14ኛው የአፍሪካ ዋና ኦዲተሮች ማህበር /AFROSAI/ ጠቅላላ ጉባዔ እ.ኤ.አ ከጥቅምት 23-27/ 2017 ዓ.ም በናሚቢያ ዋና ከተማ ዊንድሆክ ተካሄደ፡፡ በጉባኤው በኦዲት ዘርፍ ምክትል ዋና ኦዲተር በክብርት ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ የተመራ ሦስት አባላት የያዘ ልዑክ ተሳትፏል፡፡
ክብርት ወ/ሮ መሰረት እንደገለጹት በጉባኤው ላይ የAFROSAI 2015-2020 ስትራቴጂክ ዕቅድ፣ የ2018-2020 በጀት፣ የፋይናንስ የኦዲት ሪፖርት እንዲሁም የአቅም ግንባታና የእውቀት ሽግግር ኮሚቴ የስራ አፈጻጸምና የቀጣይ የስራ እቅድ የጸደቁ ሲሆን የAFROSAI ዋና መጽሄት (Africa Journal of Comprehensive Auditing) በኤሌክትሮኒክ የመገናኛ ዘዴ እንዲዘጋጅ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
በሌላ በኩል የአፍሪካ የፈረንሳይኛ ተናጋሪ ዋና ኦዲተሮች ማህበር (AFROSAI-F)፣ የአፍሪካ የእንግሊዘኛ ተናጋሪ ዋና ኦዲተሮች ማህበር (AFROSAI-E) እና የአፍሪካ የአረብኛ ተናጋሪ ዋና ኦዲተሮች ማህበር (AFROSAI-I) የሥራ ሪፖርት እንዲሁም የተለያዩ በአጋር ድርጅቶች የተዘጋጁ ጥናታዊ ፅሑፎችም ቀርበዋል፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የአካባቢ ጥበቃ ኦዲትን በተመለከተ በቻድ ወንዝ ላይ የአካባቢ ተፅዕኖ ጥናት የተደረገ የኦዲት ሪፖርት የቀረበ ሲሆን በቀጣይ የክትትል ኦዲት የሚደረግ መሆኑን እና የአባይ ወንዝ ላይም በተመሳሳይ የአካባቢ ኦዲት ለማድረግ መታሰቡን የአከባቢ ኦዲት አጥኚ ቡድን (Working Group on Environmental Auditing፡ WEGA) በእቅዱ አቅርቧል፡፡
ኢትዮጵያም የአባይን ወንዝ በተመለከተ የታሰበውን የኦዲት እቅድ አስመልክቶ ያላትን ሀሳብ ለጉባኤው በወቅቱ ያቀረበች ሲሆን የአባይን ወንዝ ኦዲት የአካባቢ ተጽእኖ ኦዲት ለማድረግ ከመታሰቡ በፊት በመጀመሪያ የተፋሰሱ ሀገራት የጋራ መግባባት ላይ መድረስ እንደሚገባቸውና ይህን የኦዲት እቅድ ለማዘጋጀት ሲታሰብ የእነዚህ የተፋሰሱ አባል ሀገራት ሊሳተፉበት እንደሚገባ ገልጻለች፡፡ ከመድረኩም በተሰጠ ምላሽ የተፋሰሱን አገሮች ሳያካትትና እውቅና ሳያገኝ ኦዲት የማይደረግ መሆኑንና ኦዲቱም ገና በእቅድ ደረጃ የሚገኝ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር ልዑክ በናሚቢያ በተደረገው ጉባኤ በርካታ ልምዶችን እንዳገኘና በተለይም የዘላቂ የልማት ግቦችን (SDG) አተገባበር መ/ቤቱ ወደፊት በክዋኔ ኦዲት ማካተት የሚችልበት ሁኔታ እንዳለ ትምህርት መገኘቱን ክብርት ወ/ሮ መስረት ገልጸዋል፡፡
በጉባኤው ቀጣይ ለሶስት አመት የሚመሩ አባላት ተሰይመዋል፡፡ በዚህም መሰረት የAFROSAI ፕሬዚዳንት የነበሩት የግብጽ ዋና ኦዲተር ለናምቢያ ዋና ኦዲተር የፕሬዚዳንት ሥልጣኑን ያስረከቡ ሲሆን የቻድ ዋና ኦዲተር ደግሞ ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን ተመርጠዋል፡፡
ስብሰባው በየሦስት አመቱ የሚካሄድና የሦስቱን ቋንቋ ተናጋሪ አገሮች (AFROSAI-F)፣ (AFROSAI-E) እና (AFROSAI-I) ያቀፈ ሲሆን ሌሎች አጋር ድርጅቶች የሚሳተፉበት እንዲሁም ላለፉት ሦስት አመታት የተከናወኑ ተግባራት የሚገመገሙበትና በቀጣይ ሦስት አመታት የሚሰሩ ስራዎች በአባሎች ታይቶ የሚፀድቁበት መድረክ ነው፡፡