News

የ2013/2014 ኦዲት በጀት ዓመት የመ/ቤቱ ዕቅድ አፈጻጸም በታቀደው መሰረት መሳካቱ ተገለጸ

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በ2013/2014 የኦዲት በጀት ዓመት ሊያከናውናቸው ያቀዳቸውን የተለያዩ ኦዲት ክንውኖች በታቀደው መሰረት መፈጸሙ ተገለጸ፡፡

ይህ የተገለጸው ከየካቲት 14-18/2014 ዓ.ም በተካሄደው የመ/ቤቱ የ2013/2014 ኦዲት በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማና የ2014/2015 በጀት ዓመት የዕቅድ ዝግጅት ዓመታዊ የሠራተኞች መድረክ ላይ ነው፡፡

መድረኩን በንግግር የከፈቱት የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የኦዲት ዘርፍ ም/ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ እንደገለጹት በዕቅዱ መሠረት ተጀምረው በጸጥታ ችግር ምክንያት ከተቋረጡት የተወሰኑ ዩኒቨርሲቲዎች ኦዲቶች በስተቀር በ2013/2014 ኦዲት በጀት ዓመት በፋይናንስና ህጋዊነት ኦዲት የታቀዱ ተግባራት በታቀደው መሰረት መቶ ፐርሰንት መፈጸማቸውን አመላክተዋል፡፡ አክለውም የክዋኔና የአካባቢ ኦዲት ዕቅድ አፈጻጸም በተመለከተም  በበጀት ዓመቱ እስከ 29 የሚደርሱ አዳዲስና የክትትል ኦዲቶችን ለማከናወን በታቀደው መሠረት መፈጸሙን ጠቅሰዋል፡፡

በተለያዩ ክልሎች፣ የከተማ መስተዳድሮች እና ወረዳዎች  የሚከናወኑ የልማት ተግባራትን ለመደገፍ ከዓለም ባንክ የተደረገው ድጋፍ በአግባቡ ስራ ላይ መዋሉን ለማረጋገጥ የተከናወነው ኦዲትም በታቀደው መሰረት መፈጸሙንና አፈጻጸሙም ለሚመለከተው አካል ሪፖርት መደረጉን በንግግራቸው ገልጸዋል፡፡ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤትን ጨምሮ በተለያዩ አካላት ተጠይቀው የተከናወኑ የልዩ ኦዲት አፈጻጸሞችም በአግባቡ ተከናውነው  ሪፖርቱ ለሚመለከታቸው አካላት መላኩንና ከእነዚህ የልዩ ኦዲት ክንዋኔዎች መካከልም የተወሰኑት በሂደት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ የተከናወኑ  የተለያዩ የድጋፍ ዘርፍ ስራዎችም  በዕቅዳቸው መሠረት የተሳኩና ውጤታማ  መሆናቸውን የጠቀሱት ክብርት ም/ዋና ኦዲተሯ የመ/ቤቱን አሠራር በቴክኖሎጂ ለማዘመን የተከናወኑ ተግባራትን ጨምሮ በተለያዩ  የመ/ቤቱ የድጋፍ ዘርፍ የስራ ክፍሎች ውጤታማ የዕቅድ አፈጻጸም መመዝገቡን አንስተዋል፡፡

በሀገሪቱ የተከሰተው የጸጥታ ችግርና የኮቪድ- 19 ወረርሽኝ  በ2013/2014 የኦዲት በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ላይ ያጋጠሙ ጉልህ ችግሮች መሆናቸውን ያስታወሱት ም/ዋና ኦዲተሯ  እነዚህን ችግሮች በጽናት በመቋቋምና በማለፍ በኦዲት  እና  በድጋፍ ዘርፎች በበጀት ዓመቱ የታቀዱ ዕቅዶችን ለማሳካት  መላው የመ/ቤቱ አመራርና ሠራተኞች ላደረጉት ርብርብና ጥረት ከፍተኛ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በመድረኩ ላይ በቀረበው  የእያንዳንዱ  የስራ ክፍል የ2013/2014 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት መሰረት በመድረኩ ተሳታፊዎች ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡ ከዕቅድ አፈጻጸም ግምገማው በመቀጠልም የቀጣዩ የ2014/2015 የኦዲት በጀት ዓመት ዋና ዋና የዕቅድ አቀጣጫዎች በክብርት ም/ዋና ኦዲተር ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ ተሰጥተዋል፡፡ በተሰጡት የዕቅድ አመላካች አቅጣጫዎች  መሰረት እያንዳንዳቸው የመ/ቤቱ የስራ ክፍሎች  የሶስት ቀናት ቀጣይ የቡድን ውይይቶችን በማድረግ የ2013/2014 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸማቸውን በጥልቀት ገምግመው የ2014/2015 በጀት ዓመት ዕቅዳቸውን በማዘጋጀት በመጨረሻ ቀን በተካሄደው አጠቃላይ የሠራተኞች መድረክ ላይ አቅርበዋል ፡፡

በሌላ በኩል  የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማና የዕቅድ ዝግጅት መርሀ ግብሩን ተከትሎ የካቲት 19 ቀን 2014 ዓ.ም የምስጋናና የዕውቅና አሰጣጥ ስነ ስርዓት በመ/ቤቱ ቅጥር ግቢ ተካሂዷል፡፡ በተካሄደው የምስጋናና የዕውቅና አሰጣጥ ስነ ስርዓት ላይ  በመ/ቤቱ ሁለንተናዊ የስራ እንቅስቃሴ ሂደት  ጉልህ ሚና ለነበራቸው የስራ ክፍሎችና ግለሰቦች የአውቅናና የምስጋና የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል፡፡

በዕለቱ በተካሄደው የዕውቅናና ምስጋና አሰጣጥ ስነስርዓት ላይ በውጭና የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀውና የመ/ቤቱን የ76 ዓመታት ጉዞ ሂደት የያዘው ታሪካዊ መጽሀፍም የቀድሞው የመ/ቤቱ ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ በክብር እንግድነት በተገኙበት ተመርቋል፡፡

የክብር እንግዳው አቶ ገመቹ ዱቢሶ መጽሀፉን ከመረቁ በኋላ እንደገለጹት “የ76 ዓመታት ጉዞ” በሚል ርዕስ የዳይሬክቶሬቱ  አባላት በነበሩት አቶ አወቀ ጤናው፣ አቶ አባይ አማረና አቶ ወንድወሰን ብርሀኑ የተዘጋጀው ታሪካዊ መጽሀፍ እርሳቸው በመ/ቤቱ በኃላፊነት በነበሩበት ወቅት የተጀመረ መሆኑንና  መጽሀፉን ለማዘጋጀት የሚረዱ የተለያዩ መረጃዎችን ከተለያዩዩ ቦታዎች ለማሰባሰብ በአዘጋጆቹ በኩል ያልተቋረጠ ትጋትና ከፍተኛ ጥረት መደረጉን አስታውሰዋል፡፡  ከብዙ ድካምና ጥረት በኋላ መጽሀፉ ተጠናቆ ለምረቃ በመብቃቱ የተደሰቱ መሆናቸውን በንግግራቸው የጠቀሱት አቶ ገመቹ  የመጽሀፉን ዝግጅት ሀሳብ ከማመንጨት ጀምሮ እስከፍጻሜው ድረስ ቁርጠኝነት ያልተለየው ከፍተኛ ጥረት ላደረጉት የመጽሀፉ አዘጋጆች ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በዕውቅናና ምስጋና አሰጣጥ ስነስርዓቱ ላይ የተገኙት የመ/ቤቱ የኦዲት ዘርፍ ም/ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው ምስጋናና እውቅና የተሰጣቸው የስራ ክፍሎችና ግለሰቦች እንዲሁም መላው የመ/ቤቱ አመራርና ሠራተኞች  ለመ/ቤቱ የዕቅድ አፈጻጸምና ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ያላቸው ሚና የጎላ መሆኑን በድጋሜ ጠቅሰው ሁሉንም አካላት እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡ አክለውም የመ/ቤቱን የ76 ዓመታት ታሪካዊ ጉዞና ውጣ ውረድ  በጥልቀት የሚያስቃኘውና በርካታ ለጥናትና ምርምር የሚሆኑ መረጃዎችን ያካተተው ታሪካዊ መጽሀፍ ህትመት ተጠናቆ ለምረቃ በመብቃቱ ደስታቸውን ገልጸው የመጽሀፉን አዘጋጆች ከልብ አመስግነዋል፡፡

 

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *