የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በ2013 በጀት ዓመት በመንግስት በጀት በሚተዳደሩ የፌዴራል ተቋማት ላይ ያካሄደውን ኦዲት የተመለከተ ዓመታዊ ሪፖርቱን ለኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ሰኔ 14 ቀን 2014 ዓ.ም አቀረበ፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በ2013 በጀት ዓመት በተለያዩ የፌዴራል ተቋማት ላይ የተካሄደውን የፋይናንሽያልና የክዋኔ ኦዲት መሰረት ያደረጉ ግኝቶችን በሪፖርታቸው በዝርዝር አቅርበዋል፡፡
የፋይናንሽያልና የክዋኔ ኦዲት ግኝቶቹን በቅደም ተከተል ያቀረቡት ክብርት ዋና ኦዲተሯ ከተከናወኑት የኦዲት ስራዎች በተጓዳኝ አስፈላጊ የሆነ የክትትል ኦዲት መደረጉንም ገልጸዋል፡፡
አያያዘውም የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የድጋፍ ዘርፍ አፈጻጸም፣ በሂሳብ ምርመራ አገልግሎት ኮርፖሬሽን እና በግል ኦዲት ድርጅቶች የተከናወኑ ኦዲቶችን በተመለከተም ለተከበረው ምክርቤት አቅርበዋል፡፡
የቀረበውን ዝርዝር የኦዲት ሪፖርት መሠረት በማድረግም ከምክር ቤቱ አባላት የተለያዩ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ቀርበው በክብርት ዋና ኦዲተሯ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
የኦዲት ሪፖርቱንና ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮችን የተመለከቱ ሀሳቦችን ያነሱት የም/ቤቱ የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ኦቶ ክርስትያን ታደለ በበኩላቸው ም/ቤቱ በኦዲት ግኝቶች ላይ የክትትልና ድጋፍ ስራውን እንዲያጠናክርና በአጥፊዎችም ላይ ጠንካራ የተጠያቂነት ስርዓት የሚሰፍንበትን ሁኔታ እንዲያመቻች አበክረው ጠይቀዋል፡፡
በመጨረሻም የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አፈ ጉባኤ የተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ በሰጡት የማጠቃለያ ሀሳብ በቀረበው የኦዲት ሪፖርት መሠረት የም/ቤቱ የተለያዩ ቋሚ ኮሚቴዎች አባላት በሚመለከቷቸው ጉዳዮች ዙሪያ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ የኦዲት ግኝቶቹ የሚስተካከሉበትን ሁኔታ እንዲፈጥሩ አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡