News

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ሠራተኞች የችግኝ ተከላ አካሄዱ

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የበላይ አመራሮችና ሠራተኞች በተቋሙ ግቢ ውስጥ ነሐሴ 2፣ 2009 ዓ.ም የችግኝ ተከላ አካሄዱ፡፡

በችግኝ ተከላው ስነ-ስርዓት ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ እንደገለፁት ከዚህ ቀደም የመ/ቤቱ ሠራተኞች በተለያዩ ስፍራዎች በመሄድ የችግኝ ተከላ ማከናወናቸውን ነገር ግን ችግኞቹ እንክብካቤ ሊደረግላቻው ባለመቻሉ አለመፅደቃቸውን ገልፀው በዚህ ዓመት በተቋሙ ጊቢ ውስጥ መትከል መወሰኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህ ፕሮግራም ችግኝ የተከሉ ሠራተኞች ችግኞችን በመንከባከብ በሙሉ መፅደቃቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባቸው ክቡር ዋና ኦዲተሩ አሳስበው እሳቸውም የተከሉትን ችግኝ በመንከባከብ የራሳቸውን ኃላፊነት እነደሚወጡ ገልፀው በቀጣይ ለሚካሄዱ የችግኝ ተከላ ፕሮግራሞች ይህንን እንደሞዴል በመጠቀም የሚሰፋ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ክቡር ዋና ኦዲተር አክለውም በመ/ቤቱ ግቢ ውስጥ ችግኝ ተከላ መካሄዱ ምቹና ነፋሻማ የሥራ አከባቢን እንደሚፈጥር ገልፀው ከዚህም ባለፈ ሠራተኛው በራስ ተነሳሽነት በቢሮ ውስጥ አበቦችን በመትከልና በመንከባከብ ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የሰው ሃብት ሥራ አመራር ዳይሬክተር አቶ አሸናፊ ጌታቸው እንደገለፁት በግቢ ውስጥ ከተተከሉት ችግኞች በተጨማሪ የቢሮ አካባቢን ምቹ ለማድረግ ያስችል ዘንድ በቀጣይ የአበባ ማስቀመጫ እቃዎች፣ ለቢሮ ተስማሚ የሆኑ አበቦችና አትክልቶች እንደሚገዙ እና ጥቅም ላይ እንደሚውሉ ገልፀው ሠራተኞች የሚተከሉትን ችግኞች በመንከባከብ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

የተቋሙ ሰራተኞችም በቅጥር ግቢው ውስጥ የችግኝ ተካላ መደረጉ አረንጓዴ የሆነ የሥራ አከባቢ የሚፈጥር ከመሆኑም ባሻገር በየዕለቱ ችግኞቹን ለመንከባከብና ለማሳደግ አመቺ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በችግኝ ተከላው ከክቡር ዋና ኦዲተሩ በተጨማሪ የኦዲት ዘርፍና የድጋፍ ዘርፍ ምክትል ዋና ኦዲተሮች እንዲሁም የተለያዩ ሥራ ክፍል ዳይሬክተሮችና ሠራተኞች ተሳትፈዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *