News

የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ለሂሳብ አያያዝና ንብረት አስተዳደሩ የበለጠ ትኩረት እንዲሰጥ ተጠየቀ

የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ለሂሳብ አያያዝና ለንብረት አስተዳደር ስርአቱ የበለጠ ትኩረት በመስጠት ሀብትን በአግባቡና በህጋዊ መንገድ ጥቅም ላይ እንዲያውል የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡ ቋሚ ኮሚቴው በመ/ቤቱ የ2007 በጀት አመት የሂሳብ ኦዲት ግኝት ላይ ይፋዊ ስብሰባ መጋቢት 20 ቀን 2009 ዓ.ም አድርጓል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ላይ ያከናወነውን የሂሳብ ኦዲት ተመስርቶ ቋሚ ኮሚቴው በሂሳብ አያያዝና በንብረት አስተዳደር ረገድ በተቋሙ ላይ የታዩ ጉድለቶችን በዝርዝር አቅርቧል፡፡

በዚህም የመንግስትን ገቢ ከመሰብሰብና ወደ ተጠቃለለ ፈንድ ገቢ ከማድረግ ጋር ተያይዞ ከ191 ሺህ ብር በላይ የሆነ የተሰበሰበ ገቢ በዕለቱ ወደ መ/ቤቱ ወይም ወደ ማዕከላዊ ግምጃ ቤት የባንክ ሂሳብ ገቢ መደረግ ሲገባው አለመግባቱ እንዲሁም መ/ቤቱ በገቢ የባንክ ሂሳቡ ያቆየውን የመንግስት ገቢ ወር በገባ እስከ አምስተኛው ቀን ድረስ ወደ ማዕከላዊ ግምጃ ቤት የባንክ ሂሳብ ፈሰስ ማድረግ ሲገባው ከሰበሰበው 2,935,596.86 ብር ውስጥ 2,557,187.71 ሚልዮን ብር ያህል ብር በወቅቱ ፈሰስ ባለመደረጉ ሰኔ 30፣ 2007 ዓ.ም ሂሳቡ ብሎክ መደረጉ በቀረበው የኦዲት ግኝት ተመልክቷል፡፡

እንደዚሁም ከ1974 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2007 ዓ.ም ድረስ በተለያዩ የሂሳብ መደቦች ለውሎ አበል፣ ለመጓጓዣና ለግዥ የተሰጠ ከ19 ሚልዮን ብር በላይ አለመወራረዱና ይህም ቀደም ባሉት አመታት ኦዲት ግኝት ላይ እንዲስተካከል አስተያየት ቢሰጥበትም አሁንም ያልተስተካከለ መሆኑን ኦዲቱ አሳይቷል፡፡

በተጨማሪም በተገቢው የሂሳብ መደብ ያልተመዘገቡ ወጪዎች መኖራቸው፣ በ2006 ዓ.ም የተከፈለ የአገልግሎት ክፍያ በ2007 ዓ.ም የተፈጸመና የተመዘገበ መሆኑ፣ እስከ ከ50 ሺ ብር የሆኑ ክፍያዎች ወደ ተከፋዩ የባንክ ሂሳብ በማስተላለፍ መከፈል ሲገባቸው ድምራቸው ከ1.5 ሚልዮን ብር በላይ የሆኑ የተለያዩ ክፍያዎች በ ሲ ፒ ኦ (CPO) መፈጸማቸውና ሌሎች የሂሳብ አመዘጋገብ ስህተቶች መኖራቸውን ኦዲቱ አመልክቷል፡፡

ከንብረት አያያዝና አጠባበቅ ጋር በተያያዘም በበጀት አመቱ የንብረት ቆጠራ ያልተደረገና ለቋሚ እቃዎች መለያ ቁጥር ያልተሰጠ መሆኑ፣ በተጠቃሚዎች እጅ ላይ ለሚገኙ ቋሚ እቃዎች መቆጣጠሪያ ካርድ አለመዘጋጀቱ እንዲሁም አገልግሎት የማይሰጡ ንብረቶች ለረጅም ጊዜ በግምጃ ቤት ተከማችተው መገኘታቸው በኦዲቱ ተገልጿል፡፡ 

ከዚህም ሌላ በድምሩ ከ23.4 ሚልዮን ብር በላይ በጀት ጥቅም ላይ አለመዋሉ፣ በስራ ሂደት የሚከሰቱ ችግሮችንና የኪራይ ሰብሳቢነት ተጋላጭነት ደረጃን መለያ ዳሰሳ ጥናት ያልተደረገና የመፍትሄ አቅጣጫ ያልተቀመጠ መሆኑም ተመልክቷል፡፡

እንደዚሁም ከ2004 እስከ 2006 በጀት አመት በተደረጉ ኦዲቶች በተሰጡ አስተያየቶች መሰረት የእርምት እርምጃ እነዳልተወሰደ ኦዲቱ ያሳየ ሲሆን ለዚህም ለሌላ ተቋም በውሰት ከተሰጡ 18 ተሽከርካሪዎች ውስጥ 1 ብቻ መመለሱ፣ የሂሳብ ሰነዶችን በአግባቡና ለአጠቃቀም ምቹ በሆነ መልኩ አደራጅቶ በመያዝ በኩል ችግሮች መኖራቸው፣ 8 ተሽከርካሪዎች አሁንም ጌጃቸው የማይሰራ መሆኑ፣ የተለያዩ ማሽኖች ካለአገልግሎት መቀመጣቸው፣ መወገድ ያለባቸው ኬሚካሎች አለመወገዳቸው እንዲሁም ንብረት ያጎደሉና በፍርድ ቤት ከነወለዱ እንዲከፍሉ የተወሰነባቸው የመስሪያ ቤቱ የቀድሞ ሰራተኛን ጉዳይ በአግባቡ ተከታትሎ አለማስፈጸሙ በምሳሌነት ቀርበዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው መ/ቤቱ በነዚህ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ እንዲሰጥና የተወሰዱ እርምጃዎችም እንዲገለጹ የጠየቀ ሲሆን የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ዋና ዳይሬክተር አቶ ማስረሻ ገ/ስላሴና ሌሎች የመ/ቤቱ የስራ ኃላፊዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

_DSC0024 with captionበምላሻቸው ገንዘብን በወቅቱ ለማዕከላዊ ግምጃ ቤት ፈሰስ ከማድረግ ጋር በተያያዘ ችግሩ የተፈጠረው ካልተጠበቀ የሰው ሀይል መፍለስና ከክልሎች የተሰበሰቡ ሂሳቦችን የሚያመጣ አካል ካለመኖሩ ጋር ተያይዞ መሆኑና በተሰጠው የኦዲት አስተያየት መሰረት ባለሙያዎችን በመመደብ በወቅቱ ሪፖርቶችን በማዘጋጀት እስከ የካቲት ወር ድረስ ያለው ሂሳብ ለገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ፈሰስ እንደተደረገና ይህም በውስጥ ኦዲት እንደተረጋገጠ  ገልጸዋል፡፡

 ከ19 ሚልዮን በላይ የሆነ ያልተወራረደ ሂሳብን አስመልክቶም ገንዘቡ ከረጅም አመታት ጀምሮ የተከማቸ መሆኑን በአሁኑ ወቅት ባለቤቶቹ የሌሉና ሊመለስ የማይችል በመሆኑ በሞዴል 6 የተሰጠና በመ/ቤቱ ሊሰረዝ የሚችልን በድምሩ 1.2 ሚልዮን ብር ለማሰረዝ የገንዘብ ስረዛ ኮሚቴ (write off committee) በማቋቋም ሰነዶችን እያጣራ እንዳለ፣ በገንዘብ ሚኒስቴር የሚሰረዘውንም ለሚኒስቴር መ/ቤቱ እየላከ እንደሚገኝ እንዲሁም ሌሎች የሚወራረዱ ሂሳቦችም እየተወራረዱ መሆኑን ኃላፊዎቹ አስረድተዋል፡፡

በወጪ ምዝገባ ረገድም ከ2008 ጀምሮ በምዝገባ ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር እየተደረገና ሂሳባቸውን የማናበብና ችግሮችን የማስተካከል ስራ እየተሰራ መሆኑን እንደዚሁም ከባንክ ሂሳብ በማስተላለፍ መከፈል የነበረባቸው ክፍያዎች በ ሲ ፒ ኦ (CPO) መከፈላቸው ስህተት እንደሆነና አሁን ግን በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር በተላለፈው አዲስ መመሪያ መሰረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በቋሚ ንብረት ቆጠራ ላይ ያለው ችግር የባለሙያ እጦት በመኖሩ የመጣ እንደሆነና ቦታውን በሰው ሀይል ለማሟላት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ችግሩ እስኪፈታ ድረስ ግን ኮሚቴ በማቋቋም ንብረት ቆጠራ እየተደረገ መሆኑ፣ በንብረት ማስወገድ በኩልም ከመንግስት ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ጋር እየተሰራና ተሽከርካሪዎችን፣ ኮምፒዩተሮችን ፕሪንተሮችን ጨምሮ የተለያዩ ንብረቶች መወገዳቸውን የቀሩትም እስከ ሰኔ 30 2008 ዓ.ም ድረስ እንዲወገዱ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ጥቅም ላይ ያልዋለውን በጀት በተመለከተም ለዚህ የመ/ቤቱ የግዥ ስርአት መጓተት፣ በመጨረሻ ሰዓት ላይ የውጭ ግዥዎች መጨናገፍና ወደቀጣዩ አመት መዛወር እንዲሁም በጀትን በአግባቡ ያለመጠቀም ችግሮችን በከፊል እንደ ምክንያትነት ጠቅሰው የበጀት አጠቃቀሙን ለማሻሻል እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በሰነድ መልክ ባይዘጋጅም የኪራይ ሰብሳቢነት ስጋት ተጋላጭነት ዳሰሳ እየተደረገ እንዳለና በአሰራርም በስጋት ምንጭነት በተለዩ ከነዳጅ ስርጭትና አጠቃቀም፣ ከጥሬ ገንዘብ አያያዝ፣ ከንብረት ማስወገድ፣ ከግዥ ወዘተ. ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ላይ ስልት በመቀየስ እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

በቀደሙ ኦዲቶች እንዲስተካከሉ አስተያየት ተሰጥቶባቸው አልተስተካከሉም በተባሉት ጉዳዮች ላይ ሲያስረዱም ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል መ/ቤት በውሰት ከተሰጡት 18 ተሸከርካሪዎች ውስጥ አንደኛው  ብቻ በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኝ በመሆኑ ሌሎቹ እንዲወገዱ ኮሚቴ ተቋቁሞ የተሽከርካሪዎቹን ሰነዶች የማሰባበስና በአወጋገዱ ዙርያ ከመንግስት ንብረት አወጋገድ አገልግሎት ጋር እየተሰራ መሆኑን፣ ጌጃቸው ከማይሰሩት 8 ተሽከርካሪዎች ውስጥ የአራቱ መስተካከሉን 4ቱ ግን የድሮ መኪኖች በመሆናቸው ጌጃቸው ገበያ ላይ እንዳልተገኘ አስረድተዋል፡፡

ከዚህም ሌላ ኬሚካሎችን ለማስወገድ ከአካባቢ ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር ምክክር ቢደረግም ችግሩ ሀገራዊ በመሆኑ አለመቻሉን ሆኖም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጋር በመሆን ለማስወገድ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ፣ አገልግሎት ሳይሰጡ ተከማችተው የነበሩትን ማሽኖችም ስራ ለማስጀመር መትከያ ስፍራ መዘጋጀቱንና የሙያ ፍላጎትን ለመሙላትም ከፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ጋር ፍላጎትን የመለየትና ሌሎች ቅድመ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ስራ እየተሰራ መሆኑን የገለጹ ሲሆን ባለዕዳ የሆኑትን የቀድሞ የመ/ቤቱን ሰራተኛ በተመለከተ ግለሰቡ እዳቸው እንዲከፍሉ ክትትል ተደርጎ አሁን እየሰሩ በሚገኙበት መ/ቤት ገንዘቡ እየተቆረጠባቸው እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው አባላት ተጨማሪ ማብራሪያ በሚጠይቁ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ጠይቀው ምላሽ የተሰጠባቸው ሲሆን አባላቱ ትኩረት ይሻሉ ባሏቸው ጉዳዮች ላይ አስተያየቶችን ሰጥተዋል፡፡

በዚህም መ/ቤቱ የፋይናንስና ን_DSC0057 with captionብረት አስተዳደሩን ማጤን እንዳለበት፣ በፋይናንስ አያያዝ ላይ ለአቅም ግንባታ ትኩረት መስጠት እንደሚስፈልግና ከዚህ በኋላ ስህተቶች እንዳይፈጠሩ መስራት እንደሚገባ፣ ቀደም ብለው የነበሩ ሂሳቦችን ለማጣራት በሚደረገው ጥረት የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት የመረጃ ምንጮቹ ጋር ሄዶ የመፈለግና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር አቅጣጫ የማሰጠት አካሄድን መከተል እንደሚገባ፣ ኦዲቱ በናሙና ካያቸው አሰራሮች በላይ አስፍቶ አሰራርን መፈተሽና ማስተካከል እንደሚያሻ እንዲሁም የስጋት ተጋላጭነት ዳሰሳን በደንብ አጥርቶ ማየትና መተግበር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ምክትል የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ በበኩላቸው መሰብሰብ ካለበት 19 ሚልዮን ብር ገና ያልተሰበሰበ 15 ሚልዮን ብር ስላለ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰበሰብ እንደሚገባ እንዲሁም በዴቢትና ክሬዲት ሚዛን ወደ 24 ሚልየን ብር የነበረው ልዩነት በ2008 በጀት አመት ወደ 5 ሚልዮን ብር እንዲወርድ ቢደረግም ልዩነቱን በሙሉ ማስተካከል እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

ከዚህም ሌላ በ2007 በጀት አመት በተሰብሳቢ መመዝገብ ሲገባው በወጪ የተመዘገበው ንብረት በ2008 ዓ.ም አመዘጋቡ ያልተስተካከለ በመሆኑ ሊስተካከል እንደሚገባውና የንብረት ቆጠራ ስርዓቱንም በሁሉም መጋዘኖች ሙሉ በሙሉ ማስተካል እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

ምክትል ዋና ኦዲተሯ አያይዘውም አሁንም ከመመሪያና ከህግ ውጭ የሚሰሩ ስራዎች ስላሉ ለነዚህ አመራሩ ትኩረት ሰጥቶ ሂሳቦች በአግባቡ እንዲሰሩ በጀትም ለታለመለት አላማ እንዲውል ማድረግ፣ እንዲሁም የውስጥ ኦዲት ይህንን እየተከታተለ ለሚመለከታቸው አካላት የተወሰዱ እርምጃዎችን ማሳወቅ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡_DSC0068with caption

የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አምባሳደር መስፍን ቸርነት በማጠቃለያ አስተያየታቸው መ/ቤቱ በኦዲት ግኝቱ ላይ መሰረት አድርጎ ለማስተካከል የሄደበት ርቀት መልካም መሆኑና በይፋዊ ስብሰባውም የኦዲት ግኝቶችን አስተማሪነት ወስዶ ለመቀበል ያሳየው ዝግጁነት በጥሩ ጎኑ እንደሚታይ ተናግረዋል፡፡

ሆኖም መ/ቤቱ ለኪራይ ሰብሳቢነት ተጋላጭ ለሚያደርጉት ጉዳዮች ትኩረት ተሰቶ ማጥናትና በተግባር የሚገጥሙ ችግሮችም ከዳሰሳ ጥናቱ ጋር እያዛመደ ማስተካከል እንደሚገባው፣ ከንብረት አመዘጋገብና አወጋገድ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችንም በአግባቡ እንደገና ማየትና እርምጃ መውሰድ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

እንደዚሁም የመ/ቤቱ አመራር ስራ ላይ ያልዋለው በጀትን ከሰው ሀይል ጋር ቢያገናኘውም ስትራቴጂክ አመራር በመስጠት የተመደበውን በጀት ከእቅድ ጋር እያናበቡ በየሩብ አመቱ እየገመገሙና ጥቅም ላይ ያልዋለውንም ምክንያቱን እየለዩ ሀብትን በአግባቡ መምራት እንዲሁም ስትራቴጂክ አመራር በመስጠት በጀትን እንዴት እየተቆጣጠርን እንመራው ነበር የሚለውን  መፈተሸ እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

ከ2006 እና 2007 በጀት የታዩ ሲንጠባጠቡ መጥተው አሁንም በ2008 በጀት አመት ኦዲት የታዩ ጉዳዮች መኖራቸው እንዲሁም አዲስ የታዩ ግኝቶች መገኘታቸው አመራሩ የሀብት አስተዳደር ስራውን ኦዲት በሚመጣ ጊዜ የሚሰራው የግርግር ስራ እንደሆነ የሚያስመስል በመሆኑ ከተለመደው አስተሳሰብ ወጥቶ ነባሮቹንም አዳዲሶቹንም ግኝቶች በፍጥነት ለማስተካከል በአግባቡ መስራት እንደሚገባ ሰብሳቢው አሳስበዋል፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *