የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት እና የፌዴራል የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ሙስናንና ብልሹ አሠራሮችን ከመታገል አንጻር በጋራ ሊሠሩ በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ የሁለትዮች የጋራ ስምምነት ሰኔ 27 ቀን 2015 ዓ.ም ተፈራርመዋል፡፡
በሁለትዮች የጋራ ስምምነት ስነ-ሥርዓቱ በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በኩል የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ እንዲሁም በፌዴራል የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን በኩል ኮሚሽነር ሳሙኤል ኡርቃቶ (ዶ/ር) በስምምነት ሰነዱ ላይ ፊርማቸውን አኑረዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በፊርማ ስነ-ሥርዓቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ከዚህ በፊትም ሁለቱ ተቋማት በቅንጅት ይሰሩ እንደነበር አስታውሰው በዛሬው ዕለት የተደረገው የስምምነት ዓላማ የአሠራር ሥርዓት ዘርግቶ ይበልጥ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ በቅንጅት ለመስራት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ለሁለትዮሽ የጋራ ስምምነቱ መነሻ የሆነው 24ኛው ዓለም አቀፍ የኦዲት ተቋማት ጉባኤ (INCOSAI) እንደሆነ ያነሱት ዋና ኦዲተሯ ጉባኤው ካስቀመጣቸው አቅጣጫዎች አንዱ የዋና ኦዲተር መ/ቤቶች ሙስናን ለማጋለጥ በሚያደርጉት ጥረት በየሀገሮቻቸው ከሚገኙ ጸረ-ሙስና ተቋማት ጋር በትብብር ሊሠሩ የሚገባ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሁለቱ ተቋማት በመቀናጀታቸው ሙስናን እና ብልሹ አሠራሮችን በመከላከል ዙሪያ ሊያከናውኗቸው የሚችሉ ተግባራት ጥቂት እንዳልሆኑ የጠቀሱት ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ ስምምነቱን ተፈጻሚ ለማድረግ በቀጣይ የትግበራ ስትራቴጂ ተነድፎ በእቅድ መስራት ይገባል ብለዋል፡፡
የፌዴራል የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሳሙኤል ኡርቃቶ (ዶ/ር) በበኩላቸው ስምምነቱ ሁለቱ ተቋማት በተናጠል ከሚሰሯቸው ሥራዎች ባለፈ በጋራ ሊሠሩባቸው የሚችሉባቸውን ጉዳዮች ለይተው ለመስራት የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡
ሁለቱ ተቋማት ግልጽነት እና ተጠያቂነትን ለማሳካት እና መልካም አስተዳደር ለማስፈን የሚጫወቱት ሚና የጎላ መሆኑንም ኮሚሽነሩ አንስተዋል፡፡
በስምምነቱ መሠረትም ከሁለቱም ተቋማት የሚመነጩ መረጃዎችን በመጠቀም የሙስና ሥጋት ጉዳዮችን የመለየትና ቀድሞ የመከላከል ሥራዎች እንደሚሠሩ ኮሚሽነር ሳሙኤል ኡርቃቶ (ዶ/ር) ገልጸው የሙስና ወንጀል ተፈጽሞ ሲገኝም ተጠያቂነትን የማስፈን ተግባር እንደሚከናወን ገልጸዋል፡፡
በስምምነቱ ወቅት ሁለቱ ተቋማት ተከታታይ የሆኑ ጥናቶችን በጋራ የማከናወን፣ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠናዎችን ለተቋማቱ እና ለሌሎች የመንግስት ተቋማት የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች የመስጠት፣ ውጤታማ የመረጃ ልውውጥ ሥርዓት የመዘርጋት፣ የምክክር መድረኮችን የማዘጋጀት፣ የመልካም አስተዳደር፣ ግልጸኝነትና ተጠያቂነትን በተሻለ ሁኔታ ተግባራዊ ላደረጉ ተቋማት እውቅና የሚያገኙበትን መንገድ የማመቻቸት፣ መልካም ተሞክሮዎችን በልምድ ልውውጥ የማጋራት እና በሁለትዮሽ በሚሠሯቸው ሥራዎች ላይ በጋራ መግለጫ የመስጠት ተግባራት እንደሚያከናውኑ ተገልጿል፡፡