የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የግንባታ ሂሳብና የግንባታ ሂሳብ ኦዲት ሂደትን በተመለከተ በመ/ቤቱ የስልጠና ማዕከል ስልጠና ተሰጠ፡፡
ከመስከረም 20 -24 / 2017 ዓ.ም ለአምስት ቀናት በተሰጠው ስልጠና የኮንስትራክሽን ግንባታ ሂደትን በተመለከተ በሚደረግ ኦዲት መከናወን ያለባቸው ዝርዝር ሂደቶች በስልጠናው የተሸፈኑ ሲሆን የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ም/ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ አበራ ታደሠ በስልጠናው መክፈቻ ላይ በመገኘት የስልጠናውን ዓላማና ፋይዳ ለሰልጣኞች ገልጸዋል፡፡
መ/ቤቱ በሚያከናውናቸው ኦዲቶች ጥራትንና ተገቢነትን መሠረት ያደረገ የኦዲት ስራ መስራት ቀዳሚ መርህ መሆኑን በመክፈቻ ንግግራቸው የጠቀሱት ክቡር አቶ አበራ በተለይም በግንባታ ዘርፍ የሚካሄዱ ኦዲቶች የበለጠ ጥንቃቄና በጥራት መስራትን የሚጠይቁ በመሆናቸው ይህንን ለማሳካት የስልጠናው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡
ስልጠናው በእርስ በእርስ መማማር ሂደት ከስራ የተገኙ ልምዶችና ተሞክሮዎች ልውውጥ የሚደረግበት መሆኑን በመክፈቻው ላይ ጨምረው የገለጹት ክቡር ም/ዋና ኦዲተሩ ሰልጣኝ ኦዲተሮች በቆይታቸው ለስልጠናው ትኩረት በመስጠትና ጥልቅ ተሳትፎን በማሳየት የስልጠናውን ተገቢ ዕውቀትና ክህሎት በመጎናጸፍ በመደበኛ የኦዲት ስራቸው ላይ የተሻለ የኦዲት ውጤት ማስመዝገብ የሚጠበቅባቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የኦዲት ጥራትን የበለጠ ለመጠበቅ የሚያስችሉ በርካታ የተለያዩ ስልጠናዎችን ለእራሱም ሆነ በክልል ደረጃ ለሚገኙ ኦዲተሮች እየሰጠ ሲሆን ከመስከረም 20-24 ቀን 2017 ዓ.ም ለአምስት ቀናት በቆየው ስልጠና አስራ አምስት የሚሆኑ የመ/ቤቱ የፋይናንሽያልና ህጋዊነት ኦዲተሮች እንደተሳተፉ ከመ/ቤቱ የትምህርትና ስልጠና ዳይሬክቶሬት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡