News

የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅና የአማኑኤል የዐዕምሮ ስፔሻላዝድ ሆስፒታል የፋይናንስ ህግና መመሪያ እየጣሱ እንደሆነ ተገለፀ

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ እና የአማኑኤል የዐዕምሮ ስፔሻላዝድ ሆስፒታልን የ2007 በጀት ዓመት የሒሳብ ኦዲት ሪፖርት መጋቢት 14፣ 2009 ዓ.ም ባየበት ይፋዊ ስብሰባ ተቋማቱ ከፍተኛ የፋይናንስ ህግና መመሪያ ጥሰት ፈፅመው መገኘታቸውን ገለፀ፡፡

በስብሰባው ላይ በሁለቱም ሆስፒታሎች የሒሳብ ኦዲት ሪፖርት ላይ የታዩ የፋይናንስ አስተዳደር ችግሮችን በዝርዝር ቀርበዋል፡፡

በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ በኩል  ከግል ጤና አገልግሎት ከሐምሌ 1 ቀን 2005 እስከ ሰኔ 30 ቀን 2006 ዓ.ም ድረስ ለኮሌጁ ገቢ ሆኖ ለመንግስት ገቢ መደረግ ያለበት 15% የኮሌጁ የትርፍ ድርሻ ብር 1,611,851.48 ፈሰስ ያልተደረገ መሆኑ፤ ኮሌጁ  በ2007 በጀት ዓመት የገቢ ዕቅድ ያላዘጋጀ መሆኑ፤ ለውሎ አበልና ለመጓጓዧ የተከፈለና   ከግንቦት 1999 ጀምሮ በሂሳብ መደብ 4201 የተያዘ ብር 51,546.22 እንዲሁም ከግንቦት 2007 ዓ.ም ጀምሮ በሂሳብ ቁጥር 4211 የተያዘ ብር 431,709.76 በድምሩ ብር 483,225.98 ተሰብሳቢ ሂሳብ ሳይወራረድ መገኘቱ ተገልጿል፡፡

ከትርፍ ሰዓት ክፍያ አፈፃፀም ጋር በተያያዘም በሚመለከተው የመንግስት አካል ሳይፈቀድ ከሐምሌ 1 ቀን 2006 ዓ.ም እስከ መጋቢት 2007 ዓ.ም ድረስ  ብር 336,240.00  ክፍያ ፈፅሞ የተገኘ መሆኑ፤ በተገቢው ሂሳብ መደብ ያልተመዘገቡ ሂሳቦችን ለማረጋገጥ ኦዲት ሲደረግ ለትርፍ ሰዓት ለኢንተርንና ለሥልጠና የተፈፀመው ክፍያ ብር 266,371.04 በተገቢው ሂሳብ መደብ ሳይመዘገብ መገኘቱ ተመላክቷል፡፡

ከግዢ ጋር በተያያዘ በሆስፒታሉ የተፈፀሙ ግዢዎች ከተለያዩ አቅራቢዎች የዋጋ ማወዳደሪያ ሳይሰበሰብ እና በቂ አቅራቢዎችን ሳያሳትፉ በድምሩ ብር 228,452.15 ግዢ የተፈፀመ መሆኑን፤ ከብር 75,000.00 በላይ የሚፈፀሙ የአገልግሎት እንዲሁም ከብር 100,000.00 ብር በላይ የሚፈፀሙ የእቃ ግዢዎች በጨረታ መፈፀም ሲኖርባቸው ሜዲካል ኮሌጁ ለግዮን ሆቴሎች ድርጅት ጨረታ ሳያወጣ ብር 218,527.07 የአገልግሎት ክፍያ መፈፀሙ በኦዲት ሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

ሜዲካል ኮሌጁ ከሥራ ለለቀቁ አራት የተለያዩ ሠራተኞች ላልሰሩበት ደመወዝ ብር 5,007.38 ክፍያ የፈፀመ መሆኑን፤ ኮሌጁ ከ11 የኮንስትራክሽን ድርጅቶች ጋር ባደረገው ስምምነት በተሰብሳቢ ሂሳብ መመዝገብ የነበረበት የቅድሚያ ክፍያ ተመላሽ ምዝገባ ሳይከናወን አየር በአየር ከክፍያ ሰርተፍኬቱ ላይ ብቻ እንዲቀናነስ በማድረግ የቅድሚያ ግብር በህጉ መሠረት እንዲቀነስ አለማድረጉ የተገለፀ ሲሆን በዚህም የተነሳ ብር 463,169.42 ያልተመዘገበ የወጪ ሂሳብ መኖሩ፣ ብር 380,882.82 በብልጫ በወጪ የተመዘገበ ሒሳብ መኖሩ፣ ብር 2,249,707.07 ያልተመዘገበና ያልተመለሰ የቅድሚያ ክፍያ ሂሳብ መኖሩ፣ ብር 90,492.53 በብልጫ የተቀነሰ የቅድሚያ ግብር ክፍያ ሂሳብ መኖሩ፣ ብር 59,725.82 በብልጫ የተቀነሰ ተጨማሪ ዕሴት ታክስ መኖሩ፣ ብር 11,971,636.37 ያልተጨመረ እሴት ታክስ መኖሩ፣ ብር 19,920.46 በብልጫ የተቀነሰ የመያዣ ሂሳብ መኖሩን፣ብር 30,000.00 ያልተቀነሰ የማያዣ ሂሳብ መኖሩ፣ ብር 3,209,925.21 በብልጫ የተከፈለ የጥሬ ገንዘብ ሂሳብ መኖሩ እና ብር 10,137.22 ያልተከፈለ የጥሬ ገንዘብ ሂሳብ መኖሩ ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም በግዢ መመሪያ መሠረት በተጨማሪነት የሚታዘዘው የግንባታ ሥራ የገንዘብ ሚዛን ከመጀመሪያው ውል ጠቅላላ ዋጋ ከ30% የበለጠ መሆን እንደሌለበት እየታወቀ ከበርካታ ድርጅቶች ጋር 47% እስከ 77% ጭማሪ ያሳ
ዩ የተለያዩ ክፍያዎች ፈፅሞ መገኘቱን የኦዲት ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡

በተመሳሳይ ለአማኑኤል የዐዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ቋሚ ኮሚቴው በሆስፒታሉ በ2007 የኦዲት ግኝቶች ላይ አመራሩ ምላሽ እንዲሠጥባቸው ማብራሪያ በሚሹ ጉዳዮች ላይ ጥያቄዎችን አቅርቧል፡፡ በኦዲት ሪፖርቱ እንደተመለከተው ሆስፒታሉ የትምህርት ምርምር እውቅና ሳይኖረው ብር 1,266,904.00 የትርፍ ሰዓት ክፍያ የፈፀመ መሆኑንና ክፍያውም በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በኩል ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ እንዲፀድቅ ያልተደረገእና ይህ ግኝት በ2005 እና 2006 በጀት ዓመታት ኦዲት ወቅትም አስተያየት የተሰጠበት ቢሆንም በአሠራሩ ላይ ለውጥ አለመኖሩ ተመላክቷል፡፡

በግዢ መመሪያ አንቀፅ 25 መሠረት በተጨማሪነት የሚታዘዘው የግንባታ ሥራ የገንዘብ ሚዛን ከመጀመሪያው ውል ጠቅላላ ዋጋ ከ30% የበለጠ መሆን እንደሌለበት የተመለከተ ቢሆንም የሣንታ ማርያ ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የተጨማሪ እሴት ታክስን ጨምሮ በጠቅላላው ብር 81,187,004.35 የለውጥ ሥራዎች ተብሎ የተፈፀመው ውል መጀመሪያ ከተፈፀመው ውል ብር 67,660,053.56 ጋር ሲነፃፀር በ120% ጭማሪ ያለው መሆኑ ተገልጿል፡፡

በሌላ በኩል የአማኑኤል የዐዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከብር 2000 በላይ የሆኑ በድምሩ ብር 113,169.00  ክፍያዎች በቼክ መከፈል ሲገባው በጥሬ ገንዘብ ክፍያቸውን የፈፀመ መሆኑ እንዲሁም ሆስፒታሉ ከብር 50,000.00 በላይ የሆኑ በድምሩ ብር 137,821.00 ክፍያዎችን በቀጥታ ወደ ባለመብቱ የባንክ ሂሳብ በማስተላለፍ ክፍያ መፈፀም ሲገባው በቼክ ክፍያ የፈፀመ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡

በተጨማሪም ሆስፒታሉ በ2007 በጀት ዓመት ለፕሮግራሞች የተፈቀደው የመደበኛና የካፒታል በጀት አጠቃቀም ከ10% በላይ ያልተሰራበት በጀት በየሂሳብ ኮዶቹ ሲታይ ከመደበኛ በጀት ብር 134,589.28 ከካፒታል በጀት ብር 31,516,509.43 በድምሩ ብር 31,651,089.71 ሥራ ላይ ያልዋለ በጀት መኖሩን የኦዲት ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡

_DSC0061 with caption - Copy
የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ብርሃኔ ረድኤ በሰጡት ምላሽ ኮሌጁ በ2007 ዓ.ም በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በተሠጡ 16 የኦዲት ግኝት ዝርዝሮች ላይ ማብራሪያ እና የወሰዷቸውን የማስተካከያ እርምጃዎች ለቋሚ ኮሚቴው አብራርተዋል፡፡ በማብራሪያቸው ሊስተካከሉ የሚገቡ የሒሳብ አመዘጋገቦች እንዲስተካከሉ ማድረጋቸውን፣ ያላግባብ ከስራ ለለቀቁ ሰራተኞች የተከፈሉ ክፍያዎች እንዲመለሱና ሌሎች አግባብነት የሌላቸው ክፍያዎች እንዲቋረጡ ማድረጋቸውንና በቀጣይ ይስተካከላሉ ባሏቸው ጉዳዮች ላይ የሚሰሩ ስራዎችን አስረድተዋል፡፡

የአማኑኤል የዐዕምሮ ስፔሻላዝድ ሆስፒታል የኦዲት ግኝት በተመለከተ የሆስፒታሉ ዋና ስራ አስኪያጅ ዶ/ር ዳዊት አሰፋ በሰጡት ምላሽ በተሠጠው የማስተካከያ ሃሳብ መሠረት በአብዛኞቹ ጉዳዮች ላይ የማስተካከከያ እርምጃ መውሰዳቸውን አስረድተዋል፡፡ ሥልጠናን ተከትሎ ሆስፒታሉ የሚከፍላቸው የትርፍ ሰዓት ክፍያዎችን በተመለከተም ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር ሥልጠናው መቆም እንደሌለበት በመታመኑ የተወሰደ እርምጃ እንደሆነ ገልፀው ነገር ግን በኦዲት ግኝቱ የታዩት አብዛኞቹ ችግሮች ሆስፒታሉ እያስገነባ ከነበረው ግንባታ ጋር ተያይዞ የመጡና በርካታ የዲዛይን ለውጦች በመደረጋቸው የተፈጠሩ ችግር መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ይሁን እንጂ የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታልም ሆነ የአማኑኤል የዐዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በኦዲት ሪፖርቱ መሠረት የማሻሻያ እርምጃ ወስደናል ያሉባቸውን ምላሾች ትክክለኛ እንዳልሆኑ ገልጸዋል፡፡ ከ2007 ኦዲት በኋላ በ2008 ዓ.ም በተደረገው ኦዲት ላይም በ2007 የተገኙት ግኝቶች ተባብሰው መቀጠላቸውንና የተደረጉ ማሻሻያዎች ውስን መሆናቸውን በሚያሳይ መልኩ ዋና ኦዲተሩ በማስረጃ አቅርበው ቋሚ ኮሚቴውም በትኩረት ጉዳዩን እንዲያየው ጠይቀዋል፡፡

_DSC0063 with captioቋሚ ኮሚቴው በሰጠው አስተያየት በኦዲት ግኝቱ እንዲታረሙ ተብለው የተገለፁ ጉዳዮች ተባብሰው መቀጠላቸውን፣ በተቋማቱ የተፈጸመው ከፍተኛ የህግና መመሪያ ጥሰት  ተቋማቱን የመከታተልና የመቆጣጠር ኃላፊነት ያለበት የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ክፍተት መሆኑን፣ በተለይም በህንፃ ግንባታ አስከ 120% የክፍያ ልዩነት የመጣበት ግንባታ ሊጣራና በተገነቡት ግንባታዎች ላይ  የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ተጨማሪ የክዋኔ ኦዲት ሊያደርግባቸው እንደሚገባ፤ ግንባታዎቹ አካባቢ የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባር ተፈጽሞባቸው ይሆናል ብሎ ቋሚ ኮሚቴው እንደሚገምት፤ የሚሠሩት ሥራዎች በህግና መመሪያ ላይ መሠረት ያደረጉ አለመሆናቸውንና ለአብዛኛው የዲዛይን መለዋወጥ አንዱ ቁልፍ ችግር ግንባታዎቹ አስቀድመው በተገቢው ሁኔታ ያልታቀዱ መሆናቸው መሆኑን ገልጿል፡፡

ክቡር ዋና ኦዲተሩ በሰጡት አስተያየት ተቋማቱ ግንባታዎችን ሲያከናውኑ ጨረታ በሚያወጡበት ጊዜ የተለያዩ ሥራዎችን በተለያየ ጨረታ ለያይተው የሚያወጡበት አሰራር ሊኖር እንደሚገባና ይህ ግን እንዳልተደረገ፣ በመሆኑም  ለዚህ ተጠያቂ መሆን ያለበት አካል ተጠያቂ ሊሆን እንደሚገባና ግለሰቦች ባጠፉት ጥፋት መንግስት ሊከስር እንደማይገባው እንዲሁም ከውስጥ ገቢ ጋር በተያያዘ ያለውን የገንዘብ አጠቃቀምና አከፋፈል በህግና መመሪያው መሠረት ሊፈፀም እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ክቡር አምባሳደር መስፍን ቸርነት  በመጨረሻ በማጠቃለያ አስተያየታቸው ሆስፒታሎቹ አገልግሎት አሰጣጣጣቸውን ለማሻሻል እየሰሩ ያሉት ሥራዎች መልካም መሆናቸውን ገልፀው ነገር ግን እነዚህ ሥራዎች በሌላ በኩል ለብልሹ አሠራር የተጋለጡ መሆን እንደሌለባቸው ገልፀዋል፡፡ በተለይም ከሂሳብ አያያዝ ጋር በተያያዘ የፋይናንስ ደንብና መመሪያን በከፍተኛ ሁኔታ እየጣሱ መሆኑን፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለው ቅንጅት የላላ መሆኑን፣ የውስጥ ኦዲታቸው በጣም ደካማ መሆኑን፣ በኦዲት ግኝቶች ላይ እርምጃ አለመውሰድና የበጀት አጠቃቀም ችግር መኖሩንና በነዚህ የጤና ተቋማት አሠራር የጎላ ችግር መታየት የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርም ጉልህ ድርሻ ያለው መሆኑን ገልፀው ሚኒስቴር መ/ቤቱ በስሩ ያሉ ተቋማትን ከመደገፍና ከመከታተል አኳያ እየሠራ ያለው ሥራ ሊፈተሽ እንደሚገባና በሆስፒታል ህንፃ ዲዛይን ስራ  የባለሙያ እጥረትን ከመቅረፍ አኳያ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በመነጋገር ባለሙያ ማፍራት ላይ ትኩረት ሰጥቶ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ሊሠራ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *