News

የጅማ ዩኒቨርሲቲ የኦዲት ግኝቶችን ለማረም እያደረገ ያለው አበረታች ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተገለጸ

የጅማ ዩኒቨርሲቲ በኦዲት ግኝቶች ላይ እየወሰደ ያለው የእርምት እርምጃ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጥር 14 ቀን 2013 ዓ.ም  ባካሄደው ይፋዊ ህዝባዊ ስብሰባ ገለጸ፡፡ ይፋዊ ህዝባዊ ስብሰባው የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የዩኒቨርሲቲውን የፋይናንስ ስርዓትና ንብረት አያያዝ አስመልክቶ በ2011 በጀት ዓመት ባካሄደው ኦዲት የተገኙ ግኝቶችን መሠረት ያደረገ ሲሆን ቋሚ ኮሚቴው የዩኒቨርሲቲው አመራሮች ማብራሪያ እንዲሰጡ ዋና ዋና ግኝቶችን አቅርቧል፡፡

በዚህም በጥሬ ገንዘብ ብር 34,771.40፣ በተሰብሳቢ ብር 2,184,379.73 እንዲሁም በተከፋይ ብር 34,140,330.65  ያልተለመደ የሂሳብ ሚዛን በመያዝ ወደ 2011 በጀት ዓመት የዞሩ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ ከዚህም ሌላ ለዩኒቨርሲቲው ማስፋፊያ በሚል በጥቅሉ ብር 19,470,100.60 ወጪ የሆነበት የህንፃ ግዥ ቢደረግም ኦዲቱ እስከተከናወነበት ጊዜ ድረስ ዩኒቨርሲቲው የባለቤትነት ካርታ ያልተረከበ መሆኑ፣ በድምሩ ብር 18,982,919.86 ወጪ በማድረግ ለዩኒቨርሲቲው ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሚውሉ የህክምና እቃዎችን ለመግዛት በአለም አቀፍ የጨረታ ዘዴ ግዥ ለመፈጸም ቀደም ብሎ የባንክ “ሌተር ኦፍ ክሬዲት” ተከፍቶ ሂሳቡ በተሰብሳቢ የተያዘ ቢሆንም ንብረቱ ለዩኒቨርስቲው ገቢ ሳይደረግ  ሂሳቡ በወጭ ተመዝግቦ ሪፖርት የተደረገ መሆኑ እንዲሁም አስፈላጊ መረጃ ያልተሟላለት ብር 40,275.00 የሙያ እገዛ ላደረጉ 9 ግለሰቦች በሚል ወጪ ተደርጎ መገኘቱ ተመልክቷል፡፡

እንደዚሁም ለመድሀኒት ግዢ 1,074,300 ወጪ ተደርጎ እያለ  በሞዴል 19 ገቢ የተደረገው መድሀኒት የብር 1,039,510 በመሆኑ ብር 34,790.00 ብልጫ ተከፍሎ መገኘቱ እና በውል የተገባን አገልግሎት ወይም እቃን በወቅቱ ባለማቅረብ ምክንያት በጉዳት ካሳነት መሰብሰብ የነበረበት ብር 192,354.24 በወቅቱ ሳይሰበሰብ መቅረቱ ተጠቅሷል፡፡ በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው በ2010 በጀት ዓመት ለተከናወነ የጽዳት ስራ አገልግሎት ለአንድ የጽዳት አገልግሎት ሰጪ ድርጅት ከከፈለው ሂሳብ በብልጫ ብር 1,492,952.60 በ2011 ዓ.ም የወቅቱ የገበያ ዋጋ ሳይጠና ይሄው ድርጅት ለሰጠው አገልግሎት የተጋነነ ክፍያ ከፍሎ ተገኝቷል፡፡

ከዚህም ሌላ ከ1 ወር አስከ 5 ዓመት በላይ በተሰብሳቢነት የቆየና በጊዜ ገደቡ ያልተወራረደ ብር 32,889,385.52 መገኘቱ፣ በበጀት ዓመቱ ከመደበኛ በጀት በድምሩ ብር 646,159.14፣ ከካፒታል በጀት ብር 73,829,345.10 እንዲሁም ከውስጥ ገቢ ብር 646,159.43 በስራ ላይ ያልዋለ በጀት መገኘቱ፣ በርካታ ንብረቶች ያለአገልግሎት በእቃ ግምጃ ቤት ተቀምጠው መገኘታቸው እንዲሁም ከ2003 አስከ 2008 በጀት ዓመት በተደረጉ የአዲት ስራዎች የተገኙ አንዳንድ ግኝቶች ላይ የእርምት እርምጃ አለመወሰዱ ተጠቅሷል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው የዩኒቨርስቲው አመራሮች በኦዲት ግኝቶቹ ላይ  ማብራሪያ እንዲሰጡ የጠየቀ ሲሆን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ.ር ጀማል አባፊጣና ሌሎች በመድረኩ ላይ የተገኙ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ አመራሮቹ በሰጡት ምላሽም የኦዲት ግኝቶቹ ከ2010 በፊት የነበሩና ሲንከባለሉ የመጡ 6 ግኝቶችን ጨምሮ የ2011 በጀት ዓመት 12  በድምሩ 18 ግኝቶች መሆናቸውን ገልጸው በኦዲት ግኝቱ መሰረት የማስተካከያ መርሀ ግብር ተዘጋጅቶ ለሚመለከታቸው አካላት መላኩን፣ የክትትልና የእርምት እርምጃዎችም እየተወሰዱ መሆኑንና በዚህም መሻሻሎች መታየታቸውን አመላክተዋል፡፡

ትክክለኛ የሂሳብ ሚዛን ሳይጠብቁ ወደ 2011 በጀት ዓመት የዞሩ ሂሳቦችን በተመለከተ ክፍተቱ ከሂሳብ አመዘጋገብ ጋር የተያያዘ መሆኑን የጠቀሱት አመራሮቹ በአሁኑ ወቅት የማስተካከያ እርምጃዎች እየተወሰዱና ችግሩ እየተስተካከለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከሚመለከተው አካል የካርታ ርክክብ ሳይደረግ የህንፃ ግዥ ክፍያ መፈጸሙ ከአሠራር አንፃር ትክክል ያለመሆኑን የጠቀሱት አመራሮቹ ዩኒቨርሲቲው ካለበት የሠራተኞች ከስራ የመልቀቅ ከፍተኛ ችግር አንፃር በተለይም በስፔሻላይዝድ ሆስፒታሉ የሚሰሩና ሌሎች አስፈላጊ ባለሙያዎችን ለማቆየት ሲባል ህንፃው ባለበት ሁኔታ ለባለሙያዎች መኖሪያነትና ለተረኛ ሀኪሞች ማደሪያነት እንዲያገለግል ግዢ መፈፀሙን አስረድተዋል፡፡ አክለውም  በከተማው አስተዳደርና በሻጭ መካከል ያለመግባባቶች የነበሩ በመሆኑና ካርታው ጠፍቷል በመባሉ የካርታ ርክክብ ሁኔታው ሳይቋጭ መቆየቱን አመላክተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ካርታው ተገኝቷል በመባሉና ከከተማው አስተዳደር ጋር የተሻለ ግንኙነት ያለ በመሆኑ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ካርታውን መረከብ የሚያስችል ክትትል እየተደረገ መሆኑን አመራሮቹ ጠቁመዋል፡፡

የህክምና እቃዎች ተጠናቀው ገቢ ሳይደረጉ ሂሳቡ በወጪ ተመዝግቦ ሪፖርት መደረጉን በተመለከተም በወቅቱ አቅራቢው ስልጠናዎችን ጨምሮ ሌሎች ቴክኒካዊ ግዴታዎችን ስላላሟላ በገቢ ደረሰኝ እንዳልተያዙና እቃዎቹ አገልግሎት እየሰጡ እንዳሉ፣ ከኦዲቱ በኋላም ቴክኒካዊ ሁኔታዎች መሟላታቸው በጥናት የተረጋገጠላቸው ንብረቶች ሞዴል-19 የተቆረጠላቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የሙያ እገዛ ላደረጉ ባለድርሻ አካላት ወጪ የተደረገውን ክፍያ በተመለከተም ክፍተቱ መረጃ ያለማሟላት በመሆኑ በአሁኑ ወቅት መረጃዎች መሟላታቸውንና  ክፍተቱም የተስተካከለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ለመድሀኒት ግዥ በብልጫ የተከፈለው ክፍያን አስመልክቶም  ድርጅቱ ልዩነቱን እንዲመልስ  መጠየቁን ገልጸዋል፡፡

ያልተሰበሰበውን  የጉዳት ካሳ በተመለከተም ችግሩ የግንባታ ስራ ካቋረጡ ተቋራጮች ጋር የሚያያዝ  መሆኑን የጠቆሙት አመራሮቹ የካሳ ገንዘቡን ለማስመለስ በዩኒቨርሲቲው እርምጃዎች መወሰዳቸውን ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም አንድ የግንባታ ተቋራጭ ክፍያውን ባለመክፈሉ ጉዳዩን ለፍርድ ቤት በማቅረብ የተቋራጩ ኢንሹራንስ ካሳውን እንዲከፍል ተወስኖ ይግባኝ በመቅረቡ ጉዳዩ በሂደት ላይ ያለ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ሌላው ከውሃ ስራዎች ድርጅት ጋር የተፈጠረውን ክፍተት ቴክኒካዊ በሆኑ ነገሮች ላይ በስምምነት ለመፍታት መግባባት ላይ በመደረሱ ሂደቱ በመፈጸም ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ለጽዳት አገልግሎት ቀደም ሲል ከተከፈለው ክፍያ ብልጫ ያለው የተጋነነ የአገልግሎት ክፍያ ተከፍሎ መገኘቱን በሚመለከት ለተነሳው ጥያቄም አመራሮቹ ምላሽ የሰጡ ሲሆን በ2011 በጀት ዓመት የተካሄደው የጽዳት ስራ ቀደም ሲል በ2010 በጀት ዓመት ከተካሄደው በመጠኑ የሰፋና በ2010 ያልተካተተውን የውጪ ግድግዳ ጽዳት ያካተተ እንዲሁም የሚጸዱት ህንፃዎች ቁጥርም የጨመረ በመሆኑ፣ አገልግሎት አቅራቢው በ2010 በጀት ዓመት አላቂ የጽዳት እቃ ብቻ ያቀረበ ሲሆን በ2011 በጀት ዓመት  ማሽኖችን ጨምሮ  ቋሚ የጽዳት እቃዎችንም ጭምር ያቀረበ በመሆኑ እና በወቅቱ በነበረው የዋጋ ግሽበት ምክንያት በ2010 በጀት ዓመት ከተከፈለው የአገልግሎት ክፍያ ብልጫ ማሳየቱን አመላክተዋል፡፡

በተሰብሳቢነት የቆዩና በጊዜ ገደቡ ያልተወራረዱ ሂሳቦች በአብዛኛው ዩኒቨርሲቲውን ከለቀቀቁ ረጅም ዓመታትን ካስቆጠሩ ተመራማሪዎች ጋር የተያያዙ መሆናቸውን የገለፁት የዩኒቨርሲቲው አመራሮች በዩኒቨርሲቲው ደረጃ ሊሰረዝ የሚችለውን ገንዘብ የመሰረዝ እንዲሁም በገንዘብ ሚኒስቴር ደረጃ ሊሰረዝ የሚገባውን ገንዘብ ለማሰረዝ ውሳኔ እንዲሰጥባቸው እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ችግሩን ለወደፊቱ ለማስቀረት ተመራቂ ተማሪዎች ከመልቀቃቸው በፊት የውስጥ እዳቸውን እንዲያወራርዱ የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱን ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በጀትን በወቅቱ ያለመጠቀምን አስመልክቶ ለተነሳው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት አመራሮቹ የማዕቀፍ ግዥ መስተጓጎል፣ የአገልግሎት ሰጪ አካላት ክፍያቸውን በወቅቱ ያለማቅረብ እና የታቀዱ ዓለም አቀፍ የምርምር ጉባኤዎች በወቅቱ ያለመካሄዳቸው በጀቱን በተመደበለት ዓመት መጠቀም እንዳላስቻሉ አብራርተዋል፡፡ በተጨማሪም ሀገሪቱ በተለይ በ2010 እና 2011 በጀት  ዓመቶች  በነበረባት የገንዘብ እጥረት ምክንያት ገንዘብ ሚኒስቴር ገንዘቡን ባለመልቀቁ የ73 ሚሊዮን ብር የካፒታል በጀት በስራ ላይ ያለመዋሉን ገልጸዋል ፡፡

በንብረት አያያዝና አጠቃቀም ላይ የታዩ ክፍተቶችን ለማረም ጥረት እየተደረገ መሆኑን የጠቀሱት የዩኒቨርሲቲው አመራሮች የማያገለግሉና አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉትን ንብረቶች በመለየትና ከሚወገዱት ውስጥም ለማህበረሰብ አገልግሎት ለማዋል እንዲሁም ሌሎቹንም አግባብ ባለው መልኩ ለማስወገድ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ከ2008 በጀት ዓመት በፊት የነበሩ ግኝቶችን በተመለከተ በዩኒቨርሲቲው ደረጃ እርምጃ የመውሰድና ከፊሎቹም በፍርድ ቤት ሂደት ላይ ያሉ በመሆኑ ክትትል የማድረግ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲውን አመራሮች ምላሽ መሠረት አድርገው አስተያየታቸውን የሰጡት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ መርሀ ግብር አዘጋጅቶ እርምጃ ለመውሰድ እየተደረገ ያለው ጥረት በበጎ ጎኑ የሚታይ መሆኑን አመላክተው በቀጣይ ሊስተካከሉ ይገባቸዋል ያሏቸውን ጉዳዮች በዝርዝር አንስተዋል፡፡

ሚዛኑን ያልጠበቀ የሂሳብ አመዘጋገብና አያያዝ ለሌላ ችግር የሚዳርግ በመሆኑ ጥንቃቄ ሊደረግበት እንደሚገባ የጠቀሱት ክቡር ዋና ኦዲተሩ ካርታ ሳይቀበሉ የህንፃ ግዥ መፈጸም ህገወጥ በመሆኑ ካርታውን በፍጥነት መረከብ እንደሚገባ ጠቁመው የተገዛ እቃ ገቢ ሳይሆን ክፍያ መከፈሉ እንዲሁም ገቢ ከተደረገው እቃ ዋጋ በላይ ክፍያ መፈጸሙ ተገቢ አሠራር ባለመሆኑ ይህንን የፈጸሙ አካላት በህግ ሊጠየቁ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ አክለውም የጉዳት ካሳን ለማስመለስ እየተደረገ ያለው ጥረት አበረታች መሆኑን ጠቅሰው የጉዳት ካሳ በወቅቱ እንዲከፈል ያላደረጉ አካላትም  በህግ መጠየቅ እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡ በበጀት ዓመቱ ለጽዳት አገልግሎት የተከፈለው ክፍያ ቀድሞ ሲከፈል ከነበረው የ50% ጭማሬ ማሳየቱንና ይህም የተጋነነ መሆኑን የጠቀሱት ክቡር ዋና ኦዲተሩ በወቅቱ የገበያ ጥናት ያለመደረጉ የአሠራር ክፍተት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

ያልተወራረዱ ሂሳቦችን ለማስመለስ የተወሰደው እርምጃ አበረታች መሆኑን ገልጸው የእቃ ግዥ ከመፈፀሙ በፊት ከእቅድ ጀምሮ ባለው ሂደት ላይ ጥንቃቄ  ማድረግና  አግባብ የሆኑ ዘዴዎችን ተጠቅሞ የሚወገዱና አገልግሎት ላይ ሊውሉ የሚችሉ ንብረቶችን በመለየት  የንብረት አያያዝና አጠቃቀም ሥርዓቱን  ማስተካከል እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው የፋይናንስ ኦዲት ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ ሶፊያ አልማሙን በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲው የታዩ ክፍተቶች በሌሎችም ዩኒቨርሲቲዎች የሚታዩ መሆኑን ጠቅሰው ግኝቶቹን በመቀበልና ለማስተካከል ዝግጁ በመሆን በግኝቶቹ ላይ እርምጃ ለመውሰድ እየተደረገ ያለው ጥረት አበረታች መሆኑን ገልጸዋል፡፡  በቀሪ ግኝቶች ላይ እርምጃ የመውሰዱ ሂደት መጠናከር አለበት ብለዋል፡፡

በመጨረሻም የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ መሀመድ የሱፍ አበረታች የሆኑ እርምጃ የመውሰድ ጥረቶች ተጠናክረው መቀጠል እንደሚኖርባቸውና የውስጥ ኦዲት ስርዓቱም መጠናከር እንደሚገባው ጠቅሰው በቋሚ ኮሚቴ አባላትና በፌዴራል ዋና ኦዲተር የተሰጡ አስተያየቶችን ወስዶ አሠራርን የበለጠ ማስተካከል እንደሚገባ ኣሳስበዋል፡፡

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *