የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ያካሄደውን የ2013 በጀት ዓመት የሒሳብ ኦዲት በሚመለከት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ግንቦት 2 ቀን 2015 ዓ.ም ይፋዊ የህዝብ ውይይት መድረክ አካሂዷል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው ከዩኒቨርሲቲው አመራሮችና ሌሎች የኦዲት ባለድርሻ አካላት ጋር ባደረገው ውይይት እንደተገለጸው ዩኒቨርሲቲው በበርካታ ብልሹ አሠራሮች ውስጥ የቆየና አሁንም ድረስ ተቀባይነት በሚያሳጣ የኦዲት አስተያየት (Adverse Audit Opinion) ውስጥ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
በቅርቡ አዳዲስ አመራሮች የተመደቡለት የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ አሁን ድረስ ቀድሞ ከነበረው ብልሹ አሠራር ተንከባለው የመጡ በርካታ ጉድለቶች እንዳሉበት በ2013 አልፎም በ2014 በጀት ዓመት በተካሄደ ኦዲት መረጋገጡ በመድረኩ ላይ ተነስቷል፡፡
በወቅቱ መሰብሰብ ያልተቻለ በብር 63.4 ሚሊዮን የሚገመት ተሰብሳቢ ሂሳብ መታየቱን ጨምሮ አዋጅና መመሪያን የጣሱ ግዥዎች መደረጋቸው፣ ከውል በላይ ለግንባታ ተቋራጭ የተከፈለ ብልጫ ክፍያ መኖሩ፣ ያለአግባብ የተከፈለ ደመወዝና አበል በኦዲቱ ወቅት መታየቱ እንዲሁም በሂሳብ አመዘጋገብ እና ህግና ስርዓትን ያልተከተለና ለብልሹ አሠራር የተጋለጠ የውስጥ ገቢ አሠራር ችግሮችና ሌሎች የአሰራር ክፍተቶች መኖራቸው በኦዲቱ መረጋገጡ በመድረኩ ላይ ተገልጿል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍቃዱ ወ/ማርያም እና ሌሎች ባለሙያዎች በመድረኩ ለተነሱ የኦዲት ግኝቶች ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ዩኒቨርሲቲው በበርካታ የአሠራር ችግሮች ውስጥ መቆየቱንና የኦዲት ግኝቶቹም ትክክለኛ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
እርሳቸውን ጨምሮ የዩኒቨርሲቲውን አመራር የተረከቡ አዳዲስ አመራሮችና ባለሙያዎች በዩኒቨርሲቲው የነበሩትን ሰፊ የአሠራርና የአቅም ውስንነት ጉድለቶች ለማረም ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ፍቃዱ የዩኒቨርሲቲውን ችግሮች ለመቅረፍ ተጨባጭ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንና ጊዜን የሚጠይቁ ቀሪ የማስተካከያ እርምጃዎችን በቀጣይ ለመውሰድ ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸው ለዚህም ቋሚ ኮሚቴውና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ጠይቀዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴ አባለትና በላድርሻ አካላት በበኩላቸው አሁን ያለው የዩኒቨርሲቲው አመራር አዲስ እንደመሆኑ የቆዩ በርካታ ክፍተቶችን ለማረም ጊዜ የሚያስፈልገው ቢሆንም ቀደም ሲል የነበሩ ችግሮችን ለመቅረፍ እና በተለይም በአስተዳደራዊ ሁኔታዎች፣ በፋይናንስ፣ በአሠራር እንዲሁም በንብረት አስተዳደር ረገድ ያሉትን ችግሮች ለማስተካከል ቀጣይነት ያለው ጥረት ማድረግ ያስፈልገዋል ብለዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በሰጡት አስተያየት ዩኒቨርሲቲው ተደጋጋሚ በሆነ ተቀባይነት በሚያሳጣ የኦዲት አስተያየት ውስጥ የቆየና አንዳንድ የአሠራር ጉድለቶችም አሁንም ድረስ እየታዩበት በመሆኑ አመራሩ ችግሮቹን በዘላቂነት ለመቅረፍ ትልቅ ሃላፊነት አለበት ብለዋል፡፡
በተሰብሳቢ ሂሳቦች፣ ህጋዊ ባልሆኑ የግዥ አፈጻጸሞች፣ ህጋዊ አሠራርን ባልተከተሉ ክፍያዎች፣ በውስጥ ገቢ አሠራሮች እና በንብረት አያያዝና አጠቃቀም ስርዓት ረገድ የሚታዩ ክፍተቶችን በአፋጣኝ ማስወገድ እንደሚገባ ያሳሰቡት ክብርት ዋና ኦዲተሯ ግዥዎች ፍላጎትንና ጥናትን መሰረት አድርገው እንዲፈጸሙና የውስጥ ገቢ ማስገኛ ፕሮጀክቶችም የተቋሙን አቅም ባገናዘበና ወጪያቸውን መሸፈን በሚያስችላቸው ሁኔታ ተጠንተው መተግበር አለባቸው ብለዋል፡፡
የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ክርስትያን ታደለ በሰጡት የማጠቃለያ ሀሰብም አዲሱ አመራር ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር አብሮ በመስራት ዩኒቨርሲቲው የሚታዩበትን በርካታ የአሠራር፣ የፋይናንስ፣ የህግ፣ የፖሊሲና ሌሎች ክፍተቶችን የማረም ከፍተኛ ኃላፊነት አለበት ብለዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው በተሰጡ የኦዲት ግኝት ማሻሻያ አስተያየቶች መሰረት በ15 ቀናት ውስጥ የድርጊት መርሀ ግብር አዘጋጅቶ እንዲያቀያርብ እና የማሻሻያ እርምጃዎችን አፈጻጸም ሂደቱንም በየሩብ ዓመቱ ሪፖርት እንዲያደርግ አቅጣጫ ያስቀመጡት ሰብሳቢው ሌሎች ባለድርሻ አካላትም በሚመለከቷቸው ጉዳዮች ዙሪያ የክትትል፣ የቁጥጥር እና የድጋፍ ስራዎችን እንዲያከናውኑ አሳስበዋል፡፡