News

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሚታዩበትበን የአመለካከት ችግሮች ፈቶ ከቆየበት የፋይናንስና የንብረት አስተዳደር ችግር መውጣት እንዳለበት ተገለጸ

 የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከነባሩ አሰራር ላለመውጣት የሚታዩበትን የአመለካከት ችግሮች ፈቶ ከቆየበት የፋይንስና የንብረት አስተዳደር ችግር መውጣት እንዳለበት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡ ቋሚ ኮሚቴው በዩኒቨርስቲው ዋናው ግቢ፣ በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ፣ በአዲስ አበባ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት፣ በተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ፤  በአርክቴክቸር፣ ህንጻ ግንባታና ከተማ ልማት ኢንስትቲዩት እንዲሁም በጤና ሳይንስ ኮሌጅ  የ2007 በጀት አመት የሂሳብ ኦዲት ግኝት ላይ ይፋዊ ስብሰባ ሚያዝያ 02 ቀን 2009 ዓ.ም አድርጓል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በዩኒቨርስቲው የ2007 በጀት ዓመት ሒሳብ ላይ ባካሄደው የሂሳብ ኦዲት ዩኒቨርስቲው እጅግ በርካታ የፋይናንስና የንብረት አስተዳደር ችግሮች ያሉበት መሆኑን ማሳየቱን እንዲሁም ቋሚ ኮሚቴው ከከፍተኛ ትምህርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ጋር በመሆን በዩኒቨርስቲውና በተለያዩ ኮሌጆቹ ያደረገውን የመስክ ጉብኝት ተከትሎ ቋሚ ኮሚቴው በሂሳብ አያያዝና በንብረት አስተዳደር ረገድ በዋናው ግቢና በስሩ ባሉት ኮሌጆች ላይ የታዩ የአሰራር ግድፈቶችን በዝርዝር በማቅረብ የትምህርት ተቋማቱ ኃላፊዎች ማብራሪያ እንዲሰጡ አድርጓል፡፡

በፋይናንስ አያያዝና አስተዳደር ረገድ ኦዲቱ በርካታ ችግሮችን ያሳየ ሲሆን ሂሳብን በአግባቡ ያለመመዝገብ ችግር ከቢዝነስ ኮሌጅ ውጪ በሁሉም የትምህርት ተቋማት እንደሚታይ፣ ዋናው ግቢና የአዲስ አበባ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ገንዘብን በወቅቱ ለሚመለከታቸው አካላት ፈሰስና ገቢ እንዳላደረጉ፣ ሁሉም ተቋማት በተለያየ ምክንያት አግባብ ያልሆኑ ክፍያዎችን፣ ለመምህራን ለተማሪዎች፣ ለሰራተኞች ወዘተ. እንደከፈሉ፤ ከቢዝነስና ከአርክቴክቸር ኮሌጆች በስተቀር ካለማስረጃ ሂሳቦችን መመዝገብ ወይም ማስተካከል በትምህርት ተቋማቱ ላይ እንደሚታይ፣ ከዋናው ግቢና ከቢዝነስ ኮሌጅ ውጪ በሌሎቹ የትምህርት ተቋማት በአንዳንድ ተሰብሳቢና ተከፋይ ሂሳቦች ላይ የተሟላ መረጃ እንደሌለ፤ በዋናው ግቢ፣ በአዲስ አበባ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትና በጤና ሳይንስ ኮሌጅ ተከፋይ ሂሳብን በወቅቱ ያለመክፈል ሁኔታ እንዳለ እንዲሁም በዋናው ግቢና በጤና ሳይንስ ኮሌጅ ከፍተኛ መጠን ያለው ሂሳብ በተከፋይ ተይዞ እንደሚገኝ ኦዲቱ አመልክቷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ኦዲቱ ከቢዝነስ ኮሌጅ በስተቀር የፋይናንስ አሰራርን ካለመከተል ጋር የተያያዙ የተለያዩ ችግሮች እንደሚታዩ፤ የሂሳብ መዛነፎችና አለመጣጣሞች በዋናው ግቢ፣ በአዲስ አበባ ቴክኖሎጂ ኢኒስቲትዩትና በተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ እንዳለ፤ በዋናው ግቢ፣ በአዲስ አበባ ቴክኖሎጂ ኢኒስቲትዩት፣ በተፈጥሮ ሳይንስ እና በጤና ሳይንስ ኮሌጅ በተሰብሳቢ ሂሳብ ተይዘው ያልተሰበሰቡ ሂሳቦች እንዳሉ፤ የአዲስ አበባ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የውስጥ ገቢን ከሚመለከተው አካል ሳያስፈቅድ ለወጪ እንደተጠቀመ፣ የፐሮጀክት ሂሳብና የውስጥ ገቢ ሂሳብንም ለይቶ ሪፖርት እንደማያዘጋጅና ሪፖርቱም በዩኒቨርስቲው ተጠቃሎ ለገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ሪፖርት እንዳልተደረገ እንዲሁም ሌሎች የፋይናንስ አስተዳደር ችግሮች በትምህርት ተቋማቱ እንዳሉ አሳይቷል፡፡

ከግዥ ጋር በተያያዘም ህግን ያልተከተሉ ግዥዎች በዋናው ግቢ፣ በአዲስ አበባ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት፣ በአርክቴክቸርና በጤና ሳይንስ ኮሌጅ እንደተፈጸሙ፣ ዋናው ግቢ አገልግሎት ሰጪ አካል ውልን ሳያከብር ሲቀር ሊከፍል የሚገባውን ገቢ እንዳልሰበሰበ፣ የአዲስ አበባ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የተወዳዳሪ ተጫራቾችን ሰነድ ለኦዲት ማቅረብ እንዳልቻለ እንዲሁም የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ ካለውል ግዥና ክፍያ ፈጽሞ እንደተገኘ በኦዲቱ ተገኝቷል፡፡

ከንብረት አወጋገድ ጋር በተ_DSC0029webያያዘም በዋናው ግቢ ያልተወገዱ ንብረቶች መኖራቸው እንዲሁም የንብረት ወጪና ገቢ አለመመዝገቡና የንብረት መዝጋቢና የንብረት ጠባቂ አለመለየቱ፤ በቢዝነስ ኮሌጅ ተጠግኖ መስራት የሚችል ጄኔሬተር በመጋዘን መቀመጡ፣ ተቀላቅለው መቀመጥ የሌለባቸው ነገሮች ተቀላቅለው መቀመጣቸውና ቢን ካርድና ስቶክ ካርድ ጥቅም ላይ አለመዋላቸው እንዲሁም በጤና ሳይንስ ኮሌጅ ጌጃቸው የማይሰራ ተሽከርካሪዎች መኖራቸውና ከተለያዩ ምንጮች የሚወጣ ፍሳሽ የአካባቢ ብክለት መፍጠሩና ለጤና ስጋት መሆኑ በኦዲቱ ታይቷል፡፡

ከዚህ ሌላም በተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ ቢን ካርድና ስቶክ ካርድ ጥቅም ላይ አለመዋላቸው፣ ንብረትን የተመለከተ የተሟላ መረጃ አለመኖሩ፣ እንዲወገድ ለሌላ አካል በተላለፈ ንብረት ላይ ክትትል አለመደረጉ፣ ባግባቡ ባለመጠበቃቸው ለብልሽት የተጋለጡ 2 ትላልቅ ጄኔሬተሮች  መኖራቸው፣ ያለአገልግሎት የተቀመጡ ንብረቶች መገኘታቸው፣ ንብረት ሳይመልሱ ከተቋሙ የለቀቁ ሰራተኞች መኖራቸው፣ ለምርምር የሚወጡ ኬሚካሎች በትክክል ጥቅም ላይ መዋላቸው አለመረጋጡ፤ ከተሽከርካሪ መረጃ አያያዝ፣ ጥገናና አስተዳደር ጋር የተያያዙ ችግሮች መኖራቸው፣ ከአቅራቢዎች የሚገቡ ዳቦና እንጀራ መጠናቸው ልክ መሆኑ ሳይረጋገጥ ጥቅም ላይ መዋላቸው በኦዲቱ ተገልጿል፡፡ በአዲስ አበባ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትም በዋናው ንብረት ክፍል፣ በቤተ መጻህፍት ግምጃ ቤት፣ በተመላሽ ንብረት ክፍል፣ በጥገና ንብረት ክፍል እና በአላቂ ግምጃ ቤት በርካታ ከንብረት አያያዝና አስተዳደር ጋር የተያያዙ ችግሮች መኖራቸውን ኦዲቱ አመልክቷል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬዘዳንት ፕሮፌሰር አድማሱ ጸጋዬ በሰጡት ጥቅል አስተየያት ተቋሙ ላለፉት 65 አመታት ሲንከባለሉ የመጡ የፋይናንስና ንብረት አስተዳደር ችግሮች እንዳሉበት፣ በሂደቱም ከ2002-2006 በሂሳብ ምርመራ አገልግሎት ኮርፖሬሽን ኦዲት እንደተረገና የ2007 በጀት ዓመት ሒሳብ ኦዲትም በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት እንደተደረገ አስታውሰው ይህንን የተከማቸ ችግር ለመፍታት ከባድ ቢሆንም ከኦዲቱ በኋላም ሆነ አስቀድሞ አመራሩ ትኩረት ሰጥቶት እየሰራበት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ፕሬዘዳንቱ ከኦዲቱ በኋላ ከሁሉም የኮሌጆች አመራሮች ጋር ችግሮች በጋራ መፈተሻቸውና የድርጊት መርሀግብር ተዘጋጅቶ ወደ ተግባር መገባቱን፣ ዋናው ችግር ሲንከባለል የመጣው ሂሳብ በመሆኑ እስከ 1987 ዓ.ም ድረስ ተሂዶ በውጭ አካል እንዲጣራ ጨረታ ወጥቶ በሂደት ላይ እንደሚገኝ፣ በ2008 ዓ.ም የተቀናጀ የፋይናንስ አስተዳደር መረጃ ሥርዓት (IFMIS) በዋናው ግቢና በተወሰኑ ኮሌጆች መጀመሩን እንዲሁም በሁሉም ኮስት ሴንተርስ (cost centers) አየተሰራበት አንደሚገኝና ስርዐቱን በሁሉም ኮሌጆች ከሀምሌ 2009 ዓ.ም ጀምሮ ለመተግበር እንደታቀደ ተናግረዋል፡፡

ፕሮፌሰር አድማሱ አያይዘውም ከገበያ ውድድር ጋር ተያይዞ  የፋይናንስ ባለሙያዎችና የኦዲተሮች ከፍተኛ እጥረት እንዳጋጠመ፣ የድሮውን አሰራር ይዞ ለመቀጠል የመፈለግ የአመለካከት ችግር በዩኒቨርስቲው ውስጥ እንዳለ እንዲሁም የአዲስ አበባ ቴክኖሎጂ ኢኒስቲትዩትና የአርክቴክቸር፣ ህንጻ ግንባታና ከተማ ልማት ኢንስትቲዩት ላይ ዩኒቨርስቲው የማዘዝ ስልጣን ስለሌለው እርምጃ ለመውሰድ አለመቻሉን እንዳጋጠሙ ችግሮች አንስተዋል፡፡

ሌሎች የዋናው ግቢና የኮሌጆች የስራ ኃላፊዎች ከፋይናንስ፣ ከግዥና ከንብረት አስተዳደር ስርአቱ ጋር ኦዲቱ ባሳያቸው የአሰራር ችግሮች መንስኤ፣ በወቅቱ ስራዎቹ በተሰሩበት አግባብና፣ ስህተቶችን ለማረም ከኦዲት ግኝቱ በኋላ በተከናወኑና እየተከናወኑ ባሉ ተግባራት ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ እንደችግሮች መንስኤነት ካነሷቸው ጉዳዮች ውስጥ የተቋሙን ሁለንተናዊ እድገት የሚመጥን የፋይናንስና የንብረት አስተዳደር ስርአት ያልነበረ መሆኑ፣ የባለሙያዎች እጥረትና ብቃት ማነስ፣ ለረጅም አመታት ሲንከባለሉ የመጡና ባለው የሰው ሀይል ሊስተካከሉ ያልቻሉ ሂሳቦች ያሉ መሆኑ፣ አሰራሮችን ባለመረዳት የተፈጠሩ ክፍተቶች እንደነበሩ፣ የመረጃ ልውውጥና የአሰራር ችግሮች መኖራቸው፣ በወቅቱ የነበሩ ሰራተኞች አለመገኘት እና ስራዎችን በቃለጉባኤ በማሰረጃ አለመያዝ ይጠቀሳሉ፡፡

በዝርዝር ጉዳዮች ላይ የስራ ኃላፊዎቹ በሰጡት ማብራሪያ በዋናው ግቢ በኩል በኦዲቱ መሰረት ያልተፈቀዱና አላግባብ የተፈጸሙ ናቸው የተባሉ ክፍያዎች በሙሉ በሁሉም ኮሌጆች እንዲቋረጡ ማስደረጉን፣ ከንብረት አያያዝና አወጋገድ ጋር ያሉ ችግሮች እንዲታረሙ የድርጊት መርሀ ግብር ተዘጋጅቶ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ለአብነትም በአንድ ግለሰብ የንብረት ክፍሉ  ይተዳደርበት የነበረውን አሰራር ማስቀረቱን፣ የነፍስ ወከፍና የቋሚ ካርድ መጠቀም መጀመሩን፣ 70 ተሽከርካሪዎች መወገዳቸውና ሌሎች ንብረቶችም እንዲወገዱ በሂደት ላይ መሆኑን፤ የትርፍ ሰዐት ክፍያን በፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ሚኒስቴር በተፈቀደው መሰረት እያከናወነ መሆኑን እንዲሁም ተሰብሳቢ ሂሳቦችን ለማስመለስ ጥረት መጀመሩን አስረድተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ዋናው ግቢ በግዥ ረገድ _DSC0032webምንም አይነት የህግ ጥሰት እንዳልፈጸመ በመግለጽ በኦዲት ግኝትነት በታዩ ጉዳዮች ማለትም በጨረታ ህግ መሰረት 5 ተወዳዳሪዎች ሳይቀርቡ የጥበቃ አገልግሎት ከአንድ ድርጅት ከ7.3 ሚልየን በላይ በሆነ ብር መገዛቱ፣ ከዩኒቨርስቲው የህትመት ኢንተርፕራይዝና ከኮንስትራክሽን ዲዛይን አገልግሎት ማህበር በድምሩ ከ7.8 ሚልየን ብር በላይ የሆነ የህትመትና የምክር አገልግሎት ግዥ ካለጨረታ ውድድር በቀጥታ መገዛቱ፣ ለሆቴል አገልግሎት በአግባቡ ተወዳድሮ ያሸነፈን ሆቴል ከመወዳደሪያ መስፈርቱ ውጪ በቂ የመኪና ማቆሚያ የለውም በሚል ግዥው ከሌላ ሆቴል መፈጸሙ እንዲሁም ለድንገተኛ ህክምና ህንጻ ግንባታ የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ከፈቀደው የጭማሪ ጣሪያ በላይ በ30 ፐርሰንት በልጦ ውል መታሰሩ ህጋዊ አግባብን ተከትሎ የተፈጸመ ነው በሚል ከነምክንያቱ አስረድተዋል፡፡

የሌሎቹ ከፍተኛ ተቋማት ኃላፊዎች በበኩላቸው በየተቋሞቻው ላይ የተገኙት የኦዲት ግኝቶች ትክክል መሆናቸውን በመቀበል በፋይናንስና በንብረት አስተዳደር በኩል ችግሮቹ በምን ምክንያት እደተከሰቱ እንዲሁም ችግሮችን ለማረም በተግባር የተወሰዱና በዕቅድ የተያዙ እርምጃዎች ምን እንደሆኑ በእያንዳንዱ ዝርዝር የኦዲት ግኝት ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በመድረኩ ተሳታፊ የነበሩ ባለድርሻ አካላትና የቋሚ ኮሚው አባላት በወቅቱ የተለያዩ አስተያየቶችን ሰጥተዋል፡፡

የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የስራ ኃላፊ የትምህርት ተቋማቱ ባብዛኛው በመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ በኩል ግዥን መፈጸም እንደማይፈልጉ፣ የሚፈጽሙት ግዥም በዕቅድ የማይመራ መሆኑንና የአዲስ አበባ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩቱት በዩኒቨርስቲው የማይታዘዝ በመሆኑ ግዥን እንዳሻው የሚፈጽም መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የስራ ኃላፊም የችግሩ መንስኤ በዩኒቨርስቲው የተቀመጠ ትክክለኛ አሰራር ያለመኖሩ እንደሆነ ገልጸው ይህንን ስርዐት መዘርጋትና በስሩ ያሉ ኮሌጆችን መምራት የዩኒቨርስቲው የአመራር ኃላፊነት መሆኑን፣ ዩኒቨርስቲው የውስጥ ኦዲተሩ በሚያቀርበው ግኝት መሰረት እርምጃ እየወሰደ አለመሆኑን፣ በዩኒቨርስቲው አሰራር መንግስት የሚያገኛቸው ገቢዎች የሚታጡበት እድል እንዳለና ኮሌጆቹ ስለሚፈጽሟቸው ግዥዎች በዝርዝር ማጥናት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴ አባላት በሰጡት አስተያየት ዩኒቨርስቲው የአዲስ አበባ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትን የማዘዝ ስልጣን የለኝም በማለት ሁሉንም ነገር ለኢንስቲትዩቱ አመራር አሳልፎ መስጠቱ ተቀባይነት እንደሌለውና የኢኒስቲትዩቱን ስልጣን የመገደብ ስልጣን ያለው በመሆኑ ይህንን መጠቀም እንዳለበት፣ የተለያዩ ክፍያዎችን የሚፈጽምበት አግባብ ትክክል ባለመሆኑ ህግን ተከትሎ መስራት እንደሚገባው፣ ኦዲቱ በማስረጃ ከሚያሳየው በተቃራኒ ከግዥ ጋር የታዩ ችግሮችን አምኖ አለመቀበልና በህጋዊ አግባብ እንደተፈጸሙ አድርጎ መከራከሩ ስህተቱን አምኖ ችግሩን ለመፍታት አለመዘጋጀቱን እንደሚያሳይ፣ ተሰብሳቢ ሂሳቦችን ማስመለስ ላይ አትኩሮ መስራት እንደሚገባው፣ የሂሳብ አመዘጋጋብ ችግሮችን ምንጭ ማጥናት እንደሚኖርበት እንዲሁም በማቀድ፣ በመግዛት፣ በመጠቀምና በማስወገድ በኩል በሁሉም_DSC0019web ተቋማት ያለውን ችግር መፈተሽ አንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ በሰጡት አስተያየት ዋናው ግቢ ከድንገተኛ የህክምና ማዕከል ግንባታ ጋር እንዲሁም ከህትመት ጋር በተያያዘ የፈጸማቸውን ግዥዎች ህጋዊ አድርጎ ማቅረቡ ስህተት እንደሆነ፣ በተቋማቱ ያሉትን ችግሮች ስረ-መሰረታዊ መንስኤ በማጥናት መፍትሄ ማበጀት እንደሚገባ፤ ከሰው ሀይል ጋር ተያይዞ በውስጥ ኦዲት፣ በግዥና በፋይናንስ በኩል ያሉትን ክ
ፍተቶች በተቋማቱ ማህበረሰብ ውስጥ ያሉ እድሎችን ተጠቅሞ በውስጥ አቅም ለማጥበብ መሞከር እንደሚቻል፣ በቀጣይ ስህተቶችን አርሞ የተስተካከለ ስራ ለመስራት በቁርጠኝነት መነሳት እንደሚገባ እንዲሁም ውሳኔ የሚፈልጉ ጉዳዮችን ለሚመለከተው አካል አቅርቦ ማስወሰን እንደሚያሻ ገልጸዋል፡፡

ዋና ኦዲተሩ አክለውም በንብረት ማስወገድ ረገድ ሁሉንም አማራጮች አሟጦ መጠቀምና የመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት መኖርን እንደ መልካም አጋጣሚ መጠቀም እንደሚያስፈልግ፣ ለምርምር የሚውል ገንዘብን በአግባቡ በመጠቀም ላይ ትኩረት መስጠት እንደሚያሻ፣ የውስጥ ገቢን መመሪያን በተከተለ አግባብ መጠቀም እንደሚያስፈልግ፣ ተመላሽ ሂሳብን ለማስመለስ ትኩረት መስጠት እንደሚገባና መመለስ የሚችለውንና የማይችለውን ሂሳብ አጥንቶ ለመንግስት ማቅረብ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡_DSC0050web

የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ ኦዲቱ የተሟላና ችግሮችን ለመፍታት እድል የሚሰጥ መሆኑን ጠቅሰው የሰው ሃይል ችግሩን እንዲሁም የኦዲት ግኝቶችን በተመለከተ የተነሱ ችግሮችን ለመፍታት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲ ኢንተርፕራይዞች ኦዲቱ እንዳመላከተው በህግ የተቋቋሙ እንዳልሆኑና ህጋዊ ሰውነት ኖሯቸው እንዲቋቋሙ ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ክቡር አምባሳደር መስፍን ቸርነት በማጠቃለያቸው የትምህርት ተቋማቱ ኦዲቱ ይጠቅመናል ብለው መቀበላቸው፣ የድርጊት መርሀግብር አዘጋጅተው ወደ ተግባር መግባታቸው፣ አንዳንድ ግኝቶች ላይ በፍጥነት እርምጃ መውሰዳቸው፣ የተቀናጀ የፋይናንስ አስተዳደር መረጃ ሥርዓትን ተግባራዊ ለማረድግ ጥረት  መጀመራቸው እና   ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ የተከማቸ ሂሳብን ለማጥራት እርምጃ መወሰድ መጀመሩ በጥሩ ጎን እንደሚታዩ ጠቅሰዋል፡፡

ሆኖም ዩኒቨርሲቲው አንጋፋ ከመሆኑ አንጻር አሁን ያለበት የፋይናንስ አስተዳደሩ ችግር ያለበት መሆኑን ገልጸው ከተለመደው አሰራር ላለመውጣት ያሉ የአመለካከት ችግሮችን ፈቶ ከቆየበት የፋይናንስና የንብረት አስተዳደር ችግር በፍጥነት መውጣት እንዳለበት፣ ኦዲቱ በናሙና ካያቸው ችግሮች በላይ በተቋማቱ ሌሎች የአሰራር ችግሮች ስለሚኖሩ አሰራርን የማስተካሉን ጉዳይ ከኦዲት ግኝቱ በላይ አስፍቶ ማየት እንደሚገባው፣ ለውስጥ ኦዲት ግኝቶች ትኩረት ሰጥቶ ተግባራዊ እርምጃ መውሰድ እንደሚኖርበት፣ በግዥ አፈጻጸም ላይ ኪራይ ሰባሳቢነት እንዳለ የሚያስጠረጥሩ ሁኔታዎች እንደሚታዩና እነዚህን ማጣራት እንደሚያስፈልግ፣ ግዥን በእቅድ ማከናወን ሲገባ በዘፈቀደ እንዲፈጸም የሚደረግበትና በዚህ ምክንያት የሚፈጠሩ ችግሮችን የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ጋር በመውሰድ መፍትሄ ለማስገኘት እየተሰራ ያለው ስራ መቀጠል እንደሌለበት አሳስበዋል፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *