የኢትዮጵያ ሥጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በሥጋና ወተት አቅርቦት በሚፈለገው የጥራት ደረጃና መጠን የሥጋና የወተት ተዋጽኦ ለህብረተሰቡ ማድረስ ባለመቻሉ አገሪቱ በከፍተኛ መጠን ከውጭ እያስገባች እንደምትገኝ በመግለፅ ኢንሲቲትዩቱ ኃላፊነቱን በአግባቡ ሊወጣ እንደሚገባ የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡
ቋሚ ኮሚቴው በኢትዮጵያ ሥጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ሁለገብ ድጋፍ አሰጣጥና የቴክኖሎጂ ሽግግር አፈፃፀምን በተመለከተ የተከናወነ የክዋኔ ኦዲት ላይ ይፋዊ ስብሰባ ጥር 24 ቀን 2009 ዓ.ም አድርጓል፡፡
በስብሰባው ወቅት ቋሚ ኮሚቴው የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በኢንስቲትዩቱ ላይ ያከናወነውን የክዋኔ ኦዲት ግኝት መሰረት በማድረግ የኢንስቲትዩቱን ሁለገብ ድጋፍ አሰጣጥና የቴክኖሎጂ ሽግግር አፈፃፀምን በተመለከተ ኢንስቲትዩት ድክመት ያሳየባቸውን ተግባራት በመዘርዘር የተቋሙ የስራ ኃላፊዎች ማብራሪያ እንዲሰጡ ጠይቋል፡፡
ማብራሪያ እንዲሰጥባቸው ከተፈለጉት ጉዳዮች ውስጥ ኢንስቲትዩቱ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ያከናወነውን ኦዲት ተከትሎ የማሻሻያ የድርጊት መርሀ ግብር አዘጋጅቶ አለመላኩ፤ ለሥጋ፣ ለወተትና መኖ ኢንዱስትሪዎች ጥራቱንና ደህንነቱ የተረጋገጠ የዓለም ዓቀፍ መስፈርትን ያሟላ ምርት ለሀገር ውስጥና ለዓለም ገበያ እንዲያቀርቡ ድጋፍ አለማድረጉን፤ በሥጋ፣ በወተትና መኖ ማቀነባበር ላይ ለተሰማሩ ባለሃብቶች በቴክኖሎጂ መረጣ፣ በድርድር፣ በግንባታ፣ በተከላና ሙከራ ምርት ድጋፍ የማያደርግ መሆኑ በናሙና ተመርጠው በኦዲት ከታዩት አምራቾች ለማወቅ መቻሉን፤ በሥጋና በወተት ኢንዱስትሪዎች ሊለሙ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎች በምርምርና በስርፀት በመለየት ኢንዱስትሪዎቹ የምርምርና የስርፀት ክፍሎችን እንዲያቋቁሙ በማድረግ እና የውጭ ባለሃብቶች በዘርፉ እንዲሳተፉ በማድረግ ወጪ ቆጣቢ ቴክኖሎጂዎችን ወደ ኢንዱስትሪዎች ሊያሸጋግር የተገባው ሆኖ ሳላ አለማሸጋገሩና ድጋፍ አለማድረጉ ይገኙባቸዋል፡፡
በተጨማሪም ኢንስቲትዩቱ በወተት ማቀነባበር የተሰማሩ አካላትን በአገር ውስጥ ፍጆታ ብቻ ሳይሆን በኤክስፖርትና ወደ አገር ውስጥ የሚገባውን ወተት ለመተካት በሚያስችል (Import Substitution) ደረጃ ተወዳዳሪ ሆነው ለመቅረብ እንዲችሉ አለመደረጉን፤ የ2006 ዓ.ም የሥጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ድርጅታዊ መዋቅር የሰው ሃይል እቅድ ማስረጃ እንደሚያመለክተው በ5 ዓመት ውስጥ 44,604,941.56 ዶላር የሚያወጣ 17 ዓይነት ምርት ወደ አገር ውስጥ መግባቱን እና ይህም ወጪ በዓመት ሲሰላ 8,920,988.31 ዶላር እንደሚሆን፤ ወደ አገሪቱ የሚገባው የወተት ውጤቶች አማካይ እድገት 35.95% እንደሆነ እና የ2007 ዓ.ም የገበያ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በዓመት 20 ሚሊዮን ዶላር በሚሆን ወጪ ከውጭ አገር ወተት የሚገባ እንደሆነና ኢንስቲትዩቱ ይህን ወጪ ለመቀነስ የሚያስችል ድጋፍ አለማድረጉን የኦዲት ግኝቱ አሳይቷል፡፡
በሌላ በኩል ኢንስቲትዩቱ ባለብዙ ዘርፍ ጉዳዮችን /የሴቶች፣ ወጣቶች፣ አካል ጉዳተኞች/ ባካተተ መልኩ አቅዶ አለመስራቱን፤ የተለያ ንብረቶች/መሣሪያዎች/ እና ኬሚካሎችን ለብክነት ሊጋለጡ በሚችሉ ደረጃ መያዛቸውን፤ ኢንዱስሪዎቹ ከውጭ የሚገቡ የእንስሳት ምርቶችን ለመተካት የሚያስችሉ ምርቶችን በአገር ውስጥ በጥራትና በብዛት እንዲመረቱ የሚያስችል ስልት ቀይሶ ተግባራዊ አለማድረጉን፤ በሥጋ በወተትና መኖ ኢንዱስትሪ ልማት መልካም ተሞክሮ ያላቸው አገራትና ካምፓኒዎች ተለይተው ተሞክሮዎቹ ተቀናብረው በኤክስፖርት ቄራዎች፣ ወተትና መኖ መቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ተግባራዊ አለመደረጋቸውን እና ኢንስቲትዩቱ ሥጋና ወተት ወደሚልክባቸው መዳረሻ ገበያዎች እስኪደርሱ ድረስ የሱፐርቪዥን ሥራ በማድረግ ለቄራዎች እና ለወተት ማቀነባበሪያዎች ግብረመልስ መስጠት የሚጠበቅበት ቢሆንም በናሙና ተመርጠው በታዩ ኢንዱስትሪዎች ላይ የማስተካከያ እርምጃዎች በአግባቡ አለመተግበሩን በኦዲት ግኝቱ ተገልጾ ማብራሪያ ተጠይቆባቸዋል፡፡
የኢንስቲትዩቱ አመራሮች ለጥያቄዎቹ ምላሽ የሰጡ ሲሆን በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የተደረገው የክዋኔ ኦዲት በኢንስቲትዩቱ ዕይታ ውስጥ ያልነበሩ ጉዳዮችንና ሊተገበሩ የሚችሉ ጉዳዮችን ያመላከተ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ከሊፋ ሁሴን ምላሽ ሲሰጡ ከኦዲት ግኝቱ በኋላ በርካታ የማስተካከያ ሥራዎችን መስራታቸውንና በተለይም ከጥራት ጋር በተያያዘ የተነሱ ችግሮችን ለመቅረፍ ብዙ ርቀት መጓዛቸውን፤ የወተት ግብይት ከባለድርሻ አካላት ጋር ቅንጅት ያልነበረው በመሆኑ ሥራውን እንደጎዳው እና የሥጋና ወተት ውጤቶችን በአገር ውስጥ ምርቶች መተካትን በተመለከተ (Import Substitution) ያለውን ችግር ለመቅረፍ የአገር ውስጥ አምረቾች ጥራት ያለው ምርት በገበያ ላይ ይዘው እንዲገኙ በሚያስችል አግባብ በፖሊሲ ለመደገፍ ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡
ሌሎች የተቋሙ አመራሮች በሰጡት ምላሽ ኢንስቲትዩቱ የተለያዩ የሥጋና ወተት ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ማሽነሪዎችን ከውጭ አገር ማስመጣት ሲፈልጉ በተቋማቸው ምክር እንደሚያገኙ፣ በላብራቶሪ ፍተሻ ላይ ለፋብሪካዎች ስልጠና እንደሚሰጡ፣ የወተት ግብይት ጥራት ላይ የተመሰረት የክፍያ ሥርዓት እንዲኖር ቢጋር ማዘጋጀታቸውን፣ የወተት ምርት በተለያየ ዓይነት በማዘጋጀት ለአገር ውስጥ ገበያ እንዲውል ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙና ምርቱ በጎረቤት አገሮችም መሸጥ በሚያስችል ደረጃ እንዲመረት ጥረት እየተደረጋ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በሰጡት አስተያየት ኢንስቲትዩቱ ለድርጅቶቹ የሚያደርገው የድጋፍና የክትትል ሥራዎች መልካም መሆናቸውን ነገር ግን በተጠናከረ መልኩ ሊሰጥ እንደሚገባ፣ ከዘርፉ ስፋትና መንግስት ከሰጠው ትኩረት አንፃር ተቋሙ ሰርቻለው ብሎ መቀመጥ እንደሌለበት በመግለፅ ተቋሙ በአዲስ አበባ ብቻ የታጠረ ተደራሽነቱን መስፋት እንደሚኖርበት፤ ፍላጎትና አቅርቦትን ማጣጣም እንደሚጠበቅበት፤ ኢንዱስትሪዎቹ በዘርፉ ጥናትና ምርምር ሥራዎችን መስራት እንዳለባቸው፤ ባለብዙ ዘርፍ ስራዎች ተድበስብሰው ሊታለፉ እንደማይገባና በተለይም መንግስት በዚህ ዘርፍ በተለየ ሁኔታ ሴቶችና አካል ጉዳተኞች ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚፈልግ በመሆኑ ስትራቴጂካሊ ታቅዶ ሊሰራበት እንደሚገባ፤ የተቀናጀ አሰራር ከባለድርሻ አካላት ጋር ሊኖር እንደሚገባ፤ አዲስነቱን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም የተደራረቡ ችግሮች ሳይፈጠሩ አስቀድሞ ስርዓት በመዘርጋት ውጤታማ ሥራ መሥራት እንደሚጠበቅበት፤ ተቋሙ የተሰማራበት ኃላፊነት የኢኮኖሚ፣ የጤና፣ የቴክኖሎጂና የፖለቲካ ጉዳዮች ያሉት በመሆኑ ኢንስቲትዩቱ የሚጠበቅበትን እድገትና የሚያጋጥሙትን ተግዳሮቶች በማሰብ ሊሠሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ በሰጡት አስተያየት አገሪቱ በአፍሪካ በቀንድ ከብት በአንደኛ ደረጃ ስሟ እየተጠራ ባለበት ሁኔታ ከዚህ ተጠቃሚ አለመሆኗን፤ ዘርፉ ስትራቴጂካሊ የህብረተሰቡን ኑሮ በመለወጥ ረገድ ትልቅ ፋይዳ ያለው በመሆኑ ታስቦ ሊሠራበት እንደሚገባ፣ የውጭ ባለሃብቶች በስፋት እንዲሰማሩበት ማድረግ እንደሚጠበቅ፣ የቁም ከብቶች ቢያንስ በአገር ውስጥ ተበልተው ወደውጭ ኤክስፖርት የሚደረጉበትን አሠራር መዘርጋት እንደሚያስፈልግ፣ ለባለሃብቶች የሚደረገው ድጋፍ አነስተኛ በመሆኑ ጥናት ተደርጎ በአግባቡ ሊደገፉ እንደሚገባ፣ የወተት አቅርቦትን በተመለከተም ከወተት ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎቹ የሚሰማው እጥረት ያለ እንደሆነ በመሆኑ ይህን ለማሳደግ የአቅርቦት ሰንሰለቱ ውስጥ ያሉ ችግሮችን ማሻሻል እንደሚያስፈልግ፣ የፋብሪካዎቹን ላብራቶሪ ከማጠናከርና ከመደገፍ ባሻገር በማዕከል ደረጃ የጥራት ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ የሚያስችል የተጠናከረ ላብራቶሪ ሊኖር እንደሚገባ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማምጣት ማለማድና ማስፋፋት እንደሚጠይቅ እንዲሁም በሥጋና ወተት ምርት የተሸለ ውጤት ማስመዝገብ የሚቻለው ጥራት ላይ አተኩሮ በመስራትም በመሆኑ ተቋሙ ለጥራት ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡
የወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አምባሰዳር መስፍን ቸርነት በመጨረሻ ባስተላለፉት መልዕክት አገሪቱ ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር በምታደርገው ሽግግር ሂደት ኢንስቲትዩቱ ትልቅ ተልዕኮ ያለው በመሆኑ የ2ኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መሠረት አድርጎ ሊሠራ እንደሚገባ፤ የቁም እንስሳት ወደውጭ አገር መላክ ላይ ያለውን ችግር ለመቅረፍ ከባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት እንደሚኖርበት፤ ጥራት ማስጠበቅ ላይ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ለአገር ውስጥና ለውጭ አቅርቦት የሚመጥን እስታንዳርድ ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ፣ የአገር ውስጥም ሆኑ የዓለም ዓቀፍ ተቋማት የአገር ውስጥ ምርት እንዲጠቀሙ ተጠናክሮ ሊሠራ እንደሚገባ እና የወተትና ሥጋ ማቀነባበሪያ ላይ ትኩረት ሰጥቶ ተቋሙ ሊሠራ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡