በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤትና በሶማሊያ ሪፐብሊክ ዋና ኦዲተር መ/ቤት መካከል የልምድ ልውውጥ ነሐሴ 04 ቀን 2009 ዓ.ም. ተካሄደ፡፡
በኢንቶሳይ ዲቨሎፕመንት ኢኒሼቲቭ (INTOSAI Development Initiative /IDI) ድጋፍ ስትራቴጂክ እቅዱን ለማዘጋጀት ወደ አዲስ አበባ ከተማ የመጣው የሶማሊያ መንግስት የዋና ኦዲተር መ/ቤት የልዑካን ቡድን በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በመገኘት ልምድ ቀስሟል፡፡
በመድረኩ ላይ የዋና ኦዲተሩ ልዩ ረዳት አቶ ሻሾ መኮንን የሶማሊያ የዋና ኦዲተር መ/ቤት የስራ ኃላፊዎች መ/ቤቱን በመጎብኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጻው ለልዑካን ቡድኑና ለኢንቶሳይ ዲቨሎፕመንት ኢኒሼቲቭ የስራ ኃላፊዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላፈዋል፡፡
በወቅቱ አቶ ሻሾ የመ/ቤቱ የኦዲት ሽፋን ስለደረሰበት የእድገት ደረጃ፣ ስለ ተቋማዊ ነጻነቱ፣ የኦዲት ስራውን ለማሳደግ እየተሰሩ ስላሉ ስራዎች፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር ስላለው ግንኙነት፣ ተቋሙ ስላሉበት ተግዳሮቶች፣ በቀጣይ ትኩረት ስለተሰጣቸው ተግባራት እንዲሁም የትግበራ ጊዜው በተጠናቀቀውና አሁን እየተተገበረ ባለው ስትራቴጂክ እቅዶች ስለተገኙ ውጤቶች ብሎም አሁን እየተተገበረ ያለው ስትራቴጂክ እቅድ ስለተዘጋጀበት ሂደት በዝርዝር አስረድተዋል፡፡ በተጨማሪም የሶማሊያ የዋና ኦዲተር መ/ቤት የኦዲት ስራ እንዲጠናከር ለማድረግ የሚያስችሉ ሀሳቦችን አቶ ሻሾ ያቀረቡ ሲሆን ከመድረኩ ለተነሱ በርካታ ጥያቄዎችም ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
የልዑካን ቡድኑ አባላት የተደረገላቸው ገለጻ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት አሰራርን እንዲያውቁ እንዳስቻላቸው ገልጻው ለተደረገላቸው ገለጻና መስተንግዶ በልዑካን ቡድኑ መሪ በሚስተር ሙሐመድ አብዲ የሶማሊያ ዋና ኦዲተር መ/ቤት የእቅድ ዝግጅት ዳይሬክተር በኩል ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በመድረኩ ላይ ስድስት የሶማሊያ ዋና ኦዲተር መ/ቤት የስራ ኃላፊዎችና ሁለት የኢንቶሳይ ዲቨሎፕመንት ኢኒሼቲቭ ተወካዮች ተካፍለዋል፡፡