News

መቀሌ ዩኒቨርስቲ በፋይናንስ ስርአቱ ውስጥ ያሉ ችገሮችን ማረም እንደሚገባው ቋሚ ኮሚቴው አሳሰበ፡፡

የመቀሌ ዩኒቨርስቲ የኦዲት ግንቶችን መሰረት በማድረግ በፋይናንስ፣ በግዥና በንብረት አስተዳደር በኩል የሚታዩበትን ድክመቶች መቅረፍ እንዳለበት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡  ቋሚ ኮሚቴው በዩኒቨርስቲው 2008 በጀት አመት ሂሳብ ላይ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ያደረገውን ኦዲት መሰረት አድርጎ መጋቢት 19/ 2010 ዓ.ም ይፋዊ ስብሰባ አካሂዷል፡፡

በስብሰባው ላይ ዩኒቨርስቲው በፋይናንስ አስተዳደር፣ በግዥና በንብረት አያያዝ በኩል ያሉበት የተለያዩ ድክመቶች ተዘርዝረው ቀርበዋል፡፡

በኦዲቱ ግኝት መሰረት ዩኒቨርስቲው ለመምህራንና ለድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች ከውስጥ ገቢ ሂሳብ 343,356.25 በብልጫ የከፈለ ሲሆን የሚመለከተውን የመንግስት አካል ሳያስፈቅድ ብር 2,912,900.42 የትርፍ ሰአት ክፍያ በሚል ከፍሏል፡፡ በተለያዩ የዩኒቨርስቲው ካፓሶችም ብር 44,896.15 የውሎ አበል በብልጫ የከፈለ ሲሆን በዩኒቨርስቲው የጤና ሳይንስ ኮሌጅም የርቀት፣ የክረምትና መደበኛ ያልሆኑ ተማሪዎችን የትምህርት ፕሮግራሞችን ላስተባበሩ ሰራተኞች ተጨማሪ የስራ ጫና በሚል ካለዩኒቨርስቲው ቦርድ ፈቃድ ብር 999,756.00 ከፍሎ ተገኝቷል፡፡

ጥቅም ላይ ያልዋለን የአመት ፈቃድ ወደ ገንዘብ ቀይሮ ስለመክፈል በወጣው መመሪያ መሰረት ፈቃዱ ያልተወሰደበትን የመጀመሪያውን አንድ አመት የስራ ቀናት ብቻ ወደ ገንዘብ ቀይሮ መክፈል ሲገባ ዩኒቨርስቲው የ2006 እና 2007 ዓም የአመት እረፍትን በገንዘብ ቀይሮ ለተለያዩ ግለሰቦች ብር 29,546.40 ከፍሏል፡፡

በእቃና አገልግሎት ግዢ በኩልም በአዋጅና በመመሪያ በተፈቀደው መሰረት ካልሆነ በስተቀር ካለጨረታ ግዢ መፈጸም ቢከለከልም በዩኒቨርስቲው የተለያዩ ኮሌጆች የብር 2,701,807.10 ግዥ ካለምንም ውድድር በቀጥታ ግዢ ተፈጽሞ ተገኝቷል፡፡ እንደዚሁም በህፀተ ዝናብ ግብርናና የተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ የብር 764,222.53 የተለያዩ ግዥዎች በተቆራረጠ መንገድ በዋጋ ማወዳደሪያ ተፈጽሟል፡፡ ከዚህ ሌላም በጤና ሳይንስ ኮሌጅ የህክምና መገልገያ ዕቃዎች ለአይደር ሪፈራል ሆስፒታል የመድሃኒት ህክምና መገልገያዎች ለኤሌክትሪክ እቃዎች ግዥ በአጠቃላይ ድምር የብር 636,003.55 ከየክፍሉ ተሰብስቦ በጨረታ መፈፀም የነበረበት ግዥ ከደንብና መመሪያ ውጪ በዋጋ ማወዳደሪያ መገዛቱ በኦዲቱ ተገኝቷል፡፡

በዩኒቨርሲቲው በተለያዩ የትምህርት ተቋማት እና በአይደር ሪፈራል ሆስፒታል የተለያዩ አገልግሎቶችና እቃዎች ግዥ ሲፈጸም ተራ ፋክቱር ቀርቦ ሂሳቡ የተወራረደ በድምሩ ብር 133,403.58፣  የኢትዮጵያ ስራ አመራር ኢንስቲትዩት ለሰጠው አገልግሎት ክፍያ የተፈፀመበትን ደረሰኝ አለመስጠቱን ጨምሮ ምንም ዓይነት ደረሰኝ ሳይቀርብ የተወራረደ ሂሳብ የብር 808,285.60 እንዲሁም ክፍያዎች ሲፈፀሙ ደረሰኝ መያያዝ እያለበት በአታችመንት ብቻ የተያያዘላቸውና ሂሳቡ የተወራረደ ብር 2,850,487.13 በአጠቃላይ በናሙና ኦዲት ከተደረጉት ውስጥ ደረሰኝ ሳይኖራቸው የተወራረዱ፤ ተራ ፋክቱር የቀረበላቸውና አታችመንት ቀርቦላቸው የተወራረዱ ሂሳቦች በድምሩ ብር 3,792,176.31 መኖሩን የኦዲት ሪፖርቱ ያሳያል፡፡

በሂሳብ ምዝገባ ረገድም በዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ካምፓሶች ብር 6,582,659.52 ያለ ትክክለኛው የሂሳብ መደብ ተመዝግቦ ሪፖርት መደረጉ በኦዲቱ ተገልጿል፡፡

ዩኒቨርሲቲው የአገልግሎትና የዕቃ ግዥዎችን ክፍያ በወቅቱ መፈጸም ሲገባው በ2007 በጀት ዓመት ለህንፃ መሳሪያ፣ ለላብራቶሪ እቃ፣ ለምግብ ዝግጅት እህል አቅርቦት፣ ለደንብ ልብስ፣ ለመድኃኒት ግዥና ሌሎች የእቃዎችና የአገልግሎቶች ግዥዎችን ፈጽሞ በ2008 በጀት ዓመት በድምሩ ብር 5,449,667.38 በጀት ዓመቱን ያልጠበቀ ክፍያ ፈጽሞ ተገኝቷል፡፡

የተሰብሳቢ ሂሳብ በመመሪያው መሰረት ስለመሰብሰቡ ሲጣራም በዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ኮሌጆች በጠቅላላው ብር 34,807.35 ቅድመ ገቢ ግብርና የተጨማሪ እሴት ታክስ ሳይቀነስ ከፍያ መፈፀሙ ታውቋል፡፡

የእቃና አገልግሎት አቅራቢዎች በወቅቱ ማቅረብ ሳይችሉ ሲቀሩ በቀረበው የውል መጠን ላይ በየቀኑ 1/1000ኛ መቀጣት እንዳለባቸው ቢደነገግም የተለያዩ እቃዎችን በውሉ መሰረት በወቅቱ ገቢ ካላደረጉ አቅራቢዎች ገቢ መሆን የነበረበት ብር 3,291,307.05 የጉዳት ካሳ ለመንግሥት ገቢ አለመደረጉም በኦዲት ግኝቱ ተረጋግጧል፡፡

ከዚህም ሌላ በግልጽ ጨረታ ለተፈፀመ የአጀንዳ ህትመት ግዥ አጀንዳው ጥራቱን ያልጠበቀ መሆኑ በቴክኒክ ኮሚቴው ቢገለጽም ገቢ ተደርጎ ብር 1,071,984.00 ክፍያ መፈጸሙን የኦዲት ግኝቱ ያሳያል፡፡

በተጨማሪም በአጠቃላይ ድምር ብር 13,111,912.15 ተሰብሳቢ ሂሳብ በወቅቱ ያልተወራረደ ሲሆን ከዚህ ውስጥ በድምሩ ብር 12,005,530.69 ከነ ተቀጽላ ሌጀራቸው ከ2007 በጀት ዓመት ለ2008 በጀት ዓመት የዞረ ተሰብሳቢ ሂሳብ በ2008 በጀት ዓመት ምንም እንቅስቃሴ ያልታየበትና ባለበት ሁኔታ ለ2009 በጀት ዓመት መተላለፉም ተመልክቷል፡፡

የዩኒቨርስቲው ተከፋይ ሂሳብ በመመሪያው መሰረት ስለመያዙ ሲጣራም ከ2007 በጀት ዓመት ለ2008 በጀት ዓመት የዞረ ተከፋይ ሂሳብ እንቅስቃሴ በአጠቃላይ ድምር ብር 88,059.04 ተከፋይ ሂሳብ በወቅቱ ሳይወራረድ ተገኝቷል፡፡

በንብረት አያያዝ በኩልም የመኖሪያ የሆኑና ያልሆኑ የዩኒቨርሲቲው ህንፃዎች እንደ ቋሚ ንብረት በተለየ መዝገብ ላይ መመዝገብ ሲገባቸው በ2008 በጀት ዓመት እና ከዚያ በፊት ባሉት የበጀት ዓመታት ርክክብ የተፈፀመባቸው ዩኒቨርሲቲው የሚገለገልባቸው ህንፃዎች እንዲሁም የጋራ መኖሪያ ቤቶች ያልተመዘገቡ መሆኑን፣ ይህ በዩኒቨርሲቲው የ2007 በጀት ዓመት ሂሳብ ኦዲት ወቅት አስተያየት ተሰጥቶበት የነበረ ቢሆንም ሳይስተካከል መገኘቱን፣ የቋሚ እና አላቂ ዕቃዎች በአንድ መጋዘን መቀመጣቸውን፣ የተለያዩ ለህፃናት ደብተር መያዣነት የሚያገለግሉ ቦርሳዎች እና ሌሎችም የህክምና እቃዎችና መሣሪያዎች ሞዴል 19 ያልተቆረጠላቸው እና ቢን ካርድ ሳይዘጋጅላቸው ከሌሎች ንብረቶች ጋር አብረው መቀመጣቸውን ኦዲቱ አሳይቷል፡፡

በተጨማሪም በንብረት መጋዘን ውስጥ ንብረቶች በአግባቡ አለመቀመጣቸው፣ በእርዳታ የተገኙ በሆስፒታል አገልግሎት ላይ የሚውሉና አገልግሎት የማይሰጡ አልጋዎች በብዛት ተበታትነው መገኘታቸው እንደዚሁም አንዳንድ የመጠቀሚያ ጊዜ ማብቂያ ያልተጠቀሰባቸው ቢን ካርዶች መኖራቸው፣ በነፃ የሚታደሉ መድኃኒቶች መረጃ ተገልጋዩ ሊያያቸው በሚችልበት ቦታ አለመለጠፉና የመድኃኒት ነክ መረጃ አያያዝና ሪፖርት አደራረግ ላይ ችግር መኖሩም ተጠቅሷል፡፡

በ2007 በተደረገው ኦዲት እርምት እንዲደረግባቸው ከተሰጡ አስተያቶች ውስጥም በ2008 በጀት አመት እርምጃ ያልተወሰደባቸው ጉዳዮች እንዳሉ ኦዲቱ አሳይቷል፡፡ በዚህ ረገድ በዋናው ግቢ በናሙና ለኦዲት ከተመረጡ ሂሳቦች መካከል ለ1 የውጪ ሀገር መምህር ደመወዝና የቤት አበል በትምህርት ዝግጅታቸውና ማዕረጋቸው መሰረት ብር 311,906.73 (15,100 ዶላር) መከፈል ሲገባው ብር 396,662.25 (19,500 ዶላር) በመክፈሉ በብልጫ ብር 86,755.52(4,200 ዶላር) የተከፈለ መሆኑ፣ በተፈጥሮ ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ውጪ ሀገር በትምህርት ላሉ 15 መምህራን በድምሩ 26,800.00 በመመሪያ ያልተደገፈ የቤት አበል የተከፈላቸው መሆኑ፤ በጤና ሳይንስ ኮሌጅ ብር 58,823.00 የውሎ አበል ያለ አግባብ በብልጫ መከፈሉ እና የተማሪዎች ህብረት ከተለያዩ የውስጥ ገቢዎች ሰብስቦ ሲጠቀምበት የነበረ ከመጋቢት 2007 በፊት በህብረቱ የተሰበሰበው የገቢ መጠን ኦዲት ሳይደረግና ከወጪ ቀሪው ሳይታወቅ በባንክና በእጅ የነበረ በድምሩ ብር 529,361.20 ወደ ዩኒቨርሲቲው የውስጥ ገቢ ሂሳብ ገቢ መደረጉ ተጠቅሰዋል፡፡

ከዚህ ሌላም ዩኒቨርሲቲው ለተለያዩ ግንባታዎች ከኮንትራክተሮች ጋር በገባው ውል መሠረት ግንባታዎቹ ሳይጠናቀቁ በመዘግየታቸው ለደረሰበት ጉዳት ከ5 ኮንትራክተሮች ማግኘት የሚገባው እስከ ዋናው ውል 10% ድረስ በየቀኑ የውሎቹ 1/1000ኛ ተሰልቶ የ5 ግንባታ ፕሮጀክቶች ከውል ጠቅላላ ዋጋ ብር 209,974.397.77 ላይ ብር 20,997,439.78 የጉዳት ካሳ ለመንግሥት ገቢ አለመደረጉ በኦዲቱ ተመልክቷል፡፡

በኦዲቱ በተገኙ ግኝቶች እና እስካሁን በተወሰዱ እርምጃዎች ላይ የመቀሌ ዩኒቨርስቲ አካዳሚክ ምክትል ፕሬዘዳንት ዶ/ር አብዱልቃድር ከድር እና ሌሎች የዩኒቨርስቲው የበላይ አመራሮች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

የውሎ አበል፣ ደመወዝና ጥቅማ ጥቅምን በተመለከተ ለመምህራን የሚደረግ የትርፍ ሰአት ክፍያ የውስጥ ገቢን መሰረት ያደረገና የከፍተኛ ትምህርት አዋጅ በሚፈቅደው መሰረት በዩኒቨርስቲው ቦርድ ጸድቆ የተከፈለ እንጂ የፐብሊክ ሰርቪስ ሚኒስቴር ፈቃድ የማይጠየቅበት ነው በሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በሌላ በኩል ለክረምት የትምህርት መርሀ ግብር የተማሪዎች ማደሪያ ክፍሎችና የምግብ ቤት ሰራተኞች ስራ የግድ መቀጠል ስላለበት በማኔጅመንት በማስፈቀድ ከሚመለከተው የመንግስት አካል ፈቃድ ሳይጠየቅ እንደተከፈለና ከዚህ ስህተትም ትምህርት በመውሰድ በቀጣይ ከፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሀብት ልማት ሚኒስቴር ፈቃድ በመጠየቅ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አላግባብ በጭማሪ ከተከፈለው አበል ውስጥም አስከ ጥር ወር 2010 ዓ.ም ድረስ ወደ 38 ብር ሺህ እንዲመለስ መደረጉና ቀሪውም እንዲመለስ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በጤና ሳይንስ ኮሌጅ ላሉ የህክምና ባለሙያዎች ለስራ ጫና በሚል የተከፈለው ገንዘብም የትምህርትና የህክምና አገልግሎት በአንድ ላይ ለሚሰጡ ሰራተኞች ከውስጥ ገቢ የተከፈለ እንደሆነ ነገር ግን ክፍያውን በቦርዱ ሳይጸድቅ መክፈሉ ስህተት መሆኑን በመረዳት ትምህርት እንደተወሰደበት አስረድተዋል፡፡

የአመት ፈቃድን በገንዘብ ቀይሮ መክፈልን በተመለከተ ለአንድ ሰራተኛ የሁለት አመት የአመት ፈቃድ አልተከፈለም ብለዋል፡፡

ከእቃ ግዢ ጋር በተያያዘ ኮሌጆቹ እስከተወሰነ የገንዘብ መጠን ድረስ በራሳቸው የመግዛት ያልተማከለ ስልጣን ያላቸው በመሆኑ እንደየተጨባጭ ሁኔታቸውና እንደሚያጋጥማቸው ችግር ፍላጎታቸውን መሰረት ያደረገ ግዢ የሚፈጽሙበት ሁኔታ በመኖሩ የተፈጠረ መሆኑን ገልጸው ከኦዲቱ በኋላ ግን የኮሌጆቹን የግዥ ፍላጎት በማሰባሰብ በማእቀፍ እንዲፈጸምና በዩኒቨርስቲ ደረጃም በማእከል እንዲገዛ እየተደረገ የተናጥል ግዢዎች እንዲቀንሱ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በየኮሌጆቹ በዚህ መልኩ ከሚፈጸም የተበጣጠሰ ግዢ ውጪም በዩኒቨርስቲው በማእከል የሚፈጸም ግዥ እንዲሁም የማዕቀፍ ግዥ ጥቅም ላይ እየዋሉ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ተራ ፋክቱር ከመጠቀም ጋር በተያያዘም በኦዲቱ ወቅት ፋክቱሮቹን ማቅረብ ያልተቻለ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ተሰብስበው መቅረባቸው እንዲሁም ፋክቱር የማይቀርብለቸው ወይም ተራ ፋክቱር የሚቀርብላቸው እንደ እንስሳት ምግብ ግብቶችና የቁም እንስሳ ግዢዎች አልፎ አልፎ እንደሚያጋጥሙ አስረድተዋል፡፡

የወጪ ሂሳቦች ምዝገባ ጉድለትን በተመለከተም ባብዛኛው ወጪዎቹ ከምርምር ስራ ጋር የተያያዙ እንደሆኑ ገልጸው በምርምር ፕሮጀክቶቹ ውስጥ ያሉ የተለያዩ በጀቶችን በአግባቡ ባለመመዝገብ የተፈጠረ ችግር እንጂ በጀቱ በአግባቡ ጥቅም ላይ እንደዋለና ከስህተቱ ትምህርት መወሰዱን ገልጸዋል፡፡

የበጀት አመቱን ባልጠበቀ ክፍያ ረገድ ችግሩ አሁንም ያላቆመ መሆኑንና አንዳንድ ግዥዎች በተለያዩ ምክንያቶች የሚዘገዩ በመሆኑ የኦዲት ግኝቱ የውሉ አመት ካለፈ በኋላ በመከፈላቸው ምክንያት የመጣ አንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የገቢ ግብር አሰባሰብን በተመለከተ ዩኒቨርስቲው አዲስ አበባ ላይ ያለው አገናኝ ቢሮ ግዥዎችና ክፍያዎች እንዳሉትና ከነርሱ ተቀንሶ ለመንግስት መግባት ያለባቸው ገቢዎች ባለመግባታቸው የመጣ ግኝት መሆኑን አስረድተው በቀጣይ ገቢው ተሰብስቦ ወደመንግስት መግባት እንዳለበት ትምህርት እንደተወሰደ ወደተግባር ግን እንዳልተገባ ገልጸዋል፡፡

አገልግሎትና እቃን አዘግይቶ በሚያቀርብ አቅራቢ ላይ የሚጣል የጉዳት ካሳን በተመለከተ ቅጣቱ በአቅራቢው ላይ ያልተጣለው የችግሩ ምንጭ ዩኒቨርስቲው በመሆኑ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ጥራቱን ያልጠበቀ አጀንዳ መረከብን በተመለከተም በዩኒቨርስቲው የቀረበው ስፔሲፊኬሽን ችግር እንዳለበት ቴክኒካል ኮሚቴው የገለጸ ቢሆንም አቅራቢው ግን በቀረበለት ስፔሲፊኬሽን መሰረት ያቀረበ በመሆኑ ዩኒቨርስቲው ንብረቱን መረከቡን ገልጸዋል፡፡

በተሰብሳቢ ሂሳብ በኩል አብዛኛው ተሰብሳቢ ሂሳብ መሰብሰቡን የተወሰኑት ግን በህግ እንደተያዙና በድርድር ላይ እንዳሉ አስረድተዋል፡፡ ከዚህ ውጪ በህይወት የሌሉና ከሀገር ውጪ ለትምህርት ሄደው የቀሩትን በተመለከተ ለገንዘብ ሚኒስቴር በማሳወቅ ምክር ተጠይቆ መልስ እየተጠበቀ ነው ብለዋል፡፡

በተከፋይ ሂሳብ ረገድ 88 ሺህ ብር እንደተከፈለና የተቀረው ወደ መንግስት ካዝና እንዲገባ መደረጉን አስረድተዋል፡፡

ንብረትን በተመለከተ የንብረት አቀማመጥና አመዘጋገብ ችግር ስለነበረ የካይዘን አሰራርን መሰረት በማድረግ ንብረቶች እንዲቀመጡ እንደተደረገና ትምህርት እንደተወሰደ ገልጸዋል፡፡ ህንጻዎቹም ምዝገባ በሶፍት ኮፒ እንደተዘጋጀ ነገር ግን በመንግስት ወደተዘጋጀው ካርድ እንዳልገባ አስረድተዋል፡፡

እርምጃ ያልተወሰደባቸው የኦዲት ግኝቶችን በተመለከተ የውጭ ዜጋ የሆኑት መምህር ክፍያ የፎረንሲክ ምርመራና ትምህርት ስራ እንዳይቋረጥ በሚል በብልጫ እንዲከፈላቸው በማኔጅመንት ውሳኔ ለሀኪሙ እንደተከፈለ ነገር ግን ክፍያውን በሚመለከተው አካል አሳውቆ አለማስፈቀዱ ስህተት እንደነበረ፣ ግንባታ ካዘገዩ ኮንትራክተሮች በጉዳት ካሳ ሊሰበሰብ ይገባ ከነበረው ገንዘብ ውስጥም ወደ 6 ሚልየን ብር ያህሉ እንደተሰበሰበና ሌሎቹም ወደፊት ለኮንትራክተሮቹ ከሚከፈሉ ቀሪ ክፍያዎች ለመቀነስ እንደታሰበ እንዲሁም የኮንትራት መራዘምና ተቀጽላ ስራዎች አሰጣጥን የተመለከቱ አስፈላጊ ሰነዶች በመቅረባቸው ተሰብሳቢው ገንዘብ በኦዲቱ ከተጠቀሰው መጠን ያነሰ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በዩኒቨርስቲው አመራሮች በተሰጠው ማብራሪያ ላይ ቋሚ ኮሚቴ አባላቱ ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡

በዚህም የሁለት አመት ጥቅም ላይ ያልዋለ ፈቃድ ወደ ደሞዝ ተቀይሮ አልተከፈለም ከተባለ በኦዲት ሪፖርቱ ላይ ግኝት ሆኖ መቅረብ እንደማይችል በመጥቀስ በዚህ ጉዳይ ላይ በኦዲቱ መውጫ ስብሰባ ላይ የነበረው ሁኔታ ምን እንደነበረ እንዲብራራ ጠይቀዋል፡፡ እንደዚሁም ለመምህራን የሚከፈሉ ጥቅማ ጥቅሞች ከመደበኛ በጀት ሳይሆን ከውስጥ ገቢ እንደሆነና ይህም ለቦርዱ የተሰጠ ስልጣን ነው በሚል በዩኒቨርስቲው ምላሽ ቢሰጥም ኦዲቱ በመመሪያው መሰረት ማንኛውም ደሞዝና ጥቅማጥቅምና አበል በሚኒስቴሮች ምክር ቤት ጸድቆ መተግበር እንዳለበትና ቦርዱ የሚያስተላልፈው ውሳኔ ተቀባይነት እንደሌለው የሚገልጽ እንደሆነ በመጥቀስ የውስጥ ገቢን ጉዳይ ለሚመለከተው የመንግስት አካል አቅርቦ ገቢውን የበጀት እቅድ አካል አድርጎ መመሪያው በሚፈቅደው አግባብ መክፈል ስላልተቻለበት ምክንያት እንዲገለጽ ጠይቀዋል፡፡

በተጨማሪም ማንኛውም ግዢ መፈጸም ያለበት የሚመከለከተው የመንግስት አካል ባዘጋጀው ህጋዊ ደረሰኝ ሆኖ ሳለ በተራ ፋክቱሮች ለምን ሂሳቡ እንደተወራረደ ጠይቀዋል፡፡ መንግስት ግዢዎች ወደ ማእቀፍ ግዢ እንዲመጡ በሚሰራበት ሁኔታ ውስጥ ዩኒቨርስቲው ያልተማከለ አሰራርን እጠቀማለሁ በሚል ግዥዎችን በተናጥል ወደየኮሌጆቹ በማውረድ መስራቱ እንዴት እንደሚታይ፤ የክረምት፣ የርቀትና የማታ ትምህርት መርሀ ግብሮች የመምህራን ክፍያን ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ማቅረብና ማጸደቅ ስላልተቻለበት ምክንያት፣ የግዥ ስርአቱም ጤናማ ስለመሆኑ የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ ጠይቀዋል፡፡ ማኔጅመንቱ የግዥ መመሪያውን መሰረት አድርጎ መስራት ያልቻለበት ምክንያት ምንድን ነው፣ የበጀት አመትን ያልጠበቀ ወጪ መከፈል እንደሌለበት ትምህርት ወስደናል እየተባለ አሁንም ያልተስተካከለ ከሆነ ትምህርቱ ምኑ ላይ ነው፣ የተያዘውን በጀት በተደጋጋሚ በወቅቱ እንዲያልቅ ማድረግ ያልተቻለበት ምክንያትስ ምንድን ነው በሚልም ጥያቄ አንስተዋል፡፡

እንደዚሁም በግዥ ስርአቱ ላይ ያለውን ችግር ለማስተካከልና ተጠያቂነትን ለማምጣት እንዳይቻልና ስህተቶች እንዳይታረሙ የሚያደርጉ ሁኔታዎችን ለማስቀረት የአመራሩ ቁርጠኝነት ምን እንደሚመስል ጠይቀዋል፡፡

ከባለድርሻ አካላት መካከልም የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ተወካይ አቶ ፍቃዱ አጎናፍር በመድረኩ ላይ የዩኒቨርስቲው የውስጥ  ኦዲት ክፍል ለምን እንዲገኝ እንዳልተደረገ እንዲሁም የውስጥ ኦዲቱ ሪፖርቶች ከፌዴራል ዋና ኦዲተር ኦዲት ግኝቶች ጋር ተመሳሳይ በመሆናቸው የውስጥ ኦዲት ክፍሉ የሚሰጣቸውን ሀሳቦች ተቀብሎ እርምጃ ያልተወሰደበት ምክንያት እንዲገለጽ ጠይቀዋል፡፡ ዩኒቨርስቲው በይፋዊ ስብሰባ መድረኩ ላይ እንደሚገልጸው ሳይሆን በዋና ኦዲተር መ/ቤት ኦዲት ግኝቶች ልክ እርምጃ እየወሰደ እንዳልሆነ ሚኒስቴሩ በዩኒቨርስቲው ተገኝቶ ባደረገው የክትትልና ድጋፍ መድረክ መታየቱንም ገልጸዋል፡፡ የሞቱና የጠፉ ሰዎች ያለባቸውን እዳ ስለማስመለስ የወጣ ህግ ያለ በመሆኑም በዚሁ አግባብ መስራት እንደሚገባው ጠቅሰዋል፡፡ ከኦዲቱ ግኝቶች ትምህርት እንደተወሰደ በዩኒቨርስቲው አመራሮች በተደጋጋሚ ከመገለጹ አኳያም እስከመቼ ድረስ ነው ትምህርት የሚወሰደው የሚለውን በመጠየቅ ባስተማሪነት ብቻ ከማለፍ ለምን እርምጃ መውሰድ አልተቻለም ሲሉ ጠይዋል፡፡ በተጨማሪም በዩኒቨርስቲው ግዥን በእቅድ አካቶ ባለመግዛት መንግስትን ተጨማሪ ወጪ እየዳረገው በመሆኑ ጉዳዩ ቀለል ተደርጎ መታየት እንደሌለበት አስገንዝበዋል፡፡

ከቋሚ ኮሚቴው አባላትና ከባለድርሻ አካላት ለቀረቡት ጥቄዎች ዩኒቨርስቲው አካዳሚክ ምክትል ፕሬዘዳንት ዶ/ር አብዱልቃድር ሲመልሱ እስከ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ድረስ ሄዶ ክፍያዎችን ማጸደቅ የሚለው ጉዳይ በዩኒቨርስቲው አቅም ሊፈጸም ይችላል ብለው እንደማያምኑ፣ በዩኒቨርስቲው ደረጃ ክፍያዎችን በአዋጁ መሰረት በቦርድ ጸድቆ መፈጸም ይቻላል የሚል እምነት እንዳለ፣ በግዢ በኩልም ግዢ በእቅድና በስርአት እንደሚመራ ነገር ግን ከዩኒቨርስቲ ልዩ ባህሪ አኳያ ክፍተት የሚፈጥሩ ሁኔታዎች እንዳሉ ግምት ውስጥ መግባት እንዳለባቸው፣ የውስጥ በጀት የማጸደቅ ስርአት አንዳለ ነገር ግን ችግሩ በትርፍ ሰአት ክፍያ ጋር ተያይዞ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ተጠያቂነትን በማስፈን ተገቢነት ላይ ጥያቄ እንደሌለም ተናግረዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ በኦዲት ግኝቶቹ በዩኒቨርስቲው አመራሮች በተሰጡ ምላሾች ላይ በዝርዝር በሰጡት አስተያየት የዩኒቨርስቲው ቦርድ ጥቅማጥቅምንና የትርፍ ሰአት ክፍያን እንዳይወስን የክፍያ ተመንንም እንዳያወጣ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቆ መመሪያው በቀድሞው ሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር በኩል መላኩን አስታውሰው ዩኒቨርስቲው ከግንዛቤ ማነስ የፈጸመው ሳይሆን ህግን በመጣስ የፈጸመው በመሆኑ ሊታረም ይገባል ብለዋል፡፡

ክቡር አቶ ገመቹ የውስጥ ገቢ ለማመንጨት የሚያስፈልጉ ወጪዎች  በቦርድ መጽደቅ ሲገባቸው 999 ሺህ ብሩ በቦርድ ሳይጸድቅ መከፈሉ አግባብ እንዳልሆነና መታረም እንዳለበት፣ ጥቅም ላይ ባለመዋሉ በደመወዝ የተለወጠው የአመት ፈቃድም ለ2006 እና 2007 የፈቃድ ቀናት በአንድነት በ2008 በጀት አመት እንደተፈጸመና ይህም ከመመሪያ ውጪ በመሆኑ ሊስተካከል እንደሚገባ ጠቅሰዋል፡፡

የእቃ ግዢ በህግና በመመሪያ መሰረት በእቅድ መፈጸም እንዳለበት፣ በቁጥቁጥ የተገዛው 2.7 ሚልየን ብር በራሱ ብዙ እንደሆነና በየኮሌጆቹ ያለው የቁጥቁጥ ግዢዎች መቅረት እንዳለባቸው፣ ተራ ፋክቱርን በተመለከተም በኦዲቱ ወቅት ማሰረጃ ያለማቅረብ ሁኔታው መታረም እንዳለበት እንዲሁም ደረሰኝ ለማይገኝላቸው ልዩ ግብዐቶች በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር በኩል በማስፈቀድ ግዢ መፈጸም እንደሚገባ፣ ለምርምር የተመደበ በጀት የአመዘጋገብ ስህተት ነው በሚል የተነሳው 6,582,659.52 ብርም ሙሉ በሙሉ ለምርምር የዋለ በጀት ባለመሆኑ በጥቅሉ ለምርምር እንደተመደበ አድርጎ ከመግለጽ ይልቅ በዝርዘር ማየት እንደሚያስፈልግ ዋና ኦዲተሩ ገልጸዋል፡፡

የበጀት አመቱን ያልጠበቀ ወጪ ዩኒቨርስቲው እንደገለጸው አቅራቢዎች በወቅቱ ባለማቅረባቸው ብቻ የመጣ ሳይሆን ዩኒቨርስቲው ከተደለደለው በጀት በላይ በመጠቀሙ ምክንያት ጭምር የመጣ በመሆኑ ሊሻሻል እንደሚገባ፣ ግዢ ከተፈጸመባቸው ነጋዴዎች ተጨማሪ እሴት ታክሱ መሰብሰብ እንደሚገባው፣ ጥራቱን ላልጠበቀው አጀንዳ ምክንያቱ የአቅራቢው ችግር ባለመሆኑ ቅጣት አልተጣለበትም ቢባልም ዩኒቨርስቲው በጥራት መጓደል ምክንያት ተመጣጣኝ ቅጣት በአቅራቢው ላይ እንደጣለበት የሚያሳይ የጽሁፍ ማስረጃ መኖሩን፣ የተሰብሳቢ ሂሳብ ቀንሷል ቢባልም የ2009 የሂሳብ ኦዲቱ ተሰብሳቢ ሂሳቡ በጣም እንደጨመረ እንደሚያሳይ ዋና ኦዲተሩ ገልጸዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በሞትና ከሀገር በመውጣት ምክንያት መሰብሰብ ያልቻለው ሂሳብ ምን ያህል እንደሆነ በመለየት በተቀመጠው አሰራር መሰረት ለመሰብሰብ መጣር እንደሚገባ፣ የህንጸዎች መረጃ በሶፍት ኮፒ ቢመዘገብም ወደ ስርአቱ ማስገባት እንደሚያስፈልግ፣ ከግንባታ የጉዳት ካሳ ጋር ተያይዞ ካለው የ20 ሚልየን ብር ውስጥ ወደ 6 ሚልየን ብር እንዲቀንስ ተደርጓል በሚል ምላሽ የተሰጠው የ2009 በጀት አመት እንደሆነና ኮንትራክተሩም ሆነ በዩኒቨርስቲው በኩል ውሳኔዎችን በወቅቱ ባለመስጠት ስራው እንዲዘገይ ያደረገው አካል መጠየቅ እንዳለበት፣ እያንዳንዱ ግዢ በእቅድ መያዝና ወደ አንድ ማእከል መሰብሰብ እንዳለበት፣ የዩኒቨርስቲው ቦርድ ስልጣን በዋና ኦዲተር ተጥሷል የሚለው ስህተት እንደሆነና የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በመስፈርቶች ላይ መሰረት በማድረግ ህጎችና መመሪያዎች እንዲከበሩ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በሰጡት የማጠቃለያ አስተያየት የዋና ኦዲተር መ/ቤትን ግኝት ለመማሪያነትና በቀጣይ ችግሮችን ለማስተካከያነት እንደግብአት መውሰዱ በጥሩ ጎን እንደሚታይና ሊቀጥል እንደሚገባ ገልጸው ዩኒቨርስቲው አሳማኝ ናቸው በሚል ከመመሪያ ውጪ የሚፈጽማቸው ተግባራት ከኦዲት ግኝትነት እንደማያድኑትና ይልቁንም አሳማኝ ምክንያቱን ጉዳዮቹን ወደሚመለከተው አካል ወስዶ መመሪያ እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል፡፡

እንደዚሁም ግኝቶችን መሰረት በማድረግ ማስተካከል እንደሚገባ፣ የወጡ ህጎችንና መመሪያዎችን በመከተል ዩኒቨርስቲው ከምርምር ስራዎች፣ ከመማር ማስተማር ስራዎችና ከማህበረሰብ አገልግሎት ሳይወጣ አስቀድሞ በማቀድ ግኝቶችን መቀነስ እንደሚቻል፣ በግዥ በኩል ያሉና ከአቅራቢዎች ጋር የተያያዙ ችግሮችን ማጥራትና ተጠያቂ ማደረግ እንደሚገባ፣ ተከፋይና ተሰብሳቢ ሂሳቦችን በተከታታይ እያወራረዱና እየከፈሉ መሄድ እንደሚያስፈልግ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ የወ/ት ወይንሸት ገለሶ በማጠቃለያ አስተያየታቸው የኦዲት ግኝቶችን ባለማረም ማስጠንቀቂያ ከተሰጣቸው ተቋማት ውስጥ አንዱ መቀሌ ዩኒቨርስቲ እንደሆነ ገልጸው መታረም ያለባቸው ጉዳዮች ሳይታረሙ እንዲቀጥሉ እድል መስጠት እንደሌለበት ገልጸዋል፡፡ ያሉ አሰራሮች እንዲተገበሩ አሰራር ያልወጣላቸው ካሉም እንዲወጣላቸው ዩኒቨርስቲው የመታገል ሚና አለበት ያሉት የተከበሩ ወ/ት ወይንሸት እርምጃ እንደተወሰደባቸው የተነሱ ጉዳዮች እንደ ጅምር በጥንካሬ ሊወሰዱ እንደሚችሉ ነገር ግን በተጨባጭ ስለመሰወዳቸው በዋና ኦዲተር መ/ቤት በኩል መረጋጥ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ መመሪያና ደንብን ያልተከተሉ አሰራሮች በኦዲት ግኝቱ መሰረት መታረም እንዳለባቸው በተለይም ለግዢ ስርአቱ ችግሮች ልዩ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ፣ ህግና መመሪያን ያልተከተሉ ስራዎች ላልተፈለጉ ተግባራት በር ስለሚከፍቱ ማስቀረት እንደሚያሻ፣ ዩኒቨርስቲው በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ሊሆን የሚችለው ከኦዲት ግኝት ነጻ ሲሆን በመሆኑ ተቋሙ ይህንን የመወጣት ሀላፊነት አለበት የሚለው በደንብ ሊጤን እንደሚገባው አክለው ተናግረዋል፡፡

ከዚህም ሌላ በንብረትና በጀት አጠቃቀም ላይ ያሉ ችግሮች ከዩኒቨርስቲው አቅም በላይ በሆነ ምክንያት የተፈጠሩ ናቸው ተብሎ እንደማይወሰድና ዩኒቨርስቲው ወደ ራሱ በደንብ ተመልክቶ መፍትሄ ካልሰጠ ወደ ትክክለኛ መፍትሄ መድረስ እንደማይቻል ግንዛቤ መወሰድ እንዳለበት፣ የዩኒቨርስቲው ማኔጅመንት፣ ቦርድና የፋይናንስ ክፍሉ ተቋሙን የመጠበቅና የፋይናንስ ስርዐቱ ጤናማ እንዲሆን የማድረግ ሀላፊነት እንዳለባቸው አሳስበው ተወሰዱ የተባሉ እርምጃዎች ለሚመለከታቸው አካላትና ለቋሚ ኮሚቴው መላክ አለባቸው ብለዋል፡፡

እንደዚሁም የዩኒቨርስቲው የውስጥ ኦዲት ክፍል የሚሰጠው አስተያየት ትኩረት ተሰጥቶት መተግበር እንዳለበትና የውስጥ ኦዲት የስራ ክፍሉም በተቋሙ ተወሰዱ የተባሉ እርምጃዎች መፈጸማቸውን ማረጋገጥ እንደሚኖርበት፣ በዚህ ይፋዊ ስብሰባ ላይም ዩኒቨርስቲው በተደረገው ጥሪ መሰረት የውስጥ ኦዲት ክፍሉ፣ የተማሪዎች ተወካዮች እንዲሁም የህዝብ ክንፍ አካላት እንዲገኙ ማድረግ እንደነበረበት ብሎም ስራዎችን በጋራ ገምግሞ በቂ መረጃና ወጥ አቋም ይዞ መቅረብ ይገባው እንደነበረ አስገንዝበዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *