News

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ሰራተኞች የፀረ-ፆታዊ ጥቃት ቀን እና የዓለም ኤድስ ቀን በዓላትን አከበሩ

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ሰራተኞች የፀረ-ፆታዊ ጥቃት ቀን (የነጭ ሪባን ቀን) “ሴቶችንና ህፃናትን ከጥቃት በመጠበቅ ሁላችንም ኃላፊነታችንን እንወጣ!” በሚል መሪ ቃል፤  የዓለም ኤድስ ቀን በዓልን ደግሞ “ማህበረሰብ የለውጥ አቅም ነው!” በሚል መሪ ቃል በመ/ቤቱ አዳራሽ ህዳር 26፣ 2012 ዓ.ም የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይት በማድረግ አከበሩ፡፡

በዓሉን በንግግር የከፈቱት የመ/ቤቱ የውጭና ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አወቀ ጤናው በዚህ መድረክ የሚፈጠረውን ግንዛቤ በስራና በመኖሪያ አካባቢያችን ዘወትር በመተግበር ቀጣይነት ያለው የመከላከል ስራ በማከናወን የዜግነት ኃላፊነታችንን መወጣት ይኖርብናል ብለዋል፡፡ አቶ አወቀ አክለውም የመከላከል ስራውን በአንድ ጊዜ በዓል አከባበር ሳይወሰን ዓመቱን ሙሉ በቀጣይነት ልንተገብረው ይገባል በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመድረኩ ላይ በዓላቱን አስመልክቶ የመወያያ ጽሑፎች በባለሙያዎች ቀርበዋል፡፡

የፀረ-ፆታዊ ጥቃት ቀንን አስመልክቶ ጽሑፍ ያቀረቡት በመ/ቤቱ የሴቶችና ወጣቶች ጉዳዮች ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ገዛኸኝ ሙሊሳ  በዓሉ ለ16 ተከታታይ ቀናት የግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄ በመፍጠር የሚከበር መሆኑን በመግለጽ የመ/ቤቱ ሰራተኞች የዚህ ንቅናቄ አካል በመሆን ጾታዊ ጥቃትን መከላከል እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡ አቶ ገዛኸኝ በመቀጠልም የህፃናትና የሴቶች ጥቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ እጨመረ መምጣቱን መረጃዎች እንደሚያሳዩ ጠቅሰው ይህንን ለመከላከል የቃል የምንገባበት በዓል ነው ብለዋል፡፡ ባቀረቡት የመወያያ ጽሑፍም የጸረ ፆታዊ ጥቃት ትርጓሜ፣ ጥቃቱ እያደረሰ ያለውን ጉዳት እና ከእያንዳንዱ ዜጋ ጥቃቱን ለመከላከል የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በዝርዝር አቅርበዋል፡፡

የአለም የኤድስ ቀንን በዓል በተመለከተ ጽሑፍ ያቀረቡት በመ/ቤቱ የስራ አካባቢ ደህንነትና ጤንነት ባለሙያ አቶ ታመነ ጌታሁን ሲሆኑ በአሁኑ ወቅት ኤች. አይቪ/ኤድስ ላይ እየተሰራ ያለው ግንዛቤ ማጨበጥ ስራ በቂ ባለመሆኑ ህብረተሰቡ ላይ መዘናጋትን በመፍጠሩ ስርጭቱ የመጨመር አዝማሚያ እየሳየ መሆኑን እየወጡ ያሉ መረጃዎች ስለሚያመለክቱ ሁሉም ሰራተኛ ራሱን በመከላከልና ለሌሎች ግንዛቤ በመፍጠር ላይ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ አቶ ታመነ በኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ዙርያ ዝርዝር ገለጻ አድርገዋል፡፡

ተሳታፊዎች በቀረቡት የመወያያ ጽሑፎች ላይ አስተያየትና ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡ በዚህ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራው የመስክ ሰራተኞችንም ያካተተ ቢሆን፣ ለተጎጂዎች እንዲሁም ለተጎጅ ቤተሰቦች ድጋፍ የምናደርግበት ስርዓት ቢዘጋጅ እና  የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ ከመ/ቤቱ ውጭ በሚጋበዙ ባለሙያዎች በየጊዜው የሚሰጥበት ሁኔታ ቢመቻች የሚሉ አስተያቶችን የሰጡ ሲሆን ጥያቄዎችንም አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል፡፡

የጽሑፍ አቅራቢዎችም ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፣ የቀረቡትን አስተያየቶች ተቀብለው በእቅድ ለመስራት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንደሚነጋገሩ ገልጸዋል፡፡

በበአላቱ አከባበር ወቅት የዳቦ መቁረስ ስነስርአት የተደረገ ሲሆን በዕለቱ ሰራተኞች የመ/ቤቱን ቅጥር ግቢ ግቢ የማጽዳት ስራ አከናውነዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *