News

ሚኒስቴር መ/ቤቱ የሰራተኞችን የሙያ ደህንነትና ጤንነትን የተመለከቱ ህጎች መተግበራቸውን ለማረጋገጥ የበለጠ መስራት እንደሚገባው ተገለጸ

የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሰራተኞችን የሙያ ደህንነትና ጤንነትን የተመለከቱ ህጎች መተግበራቸውን ለማረጋገጥ የበለጠ መስራት እንደሚገባውና ሀገሪቱ ወደ ኢንደስትሪ መር ኢኮኖሚ የምታደርገውን ሽግግር ታሳቢ ባደረገ መልኩ መንቀሳቀስ እንዳለበት የኢፌ.ዴ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው የሰራተኞች የሙያ ደህንነትና ጤንነትን አስመልክቶ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ላይ ባካሄደው የ2007 በጀት አመት የክዋኔ ኦዲት ግኝት ላይ ይፋዊ ስብሰባ ሚያዝያ 04 ቀን 2009 ዓ.ም አድርጓል፡፡

በስብሰባው ወቅት ኦዲቱ በሰራተኞች የሙያ ደህንነትና ጤንነት ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን ለመከላከል የወጡ ህጎች እንዲተገበሩ በመከታተልና በመቆጣጠር፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ በመስራት፣ በስራ ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን የተመለከተ መረጃ በማሰባሰብና በማደራጀት እንዲሁም አደጋዎች ሲከሰቱ መልሶ የማቋቋሚያ ስርዐት በመዘርጋት ረገድ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ድክመት አሳይቷል ያላቸውን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴው በዝርዝር አቅርቧል፡፡

በዚህም በናሙና በተወሰዱ ድርጅቶች ላይ በተደረገው ኦዲት መ/ቤቱ ቁጥጥር በሚያደርግባቸው አንዳንድ ድርጅቶች ውስጥ የሙያ ደህንነትና ጤንነት ኮሚቴ አለመቋቋሙ፣ የአደጋ መከላከያ ቁሳቁሶችና ልብሶች አለመቅረባቸው፣ አደጋን ለመከላከል የሚረዱ የማስጠንቀቂያና የማስተማሪያ ማስታወቂያዎች አለመለጠፋቸው፣ አዳዲስ መሳሪያዎች ሲተከሉ በጤና ላይ ጉዳት እንደማያደርሱ በሚኒስቴር መ/ቤቱም ሆነ በክልል የዘርፉ መ/ቤቶች ቁጥጥር አለመካሄዱ፣ በድርጅቶች ውስጥ የሚገኙ ጥሬ እቃዎችና ምርቶች ሰራተኞችን እንደማይጎዱ ምርመራ አለመደረጉ እንዲሁም አሰሪዎች በሰራተኛ ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችንና በሽታዎችን ለሚኒስቴሩም ሆነ ለክልል የዘርፉ መ/ቤቶች ሪፖርት አለማድረጋቸው ታይቷል፡፡

በተጨማሪም መ/ቤቱ በስራ ምክንያት የሚመጡ በሽታዎችን ዝርዝር ማዘጋጀት፣ ማሰራጨትና ወቅቱን ጠብቆ ማሻሻል ሲገባው አለማድረጉ፣ ጉዳትን ለመከላከል የሚረዳ በተግባር የተደገፈ ስልጠና በሚኒስቴር መ/ቤቱም ሆነ በክልል የዘርፉ መ/ቤቶች ባለመሰጠቱ ምክንያት አደጋዎች እየጨመሩ መምጣታቸው፤ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የሙያ ደህንነትና ጤንነትን ለማሻሻል የሚረዳ ጥናትና ምርምር አለማድረጉ፣ በሚመለከታቸው አካላት መሀከል አስፈላጊ የሆኑ የሁለትዮሽና የሶስትዮሽ ግንኙነቶች እንዲፈጠሩ በማድረግ በሰራተኞች ጤና ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ስለመስራቱ መረጃ አለመገኘቱ በኦዲቱ ተገልጿል፡፡

ከዚህም ሌላ የሰራተኞች የሙያ ደህንነትና ጤንነትን የተመለከቱ ህጎች በአግባቡ መተግበራቸውን የሚከታተልበትና ግብረመልስ የሚሰጥበት ስርአት አለመዘርጋቱ፣ ለክትትልና ቁጥጥር የሚረዱ የሙያ ደህንነትና ጤንነት መለኪያና መቆጣጠሪያ መሳሪያዎችን ባለመጠቀሙ ነባርና አዲስ መሳሪያዎች በሰራተኞች ላይ ከፍተኛ አደጋ እያስከተሉ መሆኑ፣ ከፍተኛ ወጪ ወጥቶባቸው የሚገቡ የክትትልና የቁጥጥር መሳሪያዎች በቂ ስልጠና ተሰጥቶባቸው ወደ ስራ ባለመግባታቸው ሰራተኞች ላይ የሚደርሰውን አደጋ ለመቆጣጠርና ለመቀነስ አለመቻሉ እንዲሁም በስራ አካባቢ የደረሱ ከባድ አደጋዎቸ ያደረሱትን ሰብዐዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውሶች ለመገምገምና ተመሳሳይ አደጋዎች እንዳይደርሱ ለማድረግ የሚያስችል የአደጋ ምርመራ የሚያካሂድበትን የአሰራር ስርዐት ተግባራዊ አለማድረጉ በኦዲቱ ታይቷል፡፡

እንደዚሁም የሙያ ዘርፍን ያገናዘበ የሙያ ደህንነትና ጤንነት መመዘኛ አዘጋጅቶ ለድርጅቶች አለማሰራጨቱ፣ አገር አቀፍ የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይን እንዲሁም የተከሰቱ አደጋዎችንና ክስተቶችን መረጃ የሚይዝበት የመረጃ አያያዝ ስርዐት ወይም የመረጃ ቋት አለማዘጋጀቱ ብሎም የሙያ ደህንነትና ጤንነትን በተመለከተ ከደንበኞች የሚቀርቡ ቅሬታዎች የሚስተናገዱበትና መረጃዎቹም ተጠናቅረው የሚያዙበት አሰራር አለመዘርጋቱ በኦዲቱ ተጠቅሷል፡፡

በነዚህ የኦዲት ግኝቶች ላይ ሚኒስትሩ አቶ አብዱልፈታህ አብዱላሂና ሌሎች የመስሪያ ቤቱ የስራ ኃላፊዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ሚኒስትሩ ኦዲቱ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት የሚያስችሉ ክፍተቶችን ማሳየቱንና ይህም ለስራቸው እንደ ትልቅ ግብዐት የሚቆጠር እንደሆነ ገልጸው በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ሰፊ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ክቡር አቶ አብዱልፈታህ ከኦዲቱ በኋላ የማስተካከያ የድርጊት መርሀግብር ተዘጋጅቶ ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም ከማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ጋር ውይይት እንደተደረገበትና ክልሎች በ2009 በጀት አመት እቅዳቸው ውስጥ እንዳካተቱት ገልጸዋል፡፡

ከኦዲቱ በሁዋላ የተሰሩ ስራዎችን አስመልክተው ሲናገሩም 4313 ድርጅቶች ላይ የስራ ሁኔታ ቁጥጥር በማካሄድ የሙያ ደህንነትና ጤንነት ተከታታይ ኮሚቴዎች እንዲቋቋሙ መደረጉንና የአደጋ መከላከያ መሳሪያዎችና አልባሳት አሰጣጥና አጠቃቀምን እንዲሁም ለጥንቃቄ የሚረዱ ምልክቶች መኖራቸውን የማረጋጥ ስራ መሰራቱን አስረድተዋል፡፡ በመመሪያ ረገድም የሙያ ደህንነትና ጤንነት የቴክኒክ ድጋፍ አሰጠጥ መመሪያ ለሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች መሰራጨቱንና በመመሪያው መሰረት ድጋፍ እየሰጡ መሆናቸው መረጋገጡን ተናግረዋል፡፡

ድርጅቶች ሲቋቋሙ፣ ሲስፋፉና አዳዲስ መሳሪያዎች ሲተከሉ በሰራተኞች ደህንትና ጤንነት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እና ከኢትዮጵያ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ኮሚሽን ጋር ስምምነት መፈራረሙን ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡ ለሰራተኞች ደህንነት አደጋ ናቸው የሚባሉ ንጥረ ነገሮችን፣ ጥሬ እቃዎችንና ምርቶችንም ችግሩ ሲከሰት ናሙና በመውሰድ የመመርመር ስራ እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በስራ አካባቢ ደህንነትና ጤንነት ላይ ለሚሰሩ የክልልና የከተማ አስተዳደር ሰራተኞች የአቅም ግንባታ ሙያዊ ስልጠና መሰጠቱን፣ ድጋፍ ለሚሹ ክልሎች በሙያ ደህንትና ጤንንት ዙርያ የቴክኒክ ድጋፍ መሰጠቱን፣ የክልሎችን ፍላጎት በድጋፋዊ የክትትልና ሱፐርቪዥን ጉበኝት በመለየት ድጋፍ የሚሰጥበት ሁኔታ መመቻቸቱን ጨምረው ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡

ብሔራዊ የሙያ ደህንነትና ጤንነት ፖሊሲን መሰረት በማድረግ የተጠናከረ የትብብርና ቅንጅት ስርዐትን ለመዘርጋት ከኮንስትራክሽን ሚኒስቴር እና ከአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት ሊሰሩ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ የመግባቢያ ሰነድ ተዘጋጅቶ እየዳበረ እንደሚገኝም ክቡር አቶ አብዱልፈታህ ተናግረዋል፡፡

መረጃን በማሰባበብና በማደራጀት በኩልም የ2007 ሀገራዊ የስራ ላይ አደጋዎችና የጤና ጉዳቶች ስታትስቲካል መጽሄት ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የሰራተኛና ማህበራዊ _DSC0075 improvedጉዳይ መ/ቤቶች መረጃ ተሰብስቦ መዘጋጀቱን የ2008 መረጃም እየተጠናቀረ መሆኑን፣ በሀገር አቀፍ ካላው የድርጅቶች ቁጥር አንጻር አነስተኛ ቢሆንም 279 ድርጅቶች የስራ ላይ አደጋዎችን ሪፖርት ማድረጋቸውንና የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አስተዳደር የመረጃ ስርዐት ማቋቋም በሂደት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የተከሰቱ ከባድ የስራ ላይ አደጋዎችን በመመርመር ክስተቱ እንዳይደገም ተሞክሮ የመውሰድና ብሔራዊ የስራ ላይ አደጋ ምርመራ ጋይድላይን የማዘጋጀት ስራ መሰራቱን፣ የሙያ ደህንትና ጤንትን በተመለከተ የወጡ ህጎች ተግባራዊ ስለመደረጋቸው ለማረጋገጥ የክትትልና ቁጥጥር ማገናዘቢያ (checklist) ተዘጋጅቶ ለክልሎች የማስተዋወቅ ስራ እየተሰራ መሆኑን፣ የሙያ ደህንትና ጤንነት ጠንቆች መለኪያ መሳሪያዎች ግዥ ለመፈጸም ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ፣ በ2009 በጀት አመት 6 ወራት የቀረቡ የሙያ ደህንነትና ጤንነት እንዲሁም መሰረታዊ የስራ ሁኔታዎችን የተመለከቱ 906 አቤቱታዎችን የማጣራትና የእርምት መመሪያ መሰጠት ስራ መሰራቱን እንዲሁም የተለያዩ አግባብነት ያላቸው የኤሌክትሮኒክስና የህትመት ውጤቶች ተዘጋጅተው ለክልሎች መላካቸውን ገልጸዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ከ2007 በፊት በዘርፉ ያለውን የሰለጠነ የሰው ሀይል ችግር ለመፍታት በሙያ ደህንትና ጤንነት የሁለተኛ ዲግሪ መርሀግብር በጎንደር ዩኒቨርስቲ እንዲጀመር መደረጉንና ይህ ግን ያለውን ፍላጎት ሊያሟላ የማይችል በመሆኑ በመጀመሪያ ዲግሪ ደረጃ ተማሪዎች እንዲመረቁ ለማድረግ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲና ከሌሎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር ለመስራት ጥረት እየተደረገ እንዳለ አስረድተዋል፡፡

ሌሎች የመቤቱ ኃላፊዎችም በተጨማሪነት በኦዲት ግኝቱ የታዩ ክፍተቶችን ስርዐት በማበጀት ለመፍታት ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን፣ ኮንስትራክሽን ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰበት ያለበት ዘርፍ በመሆኑ ቅድሚያ በመስጠት የኮንስትራክሽን ዘርፍ የሙያ ደህንነትና ጤንነት ፖሊሲ ተዘጋጅቶ በሀገሪቱ ላሉት አንደኛ ደረጃ ስራ ተቋራጮችና በብዛት የሰው ሀይል ለሚቀጥሩ ድርጅቶች ፖሊሲው መተዋወቁን፣ የህንጻ ተቋራጮች ማህበርም ፖሊሲውን ወደ ፕሮጀክት ቀይሮ እንዲተገብረው የተሰራ መሆኑንና ለዚህም  የመግባቢያ ሰነድ መዘጋጀቱን፣ በግብርና ዘርፍ የሙያ ደህንትና ጤንነት ፖሊሲ እየተዘጋጀ መሆኑን እንዲሁም የስራ አካባቢ ደህንነት መመሪያ እየተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከዚህም ሌላ ከኦዲት በኋላ የተሰሩትን ስራዎች ለፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት አለመላኩ ስህተት መሆኑን፣ የቴክኒካል ፍተሻ በውጭ አካላት እንዲሰራ መደረግ መጀመሩን፣ በናሙና በታዩት 11 ድርጅቶች ውስጥ የአደጋ መከላከያ አልባሳትና መሳሪያዎችን ባላቀረቡት 8 ድርጅቶች ላይ በስራ ሁኔታ ተቆጣጣሪ ባለሙያ ክትትል በማድረግ ከስራ ሁኔታቸው አኳያ ማሟላታቸው እንዲረጋገጥ መደረጉን፣ ኮንቬንሽን 81 የሚባለው የስራ ቁጥጥር ኮንቬንሽን ከሀገራችን ህጎች ጋር ስለመጣጣሙና ለሀገራችን ስለሚሰጠው ጥቅም ጥናት ለማድረግ ከአለም የስራ ድርጅት ጋር እየተወያዩበት መሆኑን እንዲሁም ከመብራት ሀይል ጋር ተያይዞ ከመላው ሀገሪቱ ክፍሎች ለተወጣጡ ለስራ ሁኔታ ተቆጣጣሪዎች ስልጠና መሰጠቱን አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም የስራ ደረጃዎችን ለክልሎች ለመላክ የህትመት ስራ እየተሰራ መሆኑን፣ የመረጃ ቋት ለማዘጋጀት መረጃዎችን የማሰባሰብ፣ የመለየትና የማደራጀት ስራ በጀት ተመድቦለት እየተሰራ መሆኑን፣ የስራ የአደጋና በሽታዎችን ዝርዝር በተመለከተ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ጥናት እየተደረገ እንደሚገኝ፣ ከኦዲቱ ቀደም ብሎ ከአበባ አምራቾችና ላኪዎች ማህበር፣ ከኢትዮጵያ አሰሪዎች ፌዴሬሽንና ከኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ጋር የሶስትዮሽ ግንኙነት አሰራር ተዘርግቶ እየተሰራ መሆኑን እንዲሁም ከአካባቢ ጥበቃ ጋርም ተያይዞ ማንኛውም አሰራርና አገልግሎት ከብክለትና ከብክነት የጸዳ እንዲሆን እየተሰራ መሆኑንና ከአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ጋር የመግባቢያ ሰነድ ለመፈራረም በሂደት ላይ እንደሆነ የስራ ኃላፊዎቹ ገልጸዋል፡፡

እንደዚሁም ለጊዜያዊና ለኮንትራት ሰራተኞች ጭምር የአደጋ መከላከያ መሳሪያዎች እንዲቀርቡ እየተሰራ እንዳለ፣ በህንጻ ግንባታ ወቅት ጥቅም ላይ የሚውለው የእንጨት ርብራብ እንዲቀርና የህንጻ ተቋራጮች በብረት ርብራብ እንዲጠቀሙ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሰራ እንደሚገኝ እንዲሁም በኮንስትራክሽንና ሌሎች ዘርፎች ያሉትን ሁኔታዎች የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲና የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎች እንዲያጠኑ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የስራ ኃላፊዎቹ በቋሚ ኮሚቴ አባላት ተጨማሪ ጥያቄ በቀረበባቸው ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴውና የማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በሰጡት አስተያየት የውጭም ሆነ ሀገር ውስጥ ባለሀብቶች እንቨስት ሲያደርጉ የሰራተኛውን ደህንነት እንዲጠብቁ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ መስራት እንደሚያስፈልግ፣ አገልግሎት የሰጡና አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉ የኢንዱስትሪ ማሽኖች ወደ ሀገራችን እየገቡ ስለሚገኙ በዚህ ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መስራት እንደሚገባ፣ ሰራተኛው ደህንነቱን ለመጠበቅ የሚሰጡትን ልብሶችና ቁሳቁሶች በአግባቡ የማይጠቀምበት ሁኔታ በመኖሩ ይህንን ለመለወጥ የሚያስችል የግንዛቤ ማሳደግ ስራ ሰራተኛው ላይ መስራት እንደሚገባና አሁን እርምጃ ተወስዶባቸው የተስተካከሉ ጉዳዮች በሂደት እንዳያገረሹ ክትትል ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡

በተጨማሪም ሰራተኛው መብቱን በይበልጥ እንዲያስከብር በማህበር የሚደራጅበት ሁኔታ እንዲፈጠር ማድረግ እንደሚገባ፣ ከግብርና መር  ወደ ኢንደስትሪ መር ኢኮኖሚ በሚደረገው ሽግግር በሰራተኛው ላይ የሚፈጠር ጫና በመኖሩ ሰራተኛው የሙያ ደህንነቱና ጤንነቱ አለመጠበቁ የመልካም አስተዳደር እጦት መገለጫ እንደሆነ ተቆጥሮ ከፍተኛ የፖለቲካ ቀውስ ምንጭ ሊሆን የሚችል ጉዳይ መሆኑን አስፍቶ በማሰብ የኢትዮጵያ ሰራተኞችን ታሪካዊና ወቅታዊ ተግዳሮቶች የተገነዘበ አሰራር ማረጋገጥ እንደሚገባ እንዲሁም አዳዲስ ተቋማት ሲመሰረቱ ስለአደጋ መከላከያ መመሪያዎች፣ ስለሪፖርትና አላላክና ስለሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡

ምክትል የፌዴራል ዋና ኦዲተ_DSC0086 improvedር ክብርት ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ በበኩላቸው በናሙና በታዩትና የሰራተኛ ጉዳት በተከሰተባቸው 6 ድርጅቶች ላይ ጥናት ለማድረግ ኮሚቴ መቋቋሙ ጥሩ ቢሆንም በመላው ሀገሪቱ ባሉ ሌሎች ድርጅቶችም ተመሳሳይ ጉዳቶች ሊደርሱ የሚችሉ በመሆኑ በዚህ መነሻነት ኮሚቴው ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ዙርያ መለስ የማጣራትና የማጥናት ስራ ሊሰራ  እንደሚገባው እንዲሁም ጉዳት ከደረሰ በኋላ የሚሰጠው ድጋፍና እንክብካቤም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ በሰጡት አስተያየት ሚኒስቴር መቤቱ በዚህ ጉዳይ ላይ ኦዲት እንዲደረግለት መጠየቁ፣ በኦዲቱ ወቅትና ዘንድሮም እየተደረገበት ባለው ኦዲት ላይ ሙሉ ትብብር ማድረጉ እውቅና ሊሰጠው እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

ክቡር ዋና ኦዲተሩ የስራ ላይ ደህንነት ጉዳይ ካሁኑ በደንብ ካልተሰራበት ወደፊት ግዙፍ ጉዳይ ስለሚሆን ከፖሊሲና ከህግ ማዕቀፍ ጋር የተያያዙ ክፍተቶች ካሁኑ ተፈትሸው የቅድመ ጥንቃቄ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚያሻ፣ ደህንነቱና ጤንነቱ ላይ ጉዳት ስለሚያደርሱ ጉዳዮችና በአደጋ መከላከያ ቁሳቁሶችና አልባሳት ጥቅም ሰራተኛው ግንዛቤው እንዲያድግ ማድረግ ትኩረት የሚሻ መሆኑን፣ በድርጅቶች ውስጥ የሙያ ደህንነትና ጤንነት ኮሚቴዎች እንዲቋቋሙ ከማድረግ ባለፈ ውጤታማ ስራ መስራታቸውን ማረጋገጥና ካልሰሩም ሌሎች አማራጮችን መፈለግ እንደሚገባ፣ በኢንደስትሪዎች ውስጥ በርካታ አደጋዎች እየደረሱ በመሆኑ አደጋ የሚደርስባቸው የትኞቹ እንደሆኑ ለይቶ ማጥናት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

ከዚህም ሌላ የአደጋ መከላከያ አልባሳትና መሳሪያዎች መቅረባቸውንና ጥቅም ላይ መዋላቸውን መከታተል እንደሚገባ፣ በተቀመጠው መመሪያ መሰረት በማይሰሩ ድርጅቶች ላይ እርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ፣ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መግባቢያ ሰነድ መፈራረሙ ብቻ በቂ ባለመሆኑ ስምምቶቹ መፈጸማቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባ፣ አደጋ ከደረሰ በኋላ ናሙና ወስዶ ጥሬ እቃዎችንና ምርቶችን ከመመርመር ባለፈ አስቀድሞ መርዛማ ኬሚካሎችና ጎጂ ጥሬ እቃዎች ያሉበትን ሁኔታ በማጣራት አደጋን መከላከል እንደሚያስፈልግ፣ የአደጋ ሪፖርት መላክ የግዴታ እንደሆነ እንዲያውቁት ጅርጅቶችን ማስገንዘብ እንደሚያስፈልግና የማይልኩትም ተጠያቂ የሚሆኑበት ስርዐት መዘርጋት እንደሚገባ እንዲሁም ቅንጅታዊ ስራ ላይ ጠንክሮ መስራት እንደሚገባና ሰራተኛውንና ህዝቡን በቅሬታ አቀራረብ ላይ ማ_DSC0088 improvedስገንዘብ እንደሚያሻ ገልጸዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ክቡር አምባሳደር መስፍን ቸርነት በማጠቃለያ አስተያየታቸው ሚኒስቴር መ/ቤቱ ከኦዲቱ ለመማር፣ ችግሮቹን ለመፍታትና ኦዲት ለመደረግ ያሳየው ትልቅ ዝግጁነት፣ በኦዲትና በኦዲቱ የመውጫ ስብሰባ ያሳየው ትብብርና ቀና መንፈስ በመልካም ጎኑ እንደሚታዩና ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

ሆኖም ኦዲቱን ተከትሎ ስለተወሰዱ እርምጃዎች ለፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት አለማሳወቁ ትክክል ባለመሆኑ ማሳወቅ እንደሚያስፈልግ፣ ኢትዮጵያ የአለም የስራ ድርጅት አባል እንደመሆኗ የግሉን ዘርፍ ጨምሮ የሰራተኞችን የስራ ደህንነትና መረጃ ለመያዝና የመረጃ ቋት ለማቋቋም ትኩረት መስጠት እንደሚገባ፣ ከግብርና ወደ ኢንደስትሪ ኢኮኖሚ እየተሸጋገርን በመሆኑ ከለውጡ ጋር ተያይዘው ሊመጡ የሚችሉ የስራ ሁኔታ ደህንነት ጉዳዮችንና ሊሰሩ የሚገቡ ጉዳዮችን ለይቶና ቀድሞ አስቦ ፈጥኖ ማከናወን እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

ሰብሳቢው አክለውም የተደራጀ ጠንካራና መብቱን የሚያስከብር ሰራተኛ እንዲኖር በሰራተኞች መደራጀት ላይ ሊሰራ እንደሚገባ ይህም አንደኛው የተረጋጋ የኢንደስትሪ ሰላም መፍጠሪያ እንደሆነ፣ በኢንደስትሪዎች በመደበኛነት ከሚደረገው ቁጥጥር በተጨማሪ ድንገተኛ ጉብኝቶችን በኢንደስትሪዎች ላይ ማድረግ እንደሚያስፈልግ፣ ከድርጅቶችና ከሰራተኛው ጋር ትስስር መፍጠርና ሰራተኛው የመረጃ ምንጭ እንዲሆን ማደረግ እንደሚገባ እንዲሁም ከግብርና መር ወደ ኢንደሰትሪ መር ኢኮኖሚ በሚደረገው ሽግግር አንደኛው ተግዳሮት በሰራተኛና አሰሪ መሀከል የሚፈጠረው ትግል በመሆኑ ይህን ጉዳይ በህግ ማዕቀፍ ውስጥ በማስገባት በኩል ቀድሞ መሄድ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *