የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የ2008/09 የኦዲት ዘመን የ10 ወራት የኦዲት ዘርፍ የዕቅድ አፈጻጻምን እና የ2009 በጀት አመት የ6 ወራት የድጋፍ ዘርፍ የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርትን ለኢ.ፌ.ዴ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሚያዚያ 18 ቀን 2009 ዓ.ም አቀረበ፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርቱን ለቋሚ ኮሚቴው ያቀረቡ ሲሆን በ2008/09 በጀት ዓመት በኦዲትና በድጋፍ ዘርፍ ታቅደው የተፈፀሙና ያልተፈፀሙ እንዲሁም በሂደት ላይ ያሉ ጉዳዮችን አብራርተዋል፡፡
የዋና ኦዲተሩን ሪፖርት ተከትሎ የመንግስት ወጪ አስተዳደር ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ተጨማሪ ማብራሪያ በሚፈልጉ ጉዳዮች ላይ ጥያቄዎችን አቅርበዋል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው በድጋፍ ዘርፍና በኦዲት ዘርፍ ከፍሎ ባቀረበው ጥያቄ መ/ቤቱ የውጤት ተኮር የምዘና ሥርዓትን ከመተግበርና ጥቅም ላይ ከማዋል አኳያ የሄደበትን ርቀት፤ የጥልቅ ተሃድሶው ውይይት ውጤታማ ስለመሆኑና ለቀጣይ ተግባር ሰራተኛውን ከማዘጋጀት አንፃር ስላበረከተው አስተዋፅኦ፤ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ከመፍታት አኳያ ስለተሰሩ ሥራዎች፤ በመ/ቤቱ የስነ-ምግባር መኮንን ምደባ አድርጎ የስነ-ምግባር ጉድለቶችን ከመፍታት አኳያ ስለተሰሩ ሥራዎች፤ ያልተጠናቀቁ የኦዲት ሪፖርቶች ስለደረሱበት ደረጃ፤ መ/ቤቱ በኦዲት ሰርቪስ ኮርፖሬሽንና በግል የኦዲት ድርጅቶች ኦዲት ለማስደረግ ያቀዳቸው የ6 መ/ቤቶች ኦዲት በዕቅዱ መሠረት በአግባቡ ክትትል ስለመደረጉ፤ ለክልል መንግስታት የሚሰጠው ድጋፍና ድጎማ ሒሳብ ኦዲት ስለሚገኝበት ደረጃ እና በኦዲት ጥራትና ኢንስፔክሽን ሥራ ባለፉት 10 ወራት ስለተፈጸሙ ተግባራት እንዲብራራ ጠይቋል፡፡
ክቡር ዋና ኦዲተር ለተነሱት ጥያቄዎች ማብራሪያ ሲሰጡ የውጤት ተኮር የምዘና ሥርዓትን ከመተግበርና ጥቅም ላይ ከማዋል አኳያ ከመጋቢት 1 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ ወደትግበራ ለመግባት ታቅዶ የነበረ ቢሆንም አዲስ አሰራርን ተቀብሎ ለመተግበር ባለው ተግዳሮትና በኦዲት ዘርፉ ከነበረው የሰው ሀይል አለመሟላት አንጻር ተፈፃሚ ለማድረግ አስቸጋሪ እንደነበር ገልፀው አሁን የነበረው ችግር በተወሰነ በመቀረፉ በሁለቱም ዘርፎች ዕቅዱ ተዘጋጅቶ ወደትግበራ መገባቱን ገልፀዋል፡፡
የጥልቅ ተሃድሶ ውይይትን በተመለከተም በሰጡት ምላሽ የጥልቅ ተሃድሶው ከእቅድ ዝግጅት ጊዜ አንድ ሳምንት አስቀድሞ መከናወኑን አስታውሰው ይህ ለዕቅድ ዘግጅቱ ጥሩ አጋጣሚ መፍጠሩን እንዲሁም በተሃድሶው የአቅም ክፍተትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ጎልተው መውጣታቸውን ተናገረዋል፡፡ የአቅም ክፍተትን ለመሙላት በአዲሱ አዋጅ መሠረት በመ/ቤቱ የስልጠና ተቋም ለመገንባት ከእንግሊዝ መንግስት በተገኘ 2.3 ሚሊዮን ዶላር ለስልጠና የሚሆኑ መሣሪያዎች ግዢ እየተፈፀመ እንዳለና ለስልጠና የሚሆን የማሰልጠኛ ሞጁል ዝግጅት እየተጠናቀቀ እንደሚገኝ ገልፀው ይህ በሚጠናቀቅበት ጊዜ በቋሚነት ያለውን የክህሎት ችግር መቅረፍ እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡ ከመልካም አስተዳደር አኳያም በተቋሙ 24 ችግሮች አስቀድመው ተለይተው እየተሠራባቸው እንደነበር አውስተው ነገር ግን አንዳንዶቹ አሁንም ድረስ መፍትሔ ባለማግኘታቸው እንደችግር መነሳታቸው ገልፀው ከተነሱት ችግሮች ውስጥ ከንብረት አያያዝና ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ለነበሩ ችግሮች መፍትሔ እንደተሰጠባቸው እና ከውስጥ ኮሙዩኒኬሽን ደካማ መሆን የተነሳ ችግር ሆነው ለተነሱ ጥያቄዎች የውስጥ ኮሚዩኒኬሽን ባህልን ማዳበር እንደሚገባ ታምኖበት ወደሥራ መገባቱን አስረድተዋል፡፡
በመ/ቤቱ የስነ-ምግባር መኮንን ምደባ አድርጎ የስነ-ምግባር ጉድለቶችን ከመፍታት አኳያ ለተነሳው ጥያቄም ምደባው እስካሁን ሳይካሔድ መቆየቱንና ለዚህም ዋናው ምክንያት በወቅቱ ከነበረው አነስተኛ የሰው ኃይል ምክንያት ለመመደብ ተቸግረው እንደቆዩ ገልፀው በአሁኑ ጊዜ የሰው ኃይል በተወሰነ ደረጃ የተሟላ በመሆኑና ስነ-ምግባር መኮንን መኖሩ ብዙ ችግሮችን በመቅረፍ ረገድ የጎላ ሚና ስለሚኖረው ምደባውን እንደሚያከናውኑ ዋና ኦዲተሩ ገልፀዋል፡፡
በአቅድ አፈፃፀም ረገድ በክዋኔ ኦዲትም ሆነ በፋይኔሺያልና ህጋዊነት ኦዲት መዘግየት የታየባቸው የ7 የክዋኔ ኦዲቶችና የ4 የክትትል ኦዲት ሪፖርቶች በሙሉ በአሁኑ ጊዜ ተጠናቀው ማለቃቸውን፤ መ/ቤቱ በኦዲት ሰርቪስ ኮርፖሬሽንና በግል የኦዲት ድርጅቶች ኦዲት ለማስደረግ ያቀዳቸው የ6ቱ መ/ቤቶች ላይም ክትትል እየተደረገባቸው እንደሚገኝና የሥራ ኃላፊዎቻቸውን በመጥራት ጭምር ውይይት መደረጉን ገልፀዋል፡፡
የኦዲት ጥራት ጋር በተያያዘ ለተነሳው ጥያቄም ምላሽ ሲሰጡ የፌዋኦ መ/ቤት የሚያወጣው የኦዲት ሪፖርት እውነትን መሠረት ያደረጉና እያንዳንዱ ግኝትም በማስረጃ የተደገፉ ካልሆኑ ግኝት ተደርገው እንደማይወጡ ገልፀው ነገር ግን አሁን ያለንበትን የኦዲት ጥራት እናሳድጋለን ስንል ኦዲቱ የሚሸፍነው ሽፋንና ጥልቀት መጠን ሲታይ የሚቀር ነገር መኖሩን ለማሳየት እንደሆነ ክቡር አቶ ገመቹ አስረድተዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴ አባላት በተጨማሪ ላነሷቸው ጥያቄዎች ዋና ኦዲተሩ ምላሽ የሰጡ ሲሆን ኦዲተሩ ሰርቶ ባመጣው ግኝት እውነታንና ማስረጃን ይዞ እስካቀረበ ጊዜ ድረስ የትኛውም የሥራ ኃላፊ ግኝቱን የማስቀየር ወይም እንዲወጣ የማድረግ ሥልጣን እንደሌለውና በግኝት እንዲካተት ወይም እንዳይካተት የሚወስነው ኦዲተሩ ራሱ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ከኦዲት ግኝት በኋላ የሚደረገው ክትትልና ድጋፍ በተመለከተ ለተነሳውም ጥያቄ በተሻለ ሁኔታ እየተጠናከረ መምጣቱን ገልፀው ነገር ግን በኦዲት ግኝቱ መሠረት ይመለሱ የተባሉ የህዝብ ሃብቶች ማስመለስ ላይ ብዙ ለውጥ አለመታየቱን እንዲሁም ህግን ጠብቀው ከመስራት አኳያም ተደጋግሞ ተገልፆላቸው አሁንም ድረስ ህግን እየጣሱ የሚሠሩ መኖራቸውን ገልፀዋል፡፡
በመጨረሻም ቋሚ ኮሚቴው አስተያየትና ትኩረት ሊሠጥባቸው ይገባሉ ባለቸው ጉዳዮች ላይ ሃሳብ የሰጡ ሲሆን መ/ቤቱ እየሠራ ያለው ሥራ የሚያስመሰግነውና በህበረተሰቡም ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትን እያስገኘለት እንደሚገኝ፤ በእቅድ አፈፃፀም ረገድ ከፍተኛ መሻሻል መታየቱንና በኦዲት ተደራጊ ተቋማት በኩልም የኦዲት ግኝቱን ለሥራቸው ውጤታማነት እንደ አንድ አጋዥ ግብዓት እየጠቀሙባቸው መሆኑን መግለፃቸውን፤ በሰው ኃይል ማሟላትና የአቅም ክፍተትን ለመሙላት እየተሰራ ያለው ሥራ ሊበረታታ እንደሚገባው፤ ከመረጃ አስተዳደርና ቴክኖሌጂ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ የወረቀት አልባ ቢሮ ለመፍጠር የተጀመረው ሥራ ሊበረታታ የሚገባውና ለሌሎች ተቋማትም ተሞክሮ ሊሆን የሚገባው መሆኑን እና ግዢ በእቅድ እና በግዥ አፅዳቂ የሚመራ መሆኑ በአርያነት የሚታይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ሊሻሻሉ ይገባሉ ባሉዋቸው ጉዳዮች ላይም ቋሚ ኮሚቴው አስተያየትና ሃሳብ የሰጠ ሲሆን የመውጫ ስብሳባ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ችግሮችን ከመፍታት አንፃር በቂ ጊዜ በመስጠት መግባባት መፍጠር እንደሚገባ፤ የለውጥ ሥራ ትግበራም በሚፈለገው ልክ ተግባራዊ ባለመሆኑ ትኩረት ተሰጥቶ ሊተገበርና በውጤት ተኮር ምዘና ስርዓት ሰራተኛው ሊመዘን እንደሚገባ፤ በኦዲት ግኝቱ መሠረት ተፈፃሚ ስለመሆናቸው የመከታተልና የመቆጣጠር ሂደቱ ተጠናክሮ ሊሠራ እንደሚገባ፤ የሰው ሃብት ማጠናከር ላይ አሁንም በቅጥር ያልተሟሉ የሥራ መደቦች ያሉ በመሆኑ በበለጠ ተጠናክሮ ሊሠራበት እንደሚገባ፤ ከአገር ውጪ የሚሠጡ ሥልጠናዎች የተቋሙን ሠራተኞች በክህሎት ብቁ ከማድረግ አኳያ ጉልህ አስተዋፅኦ የሚኖረው በመሆኑ ታቅዶበት ሊተገበር እንደሚገባ እና በመልካም አስተዳደር የተለዩ ችግሮች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራባቸው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡