News

ዩኒቨርሲቲው ህግና የአሠራር ሥርዓቶችን ተከትሎ ሊሠራ እንደሚገባ ተገለጸ

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በ2014 በጀት ዓመት በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ላይ ባካሄደው የሂሳብ ህጋዊነት ኦዲት መሰረት በርካታ የህግና መመሪያ ጥሰቶች መታየታቸው ተገለጸ፡፡

ይህ የተገለጸው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ህዳር 12 ቀን 2016 ዓ.ም ከባለድርሻ አካላትና ከዩኒቨርሲቲው አመራሮች ጋር የኦዲት ግኝቶቹን አስመልክቶ ባካሄደው ህዝባዊ ይፋዊ የውይይት መድረክ ነው፡፡

በመድረኩ እንደተገለፀው ለመሬት ባለ ይዞታዎች የካሳ ክፍያን ያለ ሰነድ መክፈሉ፣ ለተለያዩ የኮንስትራክሽን ድርጅቶች አግባብ ያልሆኑ ብልጫ ክፍያዎችን መክፈሉ፣ በመመሪያው መሰረት ያልተወራረደ ሂሳብ መኖሩ፣ በሂሳብ ኮዶቹ ከተደለደለው በጀት በላይ ስራ ላይ አውሎ መገኝቱ፣ ተከፋይ ገንዘቦች ለሚመለከታቸው አካላት በወቅቱ አለመከፈላቸው፣ ደንብና መመሪያን የጣሰ የአበል ክፍያ መኖሩ እና ህግና መመሪያን የጣሱ የጨረታ ሂደቶች መከናወናቸው በተደረገው ኦዲት መሰረት በዩኒቨርሲቲው አሠራር ላይ ታይቷል፡፡

ከዚህም ሌላ ደካማ የፕሮጀክት ክትትል መታየቱ፣ የንብረት አመዘጋገብ ክፍተት መኖሩ እና  በተሽከርካሪዎች ጥገና ሂደት የታዩ ችግሮችን ጨምሮ  በርካታ የንብረት አስተዳደር፣ አያያዝና አጠቃቀም ጉድለቶች በኦዲቱ መገኘታቸውም በመድረኩ ተጠቁሟል፡፡

የኦዲት ግኝቶቹን አስመልክቶ ማብራሪያ እንዲሰጡ የተጠየቁት የዩኒቨርሲቲው አመራሮች በመድረኩ የተጠቀሱት የኦዲት ግኝቶች ትክክለኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲውን ፕሬዚዳንት አህመድ ሙስጠፋ (ዶ.ር) ጨምሮ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች በሰጡት ምላሽ  በአሠራር ላይ የነበረ የአቅም ክፍተት ለችግሮቹ መከሰት ምክንያት መሆኑን ጠቅሰው በተጨማሪም የወቅቱ የሸቀጦች የዋጋ መናር፣ የፀጥታ ችግር እና የበጀት እጥረት መኖር በጨረታና በሌሎች አሠራሮች ላይ ህግና መመሪያን ለመከተል እንዳላስቻሏቸው እና የኦዲት ግኝቶቹን ለመቅረፍ በጥረት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴ አባላትና ባለድርሻ አካላት በበኩላቸው የዩኒቨርሲቲው ችግሮች  አሠራርና  ህግን መሰረት አድረጎ ካለመስራት የመነጩ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

የስነምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ባደረገው ጥናት መሰረት በዩኒቨርሲቲው ላይ ለሙስናና ብልሹ አሠራር ሊያጋልጡ የሚችሉ በርካታ አሠራሮች መኖራቸው የተረጋገጠ መሆኑን ጨምረው የጠቀሱት የቋሚ ኮሚቴ አባላትና ባለድርሻ አካላት መመሪያዎችና ደንቦችን  በጣሱ የዩኒቨርሲቲው የስራ ሀላፊዎች ላይ አስተማሪና  ህጋዊ እርምጃ  መውሰድ  እንደሚገባ እና በቀጣይ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

 

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው  ዩኒቨርሲቲው የጥሬ ገንዘብ ጉድለት የታየበት መሆኑ፣ ካለ በቂ ማስረጃ ክፍያዎችን መፈፀሙ፣ በማዕቀፍ መፈጸም የነበረበት ግዥ ህግና ስርዓትን ባለተከተለ መልኩ ከግለሰብ እንዲገዛ መደረጉ እንዲሁም  ከካሳ ክፍያ፣ ከውሎ አበል አከፋፈል፣ ከተመላሽ ሂሳብ  እና ከበጀት አጠቃቀም ጋር ተያይዘው የታዩ ችግሮች የህዝብና የመንግስት ሀብት እንዲባክን ምክንያት መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

ያለአግባብ የተከፈሉ የአበልና ሌሎች ክፍያዎች ተመላሽ እንዲደረጉና ከንብረት አያያዝ ጋር የሚታዩ የአሠራር ችግሮች መስተካከል እንደሚገባቸው ጨምረው ያሳሰቡት ክብርት ዋና ኦዲተሯ ዩኒቨርሲቲው ለተከታታይ ሶስት ዓመታት ተቀባይነት የሚያሳጣ የኦዲት አስተያየት የተሰጠው በመሆኑ በአጥፊዎች ላይ ለሌሎች ማስተማሪያ የሚሆን ህጋዊ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ቀደም ሲል የታዩ የኦዲት ግኝቶችን በማስተካከል ረገድ ዩኒቨርሲቲው የሚጠበቀውን ያህል ያለመስራቱን  በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ  የጠቀሱት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ አራሬ ሞሲሳ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ሀገር ተረካቢ ትውልድ የሚያፈራ ተቋም እንደመሆኑ መጠን ያሉበትን የህግና መመሪያ ግድፈቶች ማስተካከል ይገባዋል ብለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው የትምህርት ተቋም እንደመሆኑ መጠን የሠራተኞቹን የአቅም ክፍተት እራሱ ለይቶ ሊቀርፍ እንደሚገባውና የታዩ የኦዲት ግኝቶችን ማስተካከል እንደሚኖርበት አክለው ያሳሰቡት ምክትል ሰብሳቢዋ ትምህርት ሚኒስቴር በገንዘብ ሚኒሰቴር በኩል በደብዳቤ በተገለጸለት የእርምጃ አወሳሰድ አቅጣጫ መሰረት እስከ ህዳር 30 ቀን 2016 ዓ.ም ተግባራዊ እንዲያደርግ፣ ዩኒቨርሲቲውም የግኝት ማስተካከያ የድርጊት መርሀ ግብሩን እስከ ህዳር 25 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ አዘጋጅቶ እንዲያቀርብ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትም የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ አቅጥጫ ሰጥተዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *