News

ዩኒቨርሲቲው በታዩበት የኦዲት ግኝቶች ላይ የማሻሻያ እርምጃዎች ለመውሰድ እያደረገ ያለው ጥረት አበረታች መሆኑ ተገለጸ፡፡ *በቀሪ ግኝቶች ላይ ቀጣይ እርምጃዎችን እንዲወሰድ ተጠይቋል፡፡

የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በ2013 በጀት ዓመት የፋይናንስ አሠራሩ እና በንብረት አያያዝና አጠባበቅ ስርዓቱ ላይ ጉልህ ክፍተቶች እንደነበሩበት ተገለጸ፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በዩኒቨርሲቲው የ2013 በጀት ዓመት የፋይናንስ እና ንብረት አስተዳደር ሥርዓት ላይ ያደረገውን የሂሳብ ህጋዊነት ኦዲት መሰረት ያደረጉ ግኝቶች የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከዩኒቨርሲቲው አመራሮችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ሚያዚያ 18 ቀን 2015 ዓ.ም ባካሄደው ይፋዊ ህዝባዊ ስብሰባ ላይ ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

በኦዲቱ ወቅት በገቢና ወጪ ሂሳብ፣ በደመወዝ እና አበል አከፋፈል፣ በተሰብሳቢ ሂሳቦች፣ በክፍያ ስርዓት፣ በውስጥ ገቢ አሠራር፣ በሂሳብ አመዘጋገብ እና በጉዳት ካሳ አከፋፈል ረገድ በርካታ ክፍተቶች መታየታቸው የተገለጸ ሲሆን በውላቸው መሰረት ጊዜያቸውን ጠብቀው ያልተጠናቀቁ የግንባታ ፕሮጀክቶች ሂደት፣ በተሸከርካሪ ጥገና ሥርዓት እና በንብረት አያያዝና አስተዳደር ረገድም ተገቢ ያልሆኑ አሠራሮች መታየታቸው ተጠቁሟል፡፡

የዩኒቨርሲቲውን ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ደሳለኝን ጨምሮ ሌሎች የተቋሙ አመራሮች የኦዲት ግኝቶቹ ትክክለኛ መሆናቸውን ጠቅሰው በተሰጠው የኦዲት ማሻሻያ አስተያየት መሰረት በብዙዎቹ ላይ የማሻሻያ እርምጃዎች መወሰዳቸውንና ቀሪ የአሰራር ክፍተቶችን ለማስወገድ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴ አባላቱና ባለድርሻዎች ዩኒቨርሲቲው የኦዲት ግኝቶቹን ተቀብሎ የማሻሻያ እርምጃ ለመውሰድ ያደረገውን ጥረት አድንቀው በቀሪዎቹ ግኝቶች ላይ በአፋጣኝ ተገቢ የማሻሻያ እርምጃዎችን እንዲወስድ አሳስበዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ም/ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ አበራ ታደሰ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ከመ/ቤቱ በተሰጠው አስተያየት መሰረት የድርጊት መርሀ ግብር አዘጋጅቶ በበርካታዎቹ ግኝቶች ላይ ተጨባጭ እርምጃዎች መውሰዱ የሚያስመሰግነው መሆኑን ገልጸው ቀሪዎቹን ግኝቶች ለማረም ቀጣይ ስራ ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲው በኩል ተወሰዱ የተባሉት የአሠራር ማስተካከያ እርምጃዎች ተገቢና በመ/ቤቱም የተረጋገጡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም በተለይ በአሠራር ችግር እስከአሁን ያልተሰበሱ ሂሳቦች ትኩረት ተሰጥቷቸው እንዲሰበሰቡ እና በሌሎች ቀሪ ክፍተቶች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ እንዲሁም ለኦዲት ግኝቶቹ መከሰት ምክንያት በሆኑ አካላት ላይ አስፈላጊው አስተዳደራዊ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ዋና ኦዲተሯ አሳስበዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ አራሬ ሞሲሳ በሰጡት የማጠቃለያ አስተያየት ዩኒቨርሲቲው በታዩበት የአሠራር ችግሮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ የወሰዳቸው የማሻሻያ እርምጃዎች ለሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችም በሞዴልነት የሚታዩ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

አክለውም በቀሪ መፍትሔ ባልተሰጣቸው ግኝቶች ላይ በተለይም በግንባታ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም፣ በበጀት አጠቃቀም፣ በሰው ሀይል ምደባ እና የአገልግሎት ጊዜያቸው ያለፉ መድሀኒቶችን ጨምሮ በንብረት አወጋገድ ሂደት ያሉትን ክፍተቶች ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን መቅረፍ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ሙሉ የመድረኩን ሂደት ለማየት የሚከተለውን ሊንክ ይጫኑ

https://www.facebook.com/hoprparliament/videos/916195452822368

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *