በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደር ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በአሶሳ ዩኒቨርስቲ በ2012 በጀት ዓመት ያካሄደውን የሂሳብ ኦዲት መሠረት በማድረግ ይፋዊ ህዝባዊ ስብሰባ አካሂዷል፡፡
ዩኒቨርስቲው በገቢና ወጪ ሂሳብ፣ በተሰብሳቢና ተከፋይ እንዲሁም በንብረት አያያዝ በርካታ ከህግና ከመመሪያ ውጪ ፈጽሞ መገኘቱ በኦዲት ሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡
የቋሚ ኮሚቴውም የአሶሳ ዩኒቨርስቲ ከህግና መመሪያ ውጪ ለፈጸማቸው በርካታ ጥሰቶች የተቋሙ አመራሮች ምላሽና ማብራሪያ እንዲሰጡ ጠይቀዋል፡፡
የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ከማል አብዱራሂም በሰጡት ማብራሪያ የኦዲት ግኝቶቹ ትክክልና አግባብነት ያላቸው መሆኑን ጠቁመው በአብዛኞቹ የኦዲት ግኝቶች ላይ የማስተካከያ እርምጃ መውሰዳቸውን አስረድተዋል፡፡
በተለይም መመለስ ያለባቸው አላግባብ የተከፈሉ ክፍያዎችን በማስመለስ፣ በገቢና በወጪ ሂሳብ አያያዝ እንዲሁም በንብረት አያያዝ የነበሩ ችግሮችን በመቅረፍ ረገድ በርካታ ሥራዎችን መሰራታቸውን አብራርተዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው አባላት በበኩላቸው ዩኒቨርስቲው ለኦዲት ግኝቱ ትኩረት በመስጠት በግኝቶቹ ላይ ተገቢውን የእርምት እርምጃ ለመውሰድ የሄደበት እርቀት የሚያበረታታ መሆኑን ገልጸው ነገር ግን ህግና መመሪያን ተከትሎ ሥራዎችን በመስራት ረገድ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው ዩኒቨርስቲው ለኦዲት ግኝቱ ትኩረት ሰጥቶ የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ መጀመሩ ሊጠናከር የሚገባው ነው ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ ዩኒቨርስቲው አሁንም ያላስተካከላቸውና የእርምት እርምጃ ያልወሰደባቸው የኦዲት ግኝቶች እንዳሉ፤ የተሰብሳቢ ሂሰብ ከአመት ዓመት እየጨመረ እየመጣ ያለበት ሁኔታ ያለ በመሆኑ ትኩረት በመስጠት ሊሰበስብ እንደሚገባ፤ የተከፋይ ሂሳብ እየቀነሰ ቢመጣም አሁንም ያልተከፈሉ ክፍያዎች በመኖራቸው በወቅቱ መከፈል እንዳለባቸው ዋና ኦዲተሯ አስገንዝበዋል፡፡
የሚወገዱ ንብረቶችን በተመለከተም ከመንግስት ግዢና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ጋር በጋራ መሥራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመው በተለይም ከመመሪያ ውጪ በማኔጅመንት እያጸደቁ የሚሠሩ አሰራሮች በፍጹም ተቀባይነት የሌላቸው በመሆኑ ሊስተካከሉ እንደሚገባ ክብርት ወ/ሮ መሠረት አሳስበዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ክርስቲያን ታደለ በበኩላቸው ዩኒቨርስቲው የኦዲት ግኝቶቹን በመልካም ተመልክቶ ለማረምና ለማሻሻል ዝግጁ መሆኑ በጎ ቢሆንም በተደጋጋሚ የሚታዩ የመመሪያ ጥሰቶች ሊታረሙ እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
በቀጣይም ዩኒቨርስቲው አስከ ሐምሌ 5 ቀን 2014 ዓ.ም የኦዲት ማሻሻያ የድርጊት መርሃ ግብር አዘጋጅቶ እንዲያቀርብ፤ ተጠያቂነትን በሚያስከትሉ ጉዳዮች ላይ በየደረጃው እርምጃ ወስዶ በአንድ ወር ጊዜ ሪፖርት እንዲያቀርብ እንዲሁም ህግና መመሪያዎችን አክብሮ ተልዕኮውን እንዲወጣ የተከበሩ አቶ ክርስቲያን አሳስበዋል፡፡
በተመሳሳይ የመንግስት ግዢና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት በሽያጭ የሚወገዱ ንብረቶችን እንዲወገዱ በማድረግ በ3 ወር ጊዜ ውስጥ ሪፖርት እንዲያቀርብ እና የገንዘብ ሚኒስቴርም በተለይም ከተማሪዎች የምግብ ተመን ጋር በተያያዘ ያሉ ችግሮችን እልባት ሰጥቶ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ሪፖርት እንዲያቀርብ አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡