News

የደን ልማት ትግበራ ለተለያዩ ኢኮኖሚዊ ጠቀሜታዎች ሊውል እንደሚገባ ተገለጸ

የሀገሪቱ የደን ልማት ትግበራ የመሬት መራቆትን ከማስቀረትና የአካባቢ አየር ንብረት መዛባትን ከመከላከል ባሻገር ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ሊያደርጉ በሚችሉ ለተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳዎች ሊውል በሚገባው ደረጃ ትኩረት እንደሚያስፈልገው ተገለጸ፡፡

ይህ የተገለጸው የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የቀድሞውን የኢትዮጵያ የአካባቢና የደን ምርምር ኢንስቲትዩት የአሁኑን የኢትዮጵያ የደን ልማት የ2013/2014 በጀት ዓመት የአካባቢና የደን ምርምር አፈጻጸም አስመልክቶ ባካሄደው የክዋኔ ኦዲት ላይ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባካሄደው ይፋዊ ህዝባዊ ውይይት መድረክ ነው፡፡

ግንቦት 2 ቀን 2015 ዓ.ም በተካሄደው ይፋዊ ህዝባዊ የውይይት መድረክ እንደተገለጸው ተቋሙ የደን ምርምር ፖሊሲ አዘጋጅቶ ያለመተግበርን ጨምሮ በደን ምርምር ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ላይ በርካታ ክፍተቶች መኖራቸውን የተደረገው የኦዲት ሪ‹ፖረት እንደሚያሳይ ተጠቅሷል፡፡

በተጨማሪም የአካባቢ መራቆትን ሊቀንሱ የሚችሉ እና የተለያዩ የደን ውጤቶችን ለኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ማዋል የሚያስችሉ ፈጣን እድገት ያላቸው የተለያዩ የደን ዝርያዎችን በተለያዩ አካባቢዎች በማላመድ የማሰራጨት ሂደት ላይ ክፍተት እንዳለ ተገልጿል፡፡

በዘመናዊ ቴክኖሎጂና በተደራጀ የመረጃ ቅብብሎሽ ሥርዓት የተደገፈ የደን ልማት ትግበራ ያለመከናወኑ፣ የክትትልና ግምገማ ስርዓቱ ዝቅተኛ መሆኑ እና ከስራው ጋር ተዛማጅ ከሆኑ ተቋማትና አካላት ጋር ያለው ቅንጅታዊ አሠራርም በሚፈለገው ደረጃ ያለመሆኑን የኦዲት ግኝቶቹ እንደሚያሳዩ ተጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ የደን ልማት ዋና ዳይሬክተር አቶ ከበደ ይማም የኦዲት ግኝቶቹ ቀድሞ በነበረው የኢትዮጵያ የአካባቢና የደን ምርምር ኢንስቲትዩት ተቋማዊ መዋቅር የታዩ የአሠራር ክፍተቶችን የሚያሳዩ መሆናቸውን በመጥቀስ የአሁኑ የኢትዮጵያ የደን ልማት ግኝቶቹን ለማስተካከል በርካታ የማስተካከያ እርምጃዎችን እየወሰደ ነው ብለዋል፡፡

ለስራ እድል ፈጠራና ለከተሞች መስፋፋት በሚል ሁኔታ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ለደን ምርምር እየዋሉ ለሚገኙ የተወሰኑ የተቋሙ ይዞታ ለሆኑ መሬቶች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ በማግኘት ሂደት ላይ ከፍተኛ ችግር እያጋጠማቸው መሆኑን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ የሚመለከታቸው አካላት ይህን ችግር ለመፍታት የሚያስችል መፍትሔ እንዲሰጧቸው ጠይቀዋል፡፡

በመድረኩ የተገኙት የግብርና ሚኒስትሩ ክቡር ዶ.ር ግርማ አመንቴና ሌሎች የሚኒስቴር መ/ቤቱ አመራሮች በበኩላቸው የኦዲት ግኝቶቹ ወደፊት ለሚከናወነው የደን ልማትና ምርምር ስራ ግብአት መሆናቸውን ጠቅሰው የደን ልማት ፖሊሲውን እንዲጸድቅ ከማድረግና የተከለሰውን አዋጅ በአግባቡ ከመተግበር ጀምሮ የሀገሪቱ የደን ሀብት ለአካባቢ ጥበቃ፣ ለግብርና እና ለኢንዱስትሪ ዘርፎች ያለውን ጠቀሜታ ለማሳደግ የተለያዩ የተሻሻሉ ዝርያዎችን ሊያበለጽጉ የሚችሉ የምርምር ተቋማትን ማጠናከርና ቅንጅታዊ አሠራርን ማሳደግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት እንዲሁም የውይይቱ ተሳታፊ የሆኑ ባለድርሻ አካላት በበኩላቸው ፖሊሲው በአፋጣኝ ጸድቆ በተግባር እንዲውል እና በቅንጅታዊ አሠራር፣ በፕሮጀክቶች አፈጻጸም፣ በመረጃ አስተዳደር ሥርዓት እና በሌሎች አሠራሮች ላይ የሚታየውን ክፍተት ማስተካከል እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

አያይዘውም የተለያዩ የደን ዝርያዎችን በተለያዩ አካባቢዎች በማላመድ እና እየጠፉ ባሉ ሀገር በቀል የደን ዝርያዎች ላይ ትኩረት በመስጠት የደን ሀብት ለሀገሪቱና ለህብረተሰቡ ያለውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው ለደን ልማት የሚውሉ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ሊሻሻሉ እንደሚገባና ከሌሎች አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት በተለይም በአካባቢ ሂሳብ አያያዝ (Environmental Accounting) ሥርዓት ላይ ትኩረት መስጠት እንደ ሀገር ከፍተኛ ፋይዳ ያለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የምርምር ውጤቶችን ለተጠቀሚ በማድረስ፣ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው የዘርፉን ጥናቶች በማድረግ እና ሊጠፉ የተቃረቡ ሀገር በቀል የደን ዝርያዎችን በመጠበቅ የተሻለ ስራ መስራት እና በሌሎችም የኦዲት ግኝቶች ላይ የማስተካከያ እርምጃ በመውሰድ መሠረታዊ ለውጥ ማምጣት እንደሚያስፈልግም ዋና ኦዲተሯ አሳስበዋል፡፡

ከደን ሀብት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አንጻር ተቋሙ ከፍተኛ ሀገራዊ ኃላፊነት ያለበት መሆኑን የጠቆሙት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ክርስትያን ታደለ በሰጡት የማጠቃለያ አስተያየት ተቋሙ ከአደረጃጀት፣ ከመረጃ አያያዝና ቅብብሎሽ እንዲሁም ከአሠራር አንጻር ያሉ ችግሮችን መቅረፍ ይገባዋል ብለዋል፡፡

ለመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ ትኩረት መስጠት እና የሌሎች ሀገራትን የደን ሀብት አያያዝና አጠቃቀም ተሞክሮ መውሰድ እንደሚገባ እና የደን ሀብት ለማህበረሰቡ ያለውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ማረጋገጥ እንዲሁም የደን ሀብት ለኢንዱስትሪ ውጤቶች ግብአት ሊሆን በሚችልበት ሁኔታ ላይ መስራት እንደሚገባም ሰብሳቢው አሳበዋል፡፡

በቀጣይም የተሰጡ አስተያየቶችን መሰረት ያደረገ የኦዲት ግኝት ማሻሻያ የድርጊት መርሀ ግብር ተዘጋጅቶ በ10 ቀናት ውስጥ ለቋሚ ኮሚቴውና ለሚመለከታቸው አካላት እንዲቀርብና የማሻሻያ እርምጃ አፈጻጸሞችም በየሶስት ወራት እንዲቀርቡ እንዲሁም ባለድርሻ አካላት በሚመለከታቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተቋሙን ለተሻለ ስራ የሚያበቁ የክትትልና ድጋፍ ስራዎችን እንዲሰሩ አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *