የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የዋና መ/ቤቱን ባለ 10 ወለል ሕንጻን የሪኖቬሽን እና የማዘመን ሥራን ለመስራት የሚያስችለውን ስምምነት ከፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ጋር ሕዳር 15 ቀን 2015 ዓ.ም ፈጽሟል፡፡
ስምምነቱን የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ እና የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ረሻድ ከማል ፈርመዋል፡፡
በፊርማ ስነ ሥርዓቱ የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ያካሄደውን የለውጥ እና የተቋም ግንባታ እንዲሁም በአጭር ጊዜ የገነቧቸውን ዘመናዊ አፓርትመንት ሕንጻዎችን ቀደም ብለው በአካል ተዘዋውረው መጎብኘታቸውን አውስተው ጉብኝቱ ከኮርፖሬሽኑ ጋር ለመስራት እንዲወስኑ እንዳስቻለቸው ተናግረዋል፡፡
ከጉብኝቱ በኋላቧ/ቤታቸው ለኮርፖሬሽኑ ላቀረበለት ጥያቄ ፈጣን ምላሽ በመስጠት የዲዛይን ሥራውን በአጭር ጊዜ አጠናቆ መቅረቡን ክብርት ዋና ኦዲተር ጠቁመው ተቋማቸው የሚፈልገውን ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ ግንባታ በጥራትና በተያዘው የጊዜ ገደብ አጠናቆ እንደሚያስረክብም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ረሻድ ከማል በበኩላቸው ከዚህ ቀደም ኮርፖሬሽኑ የራሱን ቤቶች እንኳ መጠገን እና ቀለም መቀባት በማይችልበት ደረጃ የነበረ እንደነበረ አስታውሰው ተቋማቸው በሪፎርም ባካሄደው ተቋማዊ ግንባታ እና የመፈጸም ዓቅም ለውጥ ከራሱ አልፎ የሌሎች የመንግስት ተቋማትን፣ ዘመናዊ አፓርትመንቶችንና ሕንጻዎችን መገንባት ያቻለበት ደረጃ ላይ መድረሱን ተናግረዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ሕንጻን የሪኖቬሽን እና የማዘመን ሥራንም በተያዘለት በጀት፣ ጥራት ደረጃ እና ጊዜ ኮርፖሬሽኑ አጠናቆ እንደሚያስረክብም የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አረጋግጠዋል፡፡
የሪኖቬሽን ሥራውን የመጀመሪያ ምዕራፍ 5 ወለል የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ከ6 ወራት ጊዜ ውስጥ አጠናቆ እንዲሚያስረክብም ተገልጿል፡፡
የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ከራሱን ህንጻዎችና ቢሮዎች የሪኖቬሽን ሥራዎች በተጨማሪ የሌሎች መንግስታዊ ተቋማት የሪኖቬሽን ሥራ እየሰራ ይገኛል፡፡