News

ባለሥልጣን መ/ቤቱ የፋይናንስ አሠራር ስርዓትን አክብሮ ሊሠራ እንደሚገባ ተገለፀ

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒት፣ ጤና ክብካቤና ቁጥጥር ባለሥልጣን የ2008 በጀት ዓመት የፋይናንሺያል ኦዲት ግኝት ላይ ይፋዊ ህዝባዊ ስብሰባ ጥር 14፣ 2010 ዓ.ም አካሄደ፡፡ ተቋሙ የፋይናንስ አሠራር ሥርዓትን ተከትሎ ሊሠራ እንደሚገባም ቋሚ ኮሚቴው ገልጿል፡፡

በኦዲት ግኝቱ እንደተመለከተው በባለሥልጣን መ/ቤቱ የሒሳብ አያያዝ ሥርዓት በተገቢው የሒሳብ መደብ ተይዘው የሚመዘገቡ መሆኑን ለማረጋገጥ በናሙና ኦዲት ሲደረግ ብር 488,023.85 በትክክለኛው የሒሳብ መደብ ላይ ሳይመዘገብ መገኘቱ፤ ከ2002 በጀት ዓመት ጀምሮ በሒሳብ መደብ 4202 የተያዘ የጥሬ ገንዘብ ጉድለት ብር 17,097.98፣ ከ2006 ጀምሮ እስከ 2008 በጀት ዓመት ድረስ በሒሳብ መደብ 4211 የተያዘ ቅድሚያ ክፍያ ብር 338,286.28 በድምሩ ብር 355,384.26 በፋይናንስ ደንብና መመሪያው መሠረት በወቅቱ ያልተወራረደ /ያልተሰበሰበ ሒሳብ ተገኝቷል፡፡ል፡፡

የወጭ ሒሳቦች በተገቢው የሒሳብ መደብ የሚመዘገቡ መሆኑን ለማረጋገጥ በናሙና ኦዲት ሲደረግ ባለሥልጣን መ/ቤቱ ብር 89,342.28 በትክክለኛው የሒሳብ መደብ ሳይመዘገብ የተገኘ መሆኑ፤ የሚመለከተውን የመንግስት አካል ወይም የፐብሊክ ሰርቪስ ሚኒስቴር መ/ቤትን ሳያስፈቅድ ለሠራተኞች ብር 1,597,191.14 የትርፍ ሰዓት ሥራ ክፍያ ፈፅሞ መገኘቱ፤ ለሥልጠና ወጪ፣ ለአልጋ፣ ለምግብና  ለአዳራሽ ኪራይ በብር 2,250,494.69 አገልግሎት ግዢ እንደዚሁም ለዋና መ/ቤት፣ ለደቡብና ምስራቅ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች በብር 370,797.18 በዋጋ ማወዳደሪያ ለፈፀመው የመጋረጃ ግዢ በድምሩ ለብር 2,621,291.87 ጨረታ ሳይወጣ ግዢ የተፈፀመ መሆኑ፤ የዋጋ ማወዳደሪያ ሳይሰበሰብ የመስተንግዶና የሰራተኛ የደንብ ልብስ በድምሩ ብር 238,249.77 ግዢ የተፈፀመ መሆኑ በኦዲት ግኝቱ ተመልክቷል፡፡

የቀድሞው ሲቪል ሰርቪስ ኤጀንሲ ባስተላለፈው መመሪያ በሥራ ባህሪያቸው የተነሳ ለጤና ጠንቆች ተጋላጭ በሆኑ የሥራ መደቦች ላይ ለሚሰሩ ሰራተኞች የፈቀደውን ክፍያ መሠረት በማድረግ ለ54 ሠራተኞች ለእያንዳንዳቸው በወር ብር 80.00 በዓመት ብር 51,840.00 ክፍያ መፈፀም ሲገባው በጠቅላላው ብር 189,539.38 በመፈፀም በመመሪያ ከተፈቀደው በላይ ብር 137,699.38 ግዥ የፈፀመ መሆኑ፤ ከጥቅምት 15 እስከ 30 ቀን 2008 ዓ.ም ድረስ ለአስራ አምስት ቀን በሰርቪላንስ /በኢንተለጀንስ ፅንሰ ሃሳብ ዙሪያ በተሰጠው ሥልጣና ለ46 ሰልጣኞች ለትራንስፖርት አበል በቀን 30 ብር ሒሳብ ለሃያ ቀን ብር 27,600.00 የተከፈለ ሲሆን ስልጠናው ከተጠናቀቀ በኋላ የአምስት ቀን ብር 6,900.00 በተጨማሪ ክፍያ ተፈፅሞ የተገኘ መሆኑም ተገልጿል፡፡

እንደዚሁም ከንብረት አያያዝና አወጋገድ ጋር በተያያዘ በውጭ ምንዛሪ የተገዙ በርካታ መጽሐፍት ለብልሽት በተጋለጠ መልኩ በካርቶንና በማዳበሪያ የተቀመጡና በተጨማሪም ጠረጴዛ ወንበር፣ ኮምፒዩተር፣ የግድግዳ ሰዓት፣ ዲቪዲ፣ ፍሬም ዲዛይን ባለመስታወት ከአንድ ዓመት በላይ ያለ አገልግሎት የተቀመጡ መሆኑ፤ በ2008 በጀት ዓመት ለመደበኛና ለካፒታል ወጪ ለየፕሮግራሞቹ የተፈቀደው በጀት አጠቃቀም በየሒሳብ ኮዶቹ ሲታይ ከመደበኛ በጀት ከ10% በላይ ብር 9,964,783.40፣ ከካፒታል በጀት ደግሞ ብር 3,953,042.53 በድምሩ ብር 13,917,825.93 ሥራ ላይ ያልዋለ መሆኑ እና ከመደበኛ በጀት ብር 1,488,388.52፣ ከካፒታል በጀት ደግሞ ብር 93,000.00 በድምሩ ብር 1,581,388.52 ለየሒሳብ ኮዶቹ ከተደለደለው በጀት በላይ የወጣ መሆኑ በኦዲት ግኝቱ ተገልጿል፡፡

በአጠቃላይ ባለሥልጣን መ/ቤቱ ትክክለኛ የፋይናንስ አሠራርን ተከትሎ መሥራት ያልቻለበትን ምክንያትና የኦዲት ግኝቱን ተከትሎ በወሰዳቸው የማስተካከያ እርምጃዎች ላይ የባለሥልጣን መ/ቤቱ ኃላፊዎች ማብራሪያ እንዲሰጡ ቋሚ ኮሚቴው ጠይቋል፡፡ የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒት፣ ጤና ክብካቤና ቁጥጥር ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ የሁሉ ደነቀውና ሌሎች የባለሥልጣኑ የስራ ኃላፊዎች በተነሱት ጥያቄች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በባለሥልጣን መ/ቤቱ የፋይናንስ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አባይነህ አለማየው በሰጡት ምላሽ በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የቀረቡት የኦዲት ግኝቶች ትክክለኛ መሆናቸውን አረጋግጠው ለተነሱት ጥያቄዎች ሲመልሱ በትክክለኛ መደብ ሒሳብ ሳይመዘገብ የተገኘ ብር 488,023.85 በ2009 በጀት ዓመት እንዲስተካከል መደረጉን፤ በተለያዩ የሒሳብ መደቦች ያልተወራረዱ ሂሳቦች አስፈላጊውን ክትትል በማድረግ ከ338,286.28 ብር ውስጥ አብዛኛው ሒሳብ እንዲመለስ/እንዲወራረድ መደረጉን እና ቀሪ ያልተወራረደ ብር 4,794.00 አንድ ሠራተኛ ለሥራ ከአገር እንደወጣ ባለመመለሱ ሒሳቡን ለማወራረድ ችግር መፈጠሩን፤ የወጪ ሒሳቦችን በተገቢው የሂሳብ መደብ ባለመመዝገብ የተገኘው ግኝትም ከክህሎት ክፍተት የመጣ ስህተት መሆኑና እንዲስተካከል መደረጉን እንደዚሁም የትርፍ ሰዓት ክፍያን በተመለከተ ከኦዲት ግኝቱ በኋላ ክፍያው እንዲቆም መደረጉንና ለፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሃብት ልማት ሚኒስቴር መ/ቤት ጥያቄ ቀርቦ  ባለመፈቀዱ በባለስልጣን መ/ቤቱ ስራ ላይ ጫና ማሳደሩን ገልፀዋል፡፡

የአልጋ፣ የምግብና የአዳራሽ ኪራይን ያለ ውድድር ግዥ መፈጸሙን በተመለከተም የተቋሙ 2ኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በአስቸኳይ እንዲዘጋጅ አቅጣጫ በመሰጠቱ አጠቃላይ ሰራተኛውን በአጭር ጊዜ አሳትፎ ለማዘጋጀት ከነበረው ጫና የተፈጠረ  መሆኑን ገልፀው በቀጣይ መሰል ስህተት እንዳይፈጠር ትምህርት መወሰዱን፤ ግዢዎችም ከ2009 በጀት ዓመት ጀምሮ በመመሪያው መሠረት እየተፈፀሙ የሚገኙ መሆኑን፤ በመመሪያ ከተፈቀደው በላይ የተፈፀመን ክፍያን በተመለከተም መ/ቤቱ ለሠራተኞች በየጊዜው በግዢ ሲያቀርብ የነበረው የወተት ዋጋ መጨመሩን ተከትሎ የተፈፀመ እንደሆነ አስረድተው ክፍያው ከመመሪያው ውጪ የተፈፀመ እንደሆነ ከተገለፀላቸው በኋላ ክፍያው እንዲቆም መደረጉን፤ አላግባብ የተከፈለ የሥልጠና አበል ክፍያ ተመላሽ እንዲሆን መደረጉን አስረድተዋል፡፡

ከንብረት አያያዝና አወጋገድ ጋር በተያያዘም  ተጠግነው አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ኮምፒዩተሮች ተጠግነው ወደ አገልግሎት እንዲገቡ መደረጉን፣ ሊጠገኑ የማይችሉና ጊዜያቸው ያለፈባቸው ኮምፒዩተሮችና ሌሎች ንብረቶች ከመንግስት ግዢና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ጋር በመነጋገር እንዲወገዱ መደረጉን እንዲሁም ቀሪዎቹን ለግብረሰናይ ድርጅቶች በስጦታ መሰጠታቸውንና በቤተመፅሐፍት ሊቀመጡ ይገቡ የነበሩ ነገር ግን ቦታ ባለመገኘቱ በተለያዩ ካርቶኖች ተቀምጠው የነበሩ መፅሐፍት ቤተመፅሐፍት እስከሚደራጅ ድረስ በተገቢ ሁኔታ ተመዝግበው በጊዜያዊነት በግምጃ ቤት እንዲቀመጡ መደረጉንገልጸዋል፡፡

ከበጀት አጠቃቀም ጋር በተያያዘም በ2008 በጀት ዓመት የታየውን ክፍተት መነሻ በማድረግ በ2009 እና 2010 የተሻለ የበጀት አጠቃቀም እንዲኖር መሠራቱን አቶ አባይነህ አስረድተዋል፡፡

የባለሥልጣን መ/ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ የሁሉ ደነቀው በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ ሰራተኞች ለጤና ጠንቅ ተጋላጭ እንዳይሆኑ በህግ የተፈቀደላቸውን ጥቅማጥቅም እንዲጠበቅላቸው ከማድረግ ባለፈ ቴክኖሎጂ በመጠቀም የሥራ አካባቢያቸው ከተበከለ አየር የፀዳ እንዲሆን የአየር ማጣሪያ /Air Handling/ የመግጠም ሥራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ፤ የትርፍ ሰዓት ክፍያን ለማስቀረት ሠራተኛው በመደበኛው 8 ሰዓት በአግባቡ ስራውን እንዲያከናውን የማደረግ እና ለጊዜው በግምጃ ቤት የተቀመጡ መጽሐፍትን በተገቢው ሁኔታ እንዲያዙ እራሱን የቻለ የቤተመፅሐፍት አገልግሎት መስጫ ክፍል ለማዘጋጀት እየተሠራ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በሰጡት አስተያየት ባለሥልጣን መ/ቤቱ የኦዲት ግኝቱን መሠረት አድርጎ የድርጊት መርሃ ግብር በማዘጋጀት የተፈጠሩትን ችግሮች ለመቅረፍ የሄደውን ርቀት አድንቀው ነገር ግን የኦዲት ግኝቱን ተከትሎ እንዲቆሙ የተደረጉ አሠራሮች መፍትሔ መሆን እንደሌለባቸውና ከሚመለከተው አካል ጋር ገፍቶ በመነጋገር ዘላቂ መፍትሔ እንዲፈጠር መሥራት እንደሚያሻ፤ የትርፍ ሰዓት ክፍያን በተመለከተም ያለውን ችግር ለመፍታት የአሠራር ሥርዓትን ማስተካከል እንደሚያስፈልግ፤ ያላግባብ በመያዛቸው ለብልሽት እየተጋለጡ ያሉት መፅሐፍት በአግባቡ እዲያዙና ለአንባቢ ተደራሽ እንዲሆኑ ዘላቂ ቤተመፅሐፍት እስከሚዘጋጅ ጊዚያዊ ክፍል ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግና የበጀት አጠቃቀምም ያለውን ችግር ለመቅረፍ ባለሥልጣን መ/ቤቱ ከእቅድ ጀምሮ በትኩረት መሥራት እንደሚጠበቅበት እና ከጨረታ ውጪ የሚገዙ የአገልግሎት ግዢዎችም ህጋዊነት የሌላቸው በመሆኑ በህጉ መሠረት ሊፈፀሙ እንደሚገባና ይህን ተላልፈው የፈፀሙ ፈፃሚዎች ተጠያቂ ሊደረጉ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ በሰጡት አስተያየት በተቋሙ ኃላፊዎች አብዛኞቹ ግኝቶች ላይ የማስተካከያ እርምጃ እንደተወሰደ ቢገለፅም ተቋሙ ለዋና ኦዲተር በላከው ሪፖርት ላይ በተባለው አግባብ እርምጃ ስለመወሰዱ የውስጥ ኦዲተሩ አለማረጋገጡን፤ የትርፍ ሰዓት ክፍያን በተመለከተ የተከፈለ ከ1.5 ሚሊዮን ብር በላይ ሒሳብ ተጠያቂ መሆን ያለባቸው አካላት ህጋዊ እርምጃ ሊወሰድባቸው እንደሚገባ፣ ለጤና ጠንቅ ተጋላጭ ለሆኑ ሠራተኞች በመመሪያ የተፈቀደውን 80 ብር ተቋሙ ከኦዲት ግኝቱ በኋላ ማቋረጡን መግለፁ ትክክለኛ እርምጃ አለመሆኑና በኦዲት ግኝቱ እንዲያቋርጡ የተገለፀው በመመሪያ ያልተፈቀደውን ተጨማሪ ክፍያ እንደሆነ እንዲሁም ከገደብ በላይ የተከፈለን የትራንስፖርት ክፍያ ተመላሽ ከማድረግ ባለፈም ክፍያው እንዲፈፀም ያደረገውን አካል ተጠያቂ እንዲሆን ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ት ወይንሸት ገለሶ በመጨረሻ በሰጡት አስተያየት በኦዲት የታዩትን ችግሮች ለመፍታት የተደረገውን ጅምር ጥረት አድንቀው የቀሩትንም ለማስተካከል ምቹ ሁኔታ እንዳለ የሚያሳይ በመሆኑ ተቋሙ አጠናክሮ ሊሰራ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡

በሌላ በኩል ባለሥልጣን መ/ቤቱ ከ2002-2008 ዓ.ም ያሉ የኦዲት ግኝቶች እንደሚያሳዩት ተመሳሳይነት ያላቸው ጉዳዮች ላይ ችግሮች ያሉበት በመሆኑ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ፤ የትርፍ ሰዓት ክፍያን ከመመሪያ ውጪ እንዲፈፀም ያደረጉ አካላት በህግ ሊጠየቁ እንደሚገባ፤ ከመመሪያው ውጪ የሚፈጸም  የአገልግሎት ግዢ መታረም እንዳለበት፤ የበጀት አጠቃቀም ውጤታማ እንዲሆን እቅድን መሠረት አድረጎ ሊሠራ እንደሚገባ፤ የውስጥ ኦዲት የሥራ ክፍልን ማጠናከር እንደሚጠበቅበትና በአጠቃላይ የፋይናንስ አሠራር ሥርዓትን ተከትሎ ተቋሙ ሊሠራ እንደሚገባ የተከበሩ ወ/ት ወይንሸት አሳስበዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *