News

22ኛው የዋና ኦዲተር መ/ቤቶችና ባለድርሻ ካላት ጉባኤ ተካሄደ

22ኛው የፌዴራል፣ የክልል፣ የፌዴራል ከተሞች አስተዳደር ዋና ኦዲተር መ/ቤቶችና ባለድርሻ ካላት ዓመታዊ ጉባኤ ተካሄደ፡፡

ከጥቅምት 29 እስከ ህዳር 2 ቀን 2016 ዓ.ም ለአራት ተከታታይ ቀናት በሀዋሳ ከተማ የተካሄደው ጉባኤ በርካታ የጋራ ስራዎችን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ በመምከር ውሳኔ ያሳለፈ ሲሆን በተለይም በ2014 ዓ.ም በሀረሪ ክልል በሀረር ከተማ በተካሄደው በ21ኛው ዓመታዊ መደበኛ ጉባኤ የተቀመጡ የስራ አቅጣጫዎችን አፈጻጸም በእያንዳንዳቸው ዋና ኦዲተር መ/ቤቶችና ባለድርሻ አካላት በቀረቡ ሪፖርቶች መሰረት ገምግሟል፡፡

በጉባኤው መክፈቻ ስነስርዓት ላይ የተገኙትን የሲዳማ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞን ጨምሮ የሲዳማ ክልል ዋና አፈጉባኤ የተከበሩ ወ/ሮ ፋንታዬ ከበደ እንዲሁም የሲዳማ ክልል ዋና ኦዲተር አቶ ሲንቦ ሽብሩ የጉባኤውን ፋይዳ፣ የኦዲት አሠራርንና ጠቀሜታ እንዲሁም  በፌዴራልና በክልል ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች መካከል ያለውን ውጤታማ የስራ ግንኙነት አስመልክቶ ንግግር አድርገዋል፡፡

የክልሉ የስራ ኃላፊዎች በንግግራቸው እንደገለጹት የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በክልልና በከተማ አስተዳደር ደረጃ የሚገኙ ዋና ኦዲተር መ/ቤቶችን ለመደገፍና በኦዲቱ ስራ ለማብቃት እየሰራ ስላለው ስራ በዝርዝር ገልጸው እያደረገ ስላለው ሁለገብ ድጋፍና ትብብር መ/ቤቱን አመስግነዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው ጉባኤው ከተመሰረተበት 1989 ዓ.ም ጀምሮ ያለውን እንቅስቃሴ በዝርዝር አስቀምጠው በየጊዜው እየተካሄዱ ያሉት መደበኛ ዓመታዊ ጉባኤዎችና በ2015 ዓ.ም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ ከተማ ቦንጋ የተካሄደውን የዋና ኦዲተር መ/ቤቶች ልዩ ጉባኤ ጨምሮ ሌሎች በየጊዜው የተደረጉ የውይይት መድረኮች ለሀገሪቱ የኦዲት ስራ በርካታ ፋይዳንና ውጤትን ያስገኙ ምክክሮች የተካሄዱባቸው ናቸው ብለዋል፡፡

በተለይም የኦዲት ድግግሞሽን ለማስቀረት አግባብነት ባላቸው አዋጅና መመሪያ ተደግፎና ስልጠናን መሰረት ያደረገ አሠራር ተበጅቶለት በሙከራ ደረጃ በስራ ላይ እየዋለ ባለው የነጠላ ኦዲትና በሌሎች የጉባኤው ውሳኔ በተላለፈባቸው ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ የተሰሩ ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን ክብርት ዋና ኦዲተሯ ገልጸዋል፡፡

አክለውም በነጠላ ኦዲት የሙከራ ትግበራው አበረታች አፈጻጸም ያሳዩትን ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች እና በሌሎች መስኮችም ለተከናወኑ ውጤታማ ተግባራት የጉባኤውን ተሳታፊዎች አመስግነው ክፍተት በሚታይባቸው የኦዲት አሠራሮች ላይ የተጠናከረ ስራ መስራትና በቀጣይ ጊዜያት በሁሉም ክልሎች ተግባራዊ ለሚደረገው የነጠላ ኦዲት ትግበራ ሁሉም አካላት የድርሻቸውን በትኩረት እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

በመድረኩ ላይ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በአራት የተመረጡ ክልሎች በሙከራ ደረጃ ሲካሄድ ስለነበረው የነጠላ ኦዲት አተገባበርና ውጤት በጥናት ተደግፎ የተዘጋጀ ሪፖርቱን ለጉባኤው አቅርቦ ውይይት ተካሂዶበታል፡፡

መ/ቤቱ ባደረገው ጥናት ላይ ተመስርቶ ባቀረበው ሪፖርት መሰረት የኦዲት ድግግሞሽን የሚያስቀረውን የነጠላ ኦዲት ትግበራ በሙከራ ደረጃ ያከናወኑት የኦሮሚያ፣ የሲዳማ፣ የቀድሞው የደቡብ ብ/ብ/ሕ ክልሎች እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች ትግበራውን በውጤታማነትና ለሌሎች ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች ቀጣይ ተመሳሳይ ትግበራ ለስኬት ሊያበቁ የሚችሉ መንገዶችን በሚያመላክት ሁኔታ መፈጻመቸው ተገልጾ ለዚህም ዕውቅና የሚሆን የምስክር ወረቀት፣ የዋንጫና ላፕቶፕ ኮምፒውተር ማበረታቻ ተበርክቶላቸዋል፡፡

የምክክር ጉባኤው በቆይታው በሌሎች ጠቃሚ የኦዲት አሠራሮች ላይ በጥልቀት ተወያይቶ ፋይዳ ያላቸው ውሳኔዎችን ያሳለፈ ሲሆን በተለይም ተቋማዊ አደረጃጀትን ፈትሾ የማሻሻያ እርምጃ መውሰድ፣ የኦዲት ጥራትንና ሽፋንን ማሳደግ፣ የተመላሽ ገንዘብን በ60% ማሳደግ፣ የአቅም ግንባታ ሥራዎችን ማጠናከር፣ የሚዲያ ሽፋንን ማሳድግ፣ ለአከባቢና ለልዩ ኦዲት ትኩረት መስጠት፣ የነጠላ ኦዲት ስርዓትን በሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች መተግበር፣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ማሳደግ እንዲሁም በሰው ኃይል ላይ ሊሰሩ የሚገባቸውን ሁኔታዎች ማጠናከር የሚሉት እስከ ቀጣዩ 23ኛ ዓመታዊ ጉባኤ ድረስ በጉባኤው ተሳታፊዎች ትኩረት ተሰጥቷቸው እንዲተገበሩ አቅጣጫና ውሳኔ ተቀምጦላቸዋል፡፡

ከጉባኤው መጠናቀቅ በኋላም ተሳታፊዎች በሲዳማ ክልል የሚገኘውን የወንሾ ባህላዊ ዳኝነት የሚከናወንበትን ስፍራና በስፍራው ላይ የሚካሄደውን የባህላዊ ዳኝነት ሂደት ጎብኝተዋል፡፡

በተጓዳኝም የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤና ም/ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ አበራ ታደሠ በጉባኤው ተሳታፊ ከነበሩ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ሠራተኞች ጋር በመሆን የመ/ቤቱን የደቡብ ቅርንጫፍ ወኪል መ/ቤት የስራ እንቅስቃሴ ተመልክተዋል፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *