News

ምክር ቤቱ በኦዲት ግኝቶች ላይ እርምጃ በማይወስዱት ላይ ክትትልና ቁጥጥሩን ማጠናከር እንዳለበት ተገለጸ

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኦዲት ግኝቶች ላይ እርምጃ በማይወስዱ አካላት ላይ የሚያደርገውን ክትትል ይበልጥ ማጠናከር እንዳለበት የምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባዔ የተከበሩ ወ/ሮ ሽታዬ ምናለ አሳሰቡ፡፡

ምክትል አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ሽታዬ በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት አዘጋጅነት በኦዲት ምንነትና አሰራር ዙርያ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትና ለሌሎች ባለድርሻ አካላት ከታህሳስ 13-14/2010 ዓ.ም ድረስ የተዘጋጀውን የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ሲከፍቱ ባደረጉት ንግግር የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እያከናወናቸው ያሉ የክትትልና ቁጥጥር ስራዎች እድገት እያሳዩ ቢሆንም በኦዲት ግኝቶች ላይ እርምጃ በማይወስዱ አካላት ላይ የሚያደርገው ክትትል ከዚህ በበለጠ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል፡፡

“የሀገራችንን ሁለንተናዊ እድገት ቀጣይ በማድረግ የህዳሴ ጉዟችንን በስኬታማ መንገድ ለመምራት ያለንን ውስን ሀብት በአግባቡና ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠቀምና ህጎች በአግባቡ ስራ ላይ መዋላቸውን ማረጋገጥ ቅድሚያ የምንሰጠው ተግባር ነው፡፡” ያሉት ወ/ሮ ሽታዬ በሀገሪቱ የታቀዱ የልማት፤ የመልካም አስተዳደርና የዲሞክራሲ ግንባታ እቅዶች በአስፈጻሚ አካላት በአግባቡ እየተፈጸሙ መሆኑን ለመከታተል ምክር ቤቱ በአጠቃላይ ከሚያደርገው ቁጥጥር፣ ክትትልና ድጋፍ በተጨማሪ በየዘርፎቹ የቋሚ ኮሚቴዎች አደረጃጀት በመፍጠር በቅርበት እየተቆጣጠረ፤ እየተከታተለና እየደገፈ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ምክትል አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ሽታዬ አያይዘውም በግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ ላይ የተገኙ የምክር ቤት አባላትና የተለያዩ መ/ቤቶች የስራ ኃላፊዎች ከመድረኩ የሚያገኙትን ተጨማሪ ግንዛቤ በመጠቀም የቁጥጥር፤ የክትትልና የድጋፍ ስራቸውን የበለጠ አጠናክረው ሀገራዊ የሀብት አጠቃቀምንና የተልዕኮ አፈጻጸምን ውጤታማ የሚያደርግ እገዛ እንደሚያደርጉ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ መድረኩ የምክር ቤት አባላትና የባለድርሻ አካላት በመንግስት የፋይናንስ አስተዳደር ላይ ባሉ ጉዳዮችና በኦዲት አሰራር ዙርያ ያላቸውን ግንዛቤ በማሳደግ የክትትልና የቁጥጥር ስራውን ለማጠናከር የተዘጋጀ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በስልጠናው ወቅት የመንግስት ፋይናንስ አስተዳደር እና የፋይናንስ አስተዳደር ሪፎርም ስራዎችን፣ የመንግስት የጥሬ ገንዘብ አስተዳደርና የክፍያ ስርዐትን፣ የበጀት ዝግጅትና አስተዳደርን፣ የውስጥ ኦዲትና የውስጥ ቁጥጥር ስርዐትን የተመለከቱ ርዕሰ ጉዳዮች ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር በተጋበዙ ከፍተኛ ባለሙያዎችና የስራ ኃላፊዎች ገለጻ ተደርጓል፡፡ በተመሳሳይ መልኩም በኦዲት ምንነትና ግልጽነትና ተጠያቂነትን በማስፈን ረገድ የምክር ቤቱን ሚና፣ ዋና ዋና የኦዲት ግኝቶችና የሚሰጡ የማሻሻያ ሀሳቦችን፣ በኦዲት ዙርያ የሚታዩ ችግሮችንና የመፍትሄ ሀሳቦችን እንዲሁም በኦዲት ዙርያ እየተሰራባቸው ያሉ አለም አቀፍ የህግ ማዕቀፎችን የተመለከቱ ገለጻዎች በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የስራ ኃላፊዎች ተደርገዋል፡፡ በገለጻዎቹ ላይም ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡

በመድረኩ ላይ የኦዲት ዘርፍ ምክትል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ የመንግስት የፋይናንስ መመሪያዎች የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ለሚያካሂዳቸው ኦዲቶች መሰረት በመሆናቸው የምክር ቤት አባላት በመመሪያዎቹ ላይ ያላቸው ግንዛቤ ማደጉ የክትትልና የቁጥጥር ስራቸውን በበለጠ ለመስራት እንደሚያስችላቸው ገልጸው ሁሉም ባለድርሻ አካላት ከፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ጋር ያላቸውን ግንኙነት በማጠናከር ወደ ተሻለ ውጤት መድረስ እንደሚቻል አስገንዝበዋል፡፡

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ት ወይንሸት ገለሶ በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ግኝቶች ላይ ተመስርቶ ውጤታማ እርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው ለዚህም በመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኩል ኦዲቱን መሰረት በማደረግ እየተሰራ ካለው የክትትል፣ የቁጥጥርና የድጋፍ ስራ ባለፈ በዋናነት አስፈጻሚ አካላትን በቅርበት እያገኙ ወቅታዊ ግምገማና ክትትል ማድረግ የሚችሉት ሌሎቹ ቋሚ ኮሚቴዎች በመሆናቸው በዚህ በኩል የየራሳቸውን ኃላፊነት በይበልጥ ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበው ለዚህም የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

በመድረኩ ላይ በምክር ቤቱ የሚገኙ የተለያዩ የቋሚ ኮሚቴዎች ሰብሳቢዎችና ምክትል ሰብሳቢዎች፣ የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት እንዲሁም ከባለድርሻ አካላት የተወጣጡ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *