ ምን እንደሆነ ማብራሪያ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡ በተጨማሪም ቀንሷል የተባለው ተሰብሳቢና ተከፋይ ሂሳብ ምን ያህል ነው ብለዋል፡፡

እንደዚሁም ተቋማት የግዥ ጥያቄ ሳያቀርቡ ግዢ የሚፈጸምበት አሰራር ለምን ጥቅም ላይ እንደዋለ ጠይቀው፤ ይህ ተቋማት ግዥን አቅደው የመስራት ኃላፊነታቸውን እንዳይወጡ እድል የሚሰጥና የማእቀፍ ግዢም ግቡን እንዳይመታ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከዚህም ሌላ አገልግሎቱ አቅራቢዎች ውል ከገቡት በላይ እቃ እያቀረቡና ተጠቃሚ ተቋማትም በጊዜው የሚያስፈልጋቸው እቃ እየቀረበላቸው ነው እያለ ባለበት ሁኔታ ውስጥ እቃዎች በወቅቱ እንደማይቀርብላቸው ተጠቃሚ ተቋማት የሚያነሱት ችግር ምክንያቱ ምን እንደሆነ እንዲብራራ ጠይቀዋል፡፡ ኦዲቱ በናሙና መሰረት እቃዎች እንደማይቀርቡ ከመግለጹ አንጻርም አገልግሎቱ ይህንን የማጣራት ስራ በምን አግባብ እንደሚያከናውን ጠይቀዋል፡፡ ተቋማት የግዢ እቅዳቸውን እንዲያቀርቡና በዚሁ መሰረት ግዢ እንዲፈጸም ተቀራርቦ መስራት ያልተቻለበት ምክንያትስ ምንድን ነው ብለዋል፡፡

መ/ቤቶች ሌተር ኦፍ ክሬዲት (LC) በራሳቸው እንዲከፍቱ መታቀዱ ችግሩን ወደሌሎች ከማሸሽ ባለፈ ዘላቂ መፍትሄ አይሆንም ያሉት የቋሚ ኮሚቴው አባላት ይህን ማድረግ የተሰብሳቢና ተከፋይ ሂሳብ ክምችትን እንደ ሀገር ይቀንሳል የሚል እምነት በአገልግሎቱ በኩል ስለመኖሩ ጠይቀዋል፡፡ ጥቅም ላይ ያልዋለውን በጀት በተመለከተም ቢሮ መገንባት ባለመቻሉ የመጣ ነው ከተባለ ቢሮውን ለመገንባት እንቅፋት የሆነው ነገር ምን እንደሆነ እንዲገለጽና ቢሮው የማይሰራም ከሆነ ለምን በእቅድ እንደተያዘ እንዲብራራ ጠይቀዋል፡፡ በመጋዘን ውስጥ ተቀላቅለው በተቀመጡ አገልግሎት የሚሰጡና የማይሰጡ ንብረቶችን ላይ ምን እርምጃ ተወስዷል ሲሉም ጠይቀዋል፡፡

ተቋማት ከፍላጎታቸው ውጪ ለሚቀርብላቸው እቃ ክፍያ ላለመፈጸም ወደኋላ የሚሉበት ሁኔታ ከመኖሩ አንጻር አቅራቢዎች ለመንግስት ይዳላል በሚል የሚያቀርቡትን ቅሬታን አገልግሎቱ እንዴት እንደሚመለከተው የቋሚ ኮሚቴው አባላት ጠይቀዋል፡፡ አገልግሎቱ ተግባራትን በእቅድ ስለመፈጸሙ፣ በተፈጸሙና ባልተፈጸሙ ተግባራት ላይ ግምገማና ስለማካሄዱና ባልተፈጸሙት ላይም ክትትል ስለማድረጉ እንዲገለጽላቸውም ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

እንደዚሁም አገልግሎቱ ከኦዲት ግኘቶቹ ተምሬያለሁ ቢልም የወሰደው እርምጃ የለም በማለት ገልጸው ተግባራትን በእኔነት ስሜትና ኃላፊነትን ወስዶ በማስፈጸም ረገድ ተቋሙ ምን እንደሚመስል እንዲሁም ብልሹ አሰራርን ለመታገል ያለው ቁርጠኝነት ምን ያህል እንደሆነ ጠይቀዋል፡፡

ከግዥ አገልግሎቱ ተጠቃሚ የሆኑ ተቋማትና ባለድርሻ አካላትም ጥያቄና አስተያየታቸውን አቅርበዋል፡፡ በጸረ ሙስናና ስነምግባር ኮሚሽን በኩል አቶ አክሊሉ ሙሉጌታ በአቅራቢዎችና በተጠቃሚዎች መካከል ሚዛናዊ የንግድ ግንኙነት በመፍጠር በኩል የሚቀር ነገር እንዳለና ይህ በሌለበት ግልጽነት የጎደለውና ለኪራይ ሰብሳቢነት የተጋለጠ አሰራር የሚፈጠርበት እድል እንዳለ ገልጸዋል፡፡ ከክፍያ አፈጻጸም ጋር በተያያዘም በመንግስት ተቋማት በኩል ችግር ቢኖርም እቃን በወቅቱና በጥራት በማቅረብ በኩል ያለውን ትልቅ ጉድለት አገልግሎቱ አጉልቶ አለማሳየቱን ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ሌላም በግዥ ሂደቱ ያሉ ጉዳዮችን ለአቅራቢዎቹና ለተጠቃሚ ተቋማቱ ብቻ የሚያጋራ ከሆነ አገልግሎቱ ሚናውና ሀላፊነቱ ምንድን ነው የሚለውን ወደራሱ ወስዶ መመልከት አለበት ብለዋል፡፡

በትምህርት ሚኒስቴር ተወካዮች በኩል ባሉ ውጫዊና ውስጣዊ ችግሮች ውስጥ በውስን የሰው ሀይል ባለው አወቃቀርና ስርዓት በአገር አቀፍ ደረጃ የግዢ አገልግሎቱን ለመስጠት እየተደረገ ያለው ጥረት በበጎ እንደሚታይ እንዲሁም ተቋሙን በሚያጋጥሙት ችግሮች ውስጥ የሚመለከታቸው አካላት በየደረጃው ኃላፊነት ሊወስዱ እንደሚገባና የግዥ አዋጁ አለመጽደቅም የዚሁ አካል ሆኖ መታየት እንዳለበት ተገልጿል፡፡

ከዚህ ውጪ ግን ለዩኒቨርስቲዎችና ለሚኒስቴሩ እቃዎችን በጊዜና በጥራት በማቅረብ ረገድ አገልግሎቱ በርካታ ችግሮች እንዳሉበት ገልጸዋል፡፡ የበጀት አመቱን ያልጠበቀ ክፍያን የመፈጸም ችግር ባብዛኛው በዩኒቨርስቲዎች የሚታይ በመሆኑ ይህን ለማስቀረት የህግ ተጠያቂነት ሊቀመጥለት እንደሚገባ፣ የግዥ እቅድ ክለሳ ስርአቱም ሊጤን እንደሚያሻው፣ የግዥ መጓተት በጣም ቁልፍ የግዢ አገልግሎቱ ችግር ነው ተብሎ መወሰድ እንዳለበት፣ ከዚህ ጋር ተያይዞም በግዥ ሂደቱ ላይ በቴክኒክ ምዘና ወቅት የሚያጋጥሙ ቅሬታዎች ላይ ውሳኔ የሚሰጠው ቦርድ ባለመሟላቱ ምክንያት ግዥ ለበርካታ ወራት የሚዘገይበት ሁኔታ መፍትሄ ሊሰጠው እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ የሚኒስቴር መ/ቤቱ ተወካዮች በተጨማሪም የበጀት አመት መጠናቀቂያ ሲደርስ ግዢዎችና የንብረቶች ርክክብ የሚፈጸምበት ሁኔታ እንዲቀር ምን እየተሰራ እንደሆነና በዩኒቨርስቲዎች ከማእቀፍ ግዢ ውጪ በሚልዮኖች በሚቆጠር ብር ግዢዎች እየተፈጸሙ ስለመሆኑ አገልግሎቱ ስለማወቁ ጠይቀዋል፡፡ አገልግሎቱ ከሰው ሀይል፣ ከደመወዝና ከሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ያሉበት ችግሮች ሊታዩ እንደሚገባም የገለጹ ሲሆን ሁሉም የንብረት ማስወገድ ስራ በአገልግሎቱ እንዲከናወን ሀሳብ አቅርበዋል፡፡

በገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን በኩል የግዥና ፋይናንስ ዳይሬክተሩ አቶ መንግስተአብ ይርዳው የማእቀፍ ግዢው መጀመር እቃዎች ወደ በጀት አመቱ ማለቂያ የሚገዙበትን ሁኔታ በማስቀረት ቀድመው እንዲገዙ ማስቻሉን ገልጸዋል፡፡ ሆኖም ግን አገልግሎቱ ከ2008-2010 የማእቀፍ ግዥ ሲዋዋል የአቅራቢዎቹን የቀደመ የመልካም ስራ አፈጻጸም መገምገም አለመገምገሙን መግለጽ እንዳለበት ተናግረው የአቅርቦት ችግሩ አሁንም እንዳለና ባለስልጣኑ ለ18 ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች የጠየቃቸው የጽህፈት መሳሪያዎች፣ ኮምፒዩተሮችና ተያያዥ እቃዎች እስካሁን ገቢ እንዳልሆኑ በዚህም ለምልልስ እንደተዳረገ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም ባለስልጣኑ በአቅራቢዎች በኩል እቃን በወቅቱ ባለማቅረብ ስለሚፈጠሩ ችግሮች ለአገልግሎቱ እንዳሳወቀ ጠቅሰው በዚህ በኩል የተወሰደ እርምጃ ካለ እንዲገለጽላቸው ጠይቀዋል፡፡ በናሙና በኩልም ከኮምፒዩተር ውጪ ናሙና ለሚያስልጋቸው እቃዎች ናሙና እየቀረበላቸው እንዳልሆነም ገልጸዋል፡፡ ለእያንዳንዱ ተቋም ናሙና እንዲቀርብ ማድረግ ጥራት የሌለው እቃ መግዛት ከሚያስከትለው ወጪ ጋራ ሲነጻጸር አነስተኛ ወጪ የሚጠይቅ በመሆኑ ናሙናው በአገልግሎቱ በኩል ተገዝቶም ቢሆን ለሁሉም ተቋማት ቢቀርብ የተሻለ ይሆናል የሚል ሀሳብ አቅርበዋል፡፡

አቶ መንግስተአብ  የማእቀፍ ግዢው በከፍተኛ የመንግስት በጀት ለሶስት አመታት የሚፈጸም ግዢን ለተወሰኑ አቅራቢዎች የሚሰጥ በመሆኑ ገበያውን ተወዳዳሪ ከማድረግና ሁሉንም አቅራቢዎች ከማሳተፍ አኳያ ሀገሪቱ ካስቀመጠችው የልማት አቅጣጫና የገበያ ስርዓት ጋር የተጣጣመ ስለመሆኑ ጠይቀዋል፡፡ ከዚህ ሌላም የግዢ ውሉ ተጠቃሚዎች ከአቅራቢው ዘንድ ሄደው እቃውን እንዲወስዱ በሚል ስለተፈጸመ መ/ቤቶችን ለተደጋጋሚ ምልልስ እየዳረገ እንደሚገኝና ለኪራይ ሰብሳቢነትም እድል የሚፈጥር በመሆኑ በቀጣይ በሚታሰረው የማእቀፍ ግዥ ውል ላይ አቅራቢዎች እቃውን ወደ ተጠቃሚዎች አምጥተው የሚያስረክቡበት አሰራር እንዲቀየስ ሀሳብ አቅርበዋል፡፡

የጤና ጥበቃ የውስጥ ኦዲት ዳይሬክተር ወ/ሮ አስቴር ታከለ አገልግሎቱ ከተጣለበት ሰፊ ኃላፊነት አንጻር ከነችግሩ እየሰጠ ያለውን አገልግሎት በበጎ ጎኑ በማንሳትና ለመ/ቤታቸው ፈጣን ምላሽ በመስጠት ችግሮች በቀላሉ እንዲፈቱ እያደረገ መሆኑን በመግለጽ ከተጣለበት ኃላፊነት አንጻር ራሱን በቴክኖሎጂ፣ በአደረጃጀትና በሰው ሀይል ብቁ ማድረግ እንደሚገባውና በተለይም ከተጠቃሚ መ/ቤቶች ጋር ሰፊ ቅንጅታዊ አሰራርን በመፍጠር ግኝቶቹን ማስቀረት አንዳለበት ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ሌላም ለመ/ቤታቸው በሚደረገው አቅርቦት በኩል አሁንም ድረስ ከጊዜና ከጥራት ጋር የተያያዙ ችግሮች እንዳልተፈቱ ገልጸው ችግሮቹን የሚፈታ አሰራር መዘርጋት አለበት ብለዋል፡፡ በተጨማሪም አገልግሎቱ የውስጥ ኦዲት አደረጃጀቱን ማጠናከር፣ የውስጥ ኦዲቱ የሚሰጠውን አስተያየት እየተቀበለ ማስተካከያ ማድረግና ለዋና ኦዲተር መ/ቤት የኦዲት አስተያየት ምላሽ በመስጠት ችግሮችን መፍታት አለበት ብለዋል፡፡

ከእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር አቶ ዲሞስ ይግዛው በአገልግሎቱ በኩል ከፍተኛ የግዥ መጓተት አለ ብለዋል፡፡ በመንግስት መ/ቤቶች በኩልም ለአቅራቢዎች ሊከፈል የሚገባ ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ ይዞ የመቀመጥ ችግር እንዳለ ገልጸው መልካም አስተዳደር ይስፈን ከተባለ የመንግስት ተቋማትም ተጠያቂ የሚሆኑበት ስርአት ሊኖር እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ ባቅራቢዎች በኩልም ኃላፊነታቸውን የማይወጡትንና ህገወጥ ተግባራት የሚፈጽሙትን ተከታትሎ በቁርጠኝነት እርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ ከአገልግሎቱ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

ከዚህ ውጪ በገቢዎችና ጉምሩክ እንዲሁም በተስማሚነት ምዘና ላይ እቃዎች ተይዘው የሚቆዩበት ሁኔታም መጤን እንዳለበትና ይህ ቢሮክራሲ ባለበት ሁኔታ ያለውን ጀማሪ አቅራቢ እንቅጣው ቢባል ከገበያ ማስወጣት ሊሆን እንደሚችል መታሰብ አለበት በማለት አሰራሩ ሚዛናዊ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ በናሙና ረገድም ሩቅ ስፍራ ላሉት ብቻ ናሙና የሚላክበትና በቅርብ ያሉት ግን በናሙናው መሰረት እቃው የቀረበላቸው መሆኑን በአገልግሎቱ ዘንድ በመቅረብ ቢያረጋግጡ የተሻለ እንደሚሆን ሀሳብ ሰጥተዋል፡፡ በንብረት ማስወገድ በኩል በሚኒስቴር መ/ቤቱ ያለውን ከፍተኛ የማያገለግል ንብረት ለማስወገድ አገልግሎቱ ባለሙያ በመመደብና በሽያጭ እንዲወገዱ በማድረግ እያገዘ ቢሆንም በሚፈለገው ፍጥነት እየተወገደ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ውጪም አገልግሎቱ ወቅታዊ ዋጋ ማስተካከያ እያደረገ ባለመሆኑ አቅራቢዎች እቃው እያላቸው ከእቃዎች የዋጋ መናርና ከገንዘብ የመግዛት አቅም መቀነስ ጋር በተያያዘ የዋጋ ማስተካከያ እንዲደረግላቸው ሲጠይቁ የገበያ ጥናት በማድረግ ፈጥኖ ማስተካካያ እንደማይደረግ ገልጸው የአቅራቢዎቹን ጥያቄም በአግባቡ ማስተናገድ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር የግዥና ንብረት ዳይሬክተር አቶ መሀመድ አሚን በአገልግሎቱ በኩል በጊዜና በጥራት በማቅረብ ረገድ የተነሱትን ችግሮች እንደሚጋሩ ገልጸው እስካሁን ድረስ በአቅራቢዎች ለመ/ቤታቸው ያልገቡ እቃዎች እንዳሉ፣ በአገልግሎቱ በኩል የሚወገዱ እንደ ጎማና ባትሪ ያሉ ንብረቶች ከመ/ቤታቸው እየተወገዱ እንዳልሆኑ፣ ይህንንም መ/ቤታቸው ለአገልግሎቱ እንዳሳወቀና ምላሽ እንዳልተገኘ በመግለጽ ለችግሮች መፍትሄ መስጠት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡ ከጉዳት ካሳ ጋር በተያያዘም መ/ቤቶች ራሳቸው ከአቅራቢዎች ጋር ውል ሳይገቡ የጉዳት ካሳ እንዴት ሊቀንሱ እንደሚችሉ እንዲብራራላቸው ጠይቀዋል፡፡ አገልግሎቱ ተጠቃሚ መ/ቤቶችና አቅራቢዎች በየወቅቱ የሚገናኙበት የምክክር መድረክ የሚያዘጋጅ መሆኑን በበጎ ጎን አንስተው እነዚህን አካላት ከማገናኘት በዘለለ የእያንዳንዱ አቅራቢና ተጠቃሚ ችግር ተጠንቶ እንዲቀርብና ትምህርት እንዲወሰድበት አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ በመ/ቤታቸው በኩል ለአቅራቢዎች የሚከፈል ክፍያ መዘግየትን በየጊዜው በመገምገም የክፍያ ስርአቱ እየተሻሻለ እንደመጣም ተናግረዋል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ አገልግሎቱ በሚያዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይ ክፍያን በማዘግየት የሚጠቀሱ ተቋማት እንዳሉ በመግለጽ ምክር ቤቱ በዚህ ረገድ እገዛ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር በተነሱ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ምላሽ ሲሰጡ አገልግሎቱ የሰጠው ምላሽ የኦዲት ግኝቶቹን ወደሌላ አካል ለመግፋት ሳይሆን ያለውን ሁኔታ ለማስረዳት በሚል እንደሆነ በመግለጽ የኦዲት ግኝቶቹን ተቀብሎ የማሻሻያ ድርጊት መርሀ ግብር አዘጋጅቶ እየሰራ መሆኑን በማሳያነት አቅርበዋል፡፡ አገልግሎቱ ለአቅራቢዎች ወግኗል የሚለውም ትክክል እንዳልሆነና በአቅራቢዎችም ላይ በህጉና አሰራሩ መሰረት ቅጣት እንዲጣል እንዲሁም በትክክል ያላቀረቡትን እቃም አስተካክለው እንዲያቀርቡ እያደረገ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል፡፡

የግዢ ፍላጎታቸውን ያላቀረቡ ተቋማት የማእቀፍ ግዢው ተጠቃሚ ስለሚሆኑበት ሁኔታ ሲገልጹም በ2008-2010 የማእቀፍ ግዢ ፍላጎታቸውን የገለጹት ከዩኒቨርቲዎች 16፣ ከተጠቃሚ የመንግስት መ/ቤቶች ደግሞ ግማሾቹ ብቻ እንደነበሩና አሁንም ተመሳሳይ ሁኔታ እንዳለ በመጥቀስ የግዢ እቅዳቸውን ያላቀረቡት ተቋማት ሊፈጠርባቸው የሚችለውን ችግር ታሳቢ በማድረግ ከማእቀፍ ግዢው እንዲጠቀሙ መደረጉን አስረድተዋል፡፡

በመልካም ስራ አፈጻጸም በኩልም በ2007 የማእቀፍ ግዢ እንደተፈጸመ ነገር ግን በ2008 የሶስት አመት የማእቀፍ ግዢ ሲፈጸም የአቅራቢዎች የመልካም ስራ አፈጻጸም በዝርዝር እንዳልተገመገመና ይህም እንደስህተት ተወስዶ በ2010 ላይ በሚካሄደው የማእቀፍ ግዢ ላይ የእያንዳንዱ አቅራቢ አፈጻጸም በሚገባ እንደሚመዘን ገልጸዋል፡፡

በሚወገዱ ንብረቶች በኩል ከመጽሀፉ በቀር በኦዲቱ ወቅት የተገኙ ንብረቶች እንደተወገዱ ተናግረዋል፡፡

የግዢ መጓተት ችግር እንዳለና ይህም በወቅቱ የግዥ ሂደቱን ጨርሶ ጨረታ ካለማውጣት፣ ጨረታ ከወጣ በኋላም የቴክኒክ ምርመራ ጨርሶ ሪፖርት የማውጣት ሂደቱ ረጅም ጊዜ ከመውሰዱ፣ በወጣው ሪፖርት ላይ የሚነሱ ቅሬታዎች የሚፈቱበት ሂደት ከመርዘሙ ባጠቃላይም በውስጣዊ ችግሮች የተፈጠረ ሊሆን እንደሚችል  ገልጸዋል፡፡

ከጥራት ጋር በተያያዘም አቅራቢው በቀረበለት ዝርዝር የፍላጎት መግለጫ ካቀረበ የጥራት ጉድለት እንዳለበት እንደማይቆጠር ገልጸው ዝርዝር መግለጫው በሚመለከታቸው መ/ቤቶች እንደሚወጣ አስረድተዋል፡፡ አገልግሎቱ በዝርዝር መግለጫ መሰረት እቃው መቅረቡን ማረጋጥ እንዳለበትና ለዚህም የክትትል ስርዓት እንደዘረጋ ገልጸው  በዋናነት ግን ይህንን ማረጋገጥ ያለበት ተጠቃሚው መ/ቤት ነው ብለዋል፡፡

በተሰብሳቢና ተከፋይ ሂሳብ በኩልም ከ277 ሚሊዮን ብር በላይ ተወራርዷል ብለዋል፡፡

ተጠቃሚ መ/ቤቶች የግዢ ውሉን ከአቅራቢዎች ጋር ባይዋዋሉም ገንዘቡን የሚከፍሉት ራሳቸው በመሆናቸው በወቅቱ እቃውን የማያቀርቡ አቅራቢዎችን የጉዳት ካሳውን ማስከፈል እንዳለባቸው በደብዳቤ እንዲያውቁት ተደርጓል ብለዋል፡፡

ናሙናን በተመለከተ አገልግሎቱ ናሙናን በራሱ በጀት ገዝቶ ለሁሉም መ/ቤቶች ያቅርብ የሚለው ሀሳብ ሊታይ እንደሚችል ነገር ግን አቅራቢው ለሁሉም ተቋማት የሚሆን ናሙና እንዲያቀርብ ማድረግ አስቸጋሪ እንደሆነ አቶ ይገዙ ገልጸዋል፡፡

ጥቅም ላይ ያልዋለ በጀትን በተመለከተ የተወሰነ የሰው ሀይል ቀጥሮ ለማሰራት የሚያስችል ጊዜያዊ ቢሮ ለመስራት ታቅዶ እንደነበረ አስታውሰው የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር በግቢው ውስጥ ለመንግስት መ/ቤቶች ህንጻ የሚገነባና ትርፍ መሬት የሌለው መሆኑ በመገለጹ ግንባታው ስለተከለከለ በጀቱ ጥቅም ላይ ሳይውል ቀርቷል ብለዋል፡፡

በግዢ አዋጁ በኩልም የአዋጁን አለመውጣት ለሁሉም የግዥ ስርአቱ ችግሮች እንደምክንያት ለማቅረብ ተፈልጎ ሳይሆን አዋጁ ጸድቆ ቢወጣ ተከትለውት የሚወጡት መመሪዎች በርካታ ችግሮችን ይፈታሉ በሚል እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ከመ/ቤቶች ጋር ተቀራርቦ በመስራት ረገድ ከተጠቃሚና ከአቅራቢ ድርጅቶች ጋር የምክክር መድረክ እንደሚደረግና በሁለቱም በኩል የሚነሱ ችግሮችን የማጣራት ስራ እየተሰራ እንደሆነ ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

አገልግሎቱ በእቅድ ይመራል ለሚለው ጥያቄም ከእቅድ ውጪ የሆኑ በርካታ ግዢዎችን እንደሚፈጽም በዝርዝር አስረድተዋል፡፡

እቃዎች በወቅቱ ካለመቅረባቸው ጋር በተያያዘ የአቅራቢው አቅም ማነስ እንደተጠበቀ ሆኖ ከውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ ከሌተር ኦፍ ክሬዲት፣ ከጉምሩክ ሂደት ወዘተ. ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ግዢው በወቅቱ እዳይፈጸም የሚያደርጉ ከአገልግሎቱ ውጪ ያሉ ችግሮች እንደሆኑ ገልጸው ችግሮቹ እንዲፈቱ ጥረት እንደሚደረግ ግን አስረድተዋል፡፡

የዋጋ ማስተካከያ ከማድረግ ጋር በተያያዘም በዚህ አመት ከምንዛሪ ለውጥ በኋላ ከማእከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ ባለመገኘቱ ማስተካከያውን ማድረግ እንዳልተቻለና በተለይ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እቃ አቅራቢዎች የዋጋ ማስተካከያ ይደረግልን በሚል ጥያቄ መነሻነት እቃ እያቀረቡ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም በፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስቴር ለሚመራው የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የሚፈታ ግብረ ሀይል ጉዳዩ ቀርቦ ውሳኔ እየተጠበቀ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

መ/ቤቶች በበጀት አመቱ መጨረሻ ግዢ የሚያከናውኑበትን ሁኔታ በተመለከተም አገልግሎቱ ለሶስት አመት የሚቆይ የማእቀፍ ግዢ እንዳለውና ተቋማት በራሳቸው እቅድ ግዢውን እንደሚፈጽሙ አገልገሎቱም በዚህ ጊዜ ግዙ እንደማይል ገልጸው በቅርቡ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ግዥዎች በተወሰነው ጊዜ ብቻ እንዲከናወኑ ደብዳቤ ማስተላለፉን አስረድተዋል፡፡

ከማዕቀፍ ግዢ ውጪ በተለይ በዩኒቨርስቲዎች ስለሚፈጸሙ ግዥዎች በተመለከተ አገልግሎቱ ስለጉዳዩ እንደሚያውቅ ገልጸው የማእቀፍ ግዥው የተወሰኑ እቃዎችን በማቅረብ እንደተጀመረና በሂደት እየሰፋ እንዳለ አሁንም መ/ቤቶች የሚፈልጉት እቃ ሙሉ በሙሉ በአገልግሎቱ እየቀረበ አንዳልሆነና ወደፊት ሁሉንም ለማቅረብ ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡ አንዳንድ ተቋማት የሚፈልጓቸው ልዩ እቃዎች ግዢም ወደ ማእቀፍ ግዢ እንዳልገባ ገልጸዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ ከአቅርቦት ጋር በተያያዘ በኮምፒዩተር ረገድ ካለው የአቅርቦት ችግር ውጪ በወረቀትና የዋጋ ማስተካከያ በተደረገላቸው እቃዎች ላይ የአቅርቦት ችግር የለም ብለዋል፡፡

የማእቀፍ ግዢ አሳታፊነትንና ተወዳደሪነትን በተመለከተ በአሰራሩ በሀገሪቱ የትኛውም አካባቢ ያለ አቅራቢ መሳተፍ እንደሚችልና ይህም ውድድርን የሚያበረታታ እንደሆነ፣ የገበያ ሰርአቱንም እንደማይረብሽ ገልጸዋል፡፡ በሌላ በኩል ሞኖፖሊን ለመከላከል በአንድ እቃ ላይ በርካታ ተወዳዳሪዎች ከቀረቡና አሸናፊው ተወዳዳሪ ባቀረበው ዋጋ ለማቅረብ ከተስማሙ እንዲያቀርቡ እድል እንደሚሰጥ አስረድተዋል፡፡

አቅራቢዎች እቃዎችን ለየመ/ቤቱ እንዲያደርሱ ከማድረግ ጋር ተያይዞ ከአስራ ስድስቱ ዩኒቨርስቲዎች በስተቀር ሌሎቹ ተቋማት ከአቅራቢው መጋዘን እንዲወስዱ እንደሚደረግ ገልጸው ተቋማት መቼና ምን እንደሚፈልጉ በግዥ እቅዳቸው ላይ በማያቀርቡበት ሁኔታና በሌሎች ለአፈጻጸም አስቸጋሪ በሆኑ ምክንያቶች የተነሳ አቅራቢዎች እቃዎችን ለየመ/ቤቱ እንዲያደርሱ ማድረግ አስቸጋሪ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በተቋማት የሚገኙና አገልግሎቱ ሊያስወግዳቸው ይገቡ የነበሩ ንብረቶችን በተመለከተም ጉዳዩ ትክክል እንደሆነ፣ ቅሬታውም እንደቀረበና በቅሬታና ውሳኔ ሰጭ ቦርድ ውሳኔ የተሰጠው በመሆኑ በቅርቡ እንደሚወገዱ ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ በሰጡት አስተያየት የግዥ እቅድ የማያቀርቡ ተቋማት መቀጣት እንዳለባቸውና አገልግሎቱም ለነዚህ አካላት ግዢ የመፈጸም ግዴታ እንደሌለበት፣ መግዛትም እንደማይገባው ገልጸው ተቋማቱ በማእቀፍ ግዢ መግዛት የነበረባቸውን እቃ ሳይገዙ ከተገኙም የኦዲት ግኝት ተደርጎ እንደሚወሰድባቸው ገልጸዋል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም ተጠቃሚዎች የግዢ እቅድ ባለማቅረባቸው ሳቢያ ተጨማሪ አቅርቦት አቅራቢዎቹ እንዲያቀርቡ በመደረጉ ምክንያት ተፈጠረ የተባለውን አቅርቦት ችግር እንደማይቀበሉ ሲያስረዱም በኦዲት ወቅት በናሙና ከታዩት አቅራቢዎች ውስጥ አራት የተለያዩ ድርጅቶች በ2007 በጀት አመት በማእቀፍ ግዢ ውል ስምምነት እንዲያቀርቡ ውል የገቡባቸውን የተለያየ መጠንና አይነት ያላቸውን እቃዎች ሳያቀርቡ የቀሩ ቢሆንም በቀጣዩ የማእቀፍ ግዢ እንዲሳተፉ መደረጉንና ቅጣት ሳይጣልባቸው መቅረቱን በማሳያነት አቅርበዋል፡፡

የአቅራቢዎችን አቅም በተመለከተም ነጋዴዎች አቅም ያላቸው መሆኑ በደንብ መፈተሸ አለበት ብለዋል፡፡ ከውጪ ምንዛሪና ሌሎች ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ችግሮችን ግምት ባስገባ ሁኔታ በውላቸው መሰረት በማያቀርቡ አቅራቢዎች ላይ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ፣ ናሙናን በተመለከተም የተሻለ የሚሆነው ናሙናው አገልግሎቱ ጋር እንዳለ እንዲያውቁ ማድረግ፣ ናሙናን ተጠቅመው ጥራትን የሚያረጋግጡበት ተጨማሪ አቅም ለተጠቃሚዎቹ መፍጠር ይህ ካልሆነም ናሙና የሚጣራበት ማእከል አገልግሎቱ ማቋቋም እንደሆነ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡፡

ክፍያ ላቅራቢዎች በማይከፍሉ ተቋማት ውስጥ ክፍያን ለማስለቀቅ ማማለጃ የሚጠይቁ አካላት ካሉ ከጸረ ሙስና ኮሚሽንና የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ጋር በመሆን በፍጥነት እርምጃ መውሰድ እንደሚገባም ክቡር ዋና ኦዲተሩ ተናግረዋል፡፡

ከተሰብሳቢ ሂሳብ ጋር ተያይዞ እያንዳንዱ ተቋም ሌተር ኦፍ ክሬዲት እንዲከፍት ማድረግ አስፈላጊ እዳልሆነና ሊወራረዱ የሚገቡ ሂሳቦችን ማወራረድ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ ከኢፍሚስ ጋር ተያይዞም ከጥሬ ገንዘብ ምዝገባ ጋር የተፈጠረውን ችግር በፍጥነት መፍታት ይገባል ብለዋል፡፡

ከማእቀፍ ግዢው ጋር በተያያዘ ሞኖፖሊ ሊፈጠር የሚችልበት እድል ካለ ሌሎች ስልቶችን በመጠቀም ሁሉንም ተሳታፊ ሊያደርግ በሚችል መንገድ መጠቀም እንደሚቻልም ክቡር ዋና ኦዲተሩ ገልጸዋል፡፡

መጻህፍትን በመጋዘን ማስቀመጥ ካልተቻለ ከፕላን ኮሚሽን ጋር በመነጋገር ስካን በማድረግ በሶፍት ኮፒ ማስቀመጥ እንደሚቻል ክቡር አቶ ገመቹ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ ሶፊያ አልማሙን በሰጡት አስተያየት ተቋሙ በእቅድ መመራት አለመመራቱ ላይ ግልጽ ሀሳብ መሰጠት እንደነበረበትና እቃን በአግባቡ በማያቀርቡ አቅራቢዎች ላይ የጉዳት ካሳ ማስከፈልን በተመለከተ የተቃረነ ምላሽ መሰጠቱን ገልጸው የግዥ አዋጁ ያለበትን ሁኔታ ማጣራት ይበልጥ ጠቃሚ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ምክትል ሰብሳቢዋ ቋሚ ኮሚቴው የተከታተላቸቸው ዩኒቨርስቲዎች በፍላጎታቸው መሰረት እንዲሁም ጊዜውንና ጥራቱን ጠብቆ እቃ እንደማይቀርብላቸው የሚገልጹበት ሁኔታ እንዳለ በመጥቀስ ባንድ በኩል ዩኒቨርስቲዎች በሚልዮኖች በሚቆጠር ብር ተገዝቶ የተሰጣቸውን ንብረት ካለፍላጎታችን የተገዛ ነው በሚል አከማችተው የሚገኙበትና ለዚህም ተጠያቂ አይደለንም የሚሉበት በሌላ በኩል ደግሞ አቅራቢው በቀረበው ፍላጎት መሰረት አቅርቤያለሁ የሚልበት ያልጠራ ሁኔታ እንዳለ ገልጸው ይህ አገልግሎቱ በአቅርቦት ስራው ላይ የሚያደርገው የክትትልና ቁጥጥር ስራ የላላ መሆኑን ያሳያል ብለዋል፡፡ አቅራቢዎች ያላቸው የማቅረብ አቅም አገልግሎቱ  በአግባቡ መፈተሸ እንዳለበትና የጠራ ስራ መሰራት እንዳለበትም ገልጸዋል፡፡፣

ወ/ሮ ሶፊያ አክለውም በሂሳብ ኦዲት በኩል ውዝፍ ተሰብሳቢ ሂሳቦችን  ግልጽ አሰራር በመዘርጋት፣ የክትትልና የቁጥጥር ስራውን በማጠናከርና አሰራሮችን በማሻሻል በቀጣይ እያቀለሉ መሄድ ይገባል ብለዋል፡፡ በንብረት ማስወገድ በኩል የተሰራው ስራ በበጎ ጎኑ የሚታይና ሊቀጥል የሚገባው ነው ያሉት ምክትል ሰብሳቢዋ  የተወሰደው የመፍትሄ እርምጃ ግን ለዋና ኦዲተርና ለሚመለከተው አካል መገለጽ እንደነበረበት አስገንዝበዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ት ወይንሸት ገለሶ በማጠቃለያ አስተያየታቸው አገልግሎቱ፣ ተጠቃሚ ተቋማቱና አቅራቢዎች ካለባቸው ኃላፊነት አኳያ ተጠያቂ መሆን እንዳለባቸውና ግዥ ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ድረስም በህጉ መሰረት ሊመራ እንደሚገባው አስገንዝበዋል፡፡ አገልግሎቱ በተለያዩ መድረኮች ከግዥና ከንብረት ማስወገድ አኳያ በርካታ ችግሮች እንዳሉበት በተጠቃሚ ተቋማት በስፋት ይገለጻል ያሉት ሰብሳቢዋ ተቋሙ በአሰራር ላይ ያሉበትን ችግሮች ቢገልጽም ለነዚህ ችግሮች መፍትሄ የመስጠት ኃላፊነት በዋናት በራሱ ላይ የሚወድቅ ነው ብለዋል፡፡

የግዥ እቅድ ላላቀረቡ ተቋማት እቃ ገዝቶ ማቅረብ ከአቅርቦት ጋር ለተያያዙ ችግሮች በር የሚከፍት በመሆኑ ደንብና መመሪያን አክብሮ መስራት እንደሚያስፈልግ የተከበሩ ወ/ት ወይንሸት አሳስበዋል፡፡ በህግ መሰረት አቅራቢዎች እንዲቀጡ እየተደረገ የግዥ እቅድ የማያቀርቡና ህግ የማያከብሩ የመንግስት ተቋማት የማይቀጡበት ሁኔታ ቋሚ ኮሚቴው ትክክል ነው ብሎ እንደማይቀበልና አገልግሎቱን በማቋረጥ ወደ ትክክለኛው መስመር ማስገባት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ እንደዚሁም አገልግሎቱ የግዥ እቅድ ለማያቀርቡ ተቋማት የማቅረብ ግዴታ አለበት ብሎ ቋሚ ኮሚቴው እንደማያምን ተናግረዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የግዥ አዋጁ ያለበትን ሂደት አገልግሎቱ ማጣራት እንዳለበት ገልጸው ቋሚ ኮሚቴው ግን የኦዲት ግኝቶቹን ለመፍታት የአዋጁ አለመጽደቅ መሰረታዊ ማነቆ ነው ብሎ እንደማይወስድ ገልጸዋል፡፡ አቅራቢዎች እንዲጠናከሩና የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ አቅራቢዎች የአገልግሎቱን ድጋፍ ይሻሉም ብለዋል፡፡ ተቋሙን በሰው ሀይል፣ በአደረጃጀት፣ በቴክኖሎጂ እንዲጠናከር ለማድረግ መጣር የተቋሙ ኃላፊነት ነው ያሉት የተከበሩ ወ/ት ወይንሸት የተቋሙን የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ለማሳደግም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መቀናጀት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡ እንደዚሁም አገልግሎቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር ወቅታዊ የግንኙነት መድረኮችን በማካሄድ የቅንጅታዊ ስራዎችን ማጠናከር እንደሚገባውም ገልጸው አቅራቢዎችን ህግን ተከትለው እንዲያቀርቡ በበለጠ ጥልቀት ህጎችን ማስገንዘብና ማወያየት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም አገልግሎቱ የውስጥ ኦዲት የስራ ክፍሉ እንዲጠናከር ማድረግ እንዳለበትና ተቋማት ንብረት እንዲወገድላቸው ለሚያቀርቡት ጥያቄ ምላሽ መስጠት እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡ በተቋሙ ላይ የተገኘው ተሰብሳቢና ተከፋይ ሂሳብ በጣም ከፍተኛ እንደሆነና ከኦዲቱ በኋላ ምን እርምጃ እደተወሰደ ምን ያህሉስ እንደቀረ በግልጽ መረጃውን ይዞ በመድረኩ ላይ መቅረብ እንዲሁም በዚህ ረገድ የተወሰደውን እርምጃ ለዋና ኦዲተር መ/ቤት ማሳወቅ ይገባ እንደነበረም አስገንዝበዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *