የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገነባቸውን የህንፃ ፕሮጀክቶች የአዋጭነነት ጥናት ሳያካሂድ መሆኑ ተገለጸ፡፡
በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መጋቢት 27 ቀን 2015 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የ2013/14 በጀት ዓመት የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ላይ ይፋዊ ህዝባዊ የውይይት መድረክ አካሂዷል፡፡
ዩኒቨርስቲው የፕሮጀክቶች የአዋጭነት ጥናትና ቅድመ ትግበራ ግምገማ ስራ ሳያከናውን ወደ ግንባታ በመግባቱ በጊዜ ተጠናቀው ለተጠቃሚው ማህበረሰብ አገልግሎት መስጠት አለመቻላቸው ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም ግንባታዎቹ የፕላን ስምምነት እና የግንባታ ፈቃድ ማስረጃዎች ሳያሟሉ የተገነቡ መሆናቸው እና በውል ስምምነቱ ዝርዝር መሰረት በተቀመጠው የጥራት ደረጃ ልክ ግንባታቸው አለመከናወኑም በኦዲት ሪፖርቱ ታይቷል፡፡
ሥራቸውን ላቋረጡ የሥራ ተቋራጮች ከተከፍለ ብር 59,314,445.07 ቅድመ ክፍያ ውስጥ ብር 52,834,998.48 በወቅቱ ያልተወራረደ መኖሩ እና በወሊሶ ካምፓስ ከካሳ ክፍያ ጋር ተያይዞ ለተፈፀመ ክፍያ ማስረጃ አለመቅረቡ በውይይቱ ተነስቷል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ደሳለኝ በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲው ወደ ህንፃ ፕሮጀክቶች ግንባታ ሲገባ የማህበረሰቡን ፍላጎት መሰረት ተደርጎ እንጂ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ትንታኔ ተሰርቶ እንዳልሆነ አብራርተው ለፕሮጀክቶቹ መጓተትም በአገሪቱ ያሉ የውጭ ምንዛሬ መጠን መለዋወጥ እንቅፋት እንደሆነባቸው ገልጸዋል፡፡
አያይዘውም በዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥ የተገነቡ ህንፃዎቸ የፕላን ስምምነት እና የግንባታ ፈቃድ ማስረጃዎች ሟሟላት እንደነበረባቸው እንደማያውቁ እና ከኦዲት ግኝቱ በኋላ ግን ትምህርት እንደወሰዱበት አብራርተዋል፡፡
ያልተሰበሰቡ ሂሳብ ለማስመለስ በክስ ሂደት ላይ መሆናቸው ጠቅሰው የካሳ ክፍያ በተመለከተ ለወሊሶ ከተማ አስተዳደር ባቀረበው ማስረጃ መሰረት ክፍያው እንደተፈጸመ ፕሬዝዳንቱ ጠቁመዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ም/ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ አበራ ታደሰ በዩኒቨርሲቲው በኩል የተሰጡ ምላሾችን ተከትሎ በሰጡት አስተያየት ዩኒቨርሲቲው የኦዲት ግኝቶቹን ይጠቅመናል ብሎ ከመውሰድ አኳያ ክፍተት እንዳለ የተሰጠው ምላሽ የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡
የአዋጨነት ጥናት ሲባል የኢኮኖሚ አዋጭነት ብቻ ሳይሆን በውስጡ ብዙ ዝርዝር ጉዳዮች እንዳሉት መረዳት እንደሚያስፈልግ ም/ዋና ኦዲተሩ ጠቅሰው ዩኒቨርሲቲው ተገቢውን ጥናት ሳያከናውን ወደ ግንባታ መግባቱን ጠቅሰዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴ አባላትና ሌሎች የኦዲት ባለድርሻ አካላት በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲው ለታዩ የኦዲት ግኝቶች ዋነኛ መነሻ የህንፃ ፕሮጀክቶች የአዋጭነት ጥናት ሳይከናወን ወደ ግንባታ በመግባቱ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
አያይዘውም በአገሪቱ የዋጋ ግሽበት ባለበት ሁኔታ የህንጻ ግንባታ ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ባለመጠናቀቃቸው የመንግስት ሀብትና ገንዘብ እንዲባክን እና ተጨማሪ ወጪዎች እንዲወጡ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው በመ/ቤቱ ኦዲት ለማድረግ ሲታቀድ ዝርዝር መስፈርት ተዘጋጅቶ እንደሆነ አብራርተው በዩኒቨርሲው የታዩ የኦዲት ግኝቶች ትኩረት እንዲሰጣቸው የተፈለገው ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በተጨማሪ ሌሌች መሰል ችግር የሚታዩባቸው ተቋማት ከዚህ ግኝት መማር አለባቸው በሚል ነው ብለዋል፡፡
አያይዘውም የህንፃ ግንባታዎች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ባለመጠናቀቃቸው መስጠት የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት እንዳይሰጡ እና ለተጨማሪ ወጪ እየዳረጉ መሆናቸውን ጠቅሰው እንደሀገር የፕሮጀክት አስተዳደር ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ክርስትያን ታደለ በበኩላቸው ይህንን የኦዲት ግኝቶች መነሻ በማድረግ ዩኒቨርሲቲው ወዴት አቅጣጫ እየሄደ እንዳለ በመገንዘብ አሰራሮቹን ለማሻሻል እንዲጠቀምበት አሳስበዋል፡፡
አክለውም ዩኒቨርሲቲው የተሰጡትን አስተያየቶች መሰረት በማድረግ በግኝቶች ላይ የማሻሻያ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል የተከለሰ የድርጊት መርሀ ግብር በማዘጋጀት ማስተካከያ እንዲያደረግ እና በየወቅቱ የሚወሰዱ የማስተካከያ እርምጃዎችንም በየ3 ወሩ ለሚመለከታቸው አካላት ሪፖርት እንዲያቀርብ አሳስበዋል፡፡
ባለድርሻ አካላትም ተገቢውን ክትትልና ቁጥጥር እንዲያደርጉ፤ በወንጀል እና በፍታብሄር የሚያስጠይቁ ጉዳዩች ካሉም ተለይተው እንዲቀርቡ በተጨማሪም ውላቸውን ያቋረጡ የስራ ተቋራጮች ከተከፈለው ቅድመ ክፍያ ተሰብሳቢ በወቅቱ እንዲሰበሰብ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አሳስበው ፕላንና ልማት ሚኒስቴር “የፕሮጀክት አስተዳደር” በመንግስት መዋቅር ውስጥ እንዲካተት አስፈላጊውን ጥናት አከናውኖ እንዲያቀርብ አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡




