በፌዴራል እና በክልል ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች መሀከል ያለውን የስራ ግንኙነት በማጠናከር የኦዲት ዘርፉ የሚያስገኘውን ሀገራዊ ፋይዳ በቀጣይ ለማሳደግ እንደሚሰራ ተገለጸ፡፡ የፌዴራልና የክልል ዋና ኦዲተሮች በጋራ ጉዳዮች ላይ ሐምሌ 07 ቀን 2009 ዓ.ም በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ውይይት አድርገዋል፡፡
በውይይቱ መክፈቻ ላይ የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ በፌዴራልና በክልል ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች መሀከል የነበረው የምክክር መድረክ ከሁለት አመታት ጀምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ሳቢያ ሳይካሄድ መቅረቱንና ይህም ቀድሞ የነበረው የትብብር ስራና የልምድ ተሞክሮ ልውውጥ ተቋርጦ እንዲቆይ ማድረጉን አስታውሰዋል፡፡
ክቡር ዋና ኦዲተሩ አያይዘውም የጋራ መድረኩን የማስቀጠል ጥያቄ በተደጋጋሚ በክልል የዋና ኦዲተር መ/ቤቶች ሲቀርብ እንደነበር ገልጸው በፌዴራልና በክልል ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች መሀከል የነበረውን ግንኙነት ለማስቀጠልና በጋራ ጉዳዮች ላይ ለመስራት መድረኩን መልሶ ለማስቀጠል የውይይት መድረኩ መዘጋጀቱን አስረድተዋል፡፡
በክልልና በፌዴራል ዋና ኦዲተር ተቋማት መሀከል የሰው ሀይል ፍልሰት እንዳይኖር የተደረገውን ስምምነት መተግበር፣ ክልሎች ተጠቃሚ የሚሆኑባቸው የተለያዩ የአቅም ግንባታ ስራዎችን መስራትና ልምድ ልውውጦችን ማድረግ እንዲሁም በኦዲት ግኝቶች ላይ የሚወሰደው እርምጃ እንዲጠናከር መስራት የጋራ ትብብር ጉዳዮች እንደሆኑ ክቡር ዋና ኦዲተሩ ተናግረዋል፡፡
የክልል ዋና ኦዲተሮች በበኩላቸው የዋና ኦዲተሮች የውይይት መድረክ መኖሩ በርካታ ጥቅሞችን እንደሚያስገኝ የገለፁ ሲሆን የመድረኩ መኖር በኦዲት ስራ፣ መመሪያዎችና ስታንዳርዶች ላይ አንድ አይነት ግንዛቤና አሰራር እንዲኖር ለማስቻል፣ በክልልና በፌዴራል የዋና ኦዲተር ተቋማት ውስጥ ወጥ አደረጃጀት እንዲፈጠር ለማድረግ፣ በፌዴራልና በክልል የሚደረገው የኦዲት ስራ ተዳምሮ ከፍ ያለ ሀገራዊ ፋይዳ እንዲያመጣ ለማስቻል፣ የክልል ዋና ኦዲተር ተቋማትን ለማጠናከር፣ የኦዲት ስራውን የሚያሳድጉ የልምድ ልውውጦችና አቅም ግንባታ ስራዎችን ለማካሄድ ባጠቃላይም የኦዲት ስራ አሰራርንና ፋይዳን ለማሻሻል እንደሚረዳ ገልጸዋል፡፡
የክልል ዋና ኦዲተሮቹ አክለውም የፌዴራል ዋና ኦዲተር አሁን ባለበት ሁኔታ ተጠናክሮ መውጣቱ የክልል ኦዲተሮች ሚና ተገቢውን ስፍራ እንዲያገኝ፣ ተሰሚነታቸው እንዲጨምርና የኦዲት ስራቸውም ፋይዳ እንዲያመጣ የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ እንደዚሁም ከአቅም እና ከአወቃቀር ጋር የተያያዙ የክልል ዋና ኦዲተር መ/ቤቶችን ሙያዊ ኃላፊነትና ነጻነት የሚገዳደሩ ችግሮች ያሉ መሆናቸውን ጠቅሰው የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት እነዚህ ችግሮች ተቀርፈው መ/ቤቶቹ ወደ ጠንካራ አቋም እንዲመጡ የማድረግ ከፍተኛ ሚና መጫወት እንዳለበት አስረድተዋል፡፡
በመድረኩ ላይ በፌዴራልና በክልል ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች መሀከል ሊፈጠሩ ስለሚገቡ መድረኮች ምንነት፣ በፌዴራልና በክልል መንግስታት በጋራ እየተተገበሩ ስላሉ ፕሮጀክቶች፣ በፌዴራልና በክልሎች ደረጃ ስላሉ የኦዲት ግኝቶች ክትትልና እርምጃ አወሳሰድ እንዲሁም ከባለድርሻ አካላት ጋር ስላለ ግንኙነቶች ውይይት ተደርጓል፡፡
በመድረኩ ላይ በፌዴራልና በክልል ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች መሀከል ስለሚመሰረቱት መድረኮች አይነት፣ ስለሚሳተፉ አካላትና ስለሚኖራቸው የግንኙነት ጊዜ አስመልክቶ በተደረገው ውይይት በጉዳዩ ላይ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት፣ የኦሮሚያ ክልል ዋና ኦዲተር ቢሮና እና የአዲስ አበባ ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች ተወያይተው በሚያቀርቡት ሃሳብ ላይ ውሳኔ እንዲሰጥ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
በፌዴራልና በክልል መንግስታት በጋራ እየተተገበሩ ስላሉ ፕሮጀክቶች በተነሳው አጀንዳ ላይ በአሁኑ ወቅት እየተተገበሩ ባሉት አራት ፕሮጀክቶች ላይ (PFM, PBS, ULDDPII and DFID/TAUT) ዙርያ ክቡር አቶ ገመቹ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን ከክልል ዋና ኦዲተር ቢሮዎች ዕቅድ አስተቃቀድ፣ የድጋፍ ጥያቄ ጥያቄ አቀራራብ፣ የሪፖርት አላላክ፣ የበጀት አጠቃቀም እና የኦዲት ሽፋን ጋር በተየያዙ ያላቸውን አስተያየቶች ሰጥተዋል፡፡ የክልል ዋና ኦዲተሮችም በፕሮጀክቱ አተገባበር ላይ ያሏቸውን አስተያየቶችናና ጥያቄዎች አቅርበዋል፡፡
በፌዴራልና በክልሎች ደረጃ ስላሉ የኦዲት ግኝቶች ክትትልና እርምጃ አወሳሰድ እንዲሁም ከባለድርሻ አካላት ጋር ስላለ ግንኙነቶች በተደረገው ውይይት በፌዴራል ዋና ኦዲተር በኩል ያሉት ሁኔታዎች ላይ ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን የክልል ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች ከክልል መስተዳድሮች እና ምክር ቤቶች ጋር ያላቸው ቅንጅታዊ ስራ እየተሻሻለ መሄዱንና የኦዲት ሪፖርትን የተለያዩ የቁጥጥር አካላት ለስራቸው እየተጠቀሙበት መምጣታቸውን፤ ኦዲት ሳይደረጉ ከቆዩ ተቋማት ጭምር ኦዲት እንዲደረጉ ጥያቄ የሚያቀርቡበት ሁኔታ እየተፈጠረ መምጣቱን እንዲሁም የዋና ኦዲተር መ/ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጆች እንዲሻሻሉ ጥረቶች መደረጋቸውን በዋናነት አንስተው እንደክልል ግንዛቤ መፍጠርና ወንጀለኞችን ተጠያቂ ማድረግ ላይ ብዙ መስራት እንደሚጠበቅባቸው ገልፀዋል፡፡
በመድረኩ ላይ ከሀረሪና ከሶማሌ ክልል ዋና ኦዲተሮች በስተቀር ሁሉም የክልልና የከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተሮች ተገኝተዋል፡፡