News

የኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽንና የሚመለከተው አካል የያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታን በአግባቡ በመምራት በኩል ኃላፊነቱን እንዳልተወጣ ተገለጸ

የኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽንና ጉዳዩ የሚመለከተው አካል የያዩ ዩሪያ ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታን ተከታትሎ በአግባቡ በመምራትና በወቅቱ እንዲጠናቀቅ በማድረግ በኩል ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዳልተወጣ የመንግስት ወጪ አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ከ2006-2008 ዓ.ም የያዩ ዩሪያ የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ አፈጻጸም ውጤታማነት ላይ ባከናወነው የክዋኔ ኦዲት ላይ ጥር 30/2010ዓ.ም ቋሚ ኮሚቴው ይፋዊ ህዝባዊ ስብሰባ አድርጓል፡፡ በስብሰባው ላይ የኦዲት ግኝቶቹ በዝርዝር ቀርበው የሚመለከታቸው አካላት ምላሽ እንዲሰጡበት ተደርጓል፡፡

መንግስት የያዩ ዩሪያ የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ የአዋጭነት ጥናትን እንዲያካሂድ ቻይና ኮምፕላንት ለተባለ ድርጅት ሰጥቶ ጥናቱ ከረጅም ጊዜ በኋላ በ1999 ዓ.ም ሲጠናቀቅ በጥናቱ መሰረት ግንባታውን ራሱ በማካሄድ በአራት አመታት ውስጥ ለመጨረስና አስፈላጊውንም ፋይናንስ ለማቅረብ እንደሚችል አጥኚው ድርጅት ቢገልጽም መንግሰት ጥናቱን ለብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) እንደሰጠና ሜቴክም ጥናቱን በመከለስ በሁለት አመታት ውስጥ ፋብሪካውን ገንብቶ ለማጠናቀቅ እንዲሁም የምርት ሙከራ ለማድረግና ለአንድ አመት ፋብሪካውን በማስተዳደር ለባለቤቱ ለማስረከብ በ2004 ዓ.ም ከፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ ጋር ውል እንደገባ ኦዲቱ በመጥቀስ ከዚህና ከአፈጻጸም ጋር የተያያዙ በርካታ የኦዲት ግኝቶችን አስቀምጧል፡፡

በዚህም የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ ለሀገሪቱ አዲስ እንደመሆኑ መጠን ፋብሪካውን ለመገንባት የሚያስችል አቅም በሚፈጥርና የቴክኖሎጂ ሽግግር በሚያመጣ መልኩ ግልጽ የሆነ ጨረታ ወጥቶ በውድድር የተሻለ ብቃት ላለው ተቋራጭ አለመሰጠቱን፣ ፋብሪካውን እንዲገነባ/እንዲያስገነባ የፕሮጀክት ባለቤት የነበረው የፕራያቬታይዜሽን ኤጀንሲ ከብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ጋር ውል የፈጸመ ሲሆን የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ ኮንትራቱን የሰጠው አካል በግልጽ ያልታወቀ መሆኑን፣ ቻይና ኮምፕላንት የተባለው ድርጅትና ብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ባደረጓቸው ጥናቶች መሀከል ያለው የጊዜ ልዩነት እንዲጣጣም አለመደረጉን እንዲሁም የፋብሪካ ግንባታው በውሉ መሰረት በ2006 ዓ.ም አለመጠናቀቁና በኦዲቱ ወቅት ግንባታው 42 በመቶ ብቻ መሆኑን ኦዲቱ አመልክቷል፡፡

በተጨማሪም የግንባታው ስራ ተቋራጭ የሆነው ሜቴክ እቅዱን በመከለስ ስራውን በ2008 ዓ.ም ለማጠናቀቅ ከተጨባጭ የመፈጸም አቅም ጋር ያልተገናዘበ መርሀ ግብር እንዳቀረበና እስከ መጋቢት 2009 ዓም ድረስም አፈጻጸሙ ዝቅተኛ እንደነበረ፣ የግንባታ ፕሮጀክቱ መጠናቀቂያ ጊዜ በትክክል የማይታወቅና በውል ያልታሰረ እንደሆነ ስራውም ሜቴክ በሚያቀርበው የጊዜ ሰሌዳ ብቻ እንደሚከናወን አሳይቷል፡፡ ከዚህም ሌላ ውል ከተገባው 11,084,850,000 ብር ውጪ ሜቴክ ለተጨማሪ ስራዎች በሚል የክፍያው መጠን ወደ 14,500,000,000 ከፍ እንዲል ያቀረበውና በኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ተቀባይነት ያላገኘው ጥያቄ ውሳኔ እንዲሰጠው ባለመደረጉ   ተጨማሪ ወጪ፣ የጊዜ ብክነት እና የፕሮጀክት ስራ መጓተት ማስከተሉ፣ ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ ባለመጠናቀቁም ኮርፖሬሽኑ ከባንክ ለተበደረው ብድር ወለድ እስከ መጋቢት 2009 ዓ.ም ድረስ 1,826,513,172.20 ብር የተከፈለ መሆኑና ፕሮጀክቱ በተራዘመ ቁጥር ለባንክ የሚከፈለው ወለድ ከፍተኛ መሆኑ በኦዲቱ ተመላክቷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የስራ ተቋራጩ ለእያንዳንዱ ፕሮጀክት ስራ የተተነተነ ዝርዝር እቅድና የስራ አፈጻጸም መርሀ ግብር በየወቅቱ አጠቃሎ የማያቀርብ መሆኑ፣ በፕሮጀክቱ የጋራ ስምምነት ላይ የተደረሰበት ፕሮጀክት የሌለው መሆኑ፣ በሀገር ውስጥ ስለሚመረቱና ከውጭ ስለሚገዙ ማሽነሪዎች መከታተያ የጊዜ ሰሌዳ የሌለው መሆኑ፣ ለፕሮጀክቱ በግብአትነት የሚያስፈልጉ መሳሪያዎች ስለሚቀርቡበት እንዲሁም የውጭ አማካሪ ቅጥር ለማከናወን የሚያስችሉ ጨረታዎች ስለሚወስዱት ጊዜ የሚያሳይ የጊዜ ሰሌዳ ተዘጋጅቶ ከዋናው የመርሀግብር እቅድ ዝርዝር ውስጥ አለመቅረቡም ተጠቅሷል፡፡

እንደዚሁም ሜቴክ የፋብሪካው ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከ2008 ዓ.ም በስተቀር የማሽነሪዎችና የመሳሪያዎችን ቴክኒካል ስፔሲፊኬሽን አዘጋጅቶ ለኮርፖሬሽኑ ያላቀረበ መሆኑ፣ የማሽነሪዎች ዝግጅት በሀገር ውስጥ በሚገኙት የሜቴክ እህት ኩባንያዎችና ኢንደስትሪዎች አማካኝነት እየተዘጋጀ የሚገኝ ቢሆንም የስራ አፈጻጸሙ ከፕሮጀክቱ አጠቃላይ ክንውን ጋር የማይጣጣምና የዘገየ መሆኑ፣ በሀገር ውስጥ እየተመረቱ ባሉ የተወሰኑ ምርቶች ላይ የብየዳ ስራ ወጥነት የሌለውና የጥራት ጉድለት የሚታይ መሆኑ፣ እንዲሁም የፕሮጀክቱ ወሳኝ እቃዎችን የመግዛት፣ የማምረትና የማቅረብ ስራ በጣም የዘገየና በታቀደለት ጊዜ የተከናወነ አለመሆኑ፣ በግንባታ ቅደም ተከተል መሰረት የሚያስፈልጉ መሳሪያዎች ተለይተው አለመቅረባቸው፣ ከውጭ ሀገር ለሚመረቱ እቃዎች ውል ባለመፈጸሙ ስራው አለመጀመሩ፣ ሜቴክ ስራውን ለሌላ ተቋራጭ በንኡስ ኮንትራት ሲሰጥ የፕሮጀክቱ አማካሪ ለሆነው ለአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ወይም ለፐሮጀክቱ ባለቤት ያላሳወቀ መሆኑ እንዲሁም የኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ከመቋቋሙ በፊት ፕሮጀክቱን ያስተዳድር ለነበረው  ለፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ  በወቅቱ ስለማሳወቁ መረጃ አለመገኘቱ፣ የዲዛይን ዶክመንቶች መቅረብ ባለባቸው ጊዜ ለአማካሪው የማይቀርቡና የሚታዩ ክፍተቶች ላይ አስፈላጊው አስተያት የማይሰጥ መሆኑ፣ ለፋብሪካው የሚያስፈልግ የውሀ አቅርቦትን በተመለከተ ዲዛይኑ እንደተጠናቀቀ በተቋራጩ ቢገለጽም የዲዛይን ሪፖርት ባለመቅረቡ ያለበት ትክክለኛ ደረጃ የማይታወቅ መሆኑ በኦዲቱ ተረጋግጧል፡፡

ከዚህ ውጪም ኮርፖሬሽኑ የኬሚካል ኢንደስትሪው የሚፈልገውን የሰው ሀይል በሚፈለገው ጥራትና አይነት ለማሰልጠን ከሚመለከታቸው የትምህርት ተቋማት ጋር በማቀናጀት አሰልጥኖ ወደ ስራ እንዲገባ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ ቢገባውም ከአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ጋር ብቻ ለመስራት የመግባቢያ ስምምነት ከመፈራረም ባለፈ ወደ ዝርዝር ስራ ያልተገባ መሆኑ፣ ተቋራጩ በሁለት አመታት ውስጥ ግንባታውን አከናውኖ ስራውን አስጀምሮ የሰው ሀይሉን አሰልጥኖ ማስረከብ እንዳለበት ውል ቢገባም ከወዲሁ ከፋብሪካው ግንባታ ጎን ለጎን የሰው ሀይል ተዘጋጅቶ ወደ ስራ እንዲገባ ያልተደረገ መሆኑ እንዲሁም ለፕሮጀክቱ ከተከለለው ቦታ ቀደም ሲል የለቀቁ አንዳንድ ሰዎች እንደገና እየሰፈሩ እንደሚገኙና ከሰራተኞች ደህንነትና ከአካባቢ ጥበቃ ጋር በተያያዘ ያልተሰሩ ቀሪ ስራዎች መኖራቸው ተጠቅሷል፡፡

በማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ ቦታ ላይ የሚገኙ ማናቸውም ጥሬ ሀብቶች ባለቤታቸው የኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን መሆኑ በውል ላይ የተገለጸ ቢሆንም ሜቴክ ውሉን ከፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ ጋር ከፈረመበት ከግንቦት 2004 ዓ.ም በፊት በሚያዝያ 2/2004 ዓ.ም የባለቤትነት ፈቃድ ከማእድን ሚኒስቴር በማውጣት በፕሮጀክቱ ስፍራ ያለውን የድንጋይ ከሰል ሀብት በባህላዊ ዘዴ እያወጣ ካለኤጀንሲው ፈቃድ የሚሸጥ መሆኑ፣ የአማካሪ ተቋሙ የየዘርፉ የስራ ሀላፊዎችና ቺፍ ሬዚደንት ኢንጂነሮች ቢያንስ በየሁለት ሳምንት አንድ ጊዜ ውይይት የማያደርጉ ከመሆኑ  በላይ በሳይቱ በወር አንድ ጊዜ በመገናኘት ስራውን የሚገመግሙ ስለመሆኑ ቃለጉባኤው ሊቀርብ አለመቻሉና ተቋራጩ፣ ንዑስ ተቋራጩና አማካሪው የስራ ግንባታ ግብአቶች ጥራት በመስክ ፍተሻ በቋሚነት የማያደርጉ መሆኑ በኦዲቱ ተገልጿል፡፡

ቋሚ ኮሚቴውም እነዚህ ችግሮች የተፈጠሩበትን ምክንያት፣ አሁን ያሉበትን ደረጃ፣ ከኦዲቱ በኋላ የተወሰዱ እርምጃዎችን፣ ለችግሩ ተጠያቂ አካል ማን እንደሆነ፣ ችግሮቹን ለመፍታት የአመራሩ ቁርጠኝነት ምን እንደሚመስልና የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባርን ለመከላከል በኮርፖሬሽኑ ምን እንደተሰራ ማብራሪያ እንዲሰጥ ጠይቋል፡፡ የኬሚካል ኢንደስትሪ ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ ደሜ፣ የመንግስት ልማት ድርጅቶች ሚኒስትር ደኤታ ክቡር አቶ በየነ ገ/መስቀልና የኮርፖሬሽኑ የስራ ሀላፊዎች በኦዲቱ በታዩ ችግሮችና በተነሱት ጥያቄዎች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ስራው ለሜቴክ እንዲሰጥ ስለተደረገበት ሁኔታ ሲገልጹ በወቅቱ በሀገር ውስጥ የኢንደስትሪ አቅምን ለመገንባት፣ የውጪ ምንዛሬን ለማዳንና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማምጣት በሚል የተከናወነ እንደሆነና በዚህም ሚያዝያ 2004 ዓ.ም የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር በጻፈው ደብዳቤ በመንግስት የሚሰሩ ፕሮጀክቶች በሜቴክ እንዲሰሩ በገለጸው መሰረት በቀጥታ  ከሜቴክ ጋር ውል እንደተገባ አስረድተዋል፡፡

ሜቴክ ለተጨማሪ ስራዎች ከውሉ ውጪ ተጨማሪ ክፍያ የጠየቀባቸው ጉዳዮች ለአማካሪ ተቋሙ ቀርበው አንዳንዶቹ ተቀባይነት ያላቸው እንደሆኑ ሌሎቹ ግን ተቀባይነት የሌላቸውና ተቋራጩ አስቀድሞ በገባው ውል መሰረት ሊያከናውናቸው ሲገባ ያላከናወናቸው መሆናቸው በአማካሪው በተገለጸለት መሰረት ኮርፖሬሽኑ ለቦርዱ ለውሳኔ እንዲቀርብ መደረጉን አስረድተዋል፡፡

ለፕሮጀክቱ ስራ የተተነተነ ዝርዝር እቅድና የስራ አፈጻጸም መርሀ ግብር በማቅረብ በኩልም ኮርፖሬሽኑ የፕሮጀክቱ አማካሪ ለሆነው ለአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሳይንስና ቴክኖሎጂ መርሀ ግብሩን በመላክ እንደሚያስተችና የተሰጠውን ግብረመልስም ለሜቴክ እንደሚያቀርብ አስረድተው ነገር ግን ሜቴክ በግብረ መልሱ ላይ ምላሽ እንደማይሰጥ ተናግረዋል፡፡ ሜቴክ የአፈጻጸም ሪፖርት ቢልክም ችግሩ ግንባታው ፈቀቅ ማለት አለመቻሉ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በሀገር ውስጥ እየተመረቱ ባሉ የተወሰኑ ምርቶች ላይ የብየዳ ስራ ወጥነት የሌለውና የጥራት ጉድለት የሚታይበት መሆኑን በተመለከተ ጉድለቶቹ በኦዲቱ ወቅት የነበሩ ወቅታዊ ችግሮች እንደነበሩና በሂደት እንደተስተካከሉ ገልጸዋል፡፡

የፕሮጀክቱ ወሳኝ እቃዎችን የመግዛት፣ የማምረትና የማቅረብ ስራ በጣም የዘገየበት ምክንያትም በግንባታ ወቅት  የስትራክቸር መሰንጠቅ ማጋጠሙና ይህንንም ለማስተካከል ሲባል የችግሩ መንስኤ የሆነውን የአፈር መሸሽን የሚገታ የሪቴይኒንግ ዎል ግንባታ ስራ ረጅም ጊዜ መውሰዱ ስራው ወደፊት እንዳይራመድ ማነቆ መሆናቸው  ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በተቋራጩ በኩልም የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንደችግር እንደሚነሳ ጠቅሰዋል፡፡

ሜቴክ ለንኡስ ተቋራጮች ስለሚሰጠው ስራና ስለተቋራጮቹ ማንነት ለፕሮጀክቱ ባለቤት ሳያሳውቅ ሲሰራ መቆየቱን በተመለከተ ከኦዲቱ በኋላ ሁኔታው መስተካሉን ገልጸዋል፡፡

ለፋብሪካው የሚሆን የተማረ የሰው ሀይልን ከትምህርት ተቋማት ጋር በመሆን ማዘጋጀትን በተመለከተ በዚህ ረገድ ገፍቶ የተሰራ ስራ እንደሌለና የግንባታ ስራውም ገና በመሆኑ የሰው ሀይል አሰልጥኖ ካለስራ ማስቀመጡ ሀብት ማባከን ነው በሚል እንዳተከናወነ ተናግረዋል፡፡

የፋብሪካው ግንባታ ወቅቱን ጠብቆ ያልተጠናቀቀበትን ምክንያት ሲገልጹ በዋናነት አራት ችግሮች እንደተለዩ እነርሱም ስራውን ለማከናወን የሚያስችል የራስ አቅም በሜቴክ በኩል ያለመኖር፣ የራስ አቅም በሌለበት ሁኔታም የሌሎችን አቅም ተጠቅሞ ለመስራት ዝግጁነትና ቅልጥፍና በሜቴክ በኩል አለመኖር፣ የፋይናስ ችግርና የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንዲሁም በግንባታ ወቅት የተፈጠሩ የቴክኒክ ችግሮች ፈጥኖ አለመፍታት መሆናቸውን  አስረድተዋል፡፡ ከ2008 ዓ.ም በኋላም ሜቴክ ግንባታው ነሀሴ 2010 ዓ.ም እንደሚያልቅ ቢያሳውቅም በተባለው ወቅት ባለመጠናቀቁ እንደገናም ሀምሌ 2011 ዓ.ም እንደሚያልቅ የገለጸ መሆኑና የግንባታው ወጪም ከሀያ ቢልየን በላይ የሚደርስ መሆኑን በማሳወቁ ጉዳዩ ለቦርዱ እንደቀረበ ገልጸዋል፡፡ ሜቴክ ሊተገብረው የሚችል ዳግም ሊከለስ የማይችል መርሀ ግብር ማዘጋጀት ስለመቻሉ፣ ይህን መርሀ ግብር ለማስተግበር የሚያስችል ዝግጅት ያለው ስለመሆኑ እንዲሁም ይህንን ለማድረግ ያሉ ችግሮችን ለይቶ እንደያቀርብ ለአማካሪ ተቋሙ ስራው እንደተሰጠና አማካሪው በሚሰጠው ምላሽ ላይ ተመስርቶ በየካቲት ወር 2010 ዓ.ም ለመንግስት የውሳኔ ሀሳብ እንደሚቀርብ ተናግረዋል፡፡

ከሰዎችና ከአካባቢ ደህንነት ጥበቃ ጋር በተያያዘም የአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ ጥናት እንደተሰራና ነገር ግን ፋብሪካው የሚያደርሰውን ጉዳት በትክክል ማወቅ የሚቻለው ወደ ስራ ሲገባ መሆኑን አስረድተው በሰራተኞች ደህንነት ላይ የነበሩ ስጋቶችን ለመቀነስ በሜቴክ የማሻሻያ ስራ እንደተሰራ ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቱን በየወቅቱ ከመከታተል ጋር ተያይዞም ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጅ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን በግንባታ በቦታው ላይ በየሁለት ወሩ በመገኘት እየተገመገመ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ለባንክ ስለሚከፈለው ወለድ ሲናገሩም በቀን ወደ 3 ሚልየን ብር በወር ወደ ዘጠና ሚልየን ብር ለባንክ ወለድ እየተከፈለ እንዳለና ግንባታው በቆየ መጠን ለፕሮጀክቱ የተመደበው በጀት ለወለድ እየተከፈለ ፕሮጀክቱንና በኮርፖሬሽኑ ስር ያሉ የኬሚካል ኢንደስትሪዎችን ህልውና ስጋት ውስጥ ሊከት እንደሚችል፣ አማካሪ ድርጅቱም በፍጥነት ግንባታው ተጠናቆ ወደስራ ካልገባ አክሳሪ እንደሆነ ገልጾ እንደነበረና አሁንም ያልተጠናቀቀ በመሆኑ የፕሮጀክቱ አዋጭነት ስጋት ላይ እንደወደቀና እንዴት በፍጥነት ይጠናቀቅ የሚለው ጥያቄ በጣም አሳሳቢ ጉዳይ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ተቋራጩ፣ ንዑስ ተቋራጩና አማካሪው የስራ ግንባታ ግብአቶች ጥራት በመስክ ፍተሻ በቋሚነት የማያደርጉ መሆናቸውን በተመለከተም ሜቴክ በእህት ኩባንያዎቹ የሚያመርታቸውን መሳሪያዎች ሲፈትሽ ኮረፖሬሽኑንም ሆነ አማካሪ ተቋሙን እንደማይጠራ ነገር ግን ንዑስ ኮንትራት የያዘው የቻይና ኩባንያ ለሚያመጣው ግብአት የጥራት ማረጋገጥ ስራ አሰርቶ እንደሚያመጣና ይህንንም አማካሪ ተቋሙ በየጊዜው እንደሚከታተል አስረድተዋል፡፡

የድንጋይ ከሰሉ በሜቴክ እየተሸጠ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ድርጊቱ ተቀባይነት እንደሌለውና ፈቃዱ ከሜቴክ እንዲመለስ መደረጉን አስረድተዋል፡፡

የአማካሪው የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ የስራ ኃላፊ እንደገለጹት ሜቴክ ስራውን በጥራት፣ በተቀመጠው ጊዜና በተመደበው በጀት ሰርቶ በማጠናቀቅ ረገድ በአቅም ችግር ምክንያት ሀላፊነቱን አለመወጣቱን፣ በየወቅቱ እቅዱን እየከለሰ አጠናቅቃለሁ የሚልበት አካሄድም ትክክል እንዳልሆነ፣ እንዲሁም አስቀድሞ ውሉ ላይ የነበሩ ስራዎችን አስመልቶ ዝግጅት አለማድረጉንና ለዚህም ተጨማሪ ስራ ናቸው በማለት ተጨማሪ ጊዜ እየጠየቀ ያለበት ሁኔታን አማካሪ ተቋሙ እንደማይቀበለው ገልጸው አሁንም ሜቴክ በ2011 ዓ.ም ግንባታውን አጠናቅቃለሁ በሚል ያቀረበው እቅድ አሳማኝ እንደማይመስል ገልጸዋል፡፡

በስራ ሀላፊዎቹ በተሰጡ ማብራያዎች እንዲሁም በግኝቶቹ ላይ ያላቸውን ጥያቄዎችና አስተያቶች የቋሚ ኮሚቴው አባላት፣ የኢንደስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል እና በመድረኩ የተገኙ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የስራ ኃላፊዎች አቅርበዋል፡፡

በዚህም በዋናነት ፕሮጀክቱ መንግስት ለሰፊው የኢትዮጵያ አርሶ አደር ህዝብ ማዳበሪያ በሀገር ውስጥ በተሻለ ሁኔታ ለማቅረብ ተስፋ የሰጠበትና የሀገሪቱን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እድገት ያፋጥናል ተብሎ እምነት የተጣለበት በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን እንደሚጠናቀቅ የታቀደ ህዝብ በከፍተኛ ሁኔታ የሚጠብቀው ግዙፍ ፕሮጀክት ቢሆንም በአንጻሩ አሁን ያለበት ሁኔታ ሲታይ ግን ለተጨማሪ ወጪ ሀገሪቱን የዳረገ፣ ግንባታውን በአግባቡ በየጊዜው ተከታትሎ እንዲጠናቀቅ የሚያደርገው ባለቤት ማን እንደሆነ የማይታወቅ የመሰለበት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ጋር አያይዘውም ምንም እንኳን ፕሮጀክቱ ውስብስብና ከባድ እንደሆነና ሜቴክም ፕሮጀክቱን በአግባቡ አካሂዶ የማጠናቀቅ የአቅም ችግር እንዳለበት ቢታወቅም የፕሮጀክቱ ባለቤት እንደ መሪ ሚናውን በአግባቡ እንዳልተወጣ፣ አመራሩ ችግሮችን በየወቅቱ እየፈታ፣ ሜቴክን እየደገፈና ሜቴክ በራስ አቅም ማከወን ባልቻላቸው ጉዳዮች ላይ ሌሎች አማራጮችን እየፈለገ ፕሮጀክቱን ማስቀጠል እንዳልቻለ፣ የኦዲት ግኝቱንም እንደ ግብአት ተጠቅሞ ይህ ነው የተባለ እርምጃ አለመውሰዱንና አሁንም ድረስ ችግሮቹን ከማንሳት በዘለለ ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ የሚያስችል ስራ እንዳልሰራ ተናግረዋል፡፡ አሁንም ግንባታውን በ2011 ዓ.ም ለማጠናቀቅ በሜቴክ የቀረበው መርሀ ግብር ይፈጸማል ብለው እምነት እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡

እንደዚሁም በግንባታ ስራው ውስጥ ያሉ አካላት ኃላፊነታቸውን በሚገባ እንዲወጡ ከማድረግ አኳያ አመራሩ ያለው ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት ምን ያህል እንደሆነ፣ ፕሮጀክቱን ከማስፈጸም ጋር ከተያያዙ የአቅምና ቴክኒካል ችግሮች ባለፈ ግልጽነትና ተጠያቂነትን ከማስፈንና ከኪራይ ሰብሳቢነት ጋር የተያያዙ ችግሮች ስላለመኖራቸው ባለድርሻ አካላት ተጨማሪ ጥያቄዎችን ጠይቀዋል፡፡፡

የዘርፉ አመራር ገፍቶ በመሄድ መደረግ አለበት የሚለውን የመፍትሄ ሀሳብ ማመንጨትና መንግስትን ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ መውሰድ ይጠበቅበታል ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡ እንደዚሁም አሁን የፕሮጀክቱ ገንዘብ ከፋይ ከሚመስልበት ሁኔታ ወጥቶ የአመራርነት ሚናውን በመወጣት ሜቴክ ፕሮጀክቱን በቀነ ገደብ ውስጥ እንዲያጠናቅቅ ማድረግ ያለበት ይኸው አመራር እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡  

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዲቢሶ በሰጡት አስተያየት የችግሮቹ ዋነኛ መንስኤ የፕሮጀክት አሰራር ሂደትን አለመከተል እንደሆነ ገልጸው በስራው አለም አቀፍ ልምድ ያለው አካል ፕሮጀክቱን በ4 አመታት እሰራለሁ እያለ በፋብሪካው ግንባታ ልምድ የሌለው ሜቴክ በ2 አመታት አጠናቅቀዋለሁ ሲል እቅዱ ምን ያህል ተጨባጭ ነው የሚለው ጥያቄ አለመጠየቁንና ችግሩን እዚህ ደረጃ ያያደረሰውም ይህ አንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ከዚህም ሌላ ማንኛውም ፕሮጀክት ሲካሄድ አማካሪ ድርጅት ሊኖረው ሲገባ ለፕሮጀክቱ እስከ 2006 ዓ.ም ድረስ አማካሪ ሳይቀጠርለት መስራቱ ስህተት እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡ እንደዚሁም ፕሮጀክቱ ሲቀረጽ የፋይናንስ ምንጩ በግልጽ ያለመወሰኑ ፕሮጀክቱ እንዲዘገይ ሚና እንደነበረው አመልክተዋል፡፡ ስራው ሲጀመርም ባለቤት እንዳልነበረውና ለኬሚካል ኢንደስትሪ ልማት ኮርፖሬሽን ሲሰጥም ኮርፖሬሽኑ ይህንን ግዙፍ ፕሮጀክት ተሸክሞ ሊመራ የሚያስችለው አደረጃጀት አልነበረውም ብለዋል፡፡ ለስራው ልምድ ያለው አማካሪም እንዳልተቀጠረ ገልጸው በቂ ክትትል እንዳልተደረገ ተናግረዋል፡፡ የግንባታ ደረጃው ገና 42 በመቶ ለሆነ ፕሮጀክት 60 በመቶ ክፍያ መፈጸሙም ትክክል እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡ የፕሮጀክቱ በጀት በኦዲቱ ወቅት 11 ቢልየን ብር እንደነበር በማስታወስ አሁን ከ20 ቢልየን ብር በላይ እንደሚጠይቅ መነገሩ አስደንጋጭ ነው ያሉት ክቡር ዋና ኦዲተሩ አሳሳቢው ነገር ፕሮጀክቱ አዋጭ ይሆናል ወይ የሚለውና አሁን በሜቴክ የቀረበው መርሀ ግብር በእውን ሊተገበር የሚችል ነው ወይ የሚለው እንደሆነ በመጥቀስ ጉዳዩ ጊዜ ሳይወሰድ በፍጥነት ሊታይ ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

የመንግስት ወጪ አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሜቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ት ወይንሸት ገለሶ በማጠቃለያ አስተያየታቸው በውይይቱ የታየው ችግሩ እንደቀጠለ እንጂ የተሰጠ መፍትሄ እንደሌለና የሚሰጡ የማሻሻያ ሀሳቦችና የሚወሰዱ እርምጃዎች ለምን የሉም የሚለው ጥያቄ እንዳልተመለሰ ነው፡፡ በአመራሮቹ ከተሰጡት ማብራሪያዎች በመነሳት ይህ ነው የሚባል የማሻሻያ እንቅስቃሴ ስለመደረጉ ቋሚ ኮሚቴው እንዳላየና የቋሚ ኮሚቴው ፍላጎት አፋጣኝ መፍትሄ ተወስዶ ማየት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ከተደረገው ውይይትም ቋሚ ኮሚቴው ባጭር ጊዜ ውስጥ እርምጃ ተወስዶ መፍትሄ ይሰጣል የሚል እምነት እንዳላሳደረ ተናግረዋል፡፡

በፋብሪካው ግንባታ ላይ ባለቤቱ ማን ነው የሚል ጥያቄ እንዲነሳ ያደረገው ውሳኔ ሰጪው አካል ባለመታወቁ ነው ያሉት ክብርት ወ/ት ወይንሸት 80 በመቶ አርሶ አደር ህዝብ ይህን ምርት እየተጠባበቀ ባለበት ሁኔታ ፍላጎቱን አለመመለስ የህዝብ ተጠቃሚነትን ጉዳይ አለመመለስ እንደሆነ በአመራሩ ዘንድ ሊወሰድ እንደሚገባው አስገንዝበዋል፡፡

እንደዚሁም ከውል ውጪ ያሉ ጉዳዮች ወደ ህግ ሊሄዱና ተጠያቂነትን ሊያስከትሉ እንደሚገባ ገልጸው የኬሚካል ኢንደስትሪ ኮርፖሬሽን የተሰጠውን ተልዕኮ ሊወጣ እንደሚገባ፣ ሜቴክና አማካሪ ድርጅቱም ለጋራ ተልእኮ ተመሳሳይ ሀላፊነት ያለባቸው በመሆኑ ይህንን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል፡፡ አመራሩም ሆነ መንግሰት ለችግሩ ፈጣን መፍትሄ ሊሰጠው ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *